“22. ስጋዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እና ራስን መቻልን መገንባት ፣” ከአጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ [2023 (እ.አ.አ)]።
“22. ስጋዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እና ራስን መቻልን መገንባት፣” ከአጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ
22.
ስጋዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እና ራስን መቻልን መገንባት
22.0
መግቢያ
የቤተክርስቲያኗ አባላት “አንዳ[ቸው] የአንዳች[ቸውን] ሸክም … ለመሸከም፣ … ከሚያዝኑት ጋር ለማዘን … መፅናናትን ለሚፈልጉ ለማፅናናት” ቃል ኪዳን ገብተዋል (ሞዛያ 18፥8–9)።
የቤተክርስቲያን አባላት ጠንክሮ በመስራት እና በጌታ እርዳታ ራስን የመቻል ሁኔታቸውን እንዲያጠናክሩ ተመክረዋል። ራስን መቻል ማለት “ለራስ እና ለቤተሰብ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑትን መንፈሳዊ እና ስጋዊ ፍላጎቶች የማሟላት ችሎታ፣ ቁርጠኝነት እና ጥረት” ማለት ነው።
የግል እና የቤተሰብ ጥረቶች
22.1
ራስን መቻልን መገንባት
ከጌታ በሚመጣ እርዳታ አባላት በሚከተሉት መንገዶች ራስን መቻልን ይገነባሉ፦
-
መንፈሳዊ፣ አካላዊ እና ስሜታዊ ጥንካሬን ማዳበር።
-
ትምህርት እና ሥራ ማግኘት።
-
ስጋዊ ዝግጁነትን ማሻሻል።
22.1.4
ስጋዊ ዝግጁነት
ቅዱሳት መጻህፍት ዝግጁ ስለመሆን ያስተምሩናል (ሕዝቅኤል 38፥7፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 38፥30 ይመልከቱ)። አባላት እራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ሌሎችን በችግር ጊዜ መንከባከብ ይችሉ ዘንድ ዝግጁ እንዲሆኑ ተመክረዋል።
አባላት በገንዘብ ዝግጁነታቸውን የሚያሳድጉት፦
-
አስራትን እና የጾም በኩራትን በመክፈል (ሚልክያ 3፥8–12ን ይመልከቱ)
-
በተቻለ መጠን ዕዳን ማቃለል እና ማስወገድ።
-
በጀት ማዘጋጀት እና በበጀት መኖር።
-
ለወደፊቱ መቆጠብ።
-
ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማቅረብ እንዲረዳቸው ተገቢውን ትምህርት ማግኘት (22.3.3 ይመልከቱ)።
ዝግጁነት ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ መሰረታዊ ፍላጎቶችን እንዴት ማሟላት እንደሚቻል እቅድ ማውጣትንም ያካትታል። አባላት የአጭር እና የረዥም ጊዜ የምግብ፣ የውሃ እና የሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አቅርቦትን እንዲገነቡ ይበረታታሉ።
22.2
ስጋዊ እና ስሜታዊ ፍላጎቶች ያላቸውን ማገልገል
የጌታ ደቀ መዛሙርት “እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ እንዲሁም አንደኛው ሌላውን እንዲያገለግል” እንዲሁም “[የእነርሱን] እርዳታ ፍለጋ የቆሙትን [እንዲረዷቸው]“ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል (ሞዛያ 4፥15–16)። አባላት የተለየዩ ጥንካሬዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን በመገንዘብ ሌሎችን ጌታ እንደሚያያቸው ለማየት ይጥራሉ። እነዚህ ፍላጎቶች ምግብ፣ ልብስ፣ መኖሪያ ቤት፣ ትምህርት፣ ሥራ፣ አካላዊ ጤንነት እና ስሜታዊ ደህንነትን ሊያካትቱ ይችላሉ።
