የአገልግሎት መርሆዎች፣ ሰኔ 2019 (እ.አ.አ)
አገልግሎት ማለት ሌሎችን ጌታ እንደሚያያቸው ማየት ማለት ነው፡፡
ኢየሱስ ለየትና ገሸሽ ተደርገው ይታዩ ከነበሩ ሰዎች ጋር አብዛኛውን ጊዜውን አሳልፏል፤መለኮታዊ አቅማቸውንም አይቷል፡፡
እንደ አዳኛችን ለማገልገል በምናደርገው ጥረት ከኛ የተለየ ማንነት ያላቸውን ሰዎች እንድናገለግል ልንጠየቅ እንችላለን፡፡ ይህ ለመማርና ለማደግ መልካም አጋጣሚን ይፈጥርልናል፡፡
የባህል ፣ የትምህርት ደረጃ ፣ የዘር ፣ የኢኮኖሚ ደረጃ ፣ የቀድሞ ወይም የአሁን ባህርያት ወይም ሌሎች ልዩነቶቻችን አንዳንዶችን ገና ሳናውቃቸው በቀላሉ እንድንፈርድባቸው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህ በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ ድምዳሜ የጭፍን ጥላቻ እምብርት ነው፡፡እናም አዳኙ ከዚህ እንድንቆጠብ አስጠንቅቋል፡፡ 1ኛ ሳሙኤል 16÷7 ፣ ዮሃንስ 7፥24 ን ይመልከቱ፡፡
ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተን ሌሎችን አዳኙ እንደሚያያቸው ማየት እንችላለን? ሌሎችን በአሁን ማንነታቸው እና ወደፊት ሊሆኑ በሚችሉት ማንነታቸው እንዴት ልንወዳቸው እንችላለን?
መመልከት እና መውደድ
መጽሃፍ ቅዱስ የዘላለም ህይወትን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ስለጠየቀ ሃብታም ወጣት ታዋቂውን ታሪክ እንዲህ ይነግረናል፡-“ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ እንግዲያው አንድ ነገር ይጎድልሃል ፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ ፤ለድሆችም ስጥ ፤በሰማይ የተከማቸ ሃብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላ ና፤መስቀሉን ተሸከም ፤ተከተለኝም፡፡“ አለው::ማርቆስ 10፥21
የሰባዎቹ አባል የሆነው ሽማግሌ ኤስ.ማርክ ፓልመር ከተወሰኑ አመታት በፊት ይህን ቅዱስ ጽሁፍ ባጠናበት ወቅት አዲስ የታሪኩ ክፍል በድንገት ወለል ብሎ ታየው::
“ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፡፡“
“እነዚህን ቃላት እንደሰማኋቸው ኢየሱስ ቆም ብሎ ይህን ወጣትሲመለከተው የሚያሳይ ምስል በእዝነ-ልቦናዬ ግልጽ ብሎ ታየኝ፡፡
ከዚያም በቀላል ቋንቋ—ኢየሱስ “ተመለከተውና ወደደው፡፡“ ለዚህ መልካም ወጣት ጥልቅ ፍቅርና ርህራሄ ተሰማው እንዲሁም በዚህ ፍቅር ምክንያት እና በዚሁ ፍቅር ኢየሱስ ስለእርሱ ብዙ ጠየቀ፡፡ ያለውን ሁሉ እንደ መሸጥ እና ለድሃ እንደ መስጠት… ያለ እጅግ ከባድ ጥያቄ በመጠየቅ ላይ ሳለ እንኳን በእንዲህ ያለ ፍቅር ውስጥ መሆን ለዚህ ወጣት ምን አይነት ስሜት ፈጥሮበት ሊሆን እንደሚችል በእዝነ-ልቦናዬ አየሁት፡፡
