መመሪያ መጻህፍቶች እና ጥሪዎች
27. በህይወት ላሉ የሚደረጉ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች


“27. በህይወት ላሉ የሚደረጉ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች፣” ከአጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ [2023 (እ.አ.አ)]።

“27. በህይወት ላሉ የሚደረጉ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች፣” ከአጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ

ሙሽሪት እና ሙሽራ

27.

በህይወት ላሉ የሚደረጉ የቤተመቅደስ ሥርዓቶች

27.0

መግቢያ

ቤተመቅደስ የጌታ ቤት ነው። ወደ አዳኛችን፣ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠቁሙናል። በቤተመቅደስ ውስጥ በቅዱስ ሥርዓቶች እንሳተፋለን እንዲሁም እኛን ከእርሱ እና ከአዳኛችን ጋር የሚያስተሳስረንን ቃል ኪዳን ከሰማይ አባት ጋር እንገባለን። እነዚህ ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች ወደ ሰማይ አባት እንድንመለስ እና እንደ ቤተሰብ ለዘለአለም አንድ ላይ እንድንታተም ያዘጋጁናል።

በቤተመቅደስ ሥርዓቶች እና በቃልኪዳኖች “የአምላክ አይነት ሀይል [ይገለጣል[” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥20)።

የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች የተቀደሱ ናቸው። ከቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች ጋር የተያያዙ ምልክቶች ከቤተመቅደስ ውጭ ውይይት አይደረግባቸውም። በቤተመቅደስ ውስጥ ላለመግለፅ ቃል ስለገባነው ቅዱስ መረጃም ልንወያይ አይገባንም። ሆኖም ስለቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች እና ሥርዓቶች መሰረታዊ አላማዎች እና ትምህርቶች እና በቤተመቅደስ ውስጥ ስለነበረን መንፈሳዊ ስሜቶች ልንወያይ እንችላለን።

የአጥቢያ እና የካስማ መሪዎች በዚህ ምዕራፍ ያለውን መረጃ የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ ወይም የህትመት ሥርዓቶችን ለመቀበል እየተዘጋጁ ካሉ አባላት ጋር ይወያያሉ።

27.1

የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን መቀበል

27.1.1

የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ለመቀበል መዘጋጀት

አባላት የቤተመቅደስ ሥርዓቶች ለመቀበል እና የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ለመግባት እና ለመጠበቅ ራሳቸውን በመንፈሳዊ ማዘጋጀት አለባቸው።

ወላጆች፣ ልጆቻቸው የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ለመቀበል እንዲዘጋጁ የመርዳት እጅግ አስፈላጊ ኃላፊነት አለባቸው። የካስማ እና የአጥቢያ መሪዎች፣ የአገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም የዘመድ አዝማድ አባላት ወላጆችን በዚህ ሚና ይግፏቸዋል።

አባላት የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ለመቀበል እንዲዘጋጁ ለመርዳት የሚሆኑ ግብዓቶች በዚህ temples.ChurchofJesusChrist.orgይገኛሉ።

የራሳቸውን የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ ለመቀበል ወይም ከትዳር ጓደኛ ጋር ለመታተም በዝግጅት ላይ ያሉ አባላት በቤተመቅደስ ዝግጅት ትምህርት እንዲሳተፉ ይበረታታሉ (25.2.8ን ይመልከቱ)።

27.1.3

የአካል ጉዳት ያለባቸው አባላት

የአካል ጉዳት ያለባቸው ብቁ አባላት ሁሉንም የቤተመቅደስ ሥርዓቶች መቀበል ይችላሉ። እነዚህ አባላት የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበሉ ዘመዶች ወይም ሊረዷቸው ከሚችሉ ተመሳሳይ ጾታ ካላቸው ጓደኞች ጋር በቤተመቅደስ ውስጥ እንዲሳተፉ ይበረታታሉ። አባላት ከቤተሰብ ወይም ከጓደኛ ጋር መሳተፍ የማይችሉ ከሆነ ምን አይነት ዝግጅቶች ማድረግ እንደሚቻል ለማየት አስቀድመው ወደ ቤተመቅደስ ሊደውሉ ይችላሉ።

27.1.4

የትርጉም እገዛ

አባላት የትርጉም እገዛ ከፈለጉ፣ ይህ እንዳለ ለማወቅ አስቀድመው ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ አለባቸው።