22.2.1
የጌታ ጎተራ
ሥጋዊ ፍላጎቶች ያሏቸውን ለመርዳት በቤተክርስቲያኗ ያሉት ሁሉም ሃብቶች የጌታ ጎተራ ይባላሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 82፥18–19 ይመልከቱ)። እነዚህም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት የሚውሉ የአባላት ጊዜን፣ ተሰጥኦን፣ ርህራሄን፣ ቁሳቁስን እና የገንዘብ ምንጮች ሥጦታዎችን ያካትታሉ።
የጌታ ጎተራ በእያንዳንዱ አጥቢያ እና ካስማ አለ። መሪዎች ብዙውን ጊዜ የአጥቢያ እና የካስማ አባላት የሚሰጡትን የእውቀት፣ የችሎታ እና የአገልግሎት መሥዋዕት በመጠቀም ግለሰቦች እና ቤተሰቦች ለፍላጎቶቻቸው መፍትሄ እንዲያገኙ መርዳት ይችላሉ።
22.2.2
ጾም እና የጾም በኩራት ህግ
ጌታ ህዝቡን ለመባረክ እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የሚያገለግሉበትን መንገድ ለማዘጋጀት የፆምን እና የፆም በኩራት ህግን አቋቁሟል። አባላት በጾም ህግ በሚኖሩበት ጊዜ ወደ ጌታ ይቀርባሉ እንዲሁም በመንፈሳዊ ጥንካሬ ያድጋሉ። (ኢሳይያስ 58፥12፤ ሚልክያ 3፥8–12 ይመልከቱ)።
ፆም በማንኛውም ጊዜ ሊደረግ ይችላል። ነገር ግን አባላት አብዛኛውን ጊዜ የወሩን የመጀመሪያ ሰንበት የጾም ቀን አድርገው ያከብራሉ። የጾም ቀን ብዙውን ጊዜ የሚከተሉትን ያካትታል፦
-
ጸሎት
-
ለ24 ሰአታት ያህል ያለምግብ እና ያለመጠጥ መቆየት (በአካል ብቁ ከሆነ)
-
የጾምበኩራትን በልግስና መስጠት
የጾም በኩራት እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት የሚደረግ ስጦታ ነው። አባላት በሚጾሙበት ጊዜ ቢያንስ ካልተመገቡት የምግብ ዋጋ ጋር እኩል የሆነ የፆም በኩራት እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል።
አባላት የፆም በኩራታቸውን እና የተሞላ የአስራት እና የሌሎች በኩራቶች ቅፅን ለኤጲስ ቆጶሱ ወይም ከአማካሪዎቹ ለአንዱ ሊሰጡ ይችላሉ። በአንዳንድ ዋና አካባቢዎች፣ በdonation online [በይነመረብ ልግስና] ሊፈፅሙም ይችላሉ።
የመሪ ጥረቶች
22.3
ራስን መቻልን የመገንባት እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የማገልገል መንገድ
22.3.1
እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መፈለግ
ኤጲስ ቆጶሱ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የመፈለግ እና የመንከባከብ የተቀደሰ ኃላፊነት አለበት (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥112ን ይመልከቱ)። ኤጲስ ቆጶሱን በዚህ ኃላፊነት የመርዳት ጠቃሚ ሚና ያላቸው ሌሎችም የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
-
የአገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች።
-
የሴቶች መረዳጃ ማህበር እና የሽማግሌዎች ቡድን አመራሮች
-
የኤጲስ ቆጶስ አማካሪዎች።
-
የአጥቢያ ምክር ቤት ሌሎች አባላት።
22.3.2
አባላት የአጭር ጊዜ ፍላጎቶችን እንዲገመግሙ እና እንዲፈቱ መርዳት
አባላት በራሳቸው ጥረት እና ከዘመዶቻቸው በሚደረግ እርዳታ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ይጥራሉ። ይህ በቂ በማይሆንበት ጊዜ፣ አባላት ከሌሎች ምንጮች እርዳታ ሊፈልጉ ይችላሉ፣ ለምሳሌ፦
-
ከመንግስት እና ከማህበረሰብ ምንጮች (22.12ን ይመልከቱ)።
-
የቤተክርስቲያን እርዳታ።
የቤተክርስቲያን እርዳታ ለአጭር ጊዜ ፍላጎቶች የሚውሉ እንደ ምግብ፣ የንፅህና እቃዎችን፣ አልባሳትን፣ የመኖሪያ ቤትን ወይም ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ሊያካትት ይችላል። ኤጲስ ቆጶሳት ለእነዚህ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት የፆም በኩራትን ሊጠቀሙ ይችላሉ። የኤጲስ ቆጶሳት ማዘዣዎች ባሉበት፣ ኤጲስ ቆጶሳት በአጠቃላይ ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን ለማቅረብ እነርሱን ይጠቀማሉ (በ“Leader and Clerk Resources [LCR] [አኤልሲአር]” ውስጥ Bishops’ Orders and Referrals [የኤጲስ ቆጶሳት ማዘዣዎች እና ምንጮች] ይመልከቱ)።
22.3.3
የረዥም ጊዜ ራስን መቻል እንዲገነቡ አባላትን መርዳት
የረጅም ጊዜ ችግሮችን ለመፍታት አባላት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ትምህርት፣ የሙያ ስልጠና ወይም ሌሎች ግብአቶች ራስን መቻልን እንዲገነቡ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ፍላጎቶቻቸውን እንዲያሟሉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
Self-Reliance Plan [የራስን መቻል ዕቅድ] አባላት ጥንካሬዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን እንዲለዩ ይረዳቸዋል። ጠቃሚ ግብዓቶችን እንዲለዩም ይረዳቸዋል። ይህ ዕቅድ የቤተክርስቲያኗ ድጋፍ በሚታሰብበት ጊዜ ጥቅም ላይ መዋል አለበት።
22.3.4
ስሜታዊ ፍላጎቶች ያላቸውን ማገልገል
ብዙ አባላት ስሜታዊ ችግሮች ያጋጥማቸዋል። አገልጋይ ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም የአጥቢያ መሪዎች አባላት በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ያሉትን በመርዳት ረገድ አጋዥ ሊሆኑ ይችላሉ።
22.4
የቤተክርስቲያን እርዳታ የመስጠት መርሆዎች
በጌታ እገዛ አባላት የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሻሉ።
የቤተክርስቲያን እርዳታ አባላት ጥገኝነትን ሳይሆን በራሳቸው መተዳደርን እንዲያዳብሩ ለመርዳት የታሰበ ነው። ማንኛውም የሚሰጥ እርዳታ አባላት እራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር ይኖርበታል።
22.4.1
