2018 (እ.አ.አ)
አብረን ወደፊት ስንገፋ
ሚያዝያ 2018 (እ.አ.አ)


የቀዳሚ አመራር መልእክት፣ ሚያዝያ 2018 (እ.አ.አ)

አብረን ወደፊት ስንገፋ

ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ በዚህ ጠዋት ከእናንተ ጋር በመገኘቴ ትህትና ይሰማኛል። ከአራት ቀናት በፊት ታላቅ ሰው፣ የእግዚአብሔር ነቢይ—ፕሬዘደንት ቶማስ ኤስ. ሞንሰንን ቀበርን። ለህይወታቸው ታላቅነት እና አስደናቂነት ምንም ቃላት ሊገልጹት አይችሉም። ላስተማሩኝ ነገሮች ታላቅ ምስጋና እያለኝ ጓደኝነታችንን ለዘለአለም አከብራለሁ። አሁን፣ ይህች ቤተክርስቲያኑ በሆነችው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ እምነት፣ ወደፊት መመልከት አለብን።

ከሁለት ቀናት በፊት ሁሉም ህያው ሐዋሪያት በሶልት ሌክ ቤተመቅደስ የላይኛው ክፍል ውስጥ ተሰበሰቡ። በዚያም፣ መጀመሪያ ቀዳሚ አመራርን አሁን እንደገና ለማደራጀት፣ እና ሁለተኛ፣ እኔ እንደ ቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንት እንዳገለግል የአንድ ድምፅ ውሳኔ አደረጉ። ወንድሞቼ—በዚህ ዘመን በነቢይ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል በዳግም የተመለሱትን ቁልፎች ሁሉ የያዙት ወንድሞች—እኔን ለመቀደስ እና እንደ ቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንት ለመለየት በራሴ ላይ እጆቻቸውን ሲጭኑ ምን አይነት ስሜት እንደነበረ ልነግራችሁ ቃላት ብቁ አይደሉም። ይህም ቅዱስ እና ትሁት የሚያደርግ ድርጊት ነው።

ከዚያም ጌታ ለእኔ አማካሪዎች እንዲሆኑ ማንን እንዳዘጋጀ የመገንዘብ ሃላፊነት የእኔ ሆነ። እያንዳንዱም በጣም የማፈቅራቸው፣ ከሌሎቹ አስራ ሁለት ሐዋሪያት ሁለት ብቻ ለመምረጥ እንዴት እችላለሁ? የልብ ጸሎቴን ጌታ ስለመለሰው ጥልቅ ምስጋና ይሰማኛል። ፕሬዘደንት ዳለን ሀሪስ ኦክስ እና ፕሬዘደንት ሔንሪ ቤንየን አይሪንግ ከእኔ ጋር እንደ መጀመሪያ እና ሁለተኛ አማካሪ ለማገልገል ፈቃደኛ በመሆናቸውም ታላቅ ምስጋና አለኝ። ፕሬዘደንት ዲየተር ኤፍ. ኡክዶርፍ በአስራ ሁለት ሐዋሪያት ሸንጎ ውስጥ ወዳላቸው ቦታ ተመልሰዋል። ታላቅ የስራ ሀላፊነት ተቀብለዋል፣ ለዚህም ልዩ ብቁነት አላቸው።

እንደ ፕሬዘደንት ሞንሰን አማካሪዎች ላደረጉት አስደናቂ አገልግሎት ለእርሳቸው እና ለፕሬዘደንት አይሪንግ ምስጋና አቀርባለሁ። እነርሱም በሙሉ ችሎታ ያላቸው፣ ታማኝ፣ እና በመንፈስ የተነሳሱ ነበሩ። ለእነርሱም ታላቅ ምስጋና አለን። እያንዳንዱ አሁን በሚፈለጉበት ለማገልገል ፈቃደኛ ናቸው።

በአገልግሎት ዘመን ሁለተኛ የሆኑት ሐዋርያ፣ ፕሬዘደንት ኦክስ ደግሞም የአስራ ሁለት ሐዋሪያት ሸንጎ ፕሬዘደንት ሆነዋል። ይህም ቢሆን፣ እንደ ቀዳሚ አመራር አማካሪ በተሰጣቸው ጥሪ እና በቤተክርስቲያኗ ህግ መሰረት፣ ፕሬዘደንት ኤም. ራስል ባለርድ፣ በአገልግሎት ዘመን ተከታይ የሆኑት፣ እንደ ሸንጎው ጊዜአዊ ፕሬዘደት ያገለግላሉ። ቀዳሚ አመራር ከአስራ ሁለት ጋር የጌታን ፈቃድ ለማስተዋል እና ቅዱስ ስራውን ወደፊት ለመግፋት ጎን በጎን ይሰራሉ።

