ሊያሆና
የጌታ ታላቅ ስራ እና የእኛ ታላቅ እድል
ሐምሌ 2024 (እ.አ.አ)


“የጌታ ታላቅ ስራ እና የእኛ ታላቅ እድል፣” ሊያሆና፣ ሐምሌ 2024 (እ.አ.አ)

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሐምሌ 2024 (እ.አ.አ)

የጌታ ታላቅ ስራ እና የእኛ ታላቅ እድል

ሌሎችን ስንወድ፣ ስናካፍል እና ስንጋብዝ፣ እያንዳንዱን ዋጋ የማይተመንለት ነፍስ ወደ እርሱ ለማምጣት ከጌታ ጋር እየሰራን ነው፡፡

ምስል
ሁለት ሴቶች በመንገድ ላይ እያወሩ ሲራመዱ

በዚህ በመጨረሻው እና ታላቅ ዘመን ያሉ እያንዳንዱ ነቢያት የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እንዲያካፍሉ አስተምረዋል። በህይወት ዘመኔ ብዙ ምሳሌዎችን አስታውሳለሁ፦

የወጣትነት ጊዜዬ ነብይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዴቪድኦ. መኬይ [1873-1970 (እ.አ.አ)]፣ እንዲህ ብለዋል፣ “እያንዳንዱ አባል ሚስዮን ነው።”

ፕሬዚደንት ስፔንሰር ደብሊው ኪምባል [1895-1985 (እ.አ.አ)] እንዲህ ሲለ አስተምረዋል፣ “ወንጌልን ወደ ብዙ ቦታዎች እና ህዝቦች የመውሰድ ጊዜ ደርሷል እናም አሁን ነው፣” እንዲሁም ወንጌልን ለሌሎች የማካፈል “ጥረታችንን ማጠናከር አለብን።”

ፕሬዚዳንት ጎርደን ቢ. ሂንክሊ [1910-2008 (እ.አ.አ)] እንዲህ ብለዋል፤ “የሚማሩትን ለማግኘት በምናደርገው እገዛ ስራችን ታላቅ ነው እንዲሁም ሃላፊነታችን ልዩ ነው። ለሁሉም ፍጥረታት ወንጌልን እናስተምር ዘንድ ጌታ ሥልጣንን ሠጥቶናል። ይህ ከሁሉ የተሻለውን ጥረታችንን ይጠይቃል።”

እንዲሁም ፕሬዚዳንት ረሰል ኤም ኔልሰን እንዲህ አስተምረዋል፤ “የሚስዮናዊ ስራ የታላቁ እስራኤልን የመሰብሰብ ሥራ አስፈላጊ አካል ነው። ያ መሰብሰብ አሁን በምድር ላይ እየተሰሩ ካሉት ስራዎች እጅግ አስፈላጊው ስራ ነው። ያን ያህል ክብደት የሚሰጠው ሌላ ምንም ነገር የለም። ያን ያህል ጠቀሜታ ያለው ሌላ ምንም ነገር የለም። የጌታ ሚስዮናውያን—ደቀ መዛሙርቱ—ዛሬ በትልቁ ፈታኝ ሁኔታ፣ በታላቁ ምክንያት፣ በምድር ላይ ባለው በታላቁ ስራ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።”

በብሪቲሽ ሚሲዮን ወጣት ሚሲዮናዊ ሳለሁ ይህን በራሴ ለማወቅ ችያለው። ዛሬ ስለሱ የበለጠ እርግጠኛ ነኝ። እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ፣ ሌሎች ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ ፍቅራችንን በማሳየት፣ እምነታችንን በማካፈል፣ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ደስታ ተሞክሮን ለማግኘት ከእኛ ጋር እንዲሆኑ የመጋበዝ ዕድሎች በየቦታው እንዳሉ እመሰክራለሁ።

