2010 (እ.አ.አ)
የቤተመቅደስ መንገዳችሁ
ኦክተውበር 2010


“የቤተመቅደስ መንገዳችሁ፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2010 (እ.አ.አ)፣ 72–75

ለልጆች

የቤተመቅደስ መንገዳችሁ

የትኛው ቤተመቅደስ ከሁሉም ይበልጥ እንደሚቀርባችሁ ታውቃላችሁ? የዚያን ቤተመቅደስ ስእል ሳሉና በየቀኑ ልታዩት በምትችሉት ቦታ ስቀሉት።

ቤተመቅደስ የጌታ ቤት ነው። ስለሰማይ አባት የምንማርበት፣ ከእርሱ ጋር ቃልኪዳኖችን የምናደርግበት (ቃል የምንገባበት) እና ታላቅ በረከቶችን የምንቀበልበት ቦታ ነው። በቤተመቅደስ ውስጥ ለራሳችን እና ለሞቱ የቤተሰብ አባላት አስፈላጊ ስራ እንሰራለን። በቤተመቅደስ ውስጥ የሚሰሩ ስራዎች ለሙታን መጠመቅን፣ የቤተመቅደስ ቡራኬ መቀበልን እና መታተምን ያካትታሉ። እነዚህ የቤተመቅደስ ስርዓቶች ይባላሉ።

በቤተመቅደስ ውስጥ ምን ይካሄዳል

ለሙታን ጥምቀት

ስምንት አመት ሲሞላችሁ መጠመቅ እና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል መሆን ትችላላችሁ። ብዙዎቹ ቅድመ አያቶቻችሁ ሳይጠመቁ እና የአባልነት ማረጋገጫ ሳይሰጣቸው አልፈዋል። ምንም እንኳን አካላቸው ቢሞትም መንፈሳቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል መማር በሚችሉበት በመንፈሳዊው አለም አሁንም ድረስ አለ።

አስራ ሁለት አመት ሲሞላችሁ ቤተመቅደስ ለመሄድ እና በእነሱ ስም በመጠመቅ እንዲሁም የአባልነት ማረጋገጫ እንዲያገኙ በማድረግ እነዚህን ሰዎች ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ከዚያም እነርሱ ጥምቀቱን እና ማረጋገጫውን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መምረጥ ይችላሉ። ለራሳችሁ ስትጠመቁ እንደምታደርጉትት ሁሉ ለሙታን ስትጠመቁም እንደዚያው ሙሉ ነጭ ትለብሳላችሁ።

በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይጠመቁ የሞቱ የቤተሰብ አባላትን ስም ዝርዝር እንድታዘጋጁ እንዲረዷችሁ ወላጆቻችሁን ጠይቋቸው። ከአሁን በፊት ለእነሱ ለመጠመቅ ወደ ቤተመቅደስ የሄደ ካለ አረጋግጡ።

የቤተመቅደስ ቡራኬ (የመንፈስ ስጦታ)

ከታላቅ የቤተመቅደስ በረከቶች መካከል አንዱ የቤተመቅደስ ቡራኬ ነው። የቤተመቅደስ ቡራኬ “ስጦታ” ማለት ነው የቤተመቅደስ ቡራኬያችሁን ስትቀበሉ ስለ ደህንነት እቅድ የበለጠ ትማራላችሁ እንዲሁም ቃልኪዳኖችን ትገባላችሁ። ቃልኪዳኖች ከሰማይ አባት ጋር የምንገባቸው ስምምነቶች ናቸው። እነዚያን ቃልኪዳኖች ስትጠብቁ አንድ ቀን ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመኖር ትዘጋጃላችሁ።

ቤተመቅደስ ውስጥ የሲለስቲያል ክፍል የሚባል የሚያምር እና ሰላማዊ ክፍል አለ። በሲለስቲያል ክፍል ውስጥ ለሰማይ አባት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ቅርብ እንደሆንን ይሰማናል፤ እናም ከነሱ ጋር በሲለስቲያል መንግስት ውስጥ መኖር ማለት ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል በጥቂቱም ቢሆን ይሰማናል።

