2022 (እ.አ.አ)
የደቀመዝሙር ጉዞ
ሰኔ 2022 (እ.አ.አ)


የክልል አመራር መልእክት

የደቀመዝሙር ጉዞ

ደቀመዝሙር መሆንን መማር በህይወት ዘመን ሙሉ የሚደረግን ጉዞ ማድረግ ነው። ሁልጊዜ በመንገዱ የሚያደፍጡ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች ቢኖሩም በትጋት ሲደረግ ለልብ ታላቅ ደስታን የሚያመጣ ጉዞ ነው።

እያንዳንዱ ጉዞ ከጉዞው መጠናቀቅ በኋላ ስለሚገኘው ነገር ባለ የልብ ፍላጎት ይጀምራል።በተመሳሳይም እያንዳንዱ ጥረት የሚጀምረው ሥራው ሲጠናቀቅ ጠቃሚ ውጤት እንደሚገኝ ባለ ፅኑ እምነት ነው።ተጓዡ ከፊቱ ባለው ነገር ተስፋ በማድረግ በጉዞው ይፈጥናል፣ እንዲሁም ሰራተኛ ስራውን አንድ በአንድ በትጋት ይሠራል።

የእኔ ክርስቶስ ደቀመዝሙርነት ጉዞ የጀመረው ከእኔ ከሚበልጥ ሃይል ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በመናፈቅ ነበር። በጥልቅ ልቤ ውስጥ ያ ኃይል እንዳለ አውቅ ነበር። ሆኖም ግንኙነቱን እንዴት እንደምመሰርት አላውቅም ነበር። በስውሩ ህሊናዬ ፍለጋውን ጀምሬው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ከዋክብት የያዘውን የምሽት ሰማይ ግርማ በግርምት እና በአድናቆት ፈዝዤ እመለከት ነበር። በምድር ላይ ያሉ በርካታ የሕይወት ዓይነቶች ከየት እንደመጡና እያንዳንዱ ሕይወት ያለው ነገር ሕልውናውን እንዲያቆይ እና ራሱን እንዲጠብቅ በሚያስችለው የማሰብ ችሎታ እንዴት እንደተሞላ አደንቅ ነበር። አንዳንድ እፅዋትም ወፎችና እንስሳት ፍሬያቸውን እንዲበሉ እንዴት እንደሚስቧቸው ሌሎችም ደረቁ ወቅት ሲደርስ ዛላዎቻቸውን መሰንጠቅና ክንፍ ያላቸውን ዘሮቻቸውን እንደሚለቁ ኃይለኛ የሆነ ነፋስም ዘራቸውን በአዲስ መሬት ላይ አዳዲስ ዛፎችን ያበቅሉ ዘንድ እንደሚዘራ የሚያውቁ መሆናቸውን አስተውያለሁ።አንቴናዬ ለእግዚያብሄር ነገሮች ቀጥ አለ ለመቀበልም ዝግጁ ሆነ።

ስለዚህ በአጋጣሚ በሚመስል ሁኔታ ለባለቤቴ ለግላዲስ እና ለእኔ ስለኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የነገሩንን አረጋዊ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን ባገኘን ጊዜ—እንዲሁም በማግሥቱ መጥተን እንድናይ ቤታቸው ወዳለው ጉባኤ እንድንመጣ ሲጋበዙን—ወዲያውኑ ምላሽ ሰጠን። በዚያች ሃያ አካባቢ የሚሆኑ አባላት በተካፈሉባት ትንሽ ጉባኤ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀምጬ ሳለሁ ሲሰጥ የሰማሁት ትምህርት እውነት እንደሆነ ተሰማኝ እንዲሁም ጥሩ ስሜት ተሰማኝ። የህይወቴ ክፍል እንዲሆንም ፈለግኩኝ። በሚቀጥለው እሁድ እንደገና በጉባኤው ለመሳተፍ ወሰንን። ይህን ማድረጋችንን ቀጠልን ብዙም ሳይቆይ እሁድ እሁድ በቤተክርስቲያን መገኘት የቤተሰባችን ባህል ሆነ። በቅዱስ ቁርባን ስርዓት በተካፈልንበት ጊዜ የጌታን ቃላት ሳስታውስ ጥልቅ የሆነ የሰላም ስሜት ተሰማኝ እስከ ዛሬ ድረስም እንደዚያው ይሰማኛል:

“ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ስጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ህይወት የላችሁም።

“ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ህይወት አለው ፥ እኔም በመጨረሻው ቀን እነሳዋለሁ።