የግል እና የቤተሰብ ኃላፊነትን ማበረታታት
ግለሰቦች እና ቤተሰቦች ለስጋዊ፣ ለስሜታዊ እና ለመንፈሳዊ ደህንነት ዋነኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው መሪዎች ያስተምራሉ።
ኤጲስ ቆጶሱ (ወይም እርሱ የሚመድበው ሌላ መሪ ወይም አባል) የቤተክርስቲያን እርዳታ ከመስጠታቸው በፊት አባላት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ምን አይነት ግብዓቶችን እየተጠቀሙ እንዳሉ ይገመግማሉ።
22.4.2
የግድ ለሚያስፈልጉ ነገሮች ጊዜያዊ እርዳታ መስጠት
የቤተክርስትያን እርዳታ አላማ አባላት ራሳቸውን ለመቻል እየጣሩ ባሉበት ጊዜ በጊዜያዊነት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ነው።
ኤጲስ ቆጶሳት የሚሰጠውን የእርዳታ መጠን እና እርዳታው የሚሰጥበትን የጊዜ ርዝመት ግምት ውስጥ በሚያስገቡበት ጊዜ፣ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታን ሊያሳዩ እና መንፈሳዊ መመሪያን ሊፈልጉ ይገባል። ጥገኝነትንም ሳይፈጥሩ ሩህሩህ እና ቸር መሆን አለባቸው።
22.4.3
ከገንዘብ ይልቅ ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን መስጠት
የሚቻል ከሆነ፣ ኤጲስ ቆጶሱ ገንዘብ ከመስጠት መቆጠብ አለበት። ከዚያ ይልቅ፣ የጾም በኩራቶችን ወይም የኤጲስ ቆጶሳትን ማዘዣዎች ሸቀጣ ሸቀጦችን ወይም አገልግሎቶችን ለማቅረብ መጠቀም አለበት። ከዚያም አባላት የሌሎች ፍላጎቶቻቸውን ወጪ ለመሸፈን የራሳቸውን ገንዘብ መጠቀም ይችላሉ።
ይህ በቂ በማይሆንበት ጊዜ፣ ኤጲስ ቆጶሱ አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን በጊዜያዊነት ለመሸፈን የጾም በኩራቶችን በመጠቀም ሊረዳ ይችላል (22.5.2ን ይመልከቱ)።
22.4.4
የስራ ወይም የአገልግሎት እድሎችን መስጠት
ኤጲስ ቆጶሳት እርዳታ የሚቀበሉ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል እንዲሰሩ ወይም አገልግሎት እንዲሰጡ ይጋብዛሉ። ይህ አባላት የክብር ስሜት እንዲኖራቸው ይረዳል። በተጨማሪም ራስን የመቻል አቅማቸውን ያሳድጋል።
22.4.5
የቤተክርስቲያን እርዳታን የተመለከቱ መረጃዎችን ሚስጥራዊ አድርጉ
ኤጲስ ቆጶሱ እና ሌሎች የአጥቢያው መሪዎች የቤተክርስቲያን እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ስለሚችሉ አባላት ያለውን ማንኛውንም መረጃ በሚስጥር ይጠብቃሉ። ይህ የአባላትን የግል መረጃ የመጠበቅ ነጻነትን እና ክብር ይጠብቃል።
22.5
የቤተክርስቲያን እርዳታ የመስጠት ፖሊሲዎች
የቤተክርስቲያኗ መሪዎች በጾም በኩራት ወይም በኤጲስ ቆጶሳት ማዘዣዎች አማካኝነት ለምግብ እና ለሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች እርዳታ በሚሰጡበት ጊዜ በዚህ ክፍል የተዘረዘሩትን ፖሊሲዎች መከተል ይኖርባቸዋል።
22.5.1
የቤተክርስቲያን እርዳታ የሚሰጣቸውን ሰዎች የሚመለከቱ ፖሊሲዎች
22.5.1.1
ለአጥቢያ አባላት እርዳታ ማድረግ
