2015 (እ.አ.አ)
መንፈስ ቅዱስ እንደ የእናንተ አጋር
ኖቬምበር 2015


የሴቶች የቤት ለቤት መልእክት፣ ህዳር 2015

መንፈስ ቅዱስ እንደ የእናንተ አጋር

በብቁነት የምንኖር ከሆነ፣ የመንፈስ ቅዱስ በረከት አንዳንዴ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ከእኛ ጋር ሊሆን ይችላል።

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ በዚህ የጌታ ቤተክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሰንበት ቀን ከእናንተ ጋር በመሆኔ አመስጋኝ ነኝ። እናንተ እንደተሰማችሁ ሁሉ ሲነገሩ እና ሲዘመሩ የሰማናቸው ቃላትን እውነታ መንፈስ ሲመሰክር እኔም ተሰምቶኛል።

የዛሬ አላማዬ ከተጠመቅን በኋላ ለእያንዳንዳችን ቃል የተገቡት ስጦታዎች ይገቡናል ለማለት ፍላጎታችሁን እና ቁርጠኝነታችሁን መጨመር ነው። ማረጋገጫ በሚሰጠን ወቅት እነዚህን ቃላት ሰምተናል፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበል(ይ)።”1 ከዚያ ቅፅበት ጀምሮ፣ ህይወታችን ለዘለአለም ተቀየረ።

በብቁነት የምንኖር ከሆነ፣ የመንፈስ ቅዱስ በረከት አንዳንዴ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እንደነበረን ድንቅ ተሞክሮ፣ ሁሌም ከእኛ ጋር ሊሆን ይችላል። ከቅዱስ ቁርባን ፀሎት ላይ ያ ቃልኪዳን እንዴት እንደተሟላ ታውቃላችሁ፤ “አቤቱ የዘለአለም አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህንን ዳቦ ለሚበሉት ነብሳት ሁሉ የልጅህን ስጋ ለማሰብ ይበሉት ዘንድ፣ የልጅህንም ስም በላያቸው ለመውሰድ ፍቃደኞች ይሆኑ ዘንድ፣ እናም ሁልጊዜም እርሱን ሊያስታውሱና የተሰጣቸውንም ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ አቤቱ ለአንተ ለአምላክ፣ ዘለአለማዊ አባትም ይመሰክሩ ዘንድ።”

እና ከዛም ክቡሩ ቃል ኪዳን ይመጣል፤ “መንፈሱ ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር ይሆን ዘንድ” (ት እና ቃ 20፣27{58}፤ አፅእኖት ተጨምሮበት)።

ሁልጊዜ መንፈሱ ከእኛ ጋር እንዲኖር ማለት የመንፈስ ቅዱስ ምሬት በየቀን ህይወታችን መኖሩ ነው። ለምሳሌ፣ ክፋትን የማድረግ ፈተናን እንድንቋቋም በመንፈስ ልንገሰፅ እንችላለን።

በዚያ ምክንያት ብቻ፣ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባዎቻችን ውስጥ እግዚአብሔርን ለማምለክ ፍላጎታችን እንዲጨምር ለምን የጌታ አገልጋዮች እንደሞከሩ ለመረዳት ቀላል ነው። በእምነት ቅዱስ ቁርባንን ከተካፈልን፣ በስሜት እና በድግግሞሽ እየጨመሩ ከሚመጡት ፈተናዎች እኛን እና የምንወዳቸውን ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ሊጠብቅ ይችላል።

የመንፈስ ቅዱስ አጋርነት መልካም የሆነው ይበልጥ እንዲስበን እና የመፈተን ግዳጅ እንዲቀንስ ያደርጋል። ያ ብቻ መንፈስ ቅዱስ ሁሌ ከእኛ ጋር እንዲሆን ብቁ ለመሆን እንድንወስን ለማድረግ በቂ ነው።