ሥራው ወደፊት ይሄዳል

የመጀመሪያው ወንጌሌን ስበኩ ህትመት በ 2004 (እ.አ.አ) ሲተዋወቅ እንዲሁም ሁለተኛው ህትመት በ2023 (እ.አ.አ) ሲለቀቅ በቤበተክርስቲያኗ የሚስዮን ክፍል ውስጥ ተመድቤ የነበርኩ በመሆኔ እድለኛ ነበርኩ። ወንጌሌን ስበኩ በልዩ ሁኔታ የሚስዮን ሥራን እንደባረከ አምናለሁ።

አዲሱ ወንጌሌን ስበኩ ከ2004 (እ.አ.አ) ጀምሮ የተማርነውን፣ ከእያንዳንዱ ቀዳሚ አመራር እና ከአስራ ሁለቱ ሃዋርያት ቡድን አባላት የመጡትን መንፈሳዊ ምሪቶች እና በዲጂታል ዘመን ወንጌልን ለማካፈል የተደረጉ ለውጦችን ሁሉ ያካትታል። እነዚህ አንዳንድ ለውጦች አስፈላጊ ስኬቶችን አምጥተዋል።

በቀላል፣ የተለመደ፣ እና ተፈጥሯዊ መንገዶች “በፍቅር፣ በማካፈል፣ በመጋበዝ” መርሆዎች ወንጌልን ማካፈል መንግስቱን በታላቁ እንደሚባርክ ተገንዝበናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ጊዜ በዚህ መንገድ ነበር ወንጌልን ያካፈለው። ህይወቱን እና ፍቅሩን አካፈለ እንዲሁም ሁሉም ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋበዘ (ማቴዎስ 11፥28 ይመልከቱ)። እርሱ እንዳደረገው ማፍቀር፣ ማካፈል እና መጋበዝ ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያኗ አባል ልዩ በረከት እና ኃላፊነት ነው።

በፍቅር ጀምሩ

በጌተሴማኒ የአትክልት ስፍራ እና በመስቀል ላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእራሱ ላይ የአለምን ሃጢያት ወሰደ፣ሁሉንም ስቃይ እንዲሁም “በመከራ እናም በሁሉም አይነት ህመም እና ፈተናዎች” ተሰቃየ (አልማ 7፥11)። ይህ “ታላቅ እና ማለቂያ የሌለው መከራ [እርሱ] … ከስቃዩ የተነሳ እን[ዲ]ንቀጠቀጥ እናም ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እን[ዲ]ደማ” አደረገው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥18)። በኃጢያት ክፍያው እና በትንሳኤው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደህንነትን እና በዘለዓለማዊ ህይወት ከፍ ከፍ መደረግን ለሁሉም እንዲሆን አድርጓል።

ወደ አዳኙ ዘወር ማለት እና ያደረገልንን ሁሉ ማሰላሰላችን በእርሱ ፍቅር የተሞላ ልብ እንዲኖረን ያደርጋል። ከዚያም ልባችንን ወደ ሌሎች ይመልሣል፤ እንድንወዳቸው (ዮሐንስ 13፥34-35ን ይመልከቱ) እና ወንጌልን ለእነርሱ እንድናካፍልም ያዘናል (ማቴዎስ 28፥19)ማርቆስ 16፥15ን ይመልከቱ)። በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች በእውነት እንደምንወዳቸው እና እንደምንከባከባቸው የሚሰማቸው ከሆነ፣ በአሞን ፍቅር እና አገልግሎት ምክንያት ንጉስ ላሞኒ ወንጌልን ለመቀበል ልቡን እንደከፈተ ሁሉ ለመልእክቶቻችን ልባቸውን ይከፍቱ ይሆናል (አልማ 17-19ን ይመልከቱ)።

ወንጌልን ማካፈል ስንጀመር፣ ከፍቅር እንጀምር። ሌሎችን በፍቅር ስንረዳቸው—ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እና የተወደዱ የሰማይ አባታችን ልጆች መሆናቸውን በማስታወስ—እውነት እንደሆነ የምናውቀውን እንድናካፍል እድሎች ይከፈቱልናል።