27.1.5

ወደ ቤተመቅደስ ሲኬድ የሚለበስ ልብስ

አባላት ወደ ቤተመቅደስ ሲሄዱ፣ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንደሚለብሱት ተመሳሳይ የሆነ ልብስ መልበስ አለባቸው።

ጥንዶች በቤተመቅደስ በሚፈጸም ጋብቻ እና እትመት ላይ ስለሚለበስ ልብስ መረጃ ለማግኘት 27.3.2.6ን ይመልከቱ።

ስለሚከተሉት መረጃ ለማግኘት 38.5ን ይመልከቱ፦

  • በቤተመቅደስ ቡራኬ እና በእትመት ሥርዓቶች ስለሚለበስ ልብስ።

  • የቤተመቅደስ ሥነ ስርዓቶች ልብሶችን ማግኘት፣ መልበስ እና መንከባከብ።

27.1.6

የልጆች እንክብካቤ

ልጆች በቤተመቅደስ ግቢ ውስጥ ከሆኑ የአዋቂዎች ክትትል ያስፈልጋቸዋል። የቤተመቅደስ ሰራተኞች ልጆችን ሊቆጣጠሩ የሚችሉት በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ብቻ ነው።

  • ከወላጆች ጋር ሊታተሙ ከሆነ

  • በህይወት ያሉ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው፣ ከእንጀራ እናት ወይም አባት የተገኙ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው፣ ወይም በግማሽ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው የሆኑ ሲታተሙ ሊመለከቱ ከሆነ።

27.1.7

የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ከተቀበሉ በኋላ ከአባላት ጋር መገናኘት

አብዛኛውን ጊዜ አባላት የቤተመቅደስ ሥርዓቶችን ከተቀበሉ በኋላ ጥያቄዎች አሏቸው። የቤተመቅደስ የመንፈስ ሥጦታ የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት፣ ኤጲስ ቆጶሱ፣ ሌሎች የአጥቢያ መሪዎች እና የአገልግሎት ወንድሞች እና እህቶች ስለ ቤተመቅደስ ልምዳቸው ለመወያየት ከአባላት ጋር ሊገናኙ ይችላሉ።

ጥያቄዎችን ለመመለስ ለመርዳት የሚሆኑ ግብዓቶች በዚህ temples.ChurchofJesusChrist.orgይገኛሉ።

27.2

የቤተመቅደስ ቡራኬ

ኢንዶውመንት የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል “ስጦታ” ማለት ነው። የቤተመቅደስ ቡራኬ ( ቃል በቃል እግዚአብሔር ልጆቹን የሚባርክበት የእግዚአብሔር ሥጦታ ማለት ነው። በቤተመቅደስ ቡራኬዎች በኩል አባላት የሚቀበሏቸው አንዳንድ ስጦታዎች እነዚህን ያካትታሉ፦

  • ስለጌታ ዓላማዎች እና ትምህርቶች የላቀ እውቀት።

  • የሰማይ አባት ልጆቹ እንዲያደርጉ የሚፈልገውን ሁሉ የማድረግ ኃይል።

  • ጌታን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ሌሎችን ሲያገለግሉ መለኮታዊ መመሪያ መቀበል።

  • ተጨማሪ ተስፋ፣ መፅናኛ እና ሰላም።

የእነዚህ በረከቶች ፍጻሜ የሚወሰነው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ላይ ባለ ታማኝነት ነው።

የቤተመቅደስ ቡራኬን መቀበል በሁለት ክፍሎች ይከፈላል። በመጀመሪያው ክፍል ውስጥ፣አንድ ግለሰብ የቤተመቅደስ ቡራኬ የመጀመሪያ ክፍል ተብሎ የሚጠራውን የመጀመሪያ ሥርዓት ይቀበላል። የቤተመቅደስ ቡራኬ የመጀመሪያ ክፍል መታጠብ እና መቀባት በመባልም ይታወቃል (ዘጸአት 29፥4–9 ይመልከቱ)። ከግለሰቡ መለኮታዊ ውርስ እና አቅም ጋር የተያያዙ ልዩ በረከቶችን ያካትታል።