ለጸሎታችሁ ምስጋና አለን። በአለም አቀፍ እነዚህም ለእኛ ቀርበዋል። ፕሬዘደንት ሞንሰን ከሞቱበት ቀን በሚቀጥለው ጠዋት፣ አንድ እንደዚህ አይነት ጸሎት ስሙ ቤሰን በሚባለው በአራት አመት ልጅ ተሰጥቶ ነበር። ለባለቤቴ ዌንዲ፣ እናቱ ከጻፈችው ደብዳቤ በከፊሉ እጠቅሳለሁ። ቤንሰን እንዲህ ጸለየ፣ “የሰማይ አባት ሆይ፣ ፕሬዘደንት ሞንሰን ባለቤታቸውን እንደገና ለማየት በመቻላቸው ምስጋና አለኝ። ለአዲሱ ነቢያችንም አመሰግናለሁ። ደፋር እንዲሆን እና አዲስ በመሆኑ እንዳይፈራ እርዳታ ስጠው። ጤነኛ እና ጠንካራ በመሆን እንዲያድግም እርዳታ ስጠው። ክህነት ስላለው ሀይል እንዲኖረውም እርዳታ ስጠው። እናም ሁላችንም ጥሩ እንድንሆንም ሁልጊዜ እርዳታ ስጠን።”

ለእንደዚህ አይነት ልጅ እና ለጻድቅነት፣ ሆን ብለው የወላጅነት ሀላፊነታቸውን ለማከናወን የልብ ውሳኔ ላላቸው ወላጆች—ታላቅ ሸከም የሚሸከሙ እና ግን በፈቃደኝነት ለሚያገለገሉ እያንዳንዱ ወላጅ፣ አስተማሪና፣ አባል—እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በሌላም አባባል፣ ለእያንዳንዳችሁ፣ ትሁት ምስጋና አለኝ።

ጌታ የመርከብ መሪውን ይዟል።

አብረን ወደፊት ስንገፋ፣ ጌታ ቤተክርስቲያኑን ስለሚገዛበት ግርማዊ መንገድ እንድታስቡበት አጋብዛችኋለሁ። የቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንት ሲሞቱ፣ በዚህ ሀላፊነት ለማገልገል የሚቀጥለው ማን እንደሆነ ምንም ምስጢር አይደለም። ምንም ቅስቀሳ ማካሄድ፣ ለመመረጥ መሮጥ የለም፣ ነገር ግን ያለው በጌታ ራሱ በቦታ የተደረገው የመለኮታዊ የስልጣን የመረከብ ጸጥተኛ ስራ ነው።

የሐዋሪያ አገለግሎት እያንዳንዱ ቀን ወደፊት ለሚመጡ ተጨማሪ ሀላፊነቶች የመማር እና የመዘጋጀት ቀን ነው። ሐዋርያ በክቡ ውስጥ ከታናሽ ወንበር ወደ ታላቅ ወንበር ለመሄድ የብዙ አስር አመት አገልግሎቶች ያስፈልገዋል፡ በዚህም ጊዜ፣ በእያንዳንዱ የቤተክርስቲያኗ ስራዎች መጀመሪያ አጋጣሚዎች ያገኛል። የተመደበበት ሀላፊነት በአለም አሻገር ሲወስደውም ከምድር ህዝቦችም ጋር፣ በተጨማሪም ከታሪካቸው፣ ከባህላቸው፣ እና ከቋንቋቸው ጋር ይተዋወቃል። ይህ የቤተክርስቲያኗ መሪነት ስልጣን መረከብ አካሄድ ልዩ ነው። እንደዚህ አይነት የሆነ ሌላ ምንም አላውቅም። ያም ሊያስገርመን አይገባም፣ ምክንያቱም ይህች የጌታ ቤተክርስቲያን ናትና። እርሱ በሰው መንገድ አይሰራም።

በበፊት አምስት የቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንቶች ስር በአስራ ሁለት ሐዋሪያት ሸንጎ ውስጥ አገልግያለሁ። እያንዳንዱ ፕሬዘደንት ራዕይ ሲቀበሉ እና ለዚያ ራዕይ መልስ ሲሰጡ ተመልክቻለሁ። ጌታ ሁልጊዜም ነቢዩን ያስተምራል እናም በመንፈስ ያነሳሳል። ጌታ የመርከብ መሪውን ይዟል። ቅዱስ ስሙን በአለም አቀፍ ለመመስከር የተሾምነውም የእርሱን ፈቃድ ለማወቅና ለመከተል መፈለግን እንቀጥላለን።