መንፈስ ቅዱስ ከክፋት በተቃራኒ እንደሚያጠነክረን ሁሉ፣ በእውነት እና ውሸት መካከል እንድንለይ ኃይልንም ይሰጠናል። ለውጥ የሚያመጣው እውነት የሚረጋገጠው ከእግዚአብሔር በሆነ መገለጥ ብቻ ነው። ሰዋዊ ምክንያታችን እና የአካላዊ ስሜቶቻችንን መጠቀም በቂ አይሆኑም። ጠቢባን እንኳን እውነትን ከሀይለኛ ማጭበርበር ለመለየት በሚቸገሩበት ጊዜ ላይ ነው የምንኖረው።

የአዳኝን ትንሳኤ የአዳኝን ቁስሎች በመንካት አካላዊ ማረጋገጫ ለፈለገው ሐዋርያው ቶማስ፣ መገለጥ የተሻለ ማረጋገጫ እንደሆነ ጌታ አስተማረው፣ “ኢየሱስም፣ ስለ አየኸኝ አምነሃል፣ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው” (ዮሐነስ 20፤29)።

እግዚአብሔር ዘንድ ወዳለው ቤት የሚጠቁሙት እውነታዎች በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚረጋገጡት። ወደ ጫካው በመሄድ አብ እና ልጁ ወጣቱ ዮሴፍ ስሚዝን ሲያናግሩት ማየት አንችልም። ቃል እንደተገባው አሁን ያሉትን እና በህያው ነብይ ጥቅም ላይ ያሉትን የክህነት ቁልፎች ለመስጠት ኤልያስ ለመምጣቱ አካላዊ ማረጋገጫ ወይም ምክንያታዊነት ሊኖር አይችልም።

መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ይገባኛል ለሚሉ የእግዚአብሔር ሴት እና ወንድ ልጆች ላይ የእውነት ማረጋገጫ ይመጣል። ውሸቶች በማንኛውም ጊዜ ለእኛ ሊቀርቡ ስለሚችሉ፣ ከጥርጣሬ ጊዜያት እንዲያድነን የእውነት መንፈስ ቋሚ ተፅእኖ ያስፈልገናል።

የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጉባኤ አባል በነበሩበት ወቅት፣ መንፈስ ከእኛ ጋር እንዲሆን በቋሚነት እንድንሻ ጆርጅ ኪው ካኖን ገልፀዋል። እንዲህ ብለው ቃል ገቡ፣ እና እኔም ያንን ቃል እገባለሁ፣ ያንን መንገድ ከተከተልን፣ “የእውነት እጥረት በፍፁም አይኖርብንም”፣ “በፍፁም በጥርጣሬ እና ጨለማ ውስጥ አንሆንም”፣ እና “እምነታችን ጠንቃራ እና ደስታችን ሙሉ ይሆናል።”2

ያንን የመንፈስ ቅዱስ አጋርነት ለሌላ ምክንያትም እንፈልገዋለን። የምናፈቅራቸው ሰዎች ሞት በድንገት ሊመጣ ይችላል። የምናፈቅራቸውን በምናጣ ጊዜ ተስፋ እና መፅናናትን የሚሰጠን የተወዳጁ የሰማይ አባት እና ትንሳኤን ያደረገው አዳኝ እውነታ የሆነው የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ነው። ሞት በሚከሰትበት ወቅት ያ ምስክርነት ትኩስ መሆን አለበት።

ስለዚህ፣ ለብዙ ምክንያቶች፣ የመንፈስ ቅዱስ ቋሚ አጋርነት ያስፈልገናል። እንፈልገዋለን፣ ነገር ግን ለማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ከተሞክሮአችን እናውቃለን። መንፈስን የሚያስከፉ ነገሮችን ሁላችንም በየቀን ህይወታችን እናስባለን፣ እንናገራለን፣ እናም እናደርጋለን። ልቦቻችን በልግስና ሙሉ ሲሆኑ እና “ቅድስና ያለማቋረጥ አስተሳሰባችንን ሲያስውብ” መንፈስ ቅዱስ የእኛ ቋሚ አጋር እንደሚሆን ጌታ አስተምሮናል ( ት እና ቃ 121፣45ተመልከቱ)።