“ስጋዬ እውነተኛ መብል ፥ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።

“ስጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።

“ህያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሳ ህያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሳ ህያው ይሆናል” (ዮሃንስ 6፥53–57)።

የቤተክርስቲያኗ ትምህርት ለቤተሰብ ጠንካራ አጽንዖት እንደሚሰጥ ሳውቅ በእኔ ላይ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ ተከሰተ (ወይም ንስሃ ገባሁኝ)። በሙሴ በኩል የተሰጠውን መመሪያ እና የተስፋ ቃል ጨምሮ በዘመናት ሁሉ ጌታ በነቢያቱ በኩል የሰጠውን ምክር ወደድኩኝ፦

“እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ።

“ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሳም ተጫወተው።

“በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ።

“በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” (ዘዳግም 6፥6–9).

“እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ ስማ፤ መልካምም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚያብሄር እንደተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ (ዘዳግም 6፥3)።

ባለቤቴ ግላዲስ እና እኔ—በየዕለቱ ከቤተሰብ ጋር ጸሎት ለማድረግ እንዲሁም የመፅሐፈ ሞርሞንን ትምህርቶች የማንበብ እና የመወያየት ባህል ለመገንባት—በጋራ ሰራን። በየሳምንቱ በቤተሰብ የቤት ምሽት ለመሰባሰብ በተቻለን መጠን በጋራ ጥረት አደረግን። በገዛ ቤተሰቤ ውስጥ ሲፈጸም አይቼ ስለነበር ቤተሰብ ለዓለም የተላለፈ ዓዋጅን በ1995(እ.አ.አ) ስንቀበል በህይወት ያሉ ነቢያትና ሐዋርያት በዐዋጁ ላይ ስለተናገሩት እውነት የግል ምስክርነቴን ማግኘት ስለቻልኩኝ ተደሰትኩኝ።

“በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ደስታ የሚገኘው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ላይ ሲመሠረት ነው። የተሳኩ ትዳሮች እና ቤተሰቦች የተመሰረቱትም ሆነ የሚዘልቁት በእምነት፣ በጸሎት፣ በንስሃ፣ በይቅርታ፣ በአክብሮት፣ በፍቅር፣ በርህራሄ፣ በስራ እና ጤናማ በሆኑ የመዝናኛ አክቲቪቲዎች ላይ ነው።”1

እምነቴ በስራ ህይወቴ ላይም ተፅዕኖ አሳድሯል። በአንድ ወቅት ለአሰሪዬ ዕቃ የሚያቀርብ አንድ ሰው ወደቢሮዬ ገባና በዚያ ዓመት ከኩባንያው ላደረግናቸው ግዢዎች አድናቆት ሲል “ትንሽ ስጦታ” እንዳመጣልኝ ነገረኝ። በዚያን ጊዜ የሁሉም አላቂ ዕቃዎች የግዢ ክፍል ኃላፊ ነበርኩ። ከሰራተኞቼ መካከል ያንን “ትንሽ ስጦታ” ከእሱ ጠይቆ እንደሆነ ጠየቅኩት። ይህን እንዲያደርግ የጠየቀው ማንም እንደሌለ ሆኖም ከሌሎች ኩበንያዎች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት የተለመደ አሰራር እንደሆነ ተናገረ። “የትንሽ ስጦታውን” ዋጋ የሚያህል ተጨማሪ እቃ ያለክፍያ በሚቀጥለው ቀን ወደ ኩባንያው መደብር በነጻ እንዲወስድ ጠየቅሁት። በዚህ ምላሽ በጣም ደነገጠ ሆኖም በነገሩ ተስማምቶ ሄደ።

እምነቴን የሚፈትን ፈተና በጉዞው የተለያዩ የእድገት ደረጃዎች ላይ ወደ እኔ መጥቶ የነበረ ሲሆን እውነተኛ የአንጥረኛ እሳት ነበር። በአንድ ወቅት በደል እንደደረሰብኝ እና እንደተጠቃሁኝ ስለተሰማኝ ከአንድ የቤተሰቤ አባል ጋር መልካም ያልሆኑ ቃላት ወደመለዋወጥ ገብቼ ራሴን አገኘሁት። ምን እየሆነ እንደነበር ስገነዘብ አፌን ለመዝጋት እና ከቦታው ለመራቅ ወሰንኩኝ። ከቦታው ዘወር ለማለት መሄድ ስጀምር የመንፈስ ተግሣጽ ተሰማኝ እናም ተመልሼ በእኔ በኩል ለነገሩ አስተዋጽዖ በማድረጌ ልባዊ ይቅርታ ጠየቅሁ። ከዚያ በኋላ የሆነውም ተከስቶ ስለነበረው ነገር የፀፀት እንባ ማንባት እና እርስ በእርስ ከልብ ይቅር መባባል ነበር።

