የአገልግሎት መሰረታዊ መርሆች፣ የካቲት 2019 (እ.አ.አ.)
በአገልግሎት ላይ የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ የመመልከት ችሎታን ማዳበር
ማገልገል ከፍ ማድረግ ነው። ምን እየደረሰባቸው እንዳለ በመረዳትና ከእነሱ ጋር ለመጓዝ ፈቃደኛ መሆናችንን በማሳየት ሌሎችን ማንሳት እንችላለን።
የሰማይ አባታችን እንደ እርሱ እንድንሆን ስለሚፈልግ፣ በዚህ ህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች እርሱን ካመንን እንዲሁም በመንገዱ ለመቆየት ከፈለግን የመማርያ እድሎች ሊሆኑ ይችላሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ እነዚህን ፈተናዎች ለብቻችን የምንወጣቸው ሆኖ ሲሰማን በመንገዱ ላይ መጓዝ የበለጠ ከባድ ይሆናል፡፡
ነገር ግን እኛ በምንም በብቸኝነት በመንገድ ላይ የምንጓዝ አይደለንም። አዳኛችን በአሰቃቂ ሁኔታዎቻችን እና በህመሞቻችን እንዴት ለመርዳት ያውቅ ዘንድ ፍጹም የሆነ የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ የመመልከት ችሎታን አዳበረ፣ እንዲሁም ከሁሉም ነገሮች በታች ወረደ (አልማ 7፥11–12፤ ትምህርት እና ቃልኪዳን 122፥8 ይመልከቱ)። እያንዳንዳችን የእርሱን ምሳሌ እንድንከተል እና የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ የመመልከት ችሎታን እንድናሳይ ይጠብቀናል። እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል “ከሚያለቅሱ ጋር ለማልቀስ እናም መጽናናት የሚያስፈልጋቸውን ለማጽናናት” ቃል ኪዳን ገብቷል (ሞዛያ 18፥9)። የራሳችን ፈተናዎች ቢኖሩንም፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ በሙሉ ከኛ ውጪ እንድንመለከት እናም “የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች [አቅኑ]” እና “ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ [አድርጉ]” ተብለን እንማራለን (እብራውያን 12፥12–13፤ እንዲሁም ኢሳያስ 35፥3–4፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 81፥5–6 ይመልከቱ)።
ሌሎችን በእጃቸው ስንይዝ፣ በእኛ ላይ እንዲደገፉ ስናደርግ፣ እና ከእነሱ ጋር ስንጓዝ፣ ከአገልግሎት ቁልፍ አላማ የሆነውን አዳኝ እንዲለውጣቸው በረጅሙ መንገድ ውስጥ እንዲቆዩ መርዳት ብቻ ሳይሆን፣ እነሱን ለመፈወስ እንዲረዳቸው እናደርጋለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 112፥13 ይመልከቱ)።
የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ የመመልከት ችሎታ ምንድን ነው?
የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ የመመልከት ችሎታ ማለት የሌላ ሰውን ስሜት፣ ሃሳቦች፣ እና ሁኔታዎች ከራሳችን ይልቅ በእነርሱ አይን መመልከት ነው።1
ሌሎችን ለማገልገል እና ወንድሞችን እና እህቶችን ለማገልገል ያለንን ዓላማችንን ለማሟላት በምናደርገው ጥረት የሌሎችን ስሜት መረዳት አስፈላጊ ነው። እራሳችንን በሌላ ሰው ፋንታ እንድንመለከት ያስችለናል።
እራሳችንን በሌላ ሰው ፋንታ መመልከት
ስለ አንድ አይን አፋር የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ብቻውን ከቤተክርስቲያን በጀርባ ይቀመጥ ስለነበር ሰው ታሪክ ተነግሯል። የሽማግሌዎች ቡድን አባል የሆነ ሰው በድንገት ሲሞት፣ ኤጲስ ቆጶሱ የቤተሰቡን አባላት ለማጽናናት የክህነት በረከቶችን ሰጠ። የሴቶች መረዳጃ ማህበር እህቶች ምግብ ይዘው መጡ። መልካም የሆኑ ወዳጆች እና ጎረቤቶች ቤተሰቦቹን ለመጎብኘት በመሄድ “እኛ ልንረዳችሁ የምንችለው ነገር ካለ ያሳውቁን” አሉ።
ነገር ግን ይህ ዓይናፋር ሰው ቤተሰቡን ከቀኑ በኋላ ላይ ሲጎበኝ፣ በሩን አንኳኳ እናም ባሏ የሞተባት በሩን ስትከፍት “ጫማችሁን ለማጽዳት መጥቻለሁ” አለ። በሁለት ሰዓታት ውስጥ፣ ለቀብር ሥነ ሥርዓት ዝግጅት የሁሉም የቤተሰቡ ጫማዎች ጸዱ። በቀጣዩ እሁድ የሽማግሌው ሟች ቤተሰብ ከበስተጀርባ መቀመጫ ላይ ከአይነአፋሩ ሰው ጋር አብሮው ተቀመጡ።
ያልተሟላን ፍላጎት ማሟላት የቻለ ሰው ነበር። እርሱ እና እነርሱም የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ በመመልከት በተመራው አገልግሎት ተባርከዋል።
የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ መመልከት የምችለው እንዴት ነው?
አንዳንዶች የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ በመመልከት ስጦታ ተባርከዋል። ነገር ግን በዚህ ዙሪያ ላይ ለሚቸገሩ ሰዎች የምሥራች አለ። ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉ ተመራማሪዎች ላለፉት 30 ዓመታት የሌላውን ሰው ችግር እንደራስ መመልከትን ተመራምረዋል። ብዙዎቹ በተለየ አቀራረብ በርዕሱ ጉዳይ ላይ ያጠኑ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ግን የሌላውን ችግር እንደራስ የመረዳት ችሎታ መማር የሚቻል እንደሆነ ደምድመዋል።2
የሌሎችን ስሜት የመረዳት ስጦታን ለማግኘት መጸለይ እንችላለን። ለመሻሻል እንዲቻል፣ የሌላውን ችግር እንደራስ መመልከት እንዴት እንደሚሰራ በተሻለ መገንዘቡም የሚረዳ ነው። የሚከተሉት ሐሳቦች በአጠቃላይ ተቀባይነትን የተላበሱ መሰረታዊ የሰውን ስሜት የመረዳት ነጥቦች ናቸው።3 ብዙውን ጊዜ እነዚህ ነገሮች የሚከሰቱት መከሰታቸውን ሳናውቅ ቢሆንም፣ እነዚህን መገንዘባችን ለማሻሻል እድሎች ይሰጡናል።
1.ተረዱ
የሌላውን ችግር ለመረዳዳት የሌላውን ሁኔታ መረዳትን ይጠይቃል። ያሉበትን ሁኔታ በተሻለ መልኩ ስንረዳ፣ እነርሱ ምን እንደሚሰማቸው እና ለመርዳት ምን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ ቀላል ይሆንልናል።
በትኩረት ማዳመጥ፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ ከእነሱ እና ከሌሎች ጋር የምክር አገልግሎት ማካሄድ ሁኔታዎችን ለመረዳት አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው። ስለነዚህ ጽንሰ-ሐሳቦች በበለጠ ካለፉ የአገልግሎት መሰረታዊ መርሆች አንቀጾች ላይ ተማሩ፤