ለመንፈስ አጋርነት ስጦታ ብቁ ለመሆን በሚያስፈልገው ከፍተኛ ደረጃ ትግል ላይ ላሉ ሰዎች፣ ይህንን ማበረታቻ አቀርባለሁ። የመንፈስ ቅዱስ ተፅእኖ የተሰማችሁ ጊዜያት ነበሩ። ያ ዛሬ ተከስቶ ሊሆን ይችላል።

እነዚያን የመነሳሳት ወቅቶች ልክ አልማ እንዳብራራው የእምነት ዘር ልትንከባከቡ ትችላላችሁ። ( አልማ 32፣28ተመልከቱ)። እያንዳንዱን ትከሉት። በተሰማችሁ መነሳሻ ላይ ያንን ማድረግ ትችላላችሁ። እግዚአብሔር ምን እንድታደርጉ እንደሚፈልግ ማወቅ በጣም ጠቃሚ መነሳሻ ይሆናል። አስራት ለመክፈል ወይም ያዘነን ጓደኛ ለመጎብኘት ከሆነ ያነሳሳችሁ፣ ማድረግ አለባችሁ። ማንኛውም ነገር ቢሆን፣ አድርጉት። ለመታዘዝ ፍቃደኛነታችሁን ስታሳዩ፣ እግዚአብሔር እንድታደርጉ የሚፈልገውን መንፈስ በበለጠ ስሜቶች ይልክላችኋል።

ስትታዘዙ፣ ቋሚ አጋር ወደ መሆን እየቀረበ እየቀረበ በመምጣት፣ ከመንፈስ ስሜቶች በይበልጥ ይመጣሉ። ትክክለኛውን የመምረጥ ሀይላችሁ ይጨምራል።

ለድርጊት መነሳሻዎች ከእራሳችሁ ፍላጎት ሳይሆን ከመንፈስ የመጡ መሆናቸውን ማወቅ ትችላላችሁ። ስሜቶቹ አዳኝ እና ህያው ነብያቶቹ እና ሐዋርያቶቹ ከተናገሩት ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ፣ በድፍረት ለመታዘዝ ትመርጣላችሁ። ከዛም እንዲረዳችሁ ጌታ መንፈሱን ይልካል።

ለምሳሌ፣ በተለይ ከባድ በሚመስል ጊዜ፣ የሰንበት ቀንን ለማክበር መንፈሳዊ መነሳሻን ከተቀበላችሁ፣ ለማገዝ እግዚአብሔር መንፈሱን ይልካል።

አባቴ ለስራ ወደ አውስትራሊያ ሲሄድ ያ እርዳታ ወደ እርሱ መጥቶ ነበር። በእሁድ ቀን ብቻውን ነበር፣ እናም ቅዱስ ቁርባንን ለመውሰድ ፈልጎ ነበር። ስለ ኋለኛው ቀን ቅዱሳን ስብሰባዎች መረጃ ሊያገኝ አልቻለም ነበር። ስለዚህ የእግር ጉዞ ጀመረ። ወዴት መታጠፍ እንዳለበት ለማወቅ በእያንዳንዱ መታጠፊያ ላይ ፀለየ። ለሰአት ያህል ከተጓዘ እና ከታጠፈ በኋላ፣ ደግሞ ለመፀለይ ቆመ። በሆነ መንገድ ለመጠማዘዝ መነሳሻ ተሰማው። ብዙም ሳይቆይ በአቅራቢያ ካለው ከህንጻ ታችኛ ወለል ውስጥ ዝማሬ ይሰማው ጀመረ። በመስኮት ውስጥ ተመለከተ እና በነጭ ልብስ በተሸፈነ ጠረጴዛ እና የቅዱስ ቁርባን ማቅረቢያ አከባቢ ጥቂት ሰዎች ተቀምጠው ተመለከተ።

