2020 (እ.አ.አ)
በቤተመቅደስ አገልግሎት በኩል ማገልገል
መጋቢት 2020 (እ.አ.አ)


የአገልግሎት መርሆች፣ መጋቢት 2020 (እ.አ.አ.)

በቤተመቅደስ አገልግሎት በኩል ማገልገል

ሌሎችን በቤተመቅደስ በረከቶች እንዲደሰቱ ስንረዳቸው እያገለገልን ነው ማለት ነው፡፡

ምስል
ministering

የጀርባ ምስል ከጌቲ ምስሎች፤የቴጉቺጋልፓ ሆንዱራስ ቤተመቅደስ ፎቶግራፍ

በቤተመቅደስ ለመሳተፍ የምናደርገው ጥረት የሚገባ ነው፡፡ ፕሬዘዳንት ረሰል ኤም.ኔልሰን “ቤተመቅደስ ለእኛና ለቤተሰቦቻችን ደህንነት እና ከፍ ለመደረግ አስፈላጊ ነው፡፡…

“… እያንዳንዳችን በጌታ ቤት ብቻ ሊገኝ የሚቻለው ቀጣይ መንፈሳዊ ማጠናከሪያ እና ትምህርት ያስፈልገናል፡፡ “ ሲሉ አስተምረዋል፡፡1

የቤተመቅደስ ተሳትፎ ጊዜያችንን፣ሃላፊነቶቻችንን እና ሃብታችንን በአግባቡ መጠቀምን እንዲሁም በመንፈሳዊ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በቤተመቅደስ ከመሳተፍ የሚያግዱ እንቅፋቶችን ስንለይ እና መፍትሄዎችን ስናገኝ እያገለገልን ነው፡፡

ቤተመቅደስ ማንኛውም ሰው ሊደሰትበት የሚችል በረከት ነው፡፡

በቅርቡ ከሚስዮን የተመለሰችው ሜግ ወደኮና ሃዋይ ቤተመቅደስ በሮች እየገባች ሳለች አንዲትን ወጣት ሴት በአግዳሚ ወንበር ላይ ብቻዋን ተቀምጣ አስተውላት ነበር ፡፡ ሜግ ወጣቷን ሴት ማናገር እንዳለባት ተሰማት ነገርግን ምን እንደምትላት እርግጠኛ አልነበረችም፡፡ ስለዚህ በወጣቷ ሴት ቁርጭምጭሚት ላይ ስላለው ንቅሳት ትርጉም ጠየቀቻት፡፡ ያም የወጣቷን ሴት የላኒን ታሪክ እንድታካፍል ያስቻለ ውይይት አስጀመረ፡፡

ላኒ ወደቤተክርስቲያን ሙሉ ተሳትፎ ለመመለስ እያደረገች ስላለችው ትግል፣እየረዷት ስላሉት ጥሩ አባላት እንዲሁም አንድ ቀን ከህጻን ሴት ልጇ ጋር ለመጣመር ስላላት ተስፋ ለሜግ ነገረቻት፡፡

ሜግ ላኒን በቤተመቅደሱ መቆያ ክፍል ከእርሷ ጋር እንድትቀመጥ ጋበዘቻት፡፡ ወደ ቤተመቅደሱ ገና አልዘለቁም ነበር ነገር ግን ደጃፉን አልፈው ነበር፡፡ ሊና ተስማማች እናም በዋናው በር ወደ ውስጥ አለፉ፡፡ አንድ የቤተመቅደስ ሰራተኛ ከአዳኙ ምስል ስር ወዳለው አግዳሚ መራቸው፡፡

አብረው ተቀምጠው ሳሉ ላኒ“በእውነት ዛሬ ወደቤተመቅደሱ መግባት ፈልጌ ነበር ነገር ግን ፈራሁኝ“ ስትል አንሾካሸከችላት፡፡ ሜግ መንፈሱን እየተከተለች ስለነበረ ላኒ በሆዷ ያደረገችው ጸሎት እንዲመለስላት ረዳች፡፡

የመግቢያ ፈቃድ የሌላቸውን ለመርዳት የሚሆኑ ሃሳቦች፡፡

የመግቢያ ፈቃድ የሌላቸውም ቢሆኑ እንኳ በቤተመቅደስ ሊባረኩ ይችላሉ፡፡

  • በቤተመቅደስ ስራ ጌታ እንዴት እንደባረካችሁ ስሜታችሁን አጋሩ፡፡

  • በቤተመቅደስ ክፍት ቤቶች ወይም በጎብኚዎች ማዕከል እንዲገኝ አንድ ሰው ጋብዙ፡፡ መጪ ክፍት ቤቶችን ለማግኘት በtemples.ChurchofJesusChrist.orgይፈልጉ፡፡