-
“ጥሩ አዳማጮች የሚያደርጓቸው አምስት ነገሮች፣” Liahona{22}፣ ሰኔ 2018 (እ.አ.አ)፣ 6።
-
“ስለሚያስፈልጋቸው ነገሮች ተመካከሩ፣” Liahona{24}፣ መስከረም 2018 (እ.አ.አ)፣ 6።
-
“ሌሎችን ለመርዳት እርዳታን ማግኘት፣” Liahona፣ ጥቅምት 2018 (እ.አ.አ)፣ 6።
ለመረዳት በምንፈልግበት ጊዜ፣ ተመሳሳይ ሁኔታ ካለው ሌላ ሰው ጋር በመመሥረት ከማሰብ ይልቅ ጊዜ ወስደን የግል ሁኔታቸውን መረዳት አለብን። አለበለዚያ ምልክቱን ልንስት እና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳለን እንዲሰማቸው ልናደርግ እንችላለን።
2.በምናባችሁ አስቡ
የመጽናናት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ለማጽናናት እና ከሚያዝኑ ጋር አብሮ የማዘን ቃል ኪዳናችንን ለማክበር በምናደርገው ጥረት፣ አንድ ሰው ምን ስሜት ሊሰማውና እኛ ልንረዳው እንዴት እንደምንችል ለመረዳት መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን።4
የግለሰብን ሁኔታ አንዴ ካወቅን፣ እያንዳንዳችን፣ ተፈጥሯዊም ይሁን አይሁን፣ በዚያ ሁኔታ ምን እንደምናስብ ወይም ምን እንደሚሰማን የማሰብ ሙከራዎችን ማካሄድ እንችላለን። እነዚህን ሀሳቦች እና ስሜቶች መረዳታችን፣ ከመንፈስ ቅዱስ አመራር ጋር በመሆን፣ ለምንሰጠው ምላሽ በመምራት ሊረዱን ይችላሉ።
የሌላውን ሁኔታ ስንረዳ እና እንዴት እንደሚሰማቸው ስንገነዘብ፣ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ እንዳንፈርዳቸው መጠንቀቁ በጣም አስፈላጊ ነው (ማቲዎስ 7፥1 ይመልከቱ)። አንድ ሰው ወደ ሁኔታው እንዴት እንደገባ ማተኮር ሁኔታው ያስከተለውን ህመም ባነሰ ሁኔታ እንድንመለከት ሊያደርግ ይችላል።
3.ምላሽ ስጡ
ምላሻችን በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም የሌላውን ችግር ምን ያህል እንደራሳችን እንደምናደርገው ያሳያል። በቃልና ያለቃል የእኛን ግንዛቤን የሚያስተላልፉ በርካታ መንገዶች አሉ። ግባችን ችግሩን ለመፍታት የግድ ሁኔታ አለመሆነን ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ብዙውን ጊዜ ዓላማው ብቻቸውን እንዳልሆኑ እንዲያውቁ በማድረግ ከፍ እንዲሉ እና እንዲጠናከሩ ማድረግ ነው። ይህ “እርስዎ ስለነገሩኝ በጣም ደስ ብሎኛል” ወይም “በጣም አዝናለሁ። እንደሚያም እርግጠኛ ነኝ” ማለት ነው።
በእያንዳንዱ ሁኔታ የምንሰጠው ምላሽ እውነተኛ መሆን አለበት። ተገቢ ሲሆኖም፣ የራስን ድክመቶች እና አለመረጋጋቶች ለሌሎች ማሳየቱ ጠቃሚ ግንኙነትን መፍጠር ይችላል።
ለመስራት ግብዣ
የምታገለግሏቸውን ሰዎች ሁኔታዎችን ስትመለከቱ፣ በሁኔታቸው ውስጥ ሆናችሁ እና በእነሱ ፋንታ ሆኖ ማሰቡ በጣም ይረዳችኋል። እንዴት እንደሚሰማቸው እና እንዴት እንደምትረዱ ለማወቅ ይጸልዩ። ምላሻችሁ ቀላል ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ግን ትርጉም ያለው ይሆናል።
© 2019 በ Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፥ 6/18 (እ.አ.አ)። ትርጉም የተፈቀደበት፥ 6/18 (እ.አ.አ.)። Ministering Principles, February 2019 ትርጉም። Amharic. 15763 506