አሁን፣ ያ እምብዛም ላይሰማችሁ ይችላል፣ ነገር ግን ለእርሱ ድንቅ ነገር ነበር። የቅዱስ ቁርባን ፀሎት ቃል ኪዳን መሟላቱን አውቋል፤ “ሁሌም ያስታውሱ እና የተሰጣቸውን ትእዛዛት ይጠብቁ ዘንድ፤ መንፈሱም ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር ይሆን ዘንድ” (ት እና ቃ 20፡77)።

ያ የፀለየበት እና እግዚአብሔር እንዲያደርግ የፈለገውን መንፈስ እንደነገረው ያደረገበት አንድ ብቻ ምሳሌ ነው። እናንተ እና እኔ እንደምናደርገው፣ ለአመታትም እነደዚያው አደረገ። ስለ መንፈሳዊነቱ በፍፁም አያወራም። ለማድረግ የተነሳሳባቸውን ጥቂት ነገሮች ለጌታ በማድረግ ብቻ ቀጠለ።

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ሰዎች እንዲነግራቸው በሚጠይቁት ጊዜ ሁሉ፣ ያደርገው ነበር። ሰዎቹ 10 ወይም 50 ቢሆኑም ወይም ምንም ያህል ደክሞት ቢሆንም ያደርገው ነበር። መንፈስ እንዲያደርግ በገፋፋው ጊዜ ሁሉ ስለ አብ፣ ስለ ልጁ፣ እና ሰለ ነብያት ምስክርነቱን አካፍሏል።

በቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው ከፍተኛ ጥሪ፣ በካስማ እርሻ ውስጥ አረም ያጸዳበት፣ እና የሰንበት ትምህርት ክፍል ያስተማረበት፣ የቦንቪል ካስማ ከፍተኛ መማክርት ውስጥ ነበር። በአመታት ውስጥ፣ ባስፈለገው ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ አጋሩ በዛ ነበረው።

በሆስፒታል ክፍል ውስጥ ከአባቴ ጎን ቆሜ ነበር። እናቴ፣ የ41 አመታት ሚስቱ፣ አልጋ ላይ ተኝታለች። ለሰአታት ስንመለከታት ነበር። የህመም መስመሮች ከእርሷ ፊት ላይ ሲወገዱ ማየት ጀመርን። የእጆቿ ጣቶች፣ ጭብጥ ብለው የነበሩት፣ ፈታ አሉ። ክንዶቿ በጎኗ ላይ ሆኑ።

የካንሰር የአስርት አመታት ህመሞች እያበቁ ነበር። በፊቷ ላይ የሰላም ገፅታን ተመለከትኩ። ጥቂት አጭር ትንፋሾችን ወሰደች፣ ከዛ አቃሰተች፣ እናም ከዛ ጋደም አለች። ሌላ ትንፋሽ ይኖራል ብለን ቆመን ጠበቅን።

በመጨረሻም፣ በዝግታ አባቴ እንዲህ አለ፣ “ትንሽዋ ልጅ ወደ ቤት ሄደች።”

እምባ አላፈሰሰም። ያም የሆነበት ምክንያት እርሷ ማን እንደነበረች፣ ከየት እንደመጣች፣ ምን መሆን እንደቻለች፣ እና የት እንደምትሄድ መንፈስ ቅዱስ ግልፅ ምስልን ከሰጠው ቆይቷል። ስለሰማይ አባት፣ የሞት ሀይልን ስለሰበረው አዳኝ፣ እና ከሚስቱ እና ቤተሰቡ ጋር የተካፈለው የቤተመቅደስ መታተምን እውነታ መንፈስ ብዙ ጊዜ መስክሮለታል።

መልካምነቷ እና እምነቷ እንደ ድንቅ የቃልኪዳን ልጅነት ወደምትታወስበት እና በክብር ወደ ቤት እንኳን ደህና መጣሸ የምትባልበት የሰማይ ቤት ለመመለስ ብቁ እንዳደረጋት መንፈስ ካረጋገጠለት ቆይቷል።

ለአባቴ፣ ያ ከተስፋም በላይ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ያንን እውን አድርጎለታል።

