“የሁሉም አዳኝ፣ ለሁሉም የሚሆን ወንጌል፣” ሊያሆና፣ መጋቢት 2024 (እ.አ.አ)።
ወርኃዊ የሊያሆና መልዕክት፣ መጋቢት 2024 (እ.አ.አ)
የሁሉም አዳኝ፣ ለሁሉም የሚሆን ወንጌል
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል፣ የኃጥያት ክፍያ እና ትንሳኤ ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች ይባርካል።
ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በእነዚህ በኋለኛው ቀናት ላሉ ሁሉ የመጀመሪያ፣ ከሁሉም በላይ እና ለዘለአለም የዘላቂ ደስታ፣ የእውነተኛ ሰላም እና የሀሴት ምንጭ ነው። ከወንጌል እና ከክርስቶስ ያልተገደበ ቸርነት የሚመጣው በረከት ጥንትም ሆነ በዘመናችን ለተመረጡት ጥቂቶች ብቻ አልነበረም።
ምንም ያህል ብቁ እንዳልሆንን ቢሰማን፣ እና ኃጢያቶቻችን ለጊዜው ከእርሱ ሊያርቁን ቢችሉም፣ አዳኛችን፣ ሁላችንም ወደ እርሱ እንድንቀርብ እና ፍቅሩ እንዲሰማን “ለእኛ ቀኑን ሙሉ ክንዱን [በመዘርጋት]” (ያዕቆብ 6፥4) ግብዣን በማቅረብ ያረጋግጥልናል።
የወንጌል በረከቶች ለአለም በሙሉ
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል “በኋለኛው ቀን ዳግም የተመለሰው የሁሉንም ሃገር፣ ነገድ፣ ቋንቋ እና በምድር የሚኖር ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት ነው።” 1 ሁሉም “ለእግዚአብሔር አንድ [መሆናቸውን]” (2 ኔፊ 26፥33) ለማስተማር፣ ወንጌሉ ሁሉንም የባህል መስመሮች እያቋረጠ ከሁሉም ዜግነት እና ቀለም በልጦ ይታያል።2 መፅሐፈ ሞርሞን የዚህ አስደናቂ እውነታ ምስክር ሆኖ ይቆማል።
ይህ ታላቅ መዝገብ ክርስቶስ ሁሉንም ሃገሮች እንደሚያስታውስ ይመሰክራል (2 ኔፊ 29፥7ን ይመልከቱ) እንዲሁም “በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ እራሱን … ይገልፃል፣ … በሰው ልጆች መካከል አስደናቂ ተአምራትን፣ ምልክትን፣ እና ድንቅ ነገርን [ይሰራል]” (2 ኔፊ 26:13)። ከእነዚህ አስደናቂ ተአምራት፣ ምልክቶች እና ድንቅ ነገሮች መካከል የወንጌል መሰራጨት አንዱ ነው። ስለዚህም፣ የእርሱን መልካም ዜና እንዲመሰክሩ ሚስዮናዊያንን ወደ መላው አለም እንልካለን። በዙሪያችን ላሉትም ወንጌልን እናካፍላለን። ዳግም የተመለሱትን የክህነት ቁልፎች በህይወት ላሉ እና ለሙታን መጠቀም፣ ለእያንዳንዱ የሰማይ ወላጆቻችን ወንድ እና ሴት ልጅ—ቀደም ብለው ለኖሩት፣ አሁን ላሉት ወይም ወደፊት ለሚኖሩት ሁሉ—የወንጌል ሙላት በመጨረሻ እንደሚገኝ ያረጋግጣል።
የዚህ ወንጌል እምብርት—እስከዛሬ ወደ ሥራው የተጠራ የእያንዳንዱ ነቢይ እና ሐዋርያ ዋና መልእክት—ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ እና ሁሉንም ሰው ሊባርክ መምጣቱ ነው። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት እንደመሆናችን መጠን፣ የእርሱ የኃጥያት ክፍያ ለአለም ሁሉ እንደሆነ እናውጃለን።
መጨረሻ የሌለው እና የዘለአለማዊ የሃጢያት ክፍያ አስፈላጊነት
በአለም ዙሪያ ስጓዝ፣ ከብዙ የቤተክርስቲያን አባላት ጋር ቃለ ምልልስ አደርጋለሁ። የቆየ ሃጢያትን በሚናዘዙበት ጊዜም እንኳን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በረከቶች በህይወታቸው ውስጥ እንዴት እንደሚሰማቸው ለመስማት እነሳሳለሁ። የኃጥያት ክፍያው የማንፃት ምቾት ሁል ጊዜ ለሁላችንም የሚገኝ መሆኑ እንዴት ድንቅ ነው!