በቤተመቅደስ ቡራኬ የመጀመሪያ ክፍል ወቅት አባሉ የቤተመቅደስ ልብስ እንዲለብስ ይፈቀድለታል። የቤተመቅደስ ልብሱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን የግል ዝምድና እና በቤተመቅደስ ውስጥ የተገቡትን ቃል ኪዳኖች ለመታዘዝ ያለውን ቁርጠኝነት ይወክላል። አባላት ለቃል ኪዳኖቻቸው ታማኝ ሲሆኑ እና በህይወታቸው ሙሉ የቤተመቅደስ ልብሱን በትክክል ሲለብሱ እንደ ጥበቃም ያገለግላል። ስለቤተመቅደስ ልብስ አለባበስ እና አንክብካቤ መረጃ ለማግኘት 38.5.5 ይመልከቱ።

በሁለተኛው የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ ክፍል፣ የደህንነት እቅድን ፍጥረትን፣ የአዳም እና የሔዋን ውድቀትን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያን፣ ክህደትን እና ዳግም መመለስን የሚያካትት ትምህርት ይሰጣል። አባላት በጌታ ፊት ለመሆን እንዴት መመለስ እንደሚችሉ መመሪያ ይቀበላሉ።

በቤተመቅደስ ቡራኬ ውስጥ አባላት በሚከተለው መልኩ ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን እንዲገቡ ተጋብዘዋል፦

  • የመታዘዝን ህግ መኖር እና የሰማይ አባትን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ።

  • የመስዋዕት ህግን መታዝ፣ ይህም የጌታን ስራ ለመደገፍ መስዋዕት መክፈል እና በተሰበረ ልብ እና በተዋረደ መንፈስ ንስሃ መግባት ማለት ነው።

  • የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ህግ መታዘዝ፣ ይህም እርሱ በምድር በነበረበት ጊዜ ያስተማረው ታላቁ ህግ ነው።

  • የንፅህና ህግን መጠበቅ፣ ይህም ማለት በእግዚአብሔር ህግ መሰረት፣ በህጋዊ መንገድ እንዲሁም በህጋዊ ጋብቻ አማካኝነት ከተጋባው ወይም ከተጋባችው ሰው ጋር ብቻ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ ማለት ነው።

  • የቅድስና ህግን መጠበቅ፣ ይህ ማለት አባላት የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን በምድር ላይ ለመገንባት ጊዜያቸውን፣ ተሰጥኦዋቸውን እና ጌታ የባረካቸውን ነገሮች ሁሉ ይሰጡታል ማለት ነው።

በምላሹም፣ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳናቸውን በመጠበቅ ረገድ ታማኝ ለሚሆኑ “ከላይ የሚመጣ ኃይል” እንደሚሰጣቸው የሰማይ አባት ቃል ገብቷል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 38፥32፣ 38፤ በተጨማሪም ሉቃስ 24፥49ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 43፥16ን ይመልከቱ)።

27.2.1

የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታን ማን ሊቀበል ይችላል

ሁሉም ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ጎልማሳ የቤተክርስቲያኗ አባላት የራሳቸውን የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ ለመቀበል እንዲዘጋጁ ተጋብዘዋል። አባላት የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታውን ከመቀበላቸው በፊት አስቀድመው መደረግ ያለባቸውን ሁሉንም ሥርዓቶች መፈፀም እና መመዝገብ አለባቸው (26.3.1 ይመልከቱ)።

27.2.1.1

አዲስ የተጠመቁ አባላት

ብቁ ጎልማሳ አዲስ አባላት ማረጋገጫቸውን ከተቀበሉበት ቀን ጀምሮ ቢያንስ አንድ ሙሉ አመት ሲሆናቸው የቤተመቅደስ ቡራኬን ሊቀበሉ ይችላሉ።

27.2.1.2

የቤተመቅደስ ቡራኬን ያልተቀበሉ የትዳር ጓደኛ ያላቸው አባላት

የትዳር ጓደኛው/ዋ የቤተመቅደስ ቡራኬን ያልተቀበለ/ች ብቁ አባል የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲሟሉ የእርሱን ወይም የእርሷን የቤተመቅደስ ቡራኬ መቀበል ይችላል/ትችላለች።

  • የቤተመቅደስ ቡራኬን ያልተቀበለው/ችው የትዳር ጓደኛ ፈቃዱን/ዷን ይሰጣል/ትሰጣለች።

  • አባሉ፣ ኤጲስ ቆጶሱ እና የካስማ ፕሬዚዳንቱ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖቹ ያስከተሉት ሃላፊነት በትዳሩ ላይ መስተጓጎል እንደማይፈጥር እርግጠኞች ናቸው።