  • temples.ChurchofJesusChrist.orgውስጥ ፎቶዎችን ይመልከቱ እንዲሁም ስለቤተመቅደስ ይበልጥ ይማሩ፡፡

የቤተመቅደስ ተሳትፎን ለሌሎች ቀለል ያለ ያድርጉ፡፡

የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ ላላቸው አባላትም እንኳ በቤተመቅደስ መሳተፍ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች ረዝም ርቀትን መጓዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ ሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ትንንሽ ህጻናት ወይም በእድሜ የገፉ የቤተሰብ አባላት ሊኖሯቸው ይችላል፡፡ የቤተመቅደስ አገልግሎትን ለሁሉም የሚቻል ለማድረግ አብረን ልንሰራ እንችላለን፡፡

ሌኦላ ቻንድለር ታማሚ ባሏን እና አራት ልጆቻቸውን በመንከባከብ እንደተጨናነቀች ተሰምቷት ነበር፡፡ ስለዚህ በአቅራቢያ ወዳለው ቤተመቅደስ ለመገኘት ማክሰኞ ማክሰኞ የተወሰነ ሰዓት ለመመደብ ወሰነች፡፡ ለህይወቷ የሰላም እና የሃይል ምንጭ ሆነላት፡፡

አንድ ቀን በዋርዷ ያሉ ጥቂት አዋቂ እህቶች ቤተመቅደስ መገኘት እንደሚፈልጉ ነገር ግን የመጓጓዣ መንገድ እንደሌላቸው ሰማች፡፡ ሌኦላ ልታደርሳቸው ፈቃደኛ ሆነች፡፡ ለሚቀጥሉት 40 አመታት ለብቻዋ ወደ ቤተመቅደስ ሄዳ አታውቅም፡፡2

ሌኦላ ተባርካ ነበር ፤እንዲሁም ወደ ቤተመቅደስ ከእርሷ ጋር ሌሎችን ለመውሰድ ፈቃደኛ በመሆኗ ባርካቸዋለች፡፡

ሌሎች በቤተመቅደስ እንዲካፈሉ ለመርዳት የሚሆኑ ሃሳቦች፡፡

ሌሎች ቶሎ ቶሎ ወደ ቤተመቅደስ እንዲሄዱ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? እነዚሁ ተመሳሳይ ሃሳቦች እናንተንም የሚረዷችሁ ሆነው ልታገኟቸው ትችላላችሁ፡፡

  • አብራችሁ ሂዱ። ለአንድ ሰው የመጓጓዣ መንገድ አቅርቡ ወይም አመቻቹ፡፡ አንድን ሌላ ሰው በቤተመቅደስ እንዲካፈል ሊያበረታታውም ይችላል፡፡

  • የቤተሰብ ወይም የዋርድ አባላቶቻችሁን ለቅድመ አያቶቻችሁ ስርአቶችን ለማከናወን እንዲረዷችሁ ጠይቋቸው በተለይ ለስርአቱ የተዘጋጁ ብዙ የቤተሰብ ስሞች በሚኖሯችሁ ጊዜ፡፡

  • ወላጆች ቤተመቅደስ መካፈል ይችሉ ዘንድ ህጻናቶቻቸውን ጠብቁላቸው፡፡ ወይንም አንዳችሁ የሌላውን ልጆች በየተራ ለመጠበቅ የሚያስችል ሁኔታ አመቻቹ፡፡

ቤተመቅደሱ ሩቅ በሚሆንበት ጊዜ

የኮሎምቦ ሲሪላንካ ነዋሪ የሆኑት ቻንድራዳስ ”ሮሻን ” እና ሼረን በቤተመቅደስ ለመጣመር ወሰኑ፡፡ ጓደኞቻቸው አን እና አንቶን ኩማራሳሚ ስለነሱ ተደስተው ነበር፡፡ ነገር ግን ፊሊፒንስ ማኒላ ቤተመቅደስ መሄድ ቀላል ወይም በትንሽ ወጪ የሚደረግ እንዳልነበር አውቀው ነበር፡፡