በአጠቃላይ፣ የቤተክርስቲያንን እርዳታ የሚቀበሉ አባላት በአጥቢያው ክልል ውስጥ የሚኖሩ መሆን አለባቸው እንዲሁም የአባልነት መዝገባቸው በአጥቢያው ውስጥ መሆን አለበት። አባሉ በመደበኛነት በቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ መካፈሉ ወይም የቤተክርስቲያኗን መስፈርቶች መጠበቁ ግምት ውስጥ ሳይገባ እርዳታ ሊደረግ ይችላል።
22.5.1.2
ለኤጲስ ቆጶሳት እና ለካስማ ፕሬዚዳንቶች እርዳታ ማድረግ
ኤጲስ ቆጶስ የጾም በኩራትን ከመጠቀሙ በፊት ወይም የኤጲስ ቆጶስ ማዘዣን ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ከማፅደቁ በፊት፣ ከካስማ ፕሬዳንቱ የፅሁፍ ማረጋገጫ ማግኘት ያስፈልገዋል።
22.5.1.4
የቤተክርስቲያኗ አባላት ላልሆኑ እርዳታ ማድረግ
የቤተክርስቲያኗ አባል ያልሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ወደአካባቢው የማህበረሰብ የእርዳታ ምንጮች ይላካሉ። ኤጲስ ቆጶሱ በጣም በጥቂት ሁኔታዎች፣ በመንፈስ መሪነት፣ በጾም በኩራት ወይም የኤጲስ ቆጶሳት ማዘዣ አማካኝነት ሊረዳቸው ይችላል።
22.5.2
የጾም በኩራት አጠቃቀም ፖሊሲዎች
22.5.2.1
ህክምና እና ሌላ የጤና እንክብካቤ
እያንዳንዱ የቤተክርስቲያኗ ዋና አካባቢ ለውስጥ ደዌ ህክምና፣ ለጥርስ ህክምና ወይም ለአእምሮ ጤና ህክምና ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያውለውን የጾም በኩራት የፍቃድ ገደቦች ወስኗል።
የፍቃድ ገደቦችን እና መመሪያዎችን ለማግኘት “Use of Fast Offerings for Medical Expenses [የጾም በኩራትን ለህክምና ወጪዎች መጠቀም]ን” ይመልከቱ።
22.5.2.3
የጾም በኩራት ክፍያን መተካት
አባላት ከቤተክርስቲያኗ የተቀበሉትን የጾም በኩራት እርዳታ መልሰው አይከፍሉም።
22.5.2.4
የአጥቢያ የጾም በኩራት ወጪ መጠን
ኤጲስ ቆጶሳት ለአጥቢያው አባላት የሚደረገውን የጾምበኩራት እርዳታ ከአጥቢያው በሚሰበሰበው የልገሳ መጠን መገደብ አይጠበቅባቸውም።
22.5.3
የክፍያ አፈጸጸም ፖሊሲዎች
ከተቻለ ክፍያዎች ፍጆታዎችን እና አገልግሎቶችን ለሚያቀርቡ ተቋማት በቀጥታ መደረግ አለባቸው።
22.5.4
ለኤጲስ ቆጶስ ወይም ለካስማ ፕሬዚዳንት ጥቅም የሚሰጡ የክፍያዎች ፖሊሲዎች
አንድ ኤጲስ ቆጶስ ለአባላት የጾም በኩራት እርዳታ በሚሰጥበት ጊዜ ገንዘቡን ለፍጆታዎቹ ወይም ለአገልግሎቶቹ ክፍያ ሲፈፅም ለራሱ በሚጠቅም መልኩ አያደርግም።
ለአባል የሚከፈል የፆም በኩራት ክፍያ የካስማ ፕሬዚዳንቱን ወይም የእርሱ የሆነን ንግድ የሚጠቅም ከሆነ፣ የዋና አካባቢ አመራር ፈቃድ ያስፈልጋል።
22.6
የአጥቢያ መሪዎች ሚናዎች
22.6.1
ኤጲስ ቆጶስ እና አማካሪዎቹ
ኤጲስ ቆጶሱ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የመፈለግ እና የመንከባከብ መለኮታዊ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥112ን ይመልከቱ)። አብዛኞቹን ስራዎች ለሴቶች መረዳጃ ማህበር እና ለሽማግሌዎች ቡድን አመራሮች በውክልና ይሰጣል። ሆኖም፣ የተወሰኑ ተግባራት የሚከናወኑት በኤጲስ ቆጶሱ ብቻ ነው። ለምሳሌ ኤጲስ ቆጶሱ፦
-
የማንኛውንም ሥጋዊ እርዳታ አይነት፣ መጠን እና እርዳታው የሚሰጥበትን የጊዜ ርዝመት ይወስናል።
-