የትዳር ጓደኛቸው የቤተክርስቲያኗ አባል ቢሆኑም ባይሆኑም እነዚህ ሁኔታዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ።

27.2.1.3

አእምሯዊ እክል ያለባቸው አባላት

አእምሯዊ እክል ያለባቸው አባላት የራሳቸውን የቤተመቅደስ ቡራኬን መቀበል የሚችሉት፦

  • ሁሉንም አስቀድመው ሊፈፅሙ የሚገባቸውን ሥርዓቶች ከፈጸሙ (26.3.1 ን ይመልከቱ)።

  • ተያያዥ የሆኑትን ቃል ኪዳኖች የመረዳት፣ የማድረግ እና የመጠበቅ አዕምሯዊ ብቃት ካላቸው።

ኤጲስ ቆጶሱ ከአባሉ/ሏ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ ከእርሱ ወይም ከእርሷ ወላጆች ጋር ሲመክር። በተጨማሪም የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ይሻል። ከካስማ ፕሬዚዳንቱ ጋር ሊመክር ይችላል።

27.2.2

የቤተመቅደስ ቡራኬን መቼ ለመቀበል እንደሚቻል መወሰን

የቤተመቅደስ ቡራኬን የመቀበል ውሳኔ የግል ነው እንዲሁም በጸሎት መደረግ ይኖርበታል። የቤተመቅደስ ቡራኬን ለመቀበል ለሚዘጋጁት ሁሉ የኃይል እና የመገለጥ በረከት ነው። አባላት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ ሲያሟሉ የራሳቸውን የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ ለመቀበል መምረጥ ይችላሉ፦

  • ቢያንስ 18 ዓመት ሲሞላቸው።

  • የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ ወይም ተመጣጣኝ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወይም በአሁኑ ሰዓት እየተማሩ ያልሆኑ።

  • ማረጋገጫቸውን ከተቀበሉ አንድ ድፍን ዓመት ያለፋቸው።

  • በመላ ሕይወታቸው የተቀደሱ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን የመቀበል እና የማክበር ፍላጎት ይሰማቸዋል።

የሚስዮን ጥሪ የተቀበሉ ወይም በቤተመቅደስ ለመታተም በዝግጅት ላይ ያሉ አባላት የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታን መቀበል አለባቸው።

አንድ አባል የቤተመቅደስ ቡራኬን እንዲቀበል የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ከመስጠት በፊት፣ ኤጲስ ቆጶሱ እና የካስማ ፕሬዚዳንቱ፣ ግለሰቡ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ለመረዳት እና ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑ ሊሰማቸው ይገባል። ይህ ብቁነት ለእያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ ይወሰናል።

27.2.3

የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታውን ለመቀበል ማቀድ እና መርሃ ግብር ማውጣት

27.2.3.1

በህይወት ላሉ ለሚደረጉ ሥርዓቶች የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ

አንድ አባል በህይወት ላሉ ለሚደረጉ ሥርዓቶች ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት እና የቤተመቅደስ ቡራኬውን ለመቀበል የቤተመቅደስ መግቢያ መቀበል አለበት። ስለእነዚህ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያዎች መረጃ ለማግኘት 26.5.1ን ይመልከቱ።

27.2.3.2

ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ

የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታን ለመቀበል የሚያቅዱ አባላት ሥርዓቱን መፈጸም ይችሉ ዘንድ ቀጠሮ ለመያዝ አስቀድመው ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ አለባቸው።

27.2.3.3

የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታን የሚቀበሉ አባላትን የሚያጅቡ

የራሳቸውን የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ የሚቀበሉ አባላት በመንፈስ ሥጦታው ክፍለ ጊዜ እንዲያጅቧቸው እና እንዲረዷቸው ከእነርሱ ጋር በጾታ ተመሳሳይ የሆነ የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታን የተቀበለ ሰው ሊጋብዙ ይችላሉ። አንድ አጃቢ ወቅታዊ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ሊኖረው ይገባል። አስፈላጊ ከሆነ ቤተመቅደሱ አጃቢ ሊያቀርብ ይችላል።

27.3

የባል እና የሚስት እትመት

የባል እና የሚስት የቤተመቅደስ እትመት ለአሁን እና ለዘለአለም በአንድነት ያጣምራቸዋል። በቤተመቅደስ ውስጥ ለገቧቸው ቃል ኪዳኖች ታማኝ ከሆኑ እነዚህን በረከቶች ይቀበላሉ። በዚህ ሥርአት አማካኝነት ልጆቻቸውም የቤተሰባቸው የዘለአለም አካል ሊሆኑ ይችላሉ።