ሮሻን እና ሼረን ገንዘብ ቆጥበው ነበር እንዲሁም ከወራት በፊት በአቅማቸው የበረራ ቦታ አስይዘው ነበር፡፡ በመጨረሻም ቀኑ ደረሰ፡፡ ነገር ግን በማሌዢያ በነበራቸው የአጭር ጊዜ ቆይታ ወደ ፊሊፒንስ ለመቀጠል ቪዛ እንደሚያስፈልጋቸው አለበለዚያም በሌላ አየር መንገድ መጓዝ ግድ እንደሚላቸው ተገነዘቡ፡፡ ቪዛ ማግኘት የማይቻል ነገር ነበር እንዲሁም በሌላ አየር መንገድ ለመጓዝ ትኬት መግዛትም አይችሉም ነበር፡፡ ነገር ግን በቤተመቅደስ ሳይጣመሩ ወደቤት መመለስ የማይቀበሉት ሃሳብ ነበር፡፡

ሌላ የሚያደርገው ነገር ግራ ገብቶት ሮሻን ለአንቶን ደወለ፡፡ አንቶን እና አን የተቻላቸውን ያህል ሊረዱ ሞከሩ፡፡ በሲሪላንካ ውስጥ የሚኖሩ በቤተመቅደስ ከተጣመሩ ጥቂት ጥንዶች መካከል ነበሩ እናም ምን ያህል በረከት እንደሆነ ያውቁ ነበር፡፡ ነገር ግን የቆጠቡትን ገንዘብ በቅርቡ ለተቸገረ የቤተሰባቸው አባል ተጠቅመውት ነበር እናም ሮሻንን እና ሼረንን ለሌላ በረራ ቲኬት እንዲገዙ ለመርዳት በቂ ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡

በሲሪላንካ ሙሽራው ለሙሽሪት የወርቅ ሃብል መግዛት የተለመደ ነበር ፤ይህም ወደፊት ባሏ ቢሞት ገንዘብ እንዲኖራት ታስቦ ነው፡፡ አን ሌላ ቲኬት ለመግዛት ለመርዳት የአንገት ሀብሏን ለመሸጥ ወሰነች፡፡ ለጋስ ስጦታዋ ሮሻን እና ሼረን በማኒላ የቤተመቅደስ ቀጠሯቸው እንዲሳካ አስቻለ፡፡

“በቤተመቅደስ መጣመር ያለውን ዋጋ አውቃለሁ” ብላለች አን፡፡ “ሼረን እና ሮሻን በቅርንጫፉ ታላቅ ጥንካሬ እንደሚሆኑ አውቂያለሁ፡፡ ይህ አጋጣሚ እንዲያልፋቸው አልፈለኩም፡፡”3

ቤተመቅደስን መጎብኘት የማይችሉትን ለመርዳት የሚሆኑ ሃሳቦች፡፡

በርቀት ወይንም በዋጋ ውድነት ምክንያት በየጊዜው ወይንም ጭራሹን ወደቤተመቅደስ መሄድ ለማይችሉ እንድታገለግሉ ልትጠሩ ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን የቤተመቅደስን በረከቶች እንዲያደንቁ ለመርዳት የሚያስችሉ መንገዶችን ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡

  • በቤተመቅደስ ዝግጅት ወይንም በቤተሰብ ታሪክ ትምህርት ማስተማር ወይንም አብራችሁ መሳተፍ፡፡

  • በቤታቸው እንዲሰቅሉት የቤተመቅደስ ስእል ስጧቸው፡፡

  • በቤተመቅደስ ተሳትፋችሁ የምታውቁ ከሆነ ስለልምዳችሁ ስሜታችሁን እንዲሁም ስለቤተመቅደስ ስርአቶች ምስክርነታችሁን አካፍሉ፡፡

  • ስለገቡት ቃልኪዳኖች እና እንዴት እንደሚጠብቋቸው ይበልጥ እንዲማሩ እርዷቸው፡፡ “Understanding Our Covenants with God: An Overview of Our Most Important Promises፣” ሃምሌ 2012(እ.አ.አ)መጠቀምን አስቡ፡፡ሊያሆና

ማስታወሻዎች

  1. ረስል ኤም. ኔልሰን ፣ “አርአያ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን መሆን” ሊያሆና፣ ህዳር 2018 ፣ 114 ይመልከቱ፡፡

  2. ላሬኔ ጋውንት፣ “በቤተመቅደስ አገልግሎት ደስታን ማግኘት፣” ኤንዛይን፣ ጥቅምት 1994 (እ.አ.አ.)፣ 8።

  3. አን እና አንቶን በራሳቸው በቤተመቅደስ ለመሳተፍ አቅም ለሌላቸው የቤተክርስቲያኗ አባላት የአንድ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ በሚሰጠው በቤተክርስቲያኗ አጠቃላይ የደንበኞች ድጋፍ ፈንድ ገንዘቡ ከተመለሰላቸው በኋላ የአንገት ሃብላቸውን መልሰው ለማግኘት ቻሉ፡፡

አትም