“ቅዱሳት መጻህፍት፤ የእግዚአብሔር ቃል፣”ሊያሆና፣ ሐምሌ 2022 (እ.አ.አ.)
ወርሀዊ የ ሊያሆና መልዕክት፣ ሐምሌ 2022 (እ.አ.አ)
ቅዱሳት መጻህፍት፤ የእግዚአብሔር ቃል
ቅዱሳት መጻሕፍት በዋናነት በነቢያት የተጻፉ ቅዱስ መጻሕፍት ናቸው። ቅዱሳት መጻሕፍት ስለኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክራሉ እንዲሁም ስለወንጌሉ ያስተምራሉ። የቤተክርስቲያኗ ኦፊሴላዊ ቅዱሳት መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳንን እና አዲስ ኪዳንን ያካትታል)፣ መፅሐፈ ሞርሞን፣ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች፣ እና የታላቅ ዋጋ ዕንቁ ናቸው።
ብሉይ ኪዳን
ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በጥንት ጊዜ ከቃልኪዳን ህዝቡ ጋር ያደረገውን ግንኙነት የሚያሳይ መዝገብ ነው። እንደ ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ እና ዳንኤል ያሉ ነቢያትን ትምህርቶች ያካትታል። ምንም እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፈ ቢሆንም፣ ብዙ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለእርሱ ጽፈዋል።
አዲስ ኪዳን
አዲስ ኪዳን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት፣ ምድራዊ ህይወት፣ ትምህርቶች እና የኃጢያት ክፍያ መዝግቦ ይዟል። የክርስቶስን ሐዋርያት እና የሌሎች ደቀመዛሙርት ትምህርቶችንም ያካትታል። አዲስ ኪዳን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ዛሬ እንዴት መኖር እንዳለብን እንድንረዳ ያግዘናል።
መፅሐፈ ሞርሞን፦ ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት
መፅሐፈ ሞርሞን በጥንት አሜሪካ ይኖሩ የነበሩ የተወሰኑ ህዝቦች መዝገብ ነው። የነብያትን ትምህሮች ያካትታል፣ ዋናው አላማውም ሁሉም ህዝቦች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እንዲያምኑ ማድረግ ነው። ነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ ከወርቅ ሳህኖች በእግዚአብሔር ስጦታና ሃይል ተረጎመው።
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ለጆሴፍ ስሚዝ እና ለሌሎች የኋለኛው ቀን ነቢያት የተሰጡ መገለጦችን ይዟል። ራዕዮቹ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደተደራጀች ይገልፃሉ። እንዲሁም ስለክህነት፣ የወንጌል ስርዓቶች እና ከዚህ ህይወት በኋላ ስለሚሆነው ጠቃሚ የወንጌል ትምህርቶችን ይዘዋል።
የታላቅ ዋጋ ዕንቁ
የታላቅ ዋጋ ዕንቁ የሙሴን እና የአብርሃምን መጻህፍት፣ የጆሴፍ ስሚዝን ምስክርነት እና የቤተክርስቲያኗን የእምነት አንቀጾች ያካትታል። በተጨማሪም የጆሴፍ ስሚዝ የአዲስ ኪዳን ትርጉም አካል የሆነውን የጆሴፍ ስሚዝ-የማቴዎስ ወንጌልን ያካትታል።
ቅዱሳት መጻህፍትን ማጥናት
ነብያት ቅዱሳት መጻህፍትን በየቀኑ እንድናጠና አስተምረውናል። ይህን ማድረጋችን እምነታችን እንዲጨምር እንዲሁም ወደሰማይ አባት እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየቀረብን እንድንመጣ ይረዳናል። ቅዱሳት መጻሕፍትን በጸሎት ስናጠና፣ መንፈስ ቅዱስ ለጥያቄዎቻችን መልስ እንድናገኝ ይረዳናል።
የዘመኑ ነብያት
ዛሬ ነቢያትና ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲናገሩ ቃላቸው እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ነው። የዚህ አንዱ ምሳሌ አጠቃላይ ጉባኤ ነው። በግንቦት እና ህዳር የ ሊያሆና እትሞች የጉባኤ ትምህርቶችን ማጥናት እንችላለን።
© 2022 by Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly Liahona Message, July 2022.ትርጉም። Amharic። 18298 506