አሙሌቅ “የኃጥያት ክፍያ መኖሩ አስፈላጊ ነው፤ አለበለዚያ የሰው ዘር ሁሉ መጥፋት [አለበት]” ሲልተናግሯል። እኛም ለዘለዓለም “[እንወድቃለን እንጠፋለን]፣ … መፈጸሙ አስፈላጊ ከሆነው [የ]ኃጥያት ክፍያ በቀር።” ይኸውም “መጨረሻ የሌለው እንዲሁም ዘለዓለማዊ መስዋዕት” ይጠይቃል። “ለዓለም ኃጥያት ወሰን ከሌለው የኃጥያት ክፍያ በስተቀር ሊበቃ የሚችል ምንም የለም[ና]” (አልማ 34፥9፣ 10፣ 12)።
ታላቁ ነብይ ያዕቆብም እንዲህ ሲል አስተምሯል፦ “ሞት በሰው ልጆች ላይ ስለመጣ፣” እኛን ወደ እግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ “የትንሣኤ ኃይል ይኖር ዘንድ ያስፈልጋል” (2 ኔፊ 9፥6)።
ሁለቱም ኃጥያት እና ሞት ሊሸነፉ ይገባል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ልጆች በድፍረት ያሳካው ተልዕኮው ነበር።
የአዳኛችን መስዋዕትነት
በምድራዊ ህይወቱ የመጨረሻ ምሽት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጌተሴማኒ የአትክልት ስፍራ ገባ። እዚያም በወይራ ዛፎች መካከል ተንበርክኮ፣ እኔ እና አንናንተ መቼም ልናውቀው ወደማንችለው ጥልቅ ስቃይ መውረድ ጀመረ።
እዚያ ቦታ ላይ፣ የዓለምን ኃጥያት በራሱ ለይ መውሰድ ጀመረ። እርሱም የእያንዳንዱ ህመም፣ የልብ መሰበር እና የስቃይ ስሜቶች ተሰሙት፣ እንዲሁም በእናንተ እና በእኔ እንዲሁም እስከዛሬ በኖሩት ወይም ገና ወደፊት በሚኖሩት በእያንዳንዱ ነፍሳት ሁሉ የሚያጋጥምን ጭንቀት እና መከራ ተሸከመ። ይህ ታላቅ እና ማለቂያ የሌለው መከራ “[እርሱ] … ከስቃዩ የተነሳ እን[ዲ]ንቀጠቀጥ እናም ከእያንዳንዱ ቀዳዳ እን[ዲ]ደማ” አደረገው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 19፥18)። ይሄን ሊያደርግ የሚችለው እርሱ ብቻ ነበር።
ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቀራንዮ ተወሰደ፣ እና በዚህ አለም ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም በሚያሳዝን ኢፍትሃዊ በሆነ ጊዜ፣ ተሰቀለ። ማንም ሰው ህይወቱን ከእርሱ ሊወስድ አይችልም ነበር። እንደ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ፣ በስጋዊ ሞት ላይ ሀይል ነበረው። ወደ አባቱ መጸለይ ይችል ነበር፣ ከዚያም የሚያሰቃዩትን ለማሸነፍ እና በሁሉም ነገር ላይ ያለውን የበላይነት ለማሳየት የመላዕክት ጭፍሮች ሊመጡ ይችሉ ነበር። ኢየሱስ በተካደበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ “እንዲህ ከሆነስ እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” (ማቴዎስ 26፥54)።