አሁን፣ የእርሱ ቃላት እና ስለሰማይ ቤት የነበረው የአእምሮ ምስል ጣፋጭ ስሜት፣ ሰው በማጣቱ የሚኖር የባል ደመናማ ፍርድ መሆኑን ጥቂቶች ሊናገሩ ይችላሉ። ነገር ግን ማወቅ በሚቻለው መንገድ የዘለአለም እውነታን ያውቃል።

እርሱ በጉርምስና ህይወቱ ውስጥ በሙሉ ስለአካላዊ አለም እውነታን ሲፈልግ የነበረ ሳይንቲስት ነበር። በአለም ዙሪያ በእኩዮቹ ያስከበረውን የሳይንስ መሳሪያዎች በአግባቡ ተጠቅሟል። አብዛኛው የኬሚስትሪ ስራዎቹ የመጡት በአእምሮው አይኖች ውስጥ ቅንጣቶች ሲንቀሳቀሱ ከማየት እና ከዛም እይታውን በቤተሙከራ ውስጥ በመሞከር በማረጋገጥ ነበር።

ነገር ግን ለእርሱ እና ለእያንዳንዳችን በጣም ትርጉም የነበረውን እውነትን ለማግኘት የተለየ መንገድ ተከተለ። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ብቻ ሰዎችን እና ክስተቶችን እግዚአብሔር ልክ እንደሚያያቸው መመልከት እንችላለን።

ያ ስጦታ ሚስቱ ከሞተች በኋላም በሆስፒታል ውስጥ ቀጠለ። ወደ ቤት ለመውሰድ የእናቴን ነገሮች ሰበሰብን። ወደ መኪና ለመውጣት ስንሄድ አባቴ በመንገዱ ያገኛቸውን ነርስ እና ዶክተር ሁሉ እየቆመ አመሰገነ። ብቻችንን በሀዘን ውስጥ ለመሆን መውጣት እንደነበረብን በመሰላቸት የተሰማኝን አስታውሳለሁ።

እርሱ የተመለከተው መንፈስ ቅዱስ ያሳየውን ነገሮች ብቻ እንደነበር አሁን አስተውያለሁ። ፍቅሩን ለመንከባከብ እነዚያን ሰዎች እግዚአብሔር እንደላካቸው መላእክት ነበር የተመለከታቸው። እነርሱ እራሳቸውን እንደ ጤና ባለሙያ ይመለከቱ ይሆናል፣ አባቴ ግን ያመሰገናቸው በአዳኝ ፈንታ ስለሰሩ ነበር።

በወላጆቼ ቤት ስንደርስም የመንፈስ ቅዱስ ተፅእኖ አብሮት ቀጠለ። በሳሎን ውስጥ ለጥቂት ደቂቃዎች ተነጋገርን። አባቴ ወደ ቅርቡ መኝታ ክፍል ውስጥ ለመግባት ሄደ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ ወደ ሳሎን በእርምጃ ተመለሰ። አስደሳች ፈገግታ ይታይበት ነበር። ወደ እኛ ተራመደ እና በዝግታ እንዲህ አለ፣ “ሚልድረድ ብቻዋን ወደመንፈስ አለም ትደርሳለች ብዬ ሰግቼ ነበር። በግርግር ውስጥ የጠፋች ይመስላት ይሆናል ብዬ አሰብኩ።”

ከዛም እርሱ በደመቀ መልኩ እንዲህ አለ፣ “አሁን ፀልዬ ነበር። ሚልድረድ ሰላም እንደሆነች አውቃለሁ። እርሷን ለማግኘት እናቴ እዛ ነበረች።”

የሴት አያቴ፣ የልጇ ሚስት ስትደርስ እርሷን ለማግኘት እና ከእርሷ ጋር ለመደሰት እዚያ መሆኗን ለማረጋገጥ አጭር እግሮቿ ሲራመዱ፣ እያሰበ በፈገግታ ሲናገር አስታውሳለሁ።