“[እራሴን እንዲህ ስል ጠየኩት‘[ሌሎች] በእኔ አማካይነት የእግዚያብሄር ፍቅር እንዲሰማቸውና መለወጥ እንዲፈልጉ እንደ ክርስቶስ ባለ ፍቅር እንዴት መሞላት እችላለሁ?’ [በዙሪያዬ ያሉ ግለሰቦች] እያደረጉ ካለው ወይም እያደረጉ ካልሆነው ነገር ይልቅ በአሁኑ እና ወደፊት ሊሆኑ በሚችሉበት ማንነታቸው ልክ ጌታ ሃብታሙን ወጣት ባየበት ተመሳሳይ ሁኔታ ማየት የምችለው እንዴት ነው? ይበልጥ እንደ ጌታ መሆን የምችለው እንዴት ነው?” 1
ሌሎችን ለማየት መማር
ሌሎችን አዳኙ በሚያቸው አይን ማየትን መማር ብዙ ሽልማቶችን ያስገኛል፡፡ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ስንሰራ የሚከተሉት ጥቆማዎች ይረዱናል፡፡
-
እወቋቸው።
ሰዎችን ከውጫዊ ባህርያቶቻቸው ባለፈ በጥልቀት ለማወቅ ጥረት አድርጉ፡፡ ግንኙነቶችን መገንባት ጊዜንና እውነተኛ ጥረትን እንደሚጠይቅ እወቁ፡፡ (”እርዳታ ለማግኘት “Building Meaningful Relationships” የሚለውን የነሃሴ 2018 (እ.አ.አ) የአገልግሎት መርሆዎች ጽሁፍ ይመልከቱ፡፡) -
ራሳችሁን መርምሩ፡፡
አውቃችሁም ሆነ ሳታውቁ ልትሰጡ ስለምትችሉት ፍርድ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ስለሌሎች የምታስቀምጧቸውን ግምቶች ልብ በሉ ከዚያም ስለእነርሱ የሚሰሟችሁን ስሜቶች በተመለከተ ለምን እንደዚያ እንደሚሰማችሁ ለማወቅ ጣሩ፡፡ -
ፍርድ ከመስጠት ታቀቡ፡፡
አንድ ግለሰብ ያለበት ሁኔታዎች ግለሰቡ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እንደማይወስኑ ተገንዘቡ፡፡ ራሳችሁን በእነርሱ ቦታ አስቀምጡና በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ አንድ ሰው እንዴት እንዲያያችሁ እንደምትፈልጉ አስቡ፡፡ የአንድን ሰው ምርጫዎችና ባህርያት ከመሰረታዊ እሴቱ እና መለኮታዊ አቅሙ መለየት ሌሎችን አዳኙ በሚያያቸው ዓይን እንድናያቸው ይረዳናል፡፡ -
ትወዷቸው ዘንድ ጸልዩ።
ስማቸውን ጠቅሳችሁ ስለእነርሱ ያለማቋረጥ ጸልዩላቸው ፤ እንዲሁም እውነተኛ ጓደኝነትን ለመመስረት ትእግስት እንዲኖራችሁም ጸልዩ፡፡ አገልግሎታችሁን በጸሎት መንፈስ ተመልከቱት፡፡ እናንተ በምታደርጉት ነገር እና እነርሱ በትክክል በሚፈልጉት ነገር መካከል ክፍተት ይኖር ይሆን?
ኢየሱስ የተለያየ የህይወት ተመክሮዎች ከነበራቸው ከብዙ ሰዎች ጋር ጊዜውን አሳልፏል፡-ከባለጸጎች ፣ ከድሆች ፣ ከአለቆች እና ከተራው ህዝብ ጋር:: ሌሎች በግልጽ የሚታዩበትን ዝቅተኛ የኑሮ ወይም እዚህ ግባ የማይባሉ ሁኔታዎቹን ሲመለከቱ አብዛኛውን ጊዜ ትክክለኛ ያልሆነ ግንዛቤ ይወሰዱበት ነበር፡፡ “በምናየውም ጊዜ እንድንወደው የሚያደርግ የሚስብ መልክ የለውም ፤. … የተጠላ ነበር ፤እኛም አላከበርነውም፡፡” (ኢሳይያስ 53፥2–3).
