ቅዱሳት መጻህፍት
ሔለማን ፲፩


ምዕራፍ ፲፩

ኔፊ ጌታ ጦርነታቸውን በረሃብ እንዲለውጠው ለመነ—ብዙ ሰዎች ጠፉ—ንስሃ ገቡ፤ እናም ኔፊ ዝናብ እንዲያመጣ ጌታን በጥብቅ ለመነው—ኔፊ እና ሌሂ ብዙ ራዕዮችን ተቀበሉ—የጋድያንቶን ዘራፊዎች በምድሪቱ ላይ ተቋቋሙ። ከ፳–፮ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሰባ ሁለተኛ ዓመት የንግስና ዘመን ፀቡ ተስፋፋ፤ ስለሆነም በኔፊ ሰዎች ሁሉ መካከል በምድሪቱ ላይ በሙሉ ጦርነቶች ነበሩ።

እናም ይህንን የጥፋትና የተንኮል ስራ ያከናውኑ የነበሩት እነዚህ ሚስጥራዊ የሆኑት የሌቦች ቡድን ነበሩ። እናም ጦርነቱ በዚሁ ዓመት ሁሉ ቆይቷል፤ እናም እስከ ሰባ ሶስተኛው ዓመትም ቆይቷል።

እናም እንዲህ ሆነ በዚሁ ዓመት ኔፊ እንዲህ በማለት ወደጌታ ጮኸ፥

አቤቱ ጌታ፣ እነዚህ ሰዎች በጎራዴ እንዲጠፉ አትፍቀድ፤ ነገር ግን ጌታዬ ሆይ፣ ጌታ አምላካቸውን እንዲያስታውሱ ለማነሳሳት በምድሪቱ ረሃብ እንዲኖር አድርግ፤ እናም ምናልባት ንስሃ ይገባሉና፣ ወደ አንተ ይመለሳሉ።

እናም በኔፊም ቃል መሰረት ተከናወነ። እናም በኔፊ ሰዎች መካከልም በሙሉ፣ በምድሪቱ ላይ ረሃብ ሆነ። እናም በሰባ አራተኛው ዓመትም ረሃቡ ቀጠለና፣ የጥፋት ስራው በጎራዴ መሆኑ ቆመ፣ ነገር ግን በረሃብ ኃይለኛ ሆነ።

እናም ይህ የጥፋትም ስራ ደግሞ በሰባ አምስተኛው ዓመት ቀጠለ። ምድሪቱም በመመታትዋ ደረቅ ነበረች፣ በእህል ወቅትም እህልን አልሰጠችም፤ እናም ምድሪቱ በሙሉ ተመታች፤ በላማናውያን እንዲሁም በኔፋውያን መካከልም፣ በምድሪቱ በይበልጥ ክፉ በሆኑት አካባቢ በሺህ የሚቆጠሩት በመመታታቸው ሞቱ።

እናም እንዲህ ሆነ በረሃብ ሊጠፉ መቃረባቸውን ሰዎቹ ተመለከቱና ጌታ አምላካቸውን ማስታወስ ጀመሩ፤ እናም የኔፊንም ቃል ማስታወስ ጀመሩ።

እናም ሰዎቹ ከዋና ዳኞቻቸው እንዲሁም ከመሪዎቻቸው ጋር ኔፊን እንዲህ እንዲሉ መማፀን ጀመሩ፥ እነሆ፣ አንተ የእግዚአብሔር ሰው መሆንህን እናውቃለን፣ እናም ስለዚህ ስለጥፋታችን የተናገርካቸው ቃላት ሁሉ እንዳይፈፀሙ ዘንድ ይህንን ረሃብ ከእኛ እንዲመልሰው ወደ ጌታ አምላካችን ጩህ።

እናም እንዲህ ሆነ ዳኞቹም በተፈለገው ቃላት መሰረት ኔፊን ተናገሩት። እናም እንዲህ ሆነ ሰዎቹ ንስሃ መግባታቸውንና፣ ትቢያንም ለብሰው እራሳቸውን ዝቅ ማድረጋቸውን በተመለከተ ጊዜ በድጋሚ ወደ ጌታ እንዲህ በማለት ጮኸ፥

