ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፬


ምዕራፍ ፬

ጦርነትና እልቂት ቀጠለ—ኃጥአን ኃጥአንን ይቀጣሉ—በእስራኤል ሁሉ ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ ታላቅ ክፋት ሠፈነ—ሴቶችና ልጆች ለጣዖት መስዋዕት ሆኑ—ላማናውያን ኔፋውያንን ከፊታቸው መጥረግ ጀመሩ። ከ፫፻፷፫–፫፻፸፭ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ ስልሳ ሦስተኛው ዓመት ኔፋውያን ከወደመው ምድር ወጥተው ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ከሠራዊታቸው ጋር ሄዱ።

እናም እንዲህ ሆነ የኔፋውያን ሠራዊቶች በድጋሚ ወደ ወደመችው ምድር ተገፍተው ተመለሱ። እናም በደከሙበት ጊዜ፣ ምንም ያልደከማቸው የላማናውያን ሠራዊቶች መጡባቸው፤ እናም አሰቃቂ ጦርነት አደረጉ፤ በዚህም የተነሳ ላማናውያን የወደመችውን ከተማ ወሰዱ፣ እናም ብዙ ኔፋውያንን ገደሉና፣ ብዙ እስረኞችንም ወሰዱ።

እናም ቀሪዎቹ ሸሹና ከቴአንኩም ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተቀላቀሉ። እንግዲህ የቴአንኩም ከተማም በባሕሩ ዳርቻ ነበረች፤ እንዲሁም ደግሞ በወደመችው ከተማ አጠገብ ነበረች።

እናም የኔፋውያን ወታደሮች ላማናውያንን ለማጥቃት በመሔዳቸው መመታት ተጀመሩ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ላማናውያን በእነርሱ ላይ ኃይል ሊኖራቸው አይችልም ነበርና።

ነገር ግን እነሆ፣ የእግዚአብሔር ቅጣት በክፉዎች ላይ ይደርሳል፤ እናም ኃጥአን የሚቀጡት በኃጢአተኞች ነው፤ ምክንያቱም ኃጥአን ናቸው የሰው ልጆችን ልብ ለደም መፋሰስ የሚቀሰቅሱትና።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን በቴአንኩም ከተማ ላይ ጥቃት ለማካሄድ ዝግጅት አደረጉ።

እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ ሥልሳ አራተኛው ዓመት ላማናውያን የቴአንኩምን ከተማ ይወስዱ ዘንድ ወደ ቴአንኩም ከተማ መጡ።

እናም እንዲህ ሆነ በኔፋውያን ተሸነፉና ተገፍተው ተመለሱ። እናም ኔፋውያን ላማናውያንን ማባረራቸውን በተመለከቱ ጊዜ በጥንካሬአቸው በድጋሚ ተኩራሩ፤ በጉልበታቸውም ተማምነው ወደፊት ቀጠሉና፣ በድጋሚ የወደመችውን ከተማ ወሰዱ።

እናም እንግዲህ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ተፈፅመዋል፣ እናም በኔፋውያንም ሆነ በላማናውያን በኩል በሺህ የሚቆጠሩ ተገደሉ።

እናም እንዲህ ሆነ ሦስት መቶ ሥልሳ ስድስት ዓመት አለፈ፤ ላማናውያንም በድጋሚ ኔፋውያንን ለመውጋት መጡ፤ እናም ኔፋውያን ለሰሯቸው ክፉ ሥራዎች ንሰሃ ገና አልገቡም፤ ነገር ግን ያለማቋረጥ በክፋታቸው ቀጠሉ።

፲፩ እናም በኔፋውያን እንዲሁም በላማናውያን መካከል አሰቃቂ የነበረውን ደም መፋሰስና ዕልቂት በአንደበት ለመግለፅም ሆነ ለሰው ሁኔታውን ሙሉ ለሙሉ ለመፃፍ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ እናም የሁሉም ልብ የጠጠረ ነበር ስለዚህ ያለማቋረጥ በሚፈሰው ደም ተደሰቱ።

፲፪ እናም በጌታ ቃል መሰረት፣ በእነዚህ ሰዎች መካከል እንደነበረው አይነት ታላቅ ክፋት በሌሂም ልጆች ሆነ በእስራኤል ቤት ሁሉ መካከል በጭራሽ አልነበረም።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን የወደመችውን ከተማ ወሰዱ፤ እናም ይህም የሆነበት ምክንያት ቁጥራቸው ከኔፋውያን ይበልጥ ስለነበር ነው።

፲፬ እናም ደግሞ ወደ ቴአንኩም ከተማ ዘመቱና፣ ነዋሪዎችዋን አስወጡ፣ እናም ከሴቶችና ልጆች በተጨማሪ ብዙ እስረኞችን ወሰዱ፣ እናም ለሚያመልኩት ጣዖት መስዋዕት አቀረቡዋቸው።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ ሥልሳ ሰባተኛው ዓመት፣ ኔፋውያን ላማናውያን ሴቶቻቸውንና ልጆቻቸውን መስዋዕት ስላደረጉባቸው ላማናውያንን በእጅጉ አጠቁአቸው፤ ስለዚህ በድጋሚ ላማናውያንን አሸነፉአቸውና ከምድራቸውም አባረሩአቸው።

፲፮ እናም እስከ ሦስት መቶ ሰባ አምስተኛው ዓመት ድረስ ላማናውያን በድጋሚ ኔፋውያንን አልወጉአቸውም።

፲፯ እናም በዚህ ዓመት ባላቸው ኃይል ሁሉ ኔፋውያንን ወጉአቸው፤ እናም በቁጥርም ብዙ በመሆናቸው አልተቆጠሩም ነበር።

፲፰ እናም ከዚህ ጊዜም ጀምሮ ኔፋውያን በላማናውያን ላይ ድል አላገኙም፤ ነገር ግን ጤዛ በፀሀይ እንደሚበተን እነርሱም መጥፋት ጀመሩ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን የወደመችውን ከተማ አጠቁ፤ እናም እጅግ አሰቃቂ የሆነ ውጊያ በወደመችው ምድር ነበር፣ በዚያም ኔፋውያንን አሸነፉአቸው።

እናም በድጋሚ እነርሱ ከፊታቸው ሸሹና፣ ወደ ቦአዝ ከተማም መጡ፤ እናም በዚያም ላማናውያንን በድፍረት ተቋቋሙ፤ ስለዚህ ላማናውያንም በእነርሱ ላይ በድጋሚ እስከሚመጡ ድረስ አላሸነፉአቸውም ነበር።

፳፩ እናም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እነርሱ በመጡ ጊዜ፣ ኔፋውያን ተባረሩና፣ በታላቅ ሁኔታም ተገደሉ፤ ሴቶቻቸውና ልጆቻቸው በድጋሚ ለጣዖት መስዋዕት ተደረጉ።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን በድጋሚ በከተማዋም ሆነ በየመንደሩ ያሉትን ነዋሪዎቻቸውን በሙሉ ወስደው ከፊታቸው ሸሹ።

፳፫ እናም እንግዲህ እኔ፣ ሞርሞን፣ ላማናውያን ምድሪቱን ለማጥፋት እንደተቃረቡ በመገንዘቤ፤ ስለዚህ ወደሺም ኮረብታ ሄድኩና፣ አማሮን ለጌታ የደበቀውን መዛግብት በሙሉ ወሰድኩ።