የቤተክርስቲያን መሪዎች አባላት በቤተመቅደስ ለመጋባት እና ለመታተም እንዲዘጋጁ ያበረታታሉ። የቤተመቅደስ ጋብቻ ህጋዊ እውቅና በሌለው አካባቢ የተፈቀደላቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች ወይም ሌሎች የማዘጋጃ ቤት ጋብቻን ሊያስፈፅሙ ይችላሉ፤ ከዚያም የቤተመቅደስ እትመት ይከተላል (38.3 ይመልከቱ)። የቤተመቅደስ ጋብቻ ወላጆች ወይም የቅርብ የቤተሰብ አባላት በቤተመቅደሱ ሥርዓት ላይ አለመሳተፋቸው የመገለል ስሜት እንዲሰማቸው ሊያደርግ የሚችል ሲሆን ይህን መንገድ መከተል ይቻላል።

27.3.1

በቤተመቅደስ ማን ሊታተም ይችላል

ሁሉም ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ያላገቡ የቤተክርስቲያኗ አባላት በቤተመቅደስ ለመታተም እንዲዘጋጁ ተጋብዘዋል። በማዘጋጃ ቤት ሹም ፊት ጋብቻቸውን የፈጸሙ ሰዎች ዥግጁ እንደሆኑ ለአሁን እና ለዘለዓለአለም በቤተመቅደስ እንዲታተሙ ይበረታታሉ። አባላት ከመታተማቸው በፊት የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ መቀበል አለባቸው (27.2ን ይመልከቱ)።

በቤተመቅደስ የሚታተሙ ጥንዶች (1) ከመታተማቸው በፊት ጋብቻቸውን በማዘጋጃ ቤት የሚፈፅሙ ወይም (2) በአንድ የቤተመቅደስ ሥርዓት ላይ ጋብቻቸውን የሚፈፅሙ እና የሚታተሙ መሆን አለባቸው። 27፥.3፥2 ይመልከቱ።

27.3.1.2

አእምሯዊ እክል ያለባቸው አባላት

አእምሯዊ እክል ያለባቸው አባላት ከትዳር ጓደኛቸው፣ ከወንድ እጮኛቸው ወይም ከሴት እጮኛቸው ጋር ሊታተሙ የሚችሉት፦

  • የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ መቀበልን ጨምሮ ሁሉንም አስቀድመው ሊፈፅሙ የሚገባቸውን ሥርዓቶች ከፈጸሙ (27.2.1.3ን ይመልከቱ)።

  • ተያያዥ የሆኑትን ቃል ኪዳኖች የመረዳት፣ የማድረግ እና የመጠበቅ አዕምሯዊ ብቃት ካላቸው።

ኤጲስ ቆጶሱ ከአባሉ እንዲሁም ከእርሱ ወይም ከእርሷ የትዳር ጓደኛ፣ ከወንድ ወይም ከሴት እጮኛ ጋር ይመከራል። በተጨማሪም የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ይሻል። ከካስማ ፕሬዚዳንቱ ጋር ሊመክር ይችላል።

27.3.2

የቤተመቅደስ ጋብቻን ወይም እትመትን ማቀድ እና መርሃ ግብር ማውጣት

27.3.2.1

በህይወት ላሉ ለሚደረጉ ሥርዓቶች የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ መቀበል

አንድ አባል ከትዳር ጓደኛው/ዋ ጋር ለመታተም በህይወት ላሉ ለሚደረጉ ሥርዓቶች የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ መቀበል አለበት/ባት። ስለነዚህ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያዎች መረጃ ለማግኘት 26.3 ን ይመልከቱ።

27.3.2.2

ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ

በቤተመቅደስ ጋብቻን ለመፈጸም ወይም ለመታተም የሚያቅዱ አባላት ሥርዓቱን መፈጸም ይችሉ ዘንድ ቀጠሮ ለማስያዝ አስቀድመው ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ አለባቸው።

