“በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ በኩል ማገልገል፣” ሊያሆና፣ ሰኔ 2020 (እ.አ.አ)
የአገልግሎት መርሆዎች፣ ሰኔ 2020 (እ.አ.አ)
በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ በኩል ማገልገል
የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ከሌሎች ጋር ለመገናኘትና አገልግሎትን ለመስጠት እድልን ይሰጣል።
የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ መንፈሳዊ ምግብ የምንመገብበት እንዲሁም በአዳኙና በኃጢያት ክፍያው ላይ ግላዊ ማሰላሰል በማድረግ የምናሳልፍበት ጊዜ ነው። ቅዱስ ቁርባንን በየሳምንቱ ስንካፈል፣ በጋራ እንታነፃለን ( ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 84፥110ይመልከቱ)። ነገር ግን በአጥቢያዎቻችንና በቅርንጫፎቻችን ውስጥ አንዳንዶች ከባድ ሸክምን ከራሳቸው ጋር ይዘው ይመጣሉ ወይም በቦታው አይገኙም።
ያንን ቅዱስ የሆነ ሰዓት ሌሎችን ለማገልገልና በህይወታቸው ውስጥ ለውጥን ለማምጣት እንዴት መጠቀም እንደምንችል የተወሰኑ እድሎች የሚከተሉት ናቸው።
ለምታገለግሏቸው ሰዎች የቅዱስ ቁርባን ስብሰባን የተሻለ እንዲሆን እርዱ።
እንዴት ማገልገል እንዳለብን ለመረዳት የመጀመሪያው ደረጃ ግለሰቦቹን ወይም ቤተሰባቸውንና ፍላጎታችውን ማወቅ ነው። ዝም ብላችሁ ስለእነሱ ይበልጥ በማወቅ የቅዱስ ቁርባን አምልኮ ልምዳቸውን የምታሻሽሉባችው መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ።
የሁለት መንትዬ ህፃን ልጆች እናት ለሆነችው ሚንዲ የአገልግሎት እህቷ ያደረገችው ቀላል ጥረት በየሳምንቱ በሚደረገው የቅዱስ ቁርባን ስብሰባዋ ላይ ታላቅ ለውጥን አመጣ።
“በባለቤቴ የስራ የጊዜ ሰሌዳ ምክንያት በየሳምንቱ መንትያ ሴት ልጆቼን ወደ ቤተክርስቲያን እራሴ ነው የምወስዳቸው” በማለት ሚንዲ ገለፀች። “የቅዱስ ቁርባን ስብሰባን በሙሉ ከሁለት ህፃናት ጋር ማሳለፍ በጣም አስቸጋሪ ነው ነገር ግን የአገልግሎት እህቴ እኔን ለመርዳት በራሷ ወሰነች።
“በየሳምንቱ ከአጠገባችን ተቀምጣ ሴት ልጆቼን በመጠበቅ ትረዳኛለች። ከጎኔ መሆኗ ብቻ ትልቅ ትርጉም አለው እንዲሁም በሚያስቸግሩ ሰዓት ጭንቀቴን ቀለል ያደርግልኛል። ተግባሯ በዚህ የህይወቴ ጊዜ ምን ያህል እንደነካኝ ታውቃለች ብዬ አላስብም። እንደ በጭንቀት የተሞላች ወጣት እናት ፍላጎቴን ተመልክታ ለሁላችንም ቤተክርስቲያን ሰላማዊና አስደሳች ቦታ እንዲሆን እረዳችን።
ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት የሚቀርቡ ሀሳቦች
-
ለሽማግሌዎች ቡድንና ለሴቶች መረዳጃ ማህበር መሪዎች የአባላትን ፍላጎት ሪፖርት አድርጉ።
-
መሪዎች የአባላትን ፍላጎቶች እዲያሟሉ ለመርዳት የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ንግግሮችን ያቅዳሉ። የምታገለግሏቸው ሰዎች የሆነ መልዕክት በመስማት የሚጠቀሙ መስሎ ከታያችሁ ሃሳቡን ለመሪያችሁ አካፍሉ።
-
የቅዱስ ቁርባንን በረከቶች ለመካፈል የሚያግድ የአካል ጉድለት ወይም የምግብ አለርጂ ያለው ሰው የምታውቁ ከሆነ ለበለጠ መረጃ እና የአምልኮ ልምዳቸውን ለማሻሻል እንዲረዳ ምን ማድረግ እንደሚቻል ጠይቋቸው። ይህንን መረጃ ከመሪያችሁ ጋር ተካፈሉ።
-