የጾም በኩራት እርዳታን (22.4 እና 22.5ን ይመልከቱ) እንዲሁም የኤጲስ ቆጶሳትን የምግብ እና የሌሎች ፍጆታዎች ማዘዣን ይፈቅዳል (22.13ን ይመልከቱ)።
-
የአባላትን ራስን የመቻል ዕቅድ ራሱ ይገመግማል። እንዳስፈላጊነቱ እነዚያን ዕቅዶች እንዲከታተሉ ሌሎች የአጥቢያ አባላትን ይመድባል።
ኤጲስ ቆጶሱ እና አማካሪዎቹ የሚከተሉት ኃላፊነቶች አሉባቸው፦
-
ከሚከተሉት ጋር የተያያዙ መርሆዎችን እና በረከቶችን ያስተምራሉ (1) ስጋዊ እና ስሜታዊ ፍላጎቶች ያሏቸውን መንከባከብ እና (2) ራስን መቻልን መገንባት (22.1ን ይመልከቱ)።
-
የጾም ህግን ማስተማር እና አባላት በቸርነት የጾም በኩራት እንዲያከፍሉ ማበረታታት (22.2.2ን ተይመልከቱ)።
-
የጾም በኩራት አሰባሰብን እና የሂሳብ ቁጥጥርን በበላይነት መቆጣጠር (34.3.2 ይመልከቱ)።
22.6.2
የሴቶች መረዳጃ ማህበር እና የሽማግሌዎች ቡድን አመራሮች
በኤጲስ ቆጶሱ አመራር፣ የሴቶች መረዳጃ ማህበር እና የሽማግሌዎች ቡድን አመራሮች በአጥቢያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የመንከባከብ ቁልፍ ሚና አላቸው (8.2.2 እና 9.2.2ን ይመልከቱ)። እነዚህ መሪዎች የአጥቢያውን አባላት የሚከተሉትን ያስተምራሉ፦
-
እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማገልገል።
-
የጾምን ህግ መኖር።
-
ራስን መቻልን መገንባት።
-
የግል እና የቤተሰብ ዝግጁነትን ማበረታታት።
22.6.3
የአገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች
የመንፈሳዊ እና የሥጋዊ ፍላጎቶችን እርዳታ አብዛኛውን ጊዜ በአገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች ይጀመራል (21.1ን ይመልከቱ)። የሚያገለግሏቸው ሰዎች ያሉባቸውን ፍላጎቶች በአገልግሎት ቃለ መጠይቅ እና በሌሎች ጊዜያት ለሽማግሌዎች ቡድን ወይም ለሴቶች መረዳጃ ማህበር አመራሮች ያሳውቃሉ። ሚስጥራዊ የሆኑ ፍላጎቶችን በቀጥታ ለኤጲስ ቆጶሱ ያሳውቃሉ።
22.7
የአጥቢያ ምክር ቤት ሚናዎች
የአጥቢያ ምክር ቤት አንዱ ጠቃሚ ሚና፣ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን እንዴት መንከባከብ እንዳለበት ማቀድ እና ራሳቸውን እንዲችሉ መርዳት ነው (4.4 ይመልከቱ)። የምክር ቤቱ አባላት እነዚህን እቅዶች ከአገልግሎት ቃለ መጠይቆች እንዲሁም እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ጋር ከሚያደርጓቸው የግል ግንኙነቶች በሚያገኟቸው መረጃዎች ላይ ይመሰረታሉ። ምክር ቤቱ የአባላትን ፍላጎት በሚወያይበት ጊዜ በሚስጥር እንዲያዝ የሚጠይቁትን ሁሉ ፍላጎት ያከብራል።
22.8
የአጥቢያ የወጣቶች ምክር ቤት ሚናዎች
የአጥቢያ ወጣቶች ምክር ቤት አንዱ ዓላማ ወጣቶች የተቀደሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ መርዳት ነው (29.2.6 ይመልከቱ)።
ከኤጲስ ቆጶስ አመራሩ በሚሰጥ መመሪያ፣ የአጥቢያው የወጣቶች ምክር ቤት በአጥቢያቸው እና በማህበረሰባቸው ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የሚያገለግለሉባቸውን መንገዶች ያቅዳል።