በቃል ኪዳን መንገድ ቆዩ

አሁን፣ ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያኗ አባላት እንዲህ እላለሁ፣ በቃል ኪዳን መንገድ ቆዩ። ቃል ኪዳኖችን ከእርሱ ጋር በመግባት እና ከዚያም እነዚያን ቃል ኪዳኖች በመጠበቅ አዳኝን ለመከተል በልብ የምትወስኑበት በሁሉም ቦታ ላሉት ወንዶች፣ ሴቶች፣እና ልጆች ለሚገኙት ለእያንዳንዱ መንፈሳዊ በረከቶች እና እድሎች በር ይከፍታል።

እንደ አዲስ አመራር፣ ስለመጨረሻው እያሰብን ለመጀመር እንፈልጋለን። ለዚህ ምክንያት፣ ዛሬ እናንተን የምናነጋገረው ከቤተመቅደስ ነው። እያዳንዳችን የምንጥርበት መጨረሻም በጌታ ቤት ውስጥ በሀይል ለመቀደስ፣ እንደቤተሰብ ለመተሳሰር፣ ከሁሉም በላይ ለሆነው ለእግዚአብሔር ስጦታ፣ እንዲሁም ለዘለአለም ህይወት፣ ብቁ ለሚያደርጉን በቤተመቅደስ ውስጥ ለገባናቸው ቃል ኪዳኖች ታማኝ ለመሆን ነው። የቤተመቅደስ ስርዓቶች እና በዚያ የምትገቡት ቃል ኪዳኖች ህይወታችሁን፣ ጋብቻችሁን፣ እና ቤተሰባችሁን፣ እናም የጠላትን ጥቃቶች ለመቋቋም ያላችሁን ችሎታ ለማጠናከር ዋና ቁልፎች ናቸው። በቤተመቅደስ ውስጥ በምታመልኩበት እና ለቅድመ ዘመዶቻሁ የምታደርጉት አገልግሎት በተጨማሪ የግል ራዕይና ሰላም ይባርካችኋል እናም በቃል ኪዳን መንገድ ለመቆየት ያላችሁን የልብ ውሳኔ ያጠናክራል።

አሁን፣ ከመንገዱ ከወጣችሁ፣ በልቤ በሙሉ ባለው ተስፋ በሙሉ እባካችሁ ተመለሱ በማለት እጋብዛችኋለሁ። ሀሳባችሁ ምንም ቢሆን፣ ፈተናችሁ ምንም ቢሆን፣ በዚህች በጌታ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለእናንተ ቦታ አለ። እናንተ እና ገና ያለተወለዱት ትውልዶች ወደ ቃል ኪዳን መንገድ ለመመለስ አሁን በምታደርጉት ስራዎቻችሁ ይባረካሉ። የሰማይ አባታችን ልጆቹን ያፈቅራል፣ እናም እያንዳንዳችን ወደቤት ወደ እርሱ እንድንመለስ ይፈልጋል። ይህም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ታላቅ አላማ ነው—እያንዳንዳችንን ወደ ቤት እንድንመለስ ለመርዳት።

ለእናንተ ያለኝን ፍቅር—ለብዙ አስር አመቶች ከእናንተ ጋር በመገናኘት፣ ከእናንተ ጋር በማምለክ፣ እና እናንተን በማገልገል ያለኝን ፍቅር ለመግለፅ እፈልጋለሁ። መለኮታዊ ሀላፊነታችን ወደ እያንዳንዱ ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና፣ ህዝቦች በመሄድ አለምን ለጌታ ዳግም ምፅዓት ለማዘጋጀት መርዳት ነው። ይህን የምናደርገው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት፣ እርሱ ስልጣን እንዳለው በማወቅ ነው። ይህም ስራው እና ቤተክርስቲያኑ ነው። እኛል አገልጋዮቹ ነን።

ለእግዚአብሔር የዘለአለም አባታችን እና ለልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ያለኝን አምልኮ አውጃለሁ። እነርሱን—እናም እናንተን—አውቃለሁ፣ እወዳለሁ፣ እና በሚቀሩት በህይወት ትንፋሴ ሁሉ ለማገልገል ቃል እገባለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።