ለአሁን እና ለዘላለም መታተም

አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በቤተመቅደስ ውስጥ ሲጋቡ መሰዊያው አጠገብ ይንበረከካሉ እናም ለአሁን እና ለዘላለም ይታተማሉ። ይህ ማለት እነሱ እና ልጆቻቸው እንደዘላለማዊ ቤተሰብ በአንድነት ሊጣመሩ ይችላሉ ማለት ነው። አንድ ቀን ቤተመቅደስ ውስጥ ለማግባት አቅዱ። ይህ ከሁሉ የሚልቅ የቤተመቅደስ በረከት ነው።

የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ

ቤተመቅደስ የተቀደሰ ቦታ ነው። ኤጲስ ቆጶሶች እና የቅርንጫፍ ፕሬዚዳንቶች ቤተመቅደስ ውስጥ የሚገቡ ዝግጁ እና ብቁ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። ወደቤተመቅደስ ከመሄዳችሁ በፊት ከኤጲስ ቅጶሳችሁ ወይም ከቅርንጫፍ ፕሬዚዳንታችሁ ጋር ልዩ የሆነ ቃለመጠይቅ ይኖራችኋል። የቤተክርስቲያኗ ምስክርነት እንዳላችሁ፣ ትዕዛዛትን እንደምትጠብቁ፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችን እንደምትደግፉ፣ የጥበብ ቃልን እንደምትጠብቁ፣ አስራት እንደምትከፍሉ እና በምግባራችሁ እንዲሁም በንግግራችሁ ሃቀኛ ስለመሆናችሁ ጥያቄ ይጠይቃችኋል። ቤተመቅደስ ለመግባት ብቁ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እንድታውቁ ይረዳችኋል።

ቤተመቅደስ ለመግባት አሁን ተዘጋጁ

በጽድቅ ለሚኖሩ እና በቤተመቅደስ ለሚሳተፉ የሰማይ አባት ብዙ በረከቶችን ይሰጣል። ታዳጊ እያላችሁ ቤተመቅደስ ለመግባት መዘጋጀት አስፈላጊ ነው።

የሰማይ አባት ይወዳችኋል እናም የቤተመቅደስ በረከቶችን እንድትቀበሉ ይፈልጋል። የቤተመቅደስ ስርዓቶችን ለራሳችሁ እና ለሌሎች በመፈጸማችሁ ይባርካችኋል። አሁን ላይ ቤተመቅደስ መግባት ባትችሉ እንኳን በአቅራቢያችሁ ቤተመቅደስ ካለ ግቢውን በመጎብኘት እዚያ ያለው መንፈስ እንዲሰማችሁ ማድረግ ትችላላችሁ። የቤተመቅደስ አስፈላጊነትን እንዲያስታውሳችሁ የቤተመቅደስ ምስል ቤታችሁ ውስጥ ማስቀመጥም ትችላላችሁ። ወደ ጌታ ቤት ለመግባት ብቁ እንድትሆኑ በጽድቅ ኑሩ።

በዚህ ምስል ላይ ያለውን መስታወት ተመልከቱ። አንዳንድ የመታተም ክፍሎች እንዲህ አይነት መስታወቶች አሏቸው። በቤተመቅደስ ውስጥ በመታተሙ ምክንያት የኛ ቤተሰብ ልክ መስታወቱ ውስጥ እንዳለው ነጸብራቅ ለዘላለም ሊቀጥል ይችላል።

በዚህ ምስል ውስጥ እና በገጽ 64 ላይ ያለውን የሲለስቲያል ክፍል ምስል ተመልከቱ። የሲለስቲያል ክፍልን ስትመለከቱ ምን ተሰማችሁ?

ቦስተን ማሣቹሴትስ ቤተመቅደስ ጥቅምት 1 ቀን 2000 (እ.አ.አ) ተመረቀ።

ማታተሚያ ክፍል፣ አባ ናይጄርያ ቤተመቅደስ

ሲለስቲያል ክፍል፣ ኑኩአሎፋ ቶንጋ ቤተመቅደስ

አትም