በጽኑ ተሳተፉ እና አካፍሉ

ከፕሬዚዳንት ኤም. ረሰል ባላርድ [1928-2023 (እ.አ.አ)] የበለጠ ወንጌልን በማካፈል ታታሪ ማንም አልነበረም። በመጨረሻው የአጠቃላይ ጉባኤ መልክታቸው፣ እንዲህ ሲሉ ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል፣ “በዚህ በኋለኛው ቀን የሰማይ አባታችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሳቸውን እንደገለጡ እና ጆሴፍ የዘለዓለም ወንጌልን ሙላት ዳግም ለመመለስ መነሳቱን ማወቅ በዚህ አለም ውስጥ ያለ ማንም ሰው ሊያውቀው ከሚችለው በላይ እጅግ ከከበረ እና አስደናቂ ነገሮች አንዱ ነው።”

በህይወት ዘመናቸው እና በአብዛኛው የአለም ክፍሎች፣ ፕሬዚዳንት ባላርድ ይህን ውድ መልእክት ለሁሉም ሰው በማካፈል በጽኑ ተሳትፈው ነበር። እኛም እንዲሁ እንድናደርግ አበረታተውናል። “መልካም ባልንጀሮች በመሆን፣ በመተሳሰብና ፍቅር በማሳየት” ወንጌልን እንድናካፍል አስተምረዋል። ይህን በማድረግ፣ “ወንጌልን በሕይወታችን ውስጥ እናሰራጫለን፣ እና … ወንጌል የሚያቀርበውን በረከቶች [ለሌሎች] እናበራለን።” እናም እኛ “የምናውቀውን እና የምናምነውን እንዲሁም የሚሰማንን ምስክርነት እናካፍላለን”። ፕሬዚዳንት ባላርድ እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፣ “ንፁህ ምስክርነት በመንፈስ ቅዱስ ሀይል እሱን ለመቀበል ዝግጁ ወደሆኑት ወደ ሌሎች ሰዎች ልብ ሊወሰድ ይችላል።”

ዳግም የተመለሰውን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ማካፈል የፕሬዚዳንት ባላርድ ልብ ከፍተኛ ፍላጎት ነበር። እርሳቸው እንደነበሩት ሁሉ፣ እኛም ወንጌልን በቃል እናም በስራ ለማካፈል በጽኑ መሳተፍ እንችላለለን። ከመካከላችን እነማን የወንጌልን ብርሃን እየፈለጉ እንዳሉ ሆኖም የት ሊያገኙት እንደሚችሉ የማያውቁ ሰዎችን ማወቅ አንችልም (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 123፥12 ይመልከቱ)።

ምስል
ሁለት ወንዶች ደረጃዎችን እየወጡ

ከልብ የመነጨ ግብዣን አቅርቡ

ሌሎች ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ በመርዳት፣ አዳኙ እና ወንጌሉ የሚያመጡትን ደስታ እንዲለማመዱ እንጋብዛቸዋለን። ወደ ዝግጅቶች እንዲመጡ፣ መፅሐፈ ሞርሞንን እንዲያነቡ ወይም ከሚስዮናውያን ጋር እንዲገናኙ በመጋበዝ ይህንን ማድረግ እንችላለን። እንዲሁም ከእኛ ጋር በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ልባዊ ግብዣ ልናቀርብላቸው እንችላለን።

በየሳምንቱ “እግዚአብሔርን ለማምለክ እና ኢየሱስ ክርስቶስን እና የኃጢያት ክፍያውን ለማስታወስ ቅዱስ ቁርባንን ለመካፈል” በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንገኛለን። ይህ ሰዎች መንፈስን የሚሰማቸው፣ ወደ አዳኝ የሚቀርቡበት እና በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠነክሩበት አመቺ ጊዜ ነው።