27.3.2.3

የጋብቻ ፈቃድ ማግኘት

ጥንዶች ከመጋባታቸው በፊት ጋብቻው በሚፈጸምበት ቦታ የሚሰራ ሕጋዊ የጋብቻ ፈቃድ ማግኘት አለባቸው። ጥንዶቹ በተመሳሳይ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመጋባት እና ለመታተም ያቀዱ ከሆነ ሕጋዊ የጋብቻ ፈቃድ ወደ ቤተመቅደስ ይዘው መምጣት አለባቸው።

ጥንዶቹ በመዘጋጃ ቤት ጋብቻቸውን ከፈጸሙ በኋላ የሚታተሙ ከሆነ ሕጋዊ የጋብቻ ፈቃድ ወደ ቤተመቅደስ ይዘው መምጣት አያስፈልጋቸውም። ከዚያ ይልቅ በመዘጋጃ ቤት ጋብቻቸውን የፈጸሙበትን ቀን እና ቦታ እንደ መዝገብ ማረጋገጥ ሂደት ያቀርባሉ።

27.3.2.4

ሙሽራውን እና ሙሽራዋን የሚያጅቡ

የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበለች እህት በመላበሻ ክፍል እንድታግዛት ከሙሽራዋ ጋር ልትሆን ትችላለች። የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበለ ወንድም ይህንኑ ለሙሽራው ሊያደርግ ይችላል። አንድ አጃቢ ወቅታዊ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ሊኖረው ይገባል። አስፈላጊ ከሆነ ቤተመቅደሱ አጃቢ ሊያቀርብ ይችላል።

27.3.2.5

የቤተመቅደስ ጋብቻን ወይም እትመትን ማን ሊፈፅም ይችላል

የቤተመቅደስ ጋብቻ ወይም አትመት ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው ጥንዶቹ በሚጋቡበት ወይም በሚታተሙበት ቤተመቅደስ ውስጥ በተመደበው አታሚ ነው። አንድ የቤተሰብ አባል ወይም የሚያውቁት ሰው የማተም ሥልጣን ካለውና ጥንዶቹ በሚጋቡበት ወይም በሚታተሙበት ቤተመቅደስ ውስጥ ከተመደበ ጋብቻውን ወይም እትመቱን እንዲያከናውን ሊጋብዙት ይችላሉ።

27.3.2.6

ለቤተመቅደስ ጋብቻ ወይም እትመት ተገቢ የሆነ አለባበስ

የሙሽራዋ ቀሚስ በቤተመቅደስ ውስጥ የሚለበሰው የሙሽራዋ ልብስ ነጭ፣ ንድፉ እና ጨርቁ ልከኛ የሆነ እንዲሁም ከተራቀቀ ጌጣጌጥ የጸዳ መሆን አለበት። በተጨማሪም የቤተመቅደስ ልብሱን መሸፈን ይኖርበታል። ወደውስጥ የሚያሳይ ጨርቅ በሌላ የሚከልል ጨርቅ መደረብ አለበት።

በቤተመቅደስ ውስጥ ከሚለበሱ ሌሎች ቀሚሶች ጋር የሚጣጣም ለማድረግ የሙሽራዋ ቀሚስ ረጅም እጅጌዎች ያሉት ወይም ሶስት አራተኛውን ክፍል የሚሸፍን ሊሆን ይገባል። በእትመት ጊዜ ወደላይ የሚታሰሩ ወይም የሚነሱ ካልሆነ በስተቀር ቀሚሶች ቬሎ ሊኖራቸው አይገባም።

አስፈላጊ ከሆነ ቤተመቅደሱ ቀሚስ ሊያቀርብ ይችላል።

የሙሽራው አለባበስ ሙሽራው በጋብቻ እና በእትመት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተለመደውን የቤተመቅደስ ልብስ ይለብሳል (38.5፥1 እና 38.5፥2ን ይመልከቱ)።

የእንግዶች አለባበስ። በጋብቻ ወይም በእትመት ሥነ ሥርዓት ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ እንደሚለብሱት ተመሳሳይ የሆነ ልብስ ይለብሳሉ። ከቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ መቀበል ክፍለ ጊዜ በቀጥታ ወደ እትመቱ የመጡ አባላት የቤተመቅደስ ሥርዓት አለባበስ ሊለብሱ ይችላሉ።