የምታገለግሉት ወይም የምታውቁት ሰው ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረጅም ጊዜ የቤት ጥገኛ መሆኑን ካወቃችሁ ቅዱስ ቁርባን ወደቤት ሊወሰድ ይቻል እንደሆነ ኤጲሰ ቆጶሱን ጠይቁ። በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ወቅት ማስታወሻ በመያዝ በስልክ፣ በኢሜል፣ ወይም በአካል ማካፈል እራሱ ትችላላችሁ።
-
የምታገለግሏቸው ሰዎች ትትንሽ ልጆች ካላቸው በቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎች ጊዜ ለመርዳት ሃሳብ ማቅረብም ትችላላችሁ።
-
የምታገለግሏቸው ሰዎች ወደ ቅዱስ ቁርባን ስብሰባ በቋሚነት የማይመጡ ከሆነ ልትረዱ እና ልታግዙ የምትችሉባቸውን መንገዶች ፈልጉ። የትራንስፖርት መጓጓዣ መንገድ ካስፈለጋቸው ልታጓጉዟቸው ሃሳብ ማቅረብ ትችላላችሁ። በቤተሰባቸው የማይደገፉ መስሎ ከተሰማችው አብረዋችሁ እንዲቀመጡ መጋበዝ ትችላላችሁ። በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ የተቀባይነትና የተፈላጊነት ስሜት እንዲሰማቸው ለመርዳት የተለየ ግብዣ ማድረግ ትችላላችሁ።
ትንሽ ድርጊት ረጅም ርቀት እንደሚሄድ አስታውሱ።
ስለ አገልግሎት በመናገር፣ የሴቶች መረዳጃ ማህበር አጠቃላይ ፕሬዝዳንት እህት ጂን ቢ. ቢንገም እንዲህ ስትል አስትምራለቸ፤ “አንዳንዴ ጎረቤታችንን ለማገልገል ታላቅንና ጀግናዊ ነገሮችን ማድረግ እንዳለብን እናስባለን። ትንሽዬ የሆነ የአገልግሎት ተግባር በሌሎች ላይ እንዲሁም በራሳችን ላይ ታላቅ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል።”1
በቤልጂየም በትንሽ አጥቢያ ውስጥ፣ ኤቪታ ብዙውን ጊዜ ለስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጎብኚዎችና አባሎች በቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ወቅት ለመተርጎም ፍቃደኛ ትሆናለች። አንድ ጊዜ ኤቪታ ስለቤተክርስቲያን ከሚማር የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ግለሰብ ጋር ተዋወቀች። የተወሰነ እንግሊዝኛ ያውቅ ነበር፣ ነገር ግን አፉን የፈታው በስፓንኛ ቋንቋ ነበር። ስለዚህ ኤቪታ ቀስ ብላ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ውስጥ ለእሱ ለመተርጎም ፍቃደኛ ሆነች እርሱ ይበልጥ ምቾት ተሰማው ።
“መተርጎም አንዳንዴ ሰንበቴን ትንሽ ያጨናንቀዋል” በማለት ትናገራለች ኤቪታ። “ነገር ግን ሌሎችን ተርጓሚ ይፈልጉ እንደሆነ ለመጠየቅ መነሳሳትን መከተልና መንፈስን እንዲሰማቸውና ስብሰባቸውን እንዲደሰቱበት መርዳቴን ማወቄ በትክክል ደስታ ይሰጠኛል።”
በትንንሽ ድርጊቶች አማካኝነት የመርዳት ሃሳቦች
-
በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ጊዜ ትንሽ ተጨማሪ አገልግሎት ማን እንደሚፈልግ ለማየት ከመሪያችሁ ጋር ተነጋገሩ። ወይም የሚያስፈልገውን ሰው ካወቃችሁ መሪዎቻችሁ ስለነሱ እንዲያውቁ ማድረጋችሁን እርግጠኛ ሁኑ።
-
ስብሰባው እስኪጀመር በምትጠብቁበት ጊዜ በጸጥታ ተቀመጡ። ይህም በቅዱስ ቦታ ክብር አማካኝነት የሚመጣውን ሰላም የሚፈልጉትን በዙሪያችን ያሉትን “የተሰበሩ ልቦችንና ያዘኑ መንፈሶችን”2 ይረዳል።
-
በፆም ሰንበት ወቅት ፆማችሁንና ፀሎታችሁን ተጨማሪ ምቾትን ወደሚፈልጉት ለምታገለግሏቸው ሰዎች እንዲሆን አስቡ።
-
በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ጊዜ ከጎን ወይም ከአጠገብ በመቀመጥ የሚጠቀም ሰው እንዳለ ወይም እናንተ ለመርዳት የምትችሉበት ሌላ መንገድ እንዳለ ለማወቅ እንድትችሉ ፀልዩ።
የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ለሁሉም የተቀባይነት ቦታ ሊሆን ይችላል።
ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ፊልዲንግ ስሚዝ (1876–1972) እንዲህ አስተምረዋል፣ “የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ከቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ሁሉ በጣም የተቀደሰ ነው።”3 የቅዱስ ቁርባን ስብሰባን የሚካፈሉ ሁሉ ተቀባይነት እንዲሰማቸውና በመንፈስ መመገባቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፣ በተለይም አዲስ አባሎችን ወይም ለረጅም ጊዜ አገልግሎትን ያልተካፈሉ አባሎችን ጨምሮ።
በኒው ሳውዝ ዌልስ፣ አውስትራሊያ የምትኖረው ሜራኒያ በአጥቢያዋ ውስጥ ስለቤተክርስቲያን እየተማረች ያለችን አንድ ሴት ልጅን ጓደኛ አደረገች። “አሁን ከውድ ጓደኞቼ መካከል አንዷ ሆናለች፣” ሜራኒያ አለች። “በየሳምንቱ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ውስጥ ከእሷ ጋር መቀመጥን እወዳለው፣ እንዴት እንደሆነችና እሷን ለመርዳት ማድረግ የምችለው ነገር እንዳለ ሁሌም እጠይቃለው።” ከትንሽ ጊዜ በኋላ የሜራኒያ ጓደኛ ተጠመቀች። የአጥቢያ አባላት ድጋፍ፣ እንዲሁም በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የነበረው የተቀባይነት ሁኔታ፣ በውሳኔዋ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሮባታል።
ተመላሽ ወይም አዲስ አባላትን ለማገልገል የሚቀርብ ሃሳብ
-
በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ውስጥ ንግግር ልታደርጉ ስትሉ ጓደኞችን፣ ቤተሰቦችን እና ሌሎች ሰዎችን መልዕክታችሁን መጥተው እንዲሰሙ መጋበዝ ትችላላችሁ።
-
ብቻቸውን ያሉ እና እርዳታ ሊሹ የሚችሉ ሰዎችን ለመመልከት እና ተቀባይት እንዲሰማቸው ለማድረግ ትችላላችሁ። ከጎናቸው መቀመጥ ትችሉ ዘንድ ጠይቋቸው ወይም ከአጠገባችሁ እንዲቀመጡ ጋብዟቸው።
-
ስብሰባው ሲጠናቀቅ የምታገለግሏቸውን ሰዎችና ሌሎችን ለቀጣይ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎች፣ ለቤተ መቅደስ ጉዞ፣ ወይም ለማህበራዊ ክስተቶች ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ።
-
የምታገለግሏቸው ሰዎች የቅዱስ ቁርባን ስብሰባን የሚካፈሉ ከሆነ፣ ነገር ግን ከተካፈሉ ብዙ ጊዜ ከሆናቸው፣ ስለትምህርቱ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳላቸው ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ያልተረዱት ሃረግ፣ ታሪክ፣ ወይም የትምህርት አካል ካላ ሁሌም መጥተው ሊጠይቋችሁ እንደሚችሉ ንገሯቸው። አስፈላጊ ከሆነ መልሶቹን በጋራ መመልከት ትችላላችሁ።
© 2020 (እ.ኤ.አ) በ Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፥ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፥ 6/19። ትርጉም Ministering Principles, June 2020. Amharic. 16988 506