አቤቱ ጌታ፣ እነሆ እነዚህ ሰዎች ንስሃ ገብተዋል፤ እናም ከመካከላቸው የጋድያንቶን ቡድን የሆኑትን ጨርሰው እስከሚጠፉ አባረዋቸዋል፤ እናም ሚስጥራዊ አሴራቸውንም በምድር ቀብረዋል።

፲፩ እንግዲህ፣ ጌታ ሆይ፣ በዚህ በትሁትነታቸው ምክንያት ቁጣህን ትመልሳለህን፣ እናም አንተ ባጠፋሃቸው ኃጢአተኛ ሰዎች ቁጣህ በዚህ ያብቃ።

፲፪ ጌታ ሆይ ቁጣህን አዎን፣ ኃያሉ ቁጣህን ትመልሳለህን፤ እናም ይህ ረሃብ በዚህ ምድር እንዲጠፋም አድርግ።

፲፫ ጌታ ሆይ፣ እኔንም አድምጥ፤ እናም እንደቃሌም ይሆን ዘንድ አድርግ፤ እናም ምድርም ፍሬን እንድታፈራና በእህል ወቅት እህል እንድታፈራ በምድር ገፅ ዝናብን አዝንብ።

፲፬ ጌታ ሆይ፣ የጎራዴው ቁጣም ይቆም ዘንድ ረሃብ ይሁን ባልኩ ጊዜም ቃሌን አደመጥህ፤ እና በዚህ ጊዜም እንኳን ቃላቶቼን እንደምታደምጥ አውቃለሁ፣ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ንስሃ ከገቡ አድናቸዋለሁ በማለት ተናግረሃልና።

፲፭ አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ በረሃቡና፣ በቸነፈሩ፣ እናም በእነርሱ ላይ በመጣው ጥፋትም የተነሳ ንስሃ እንደገቡ ተመልክተሃል።

፲፮ እናም እንግዲህ ጌታ ሆይ፣ ቁጣህን ትመልሳለህ፣ እናም እንደሚያገለግሉህ እንደገና ትሞክራቸዋለህን? እንደዚህ ካደረግህ፣ ጌታ ሆይ በተናገርከው ቃል መሰረት ልትባርካቸው ትችላለህ።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ በሰባ ስድስተኛው ዓመት ጌታ ቁጣውን ከህዝቡ መለሰና፣ በምድር ላይም ዝናብ እንዲዘንብ አደረገ፤ ስለዚህ ይህም በምድር በፍሬዋ ወቅት ፍሬ ሰጣት። እናም እንዲህ ሆነ በእህል ወቅትም እህል እንዲሆን አደረገ።

፲፰ እናም እነሆ፣ ህዝቡ ተደሰተና፣ እግዚአብሔርን አከበረ፤ የምድሪቱም ገፅ በሙሉ በደስታ ተሞላ፤ እናም ኔፊን ለማጥፋት ሙከራ አላደረጉም፤ ነገር ግን እንደታላቅ ነቢይና፣ የእግዚአብሔር ሰው፣ ታላቅ ኃይልና ስልጣን ከእግዚአብሔር የተሰጠው በማድረግ አከበሩት።

፲፱ እናም እነሆ፣ ሌሂ የፅድቅ ነገሮችን በተመለከተ ወንድሙም ከእርሱ ያነሰ አልነበረም።

እናም እንዲህ ሆነ የኔፊ ሰዎች በምድሪቱ ላይ እንደገና መበልፀግ ጀመሩ፣ እናም ከሰሜን በኩልና፣ ከደቡብ ከባህሩ በስተምዕራብ እስከባህሩ በስተምስራቅ ምድሪቱን በሙሉ እስከሚሸፍኑ ድረስ መብዛት እንዲሁም መሰራጨት ጀመሩ፣ የፈራረሱ ስፍራዎችንም መገንባት ጀመሩ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ሰባ ስድስተኛው ዓመት በሰላም ተፈፀመ። እናም ሰባ ሰባተኛው ዓመትም በሰላም ተጀመረ፤ ቤተክርስቲያኗም በምድር ገፅ ሁሉ ላይ ተሰራጨች፤ የኔፋውያን እንዲሁም የላማናውያን ሰዎች በአብዛኛው የቤተክርስቲያኗ አባላት ነበሩ፣ እናም በምድራቸውም እጅግ ታላቅ ሰላም ነበራቸው፤ እንደዚህም ሰባ ሰባተኛው ዓመት ተፈፀመ።