በቤት ውስጥ ወንጌልን የመኖር ልምድ ከተገኘ በኋላ ቀጣዮቹ የመንፈሳዊ እድገት እድሎች የመጡት በቤተክርስቲያን ጥሪዎች አማካኝነት ሌሎችን ከማገልገል ነበር። የወንጌል ዘላቂ ደስታ ሌሎች የቃል ኪዳኑን መንገድ እንዲያገኙ ወይም ወደዚያው መንገድ እንዲመለሱ በመርዳት እንደሆነ ተምሪያለሁ። በቅድመ ህይወት በተካሄደው ጉባኤ ውስጥ “ማንን ልላክ” የሚለው በአብ ቀርቦ የነበረው ጥያቄ (አብርሃም 3፥27) የሰማይን ዘላለማዊ በረከቶች እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው። ቅዱሳንን በተለያየ መንገድ በቤታቸው እንዲሁም በመደበኛው የቤተክርስቲያኗ ስብሰባዎች በኩል በማገልገሌ ብዙ ደስታን አግኝቻለሁ።

በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ ላይ በህመም ወደ አብ እንዲጮህ ስላደረገው በቆመ መስቀል ላይ ከነህይወቱ በምስማር ተቸንክሮ ስለሚያሳየው የጌታ ምስል ለረጅም ጊዜ አሰላስል ነበር። እስከዛሬ በሰው አእምሮ ተጸንሰው በሰው እጅ ከተደረጉት ሁሉ ከባድ የአካል ህመም ያስከተለ ጊዜ ነበር። በዚያን ዘመን ከኖሩት ውስጥ ጥቂቶች ብቻ ይህ ነገር ተደርጎባቸዋል። ጌታ ያንን ሁኔታ በመታገስ ከሚያሠቃየው የራሱ አካላዊ ህመም ይልቅ አእምሮውን እየሰቀሉት በነበሩት ሰዎች መንፈሳዊ ደህንነት ላይ ለማተኮር እንዳዞረ ማሰብ—ለአብ እና ለህጉ እንዲሁም ለሰዎች ደህንነት ሙሉ በሙሉ መገዛቱን የሚያሳይ ምስክር ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተነስቷል እንዲሁም የማንኛውም ምድራዊ ህመም ስጋት ለዘላለም የለበትም። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይ እና በምድር ተሰጠኝ” ሲልም ተናግሯል (ማቴዎስ 28፥18)።

በእርሱ ምሳሌነት የአጽናፈ ዓለሙ እና የሕይወት ሁሉ አባት ለሆነው ራሱን አስገዝቶ በታላቅ ክብር ዘውድ ስለተቀዳጀ በጌታ በክርስቶስ የሃጥያት ክፍያ አማካኝነት የእርሱ ደቀመዝሙር ለመሆን “እንደልጅ ሁሉን የሚቀበል፣ የዋህ፣ ትሁት፣ ትዕግሰተኛ፣ በፍቅር የተሞላ፣ ልጅ ከአባቱ ተቀባይ እንደሚሆን ጌታ ብቁ ነው ብሎ የሚያደርስ[ብኝን] ሁሉንም ነገሮች ለመቀበል ፈቃደኛ” መሆን እንዳለብኝ በራሴ ወደማወቅ ያመጣኝን መንገድ ተጉዣለሁ።

ደቀመዝሙር መሆንን መማር በህይወት ዘመን ሙሉ የሚደረግን ጉዞ ማድረግ ነው። ሁልጊዜ በመንገዱ የሚያደፍጡ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች ቢኖሩም በትጋት ሲደረግ ለልብ ታላቅ ደስታን የሚያመጣ ጉዞ ነው። አንድ ሰው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቅና እንዲወደው እንዲሁም በእርሱ እንዲደሰት የሚያደርግ ጉዞ ነው።

ጆሴፍ ደብልዩ. ሲታቲ እንደሰባዎቹ አጠቃይ ባለስልጣን ድጋፍ ያገኙት በሚያዚያ 2009(እ.አ.አ) ነው። ከግላዲስ ናንጎኒ ጋር ጋብቻቸውን መስርተዋል፤ የአምስት ልጆች ወላጆችም ናቸው።

ማስታወሻዎች

  1. “የቤተሰብ፦ ለአለም የተላለፈ አዋጅ”፣ ChurchofJesusChrist.org.

አትም