አሁን፣ አባቴ የጠየቀበት እና ያንን መፅናናት ያገኘበት አንዱ ምክንያት ከልጅነቱ ጀምሮ በእምነት በመፀለዩ ነበር። ምቾት እና መመሪያን ወደ ልቡ ለመስጠት የሚመጡትን መልሶች መቀበልን ተለማምዶ ነበር። የፀሎት ልምድ ከማኖሩም በተጨማሪ፣ ቅዱሳን መጽሐፍቶችን እና የህያው ነብያትን ቃላቶች ያውቅ ነበር። ስለዚህ ዛሬ ተሰምቷችሁ ሊሆን የሚችለውን፣ የመንፈስ ሹክሹክታዎችን ያስተውል ነበር።

የመንፈስ አጋርነት ለእርሱ ከመፅናኛ እና መመሪያም በላይ ነበር። በኢየሱስ ክርስቶስ የሀጢአት ክፍያ አማካኝነት እርሱን ለውጦታል። ያንን መንፈስ ሁሌ ከእኛ ጋር እንዲሆን ያለውን ቃልኪዳን ስንቀበል፣ ከስጦታዎች ሁሉ ታላቅ ለሆነው የዘለአለም ህይወት የሚያስፈልገውን ንፅህና አዳኝ ሊሰጠን ይችላል (ት እና ቃ 14፣7ተመልከቱ)።

የአዳኝን ቃላት ታስታውሳላችሁ፤ “እንግዲህ ትእዛዜ ይህች ናት፤ በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ንሰሃ ግቡ፣ እናም ወደ እኔ ኑ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ትቀደሱ ዘንድ፤ በመጨረሻው ቀን በፊቴ ያለእንከን ትቆሙ ዘንድ በስሜ ተጠመቁ” (3ኛ ኔፊ 27:20)።

እነዚያ ትእዛዛት ከጌታ ከሆኑት እነዚህ ቃልኪዳኖች ጋር አብረው ይመጣሉ፤

“እናም አሁን፣ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ በፍትህ ለመስራት፣ በትህትና ለመጓዝ፣ በቅድስና ለመፍረድ ወደ መልካም በሚመራው መንፈስ ላይ እምነታችሁን አድርጉ፤ እናም ይሄ የእኔ መንፈስ ነው።

“እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ አእምሮአችሁን ከሚያበራው፣ መንፈሴን ለእናንተ አካፍላለሁ፣ ነብሳችሁንም በደስታ ይሞላል” (ት እና ቃ 11:12–13)።

አብ እግዚአብሔር ህያው እንደሆነ፣ ትንሳኤን ያደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑን እንደሚመራ፣ ቶማስ ኤስ ሞንሰን የክህነት ቁልፎችን ሁሉ እንደያዙ፣ እና ያ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እናም ትሁት አባሎቹን እንደሚመራ ምስክርነቴን አካፍላችኋለሁ፡፡

እንደ የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጉባኤ አባላት፣ እንደ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች ዛሬ ለእኛ ንግግር ሲያደርጉ የነበሩት እነዚህ ድንቅ ሰዎች በእግዚአብሔር የተጠሩ መሆናቸውን ጨምሬ እመሰክራለሁ። ጥሪ እንዲደረግላቸው መንፈስ ፕሬዘዳንት ሞንሰንን እንደመራቸው አውቃለሁ። እናም እነርሱን እና ምስክርነቶቻቸውን ስታዳምጡ፣ እኔ አሁን የምለውን ነገር መንፈስ ቅዱስ ለእናንተ አረጋግጦላችኋል። በእግዚአብሔር የተጠሩ ናቸው። እደግፋቸዋለሁ እናም እወዳቸኋለሁ እና ጌታ እንደሚወዳቸው እናም በአገልግሎታቸውም እንደሚደግፋቸው አውቃለሁ። እናም ይህን የማደርገው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ሀንድቡክ 2፤ Administering the Church (2010 እ.አ.አ), 20.3.10።

  2. ጆርጅ ኪው ካነን፣ in “Minutes of a Conference,” Millennial Star, ግንቦት 2, 1863 (እ.አ.አ), 275–76።

አትም