2023 (እ.አ.አ)
በቤተመቅደስ ለመሳተፍ መዘጋጀት
ታህሳስ 2023 (እ.አ.አ)


“በቤተመቅደስ ለመሳተፍ መዘጋጀት” ሊያሆና፣ ታህሳስ 2023 (እ.አ.አ)።

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ታህሳስ 2023 (እ.አ.አ)

በቤተመቅደስ ለመሳተፍ መዘጋጀት

ወደ ኦግደን ዩታ ቤተመቅደስ የሚጓዙ ሰዎች

የኦግደን ዩታ ቤተመቅደስ ፎቶግራፍ በማርክ ብረንሰን

በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ቤተመቅደሶች ውስጥ ለራሳችን እና ለቀደሙ አያቶቻችን ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን እና ስርዓቶችን መቀበል እንችላለን። ለሰማይ አባት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ፍቅር እና ምስጋና ለማሳየት ወደ ቤተመቅደስ እንሄዳለን። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በመማር እና በመኖር ወደ ቤተመቅደስ ለመሄድ መዘጋጀት እንችላለን። ስለ ቤተመቅደሶች የበለጠ መረጃ ለማግኘት “የቤተመቅደስ ስራ” የሚለውን የወንጌል መሰረታዊ አንቀጽ በጥቅምት 2021 (እ.አ.አ) ሊያሆና እትም ላይ ተመልከቱ።

በደርባን ደቡብ አፍሪካ ቤተመቅደስ በውጭ በኩል ያሉ ቃላት

የደርባን ደቡብ አፍሪካ ቤተመቅደስ ፎቶ በማቴዎስ ሬየር

የጌታ ቤት

ቤተመቅደሶች “የጌታ ቤት” በመባል ይታወቃሉ። የእግዚአብሔር መንፈስ እና ለእኛ ያለው ፍቅር ሊሰማን የሚችልበት የተቀደሰ ቦታ ነው። እንዲሁም የዘለአለም ህይወትን እንድናገኝ የሚያዘጋጁንን ልዩ ስርዓቶች የምንቀበልባቸው እና ቃል ኪዳኖችን የምንገባባቸው ቦታዎች ናቸው። (ቃል ኪዳኖች በእግዚአብሔር እና በልጆቹ መካከል የተገቡ የተቀደሱ ሥምምነቶች ናቸው።) ለቃል ኪዳኖቻችን ታማኝ መሆን እና እነዚህን ስርዓቶች መቀበል ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ልዩ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል።

ከጓያኪል ኢኳዶር ቤተመቅደስ ውጭ ወጣቶች ቆመው

የጓያኪል ኢኳዶር ቤተመቅደስ ፎቶ በጃኔ ቢንጋም

በቤተመቅደስ ውስጥ መሳተፍ የሚችለው ማን ነው?

የቤተክርስቲያኗ አባላት 12 ዓመት ከሚሞላቸው አመት ጀምሮ ለሙታን ጥምቀት ማድረግ ይችላሉ። አንድ አባል ቢያንስ 18 ዓመት ከሆነው፣ ለአንድ ዓመት የቤተክርስቲያኗ አባል ከሆነ እና በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ለመግባት እና ለመጠበቅ ከፈለገ የቤተ መቅደስ ቡራኬን ለመቀበል ይችላል (አጠቃላይ መመሪያ መጽሐፍ፡ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል፣ 27.2.2፣ ChurchofJesusChrist.org ተመልከቱ)። የቤተመቅደስ ቡራኬን የተቀበሉ ወንዶች እና ሴቶች በቤተመቅደስ ውስጥ ለዘለአለም መታተም (መጋባት) ይችላሉ።

ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች

በቤተመቅደስ ውስጥ ቃል ኪዳኖችን ትገባላችሁ እንዲሁም ሥርዓቶችን ትቀበላላችሁ። “ከእግዚአብሔር ጋር የቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ መግባታችን በሕይወት ሁሉንም ነገር በሚያቀልል መንገድ ከእርሱ ጋር ያገናኘናል” (ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አለምን ማሸነፍ እና እረፍትን ማግኘት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 97)። ሥርዓት በክህነት ስልጣን የሚከናወን የተቀደሰ አካላዊ ተግባር ነው። ሥርዓቶች ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አላቸው። ለምሳሌ፣ በስርዓት ውስጥ ስትሳተፉ፣ ቃል ኪዳኖቹን ለመቀበል እና ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆናችሁ ለእግዚአብሔር ታሳያላችሁ።

የግል ዝግጅት

የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች በመከተል እና በጥምቀት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን በመጠበቅ መንፈሳዊ ዝግጅት አድርጉ። በተጨማሪም እንደ ቅዱሳት መጻህፍት እና የአጠቃላይ ጉባኤ ንግግሮች ያሉ የቤተክርስቲያን ግብዓቶችን ማጥናት ትችላላችሁ። Temples.ChurchofJesusChrist.org ወደ ቤተመቅደስ ስትገቡ በዚያ ምን መጠበቅ እንዳለባችሁ መረጃ ይሰጣል። እንዲሁም ስለ ቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች፣ ስርዓቶች እና ምሳሌያዊ ምልክትነትነት ተጨማሪ ዝርዝሮችን ያካትታል።

ከናቩ ኢለኖይ ቤተመቅደስ ውጪ

የናቩ ኢለኖይ ቤተመቅደስ ፎቶ በኢቭ ታፍት

ምሳሌያዊ ምልክትነት

ጌታ ብዙ ጊዜ ምሳሌያዊ ምልክቶችን በመጠቀም ያስተምራል። ለምሳሌ፣ ጥምቀት—በውሃ ውስጥ መጥለቅ እና እንደገና መውጣት—የአሮጌው ማንነታችሁ መሞት እና የአዲሱ ማንነት ዳግም መወለድ ምሳሌ ነው (ሮሜ 6፥3–6 ተመልከቱ)። የቤተመቅደስ ስርዓቶች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ወደ ኃጢያት ክፍያው ያመለክታሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተመቅደስ ስትገቡ ሁሉንም ምሳሊያዊ ምልክቶች ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን በህይታችሁ ሙሉ ወደ ቤተመቅደስ በመሄድ መማራችሁን መቀጠል ትችላላችሁ።

የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ

ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት ዝግጁ እና ብቁ መሆን አለባችሁ። ከኤጲስ ቆጶሳችሁ ወይም ከቅርንጫፍ ፕሬዚዳንታችሁ እና ከካስማ ወይም ከሚስዮን ፕሬዚዳንቱ ጋር ቃለ መጠይቅ ካደረጋችሁ በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት የቤተመቅደስ መግቢያ ፈቃድ ማግኘት ትችላላችሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እየኖራችሁ ስለመሆናችሁ ለማረጋገጥ እነዚህ መሪዎች የተወሰኑ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። መሪዎቻችሁ ስለእነዚህ ጥያቄዎች አስቀድመው ሊያነጋግሯችሁ ይችላሉ።

ለቅድመ አያቶች ወደ ቤተመቅደስ መመለስ

የሰማይ አባት ሁሉም ልጆቹ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ እና ቅዱስ ስርዓቶችን እንዲቀበሉ ይፈልጋል። ወንጌልን ሳይቀበሉ ላለፉትም እንደ ጥምቀት እና የቤተመቅደስ ቡራኬ ያሉ ስርዓቶች በቤተመቅደስ ውስጥ መከናወን አለባቸው። ለሞቱ የቤተሰብ አባሎቻችሁ ስርዓቶችን ለመፈጸም ወደ ቤተመቅደስ መሄድ ትችላላችሁ።