ለመውደድ፣ ለማካፈል እና ለመጋበዝ መንገዶችን ስንፈልግ እቅዳችን እና ጥረታችን ሰዎች በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ መርዳትን ማካተት አለበት። ጥሪያችንን ከተቀበሉ እና በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ ከተገኙ፣ ወደ ጥምቀት እና ወደ መለወጥ መንገድ የመቀጠል ዕድላቸው ሰፊ ነው። ሌሎችን በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ስንጋብዝ እና ይህን በማድረግ የሚያገኟቸውን በረከቶች እንዲገነዘቡ ስንረዳ ታላቅ ስኬት እንደሚመጣ በሙሉ ልቤ አምናለሁ።

ጌታ ይመራናል

ስንወድ፣ ስናካፍል እና ስንጋብዝ ምን አይነት ስኬቶች እና ፈተናዎች እንደሚኖሩን አናውቅም። የሞዛያ ልጆች “ከከተማ ወደ ከተማ፣ እና ከአንዱ የአምልኮ ቤት ወደ ሌላው፣… በላማናውያን መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ እና ለማስተማር ወጡ፣ እናም ታላቅ ስኬት ማግኘት ጀመሩ።” በጥረታቸው፣ “ሺዎች ወደ ጌታ እውቀት መጡ” እና ብዙዎች “ተለወጡ… [እና] በጭራሽ አልወደቁም” (አልማ 23፥4–6)።

ይህ ሁልጊዜ የእኛ ተሞክሮ ባይሆንም፣ እያንዳንዱ ነፍስ ለእርሱ ውድ ስለሆነች ከእኛ ጋር እንደሚሠራ ጌታ ቃል ገብቷል። በጌታ ስንታመን እና በአገልግሎቱ ስንሳተፍ፣ እርሱን በመውደድ፣ ህይወታችንን እና ምስክርነታችንን ከእነሱ ጋር በማካፈል እና እርሱን እንድንከተል በመጋበዝ ወንጌሉን እንዴት እንደምናካፍል ይመራናል።

ነፍሳትን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የማምጣት ታላቅ ሥራውን ለመርዳት በዙሪያችን ያሉትን እድሎች ስንጠቀም “ደስታ[ችን] ታላቅ ይሆናል” (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 18፥15)።

ማስታወሻ

  1. Teachings of Presidents of the Church: David O. McKay[የቤተክርስቲያና ፕሬዚዳንቶች ትምህርቶች፦ ስፔንሰር ደብሊው ኪምባል] (2003 እ.አ.አ)፣ 14።

  2. Teachings of Presidents of the Church: Spencer W. Kimball[የቤተክርስቲያና ፕሬዝደንቶች ትምህርቶችት፦ ስፔንሰር ደብሊው ኪምባል] [2006 (እ.አ.አ)]፣ 261፣ 262።

  3. ጎርደን ቢ ሂንክሊ፣ “Find the Lambs, Feed the Sheep፣”ሊያሆና፣ ሐምሌ 1999 (እ.አ.አ), 121። ይህ መልዕክት የተላለፈው የካቲት 21፣ 1999 (እ.አ.አ)፣ ከሶልት ሌክ ሲቲ ታበርናክል ሳተላይት ማሰራጫ ነበር።

  4. ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2022 (እ.አ.አ)፣ 9።

  5. ኤም. ረሰል ባላርድ “Praise to the Man፣”ሊያሆና፣ ግንቦት 2003 (እ.አ.አ)፣ 74።

  6. ኤም. ረሰል ባላርድ “The Essential Role of Member Missionary Work፣”ሊያሆና ግንቦት 2003 (እ.አ.አ)፣ 40።

  7. ኤም. ረሰል ባላርድ፣ “በበለጠ ወሳኝ የሆነውን ነገር አስታውሱ፣”ሊያሆና፣ ግንቦት 2003 (እ.አ.አ)፣ 107።

  8. ወንጌሌን ስበኩ፦ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የማካፈል መመሪያ [2023 (እ.አ.አ)]፣ 88።

  9. ወንጌሌን ስበኩ፣ 172 ይመልከቱ።

አትም