አበቦች። ጥንዶቹ እና እንግዶቻቸው በጋብቻ እና በእትመት ሥነ ሥርዓቱ ላይ አበቦችን መያዝ የለባቸውም።

27.3.2.7

ከቤተመቅደስ ጋብቻ ወይም እትመት በኋላ ቀለበት መለዋወጥ

ቀለበት መለዋወጥ የቤተመቅደስ እትመት ሥነ ሥርዓቱ ክፍል አይደለም። ሆኖም ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ጥንዶች በመታተሚያ ክፍሉ ውስጥ ቀለበት ሊለዋወጡ ይችላሉ። ጥንዶች በቤተመቅደስ ውስጥ በሌላ በማንኛውም ጊዜ ወይም ቦታ ወይም በቤተመቅደስ ግቢ ውስጥ ቀለበት መለዋወጥ የለባቸውም።

በተመሳሳይ ሥነ ሥርዓት ላይ ጋብቻቸውን የፈጸሙ እና የታተሙ ጥንዶች በቤተመቅደስ ጋብቻ ላይ መገኘት ያልቻሉ የቤተሰብ አባላትን ለማካተት ሲሉ በሌላ ጊዜ ቀለበት መለዋወጥ ይችላሉ። ቀለበት መለዋወጥ የቤተመቅደስ እትመት ሥነ ሥርዓቱ ክፍል አይደለም። ባልና ሚስቱ በቤተመቅደስ ውስጥ ጋብቻቸውን ከፈጸሙ ወይም ከታተሙ በኋላ ቃለ መሐላ መለዋወጥ የለባቸውም።

በቤተመቅደስ ከመታተማቸው በፊት በማዘጋጃ ቤት የተጋቡ ጥንዶች በማዘጋጃ ቤት ሥነ ሥርዓቱ ላይ፣ በቤተመቅደስ በሚታተሙበት ጊዜ ወይም በሁለቱም ሥነ ሥርዓቶች ላይ ቀለበት መለዋወጥ ይችላሉ።

27.3.4

በቤተመቅደስ ጋብቻ ወይም እትመት ማን ሊሳተፍ ይችላል

ጥንዶች በቤተመቅደስ በሚፈጸም ጋብቻ እና እትመት ላይ የቅርብ የቤተሰብ አባላትን እና ጓደኞችን ብቻ መጋበዝ አለባቸው። ተጠያቂነት ያላቸው አባላት ለመሳተፍ የቤተመቅደስ የመንፈስ ስጦታ የተቀበሉ እና ወቅታዊ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል።

የካስማ ፕሬዚዳንቱ በአእምሮ እክል ምክንያት ያልተጠመቀ ወይም የቤተመቅደስ ቡራኬን ያልተቀበለ ሰው፣ የቤተመቅደስ ጋብቻን ወይም በህይወት ያሉ ወንድሞቹ እና እህቶቹ ሲታተሙ እንዲመለከት ሊፈቅድለት ይችላል። ግለሰቡ፦

  • ቢያንስ 18 ዓመት መሆን አለበት።

  • በሥነ ሥርዓቱ ወቅት አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ለመቆየት የሚችል መሆን አለበት።

የካስማ ፕሬዚዳንቱ፣ ግለሰቡ እትመቱን ለመመልከት የተፈቀደለት መሆኑን ጠቅሶ ደብዳቤ ይፅፋል። ይህ ደብዳቤ ለቤተመቅደስ ይሰጣል።

27.4

በህይወት ያሉ ልጆችን ከወላጆቻቸው ጋር ማተም

እናታቸው በቤተመቅደስ ከባል ጋር ከታተመች በኋላ የተወለዱ ልጆች የሚወለዱት በዚያ የእትመት ቃል ኪዳን ውስጥ ነው። ከወላጆች ጋር የመታተም ሥርዓትን መቀበል አያስፈልጋቸውም።

በቃል ኪዳኑ ውስጥ ያልተወለዱ ልጆች ከሥጋ ወላጆቻቸው ወይም ከአሳዳጊ ወላጆቻቸው ጋር በመታተም የዘለዓለም ቤተሰብ አካል መሆን ይችላሉ። እነዚህ ልጆች በቃል ኪዳን ከተወለዱት ጋር ተመሳሳይ በረከቶችን ያገኛሉ።

27.4.2

ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ

ልጆቻቸው ከእነርሱ ጋር እንዲታተሙ የሚፈልጉ ጥንዶች ወይም ከሞቱ ወላጆቻቸው ጋር መታተም የሚፈልጉ ልጆች ሥርዓቱን መፈጸም ይችሉ ዘንድ ቀጠሮ ለማስያዝ አስቀድመው ከቤተመቅደሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ አለባቸው።