እንደ ክርስቶስ ያለ እይታ
አንዲት እህት ጎረቤትን እንደ ክርስቶስ ባሉ አይኖች ለማየት ስለመማር ይህን ታሪክ ታካፍላለች-
“ጁሊያ(ስሟ ተቀይሯል)በአቅራቢያዬ የምትኖር ሲሆን ምንም ጓደኞች ያሏት አይመስልም፡፡ ሁልጊዜ ቁጡና የተናደደች መስላ ትታያለች፡፡ ቢሆንም ግን ጓደኛዬ ላደርጋት ወሰንኩኝ። ዝም ብሎ ተራ ጓደኛ ሳይሆን ግን እውነተኛ ጓደኛ፡፡ ባየኋት ቁጥር አነጋግራት ነበር እንዲሁም በምትሰራቸው ነገሮች ሁሉ ፍላጎቴን አሳይ ነበር:: ቀስበቀስ ከእርሷ ጋር የጓደኝነት ጥምረት ፈጠርኩኝ እናም ለልቤ ደስታን አመጣልኝ፡፡
“አንድ ቀን ጁሊያን ልጎበኛትና ቤተክርስቲያን ላለመሄድ ስለወሰነችው ውሳኔ ልጠይቃት ወሰንኩኝ፡፡
“በአቅራቢያዋ ቤተሰቦችም ሆኑ ዘመዶች እንደሌሉዋት አወቅኩኝ:: አንድ ብቸኛ ወንድሟ እሩቅ አገር የሚኖር ሲሆን ከርሷ ጋር ግንኙነት የሚያደርገውም በአመት አንዴ ብቻ ያውም በስልክ ነው፡፡ ስለቤተሰቧ እና ስለቤተክርስቲያን ያላትን ምሬት ፣ብስጭት እና ንዴት አንድም ሳታስቀር አውጥታ ስትናገር ባዳመጥኳት ጊዜ ሊካድ የማይቻል ጥልቅ የርህራሄ እና የፍቅር ስሜት ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ ህመሟ እና ንዴቷ ተሰማኝ፡፡ ህይወቷ እንዴት በብቸኝነት የተሞላ እንደነበር ተገነዘብኩኝ፡፡ ልክ ከኋላዬ ‘እኔም እወዳታለሁ አንተም ውደዳት አክብራት‘ የሚል የለሆሳስ ቃል እንደሰማሁኝ ያህል ነበር፡፡
“ልትናገር የምትፈልገውን በሙሉ ተናግራ እስክትጨርስ ቁጭ ብዬ አዳመጥኳት፡፡ ለእርሷም ፍቅርና ርህራሔ ተሰማኝ፡፡ ይህች መወደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አይታ የማታውቅ እህት ናት፡፡ በድንገት ይበልጥ በጥልቀት ተገነዘብኳት፡፡ እንድጎበኛት ስለፈቀደችልኝ አመሰገንኳት ከዚያም ፤ አቀፍኳት ለእርሷ ያለኝን ፍቅርና ከበሬታም ይዤ ተለየኋት፡፡ በዚያ ጉብኝት ምን ያህል በእርሷ እንደተነካሁኝ መቼም አታውቅም፡፡ የሰማይ አባት አይኖቼን ከፍቷቸው ከፍ ባለ ርህራሄ የማፍቀር አቅም እንደነበረኝ አስተማረኝ፡፡ ጓደኛዋ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቧም ለመሆን ባደረኩት ውሳኔ ጸንቻለሁ::”
ወደ አንድ ሌላ ሰው ህይወት ውስጥ ለመግባት መጋበዝ የተቀደሰ ነገር ነው፡፡ በጸሎት ፣ በትዕግስት እና ከመንፈስ በሚገኝ እርዳታ እንደዚህ ያለውን ነገር በላቀ እንደክርስቶስ ያለ እይታ ለማድረግ መማር እንችላለን፡፡
© 2019 በ Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved። በዩ.ኤስ.ኤ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፥ 6/18 (እ.አ.አ)። ትርጉም የተፈቀደበት፥ 6/18 (እ.አ.አ.)። Ministering Principles, June 2019 ትርጉም። Amharic. 15767 506