ምዕራፍ ፮
ኔፊ ስለ እግዚአብሔር ነገሮች ፃፈ—የኔፊ ዓላማ ሰዎችን ወደ አብርሃም አምላክ መጥተው እንዲድኑ ማስረዳት ነው። ከ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እና አሁን እኔ፣ ኔፊ፣ የአባቶቼን የትውልድ ሀረግ በዚህ የመዝገቤ ክፍል አልፅፍም፣ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በዚህ በምፅፍበት ሰሌዳ ላይ አልፅፈውም፤ አባቴ ባቆየው መዝገብ ላይ ተፅፏልና፤ ስለዚህ በዚህ ሥራ ውስጥ አልፅፈውም።
፪ እኛ የዮሴፍ ትውልዶች ነን ማለት ብቻ ይበቃኛል።
፫ ሁሉንም የአባቴን ነገሮች በመፃፍ ጥንቁቅ መሆኔ ልዩነት አያመጣም፣ በእነዚህ ሰሌዳ ላይ መፃፍ አይችሉምና፣ እኔ የእግዚአብሔርን ነገሮች ለመፃፍ ቦታውን እፈልገዋለሁና።
፬ ሙሉ አላማዬም ሰዎችን ወደ አብርሃም አምላክ፣ ወደ ይስሀቅ አምላክና፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ እንዲመጡና እንዲድኑ ለማሳመን ነውና።
፭ ስለዚህ፣ ለዓለም አስደሳች የሆኑትን ነገሮች እኔ አልፅፍም፣ ነገር ግን ለእግዚአብሔርና ከዓለም ላልሆኑት የሚያስደስቱ ነገሮችን እፅፋለሁ።
፮ ስለዚህ ሰሌዳዎቹን ለሰው ልጆች ዋጋ በሌላቸው ነገሮች እንዳይሞሏቸው ለዘሮቼ ትዕዛዝን እሰጣለሁ።