ለአባቱ ባለው ፍፁም ታዛዥነት—እና ለእኛ ባለው ፍጹም ፍቅር—ኢየሱስ በፈቃዱ ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ እና ማለቂያ የሌለውን እና ዘለአለማዊውን የሃጢያት ክፍያ ፈጸመ፣ ይህም በጊዜ ወደ ኋላ እና ወደ ፊት ዘለዓለም ይደርሳል።
የአዳኛችን ድል
ከእርሱ ሞት በኋላ የእርሱ ሐዋርያት ስራውን እንዲቀጥሉ ኢየሱስ አዟቸው ነበር። ይህን የሚያደረጉት እንዴት ነው? ከመካከላቸው ብዙዎቹ ተራ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ፣ እንዲሁም አንዳቸውም ለአገልግሎት በምኩራቦች ውስጥ የሰለጠኑ አልነበሩም። በዚያን ጊዜ፣ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለመጥፋት የተቃረበች ትመስል ነበር። ነገር ግን ሐዋርያት ጥሪያቸውን ለመሸከም እና የዓለምን ታሪክ ለመቅረጽ ብርታት አገኙ።
እንዲህ ከመሰለው ግልፅ ድክመት ጥንካሬ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? የአንግሊካን ቤተክርስቲያን መሪና ምሁር የሆኑት ፍሬድሪክ ፋራር እንዲህ ብለዋል፣ “አንድ እና አንድ ብቻ ሊሆን የሚችል መልስ አለ—ይኸውም ከሞት መነሳት ነው። ይህ ሁሉ ትልቅ አብዮት የመጣው በክርስቶስ ትንሣኤ ኃይል ነው።”4 ከሙታን የተነሳው ጌታ ምስክሮች እንደመሆናቸው፣ ሐዋርያቱ ይህን ስራ ወደፊት ከመግፋት የሚያግደው ምንም ነገር እንደሌለ አውቀው ነበር። የጥንቷ ቤተክርስቲያን ሁሉንም ችግሮች በምታሸንፍበት ጊዜ የእነርሱ ምስክርነት ቀጣይነት ያለው የኃይል ምንጭ ነበር።
በዚህ የትንሳኤ ወቅት፣ ከተሾሙ ምስክሮቹ እንደ አንዱ፣ በአንድ የሚያምር እሁድ ማለዳ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ሊያበረታን እና ለሁሉም የሞትን እስራት ሊፈታ ከሞት መነሳቱን አውጃለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ ህያው ነው! በእርሱ ምክንያት ሞት መጨረሻችን አይደለም። ትንሳኤ፣ የክርስቶስ ነጻ እና ለሁሉም የሚሆን ስጦታ ነው።
ወደ ክርስቶስ ኑ
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና የኃጥያት ክፍያው ለሁሉም ሰዎች ነው—ይህም ማለት ለሁሉም ሰዎች ማለት ነው። የአዳኙን የኃጥያት ክፍያ መስዋዕት ሙሉ በረከቶች ለመጠቀም የምንችልበት ብቸኛው መንገድ “ወደ እኔ ኑ” (ማቴዎስ 11፥28) የሚለውን ግብዣውን በግለሠብ ደረጃ በመቀበል ነው።
በእርሱ ላይ እምነትን ስንለማመድ እና ንሰሃ ስንገባ ወደ እሱ እንቀርባለን። በስሙ ስንጠመቅ እና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ስንቀበል ወደ እርሱ እንመጣለን። እኛ ትእዛዛቱን ስንጠብቅ፣ ሥርአቶችን ስንቀበል፣ ቃል ኪዳኖችን ስንጠብቅ፣ በቤተመቅደስ ውስጥ ልምዶችን ስንቀበል እና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚኖሩትን ዓይነት ህይወት ስንኖር፣ ወደ እሱ እንመጣለን።
