2022 (እ.አ.አ)
የእኔ ናቸው እና አውቃቸዋለሁ
ጥር 2022 (እ.አ.አ)


“የእኔ ናቸው እና አውቃቸዋለሁ፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፣ ጥር 2022 (እ.አ.አ)።

ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ጥር 2022 (እ.አ.አ)

“የእኔ ናቸው እና አውቃቸዋለሁ”

ሙሴ 1

ወጣት ሴት በህዝብ ውስጥ

ፎቶግራፍ ከጌቲ ምስሎች

ከንቱነት ተሰምቷችሁ ያውቃልን? ምን ያህል ሰዎች በዓለም ውስጥ እንዳሉ ስታስቡ ወይም በሰማይ ላይ ምን ያህል ክዋክብቶች እንዳሉ ስትመለከቱ እንደዚህ ተሰምቷችሁ ይሆናል። እግዚአብሔር ማን እንደሆናችሁ እና ሕይወታችሁ ምን እንደሚመስል በእርግጥ እንደሚያውቅ ተገርማችሁ ታውቃላችሁን? ከሆነ፣ እንግዲያው ሙሴ ለእናንተ መልዕክት አለው።

በራዕይ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ የመሬትን እያንዳንዱን ክፍል እና በእርሷ ላይ የኖሩትንና የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ አሳየው። እነሱም “እንደ ባህር ዳርቻ እንደሚገኙ አሸዋ ተቆጥረው አያልቁም” ነበር (ሙሴ 1፥28)። ከዚያም እግዚአብሔር ለሙሴ “ለመቁጠር የማይቻል አለማትንም” እንደፈጠረ (ሙሴ 1፥33)—የእርሱ ፍጥረቶችም ከዚህ ምድር ባሻገር እንደሚደርሱ ነገረው።

ሙሴ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሲመለከት ምናልባት የመጨናነቅ ስሜት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ምናልባት እንዲህ ተገርሞ ሊሆን ይችላል፦ በብዙ ፍጥረቶች መካከል የት ቦታ ላይ እገኛለው? እናም እግዚአብሔር እንዴት ይህን ሁሉ ይከታተላል?

የእግዚአብሔር ምላሽ ቀላል ነበር፦ “ሁሉም ነገሮች በእኔ የሚቆጠሩ ናቸው።” እንዴት? “የእኔ ናቸው እና አውቃቸዋለሁ” (ሙሴ 1፥35)። እግዚአብሔር ሁሉንም ልጆቹን እና ሁሉንምን ፍጥረቱን እንደሚያውቀው ሁሉ፣ ሙሴ ማን እንደሆ አውቋል። ሁሉም የእርሱ ናቸው—ክዋክብቱ፣ አሸዋው እና በተለይም በምድር ላይ ያሉ የእርሱ ልጆች። እርሱ ምድርን የፈጠረበት ሙሉ ምክንያት እነርሱ ናቸው። የእነርሱ የዘለዓለም ደህንነት የእግዚአብሔር በጣም አስፈላጊው ስራ ነው።

“እነሆ፣ የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ማምጣት ስራዬ እና ክብሬ ይህ ነው” (ሙሴ 1፥39)።

ልክ ሙሴ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የት ቦታ ላይ እንደሚገኝ እንደተማረው ሁሉ፣ እናንተም እግዚአብሔር እንደሚያውቃችሁ ማረጋገጫን መቀበል ትችላላችሁ። እናንተን ወደ እርሱ እንድትመለሱ መርዳት የእርሱ ስራ እና ክብር ነው። ለምን? ምክንያቱም እናንተ የእርሱ ናችሁ። እናም ስለዚያ ነገር ምንም ከንቱ የሆነ የለውም!