2023 (እ.አ.አ)
የክህነት በረከቶች
መጋቢት 2023 (እ.አ.አ)


“የክህነት በረከቶች፣” ሊያሆና፣ መጋቢት 2023 (እ.አ.አ)።

ወርኃዊ የሊያሆና መልዕክት፣ መጋቢት 2023 (እ.አ.አ)

የክህነት በረከቶች

ክርስቶስ አስራ ሁለቱን ሐዋሪያት ሲሾም

ክርስቶስ አስራ ሁለቱን ሐዋሪያት ሲሾም፣ በሔሪ አንደርሰን

የክህነት በረከት በመልከ ጼዴቅ የክህነት ስልጣን ተሸካሚ በኩል በመነሳሳት ይሰጣል። የክህነት በረከቶች ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ኃይሉን፣ ፈውሱን፣ መፅናናቱን እና መመሪያውን እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል።

ክህነት

ክህነት የእግዚያብሔር ሃይል እና ስልጣን ነው። ብቁ የሆኑ የመልከ ጼዴቅ ክህነት ተሸካሚዎች የክህነት በረከቶችን በሚሰጡበት ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰራሉ። እነዚህን በረከቶች ሲሰጡ፣ ሌሎችን የመባረክን የአዳኙን ምሳሌ ይከተላሉ።

እጆች በጭንቅላት ላይ ተጭነው

ፎቶ በዴቪድ ዊንተርስ

በረከቶች የሚሰጡት እንዴት ነው

የክህነት በረከቶች የሚሰጡት እጅን በመጫን ነው። የመልከ ጼዴቅ ክህነት ተሸካሚ እጆቹን በረከቱን በሚቀበለው ሰው ራስ ላይ ይጭናል። ከዚያም መንፈሱ እንደሚመራው በረከቱን ይሰጣል። በረከቶችን የሚሰጡ እና የሚቀበሉ በእግዚአብሔር ያምናሉ እንዲሁም በፈቃዱና በጊዜው ይታመናሉ።

ልጆችን መሰየም እና መባረክ

ልጅ ከተወለደ/ች በኋላ፣ የክህነት ስልጣን ተሸካሚ እርሱን/እርሷን ይሰይማል እንዲሁም ይባርካል።( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥70ተመልከቱ)። ይህ በአብዛኛው ጊዜ የሚከናወነው በጾም እና ምስክርነት ስብሰባ ላይ ነው። በመጀመሪያ ልጁ ይሰየማል። ከዚያም የክህነት ተሸካሚው ለልጁ በረከትን ይሰጣል።

የታመመ ወንድ ልጅ የክህነት በረከትን ሲቀበል።

ፎቶ በ ዌልደን ሲ. አንደርሰን

ለታመሙ በረከትን መስጠት

የመልከ ጼዴቅ ክህነት ተሸካሚዎች ለታመሙ ሰዎች በረከትን መስጠት ይችላሉ። እንደዚህ አይነት በረከት ሁለት ክፍል አለው፦ በዘይት መቀባት እና ቅብዓትን ማተም። በመጀመሪያ፣ የክህነት ስልጣን ተሸካሚ የተቀደሰ ወይም የተባረከ የወይራ ዘይት ጠብታ በሰውዬው ራስ ላይ ያደርጋል ከዚያም አጭር ጸሎት ይሰጣል። ከዚያም ሌላ የክህነት ስልጣን ተሸካሚ ቅብዓቱን ያትማል እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለግለሰቡ በረከትን ይሰጣል።

የመጽናናት እና የምክር በረከቶች

የመልከ ጼዴቅ ክህነት ተሸካሚዎች ለቤተሰብ አባላት እና ለሌሎች ለሚጠይቁ የማጽናኛ እና የምክር በረከቶችን ሊሰጡ ይችላሉ። የመልከ ጼዴቅ ክህነት ተሸካሚ የሆነ አባት የአባትን በረከቶች ለልጆቹ መስጠት ይችላል። እነዚህ በተለይ ልጆች ልዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ለማገልገል ጥሪ የተሰጣቸውን መለየት

የቤተክርስቲያኗ አባላት ጥሪዎችን ሲቀበሉ፣ ለማገልገል በሚለዩበት ጊዜ በረከት ይሰጣቸዋል። የክህነት መሪ በጥሪው ለመስራት እንዲችሉ ስልጣን የሚሰጥ በረከት ይሰጣቸዋል። የክህነት መሪው በአገልግሎታቸው እንዲረዳቸውም በረከትን ይሰጣቸዋል።

ሴት የፓትርያርክ በረከቷን እያነበበች

ፎቶ በሻና ስቲቨንሰን

የፓትሪያርክ በረከቶች

እያንዳንዱ ብቁ የቤተክርስቲያን አባል የፓትርያርክ በረከትን ማግኘት ይችላል። ይህ በረከት ከጌታ የመጣ የግል ምክር ይሰጣል። በአንድ ሰው መላ ህይወት ውስጥ መመሪያ እና ማጽናኛ ሊሰጥ ይችላል። በእስራኤል ቤት ውስጥ ያለውን የሰውየውን የዘር ሐረግም ይናገራል። የተሾመ ፓትሪያርክ ብቻ እንደዚህ አይነት በረከትን መስጠት ይችላል።