አንዳንድ ጊዜ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሃዘን ያጋጥማችኋል። በራሳችሁ ወይም በምትወዱት ሌላ ሰው የተነሳ ልታዝኑ ትችላላችሁ። የሌሎች ሰዎች ኃጥያት ሸክም ሆኖባችሁ ሊሆን ይችላል። የሰራችኋቸው ስህተቶች—ምናልባትም ከባድ የሆኑት—ሰላም እና ደስታ ለዘለአለም ጥለዋችሁ እንደሄዱ እንድትፈሩ ሊያደርጓችሁ ይችላሉ። በእንደዚህ አይነት ጊዜያት፣ አዳኙ የኃጥያትን ሸክም እንደሚያነሳ ብቻ ሳይሆን የእናንተን ጨምሮ “መከራና ሁሉም ዓይነት ህመምና ፈተናዎች [እንደተሠቃየ]” (አልማ 7፥11) አስታውሱ! ለእናንተ ሲል በሄደበት መንገድ ምክንያት፣ “ወደ እኔ ኑ” የሚለውን ህይወትን የሚቀይር ግብዣውን ስትቀበሉ እንዴት እንደሚረዳችሁ በግል ያውቃል።
ሁሉም እንዲመጡ ተጋብዘዋል
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሁሉም የሰማይ አባት ልጆች ወንጌሉ እና የኃጢያት ክፍያው በረከቶች በእኩል ደረጃ እንደሚገባቸው ግልጽ አድርጓል። “ሁሉም ሰው እንደሌላው ታድሏል፤ እናም ማንም አልተከለከለም” ሲል ያስታውሰናል(2 ኔፊ 26:28)።
“ወደ እርሱ የሚመጡትን ማንንም፣ ጥቁርም ነጭም፣ ባሪያውንና ነፃውን፤ ሴትና ወንድን አይክድም፤ እምነተቢሶችንም ያስታውሳል፤ እናም አይሁድም ሆኑ አህዛብ፣ ሁሉም ለእግዚአብሔር አንድ ናቸው” (2 ኔፊ 26፥33)።
“ሁሉም ወደ እርሱ እንዲመጡ ይጋብዛል”— ያ ማለት ሁላችንም ማለት ነው! በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ እውነተኛ ያልሆኑ መለያዎችን እና ሠው ሠራሽ ልዩነቶችን ማስቀመጥ የለብንም። በአዳኙ ፍቅር ላይ ማናቸውንም እንቅፋቶች ማድረግ ወይም እኛ ወይም ሌሎች ከእርሱ አቅም በላይ እንደሆንን የሚያንፀባርቁ ሃሳቦችን በፍፁም ማስተናገድ የለብንም። ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት፣ “ማለቂያ የሌለው የክርስቶስ የኃጥያት ክፍያ ብርሀን ከሚበራው በታች [ማንም] ለመስመጥ አይችልም።”5
ከዚያ ይልቅ፣ እርሷ በህይወት ከማለፏ ክጥቂት ወራት በፊት፣ እህት ሆላንድ እና እኔ እንዳስተማርነው፣ “ለጋስ መሆን እንዳለ[ብን] ትዕዛዝን ሰጥቷል፣ ይህም ልግስና ፍቅር ነው” (2 ኔፊ 26፥30)።6 ይህ አዳኙ የሚያሳየን ፍቅር ነው፣ ምክንያቱም “እርሱም ለዓለም ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም አያደርግም፤ ምክንያቱም ሰዎችን ሁሉ ወደ እርሱ ይስብ ዘንድም ሕይወቱን አሳልፎ እስከመስጠት ዓለምን ይወዳል” (2 ኔፊ 26፥24)።
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና የኃጥያት ክፍያው ለሁሉም ሰዎች እንደሆነ እመሰክራለሁ። እርሱ የሚያመጣቸውን በረከቶች በደስታ እንድትቀበሉ እጸልያለሁ።
© 2024 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። የMonthly Liahona Message, March 2024 ትርጉም። Amharic. 19284 506