፳፪ እናም ደግሞ በሰባ ስምንተኛው ዓመት በነቢያት በሚወጡ የእምነት ነጥቦችን በተመለከተ ከነበረው ጥቂት ፀብ በቀር ሰላም ነበር።

፳፫ እናም በሰባ ዘጠነኛው ዓመት ኃያል የሆነ ጥል ተጀመረ። ነገር ግን እንዲህ ሆነ ኔፊና፣ ሌሂ፣ እናም ብዙዎቹ ወንድሞቻቸው ስለእምነቱ እውነት የሆነውን ነጥብ የሚያውቁት፣ በየቀኑ ብዙ ራዕዮችን ይመለከቱ የነበሩ፤ ስለሆነም ለህዝቡ ሰበኩ፣ በዚሁ ዓመት ሰዎቹ ጥሉን እንዲያቆሙ አደረጉ።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ የሰማንያ ዓመት የንግስ ዘመን ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደላማናውያን የሄዱ፣ ያልታወቀ ቁጥር የነበራቸው ተቃዋሚ የኔፊ ሰዎች ነበሩ፤ እናም የላማናውያንን ስም ለራሳቸው ወስደው ነበር፤ እናም ደግሞ ቁጥራቸው ያልታወቀው እውነተኛ የላማናውያን ዝርያዎች፣ በእነርሱ በቁጣ እንዲነሳሱ ተደረጉ፣ ስለዚህ ከወንድሞቻቸው ጋር ጦርነት ጀመሩ።

፳፭ እናም ግድያን እንዲሁም ዝርፊያን ፈፀሙ፤ እናም ወደ ተራራውና፣ ምድረበዳው እንዲሁም ሚስጥራዊ ስፍራዎች እያፈገፈጉ፣ ሊገኙ እንዳይችሉም እራሳቸውን ደበቁ፤ ተቃዋሚዎች ወደ እነርሱ ስለሚመጡ ተጨማሪዎችንም በየቀኑ ተቀበሉ።

፳፮ እናም ከጊዜ በኋላ፣ አዎን፣ በትንሽ ዓመታትም፣ እጅግ ታላቅ የሌቦች ቡድን ሆኑ፤ እናም የጋድያንቶንን ሚስጥራዊ አሴር በሙሉ ፈልገው አገኙ፤ እንደዚህም የጋድያንቶን ዘራፊዎች ሆኑ።

፳፯ አሁን እነሆ፣ እነዚህ ሌቦች ታላቅ ጥፋትን፤ አዎን፣ በኔፊ ሰዎች መካከልም፣ እናም ደግሞ በላማናውያን ሰዎች መካከል እንኳን ታላቅ ጥፋትን ሰሩ።

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ለዚህ የጥፋት ሥራ ማቆሚያ ማድረግ አስፈላጊ ነበር፤ ስለዚህ እነርሱ ወደ ምድረበዳው፣ እናም በተራራው እነዚህን የሌቦች ቡድን እንዲያገኙ እንዲሁም እንዲያጠፉ ጠንካራ ወታደሮችን ላኩ።

፳፱ ነገር ግን እነሆ፣ እንዲህ ሆነ በዚሁ ዓመት ወደራሳቸው ምድርም በመነዳት ተመልሰው ነበር። እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ ሰማንያኛው ዓመት የንግስና ዘመን በዚሁ ተፈፀመ።

እናም እንዲህ ሆነ በሰማንያ አንደኛው ዓመት መጀመሪያ ወታደሮቹ በእነዚህ የዘራፊዎች ቡድን ላይ ሄዱ፤ ብዙዎችንም አጠፉ፤ እናም ደግሞ እነርሱም እጅግ ብዙ በሆነ ጥፋትም ተጎብኝተው ነበር።

፴፩ እናም ተራራውን እንዲሁም ምድረበዳውን የወረሩት የዘራፊዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ስለነበር ወታደሮቹ ከምድረበዳው እንዲሁም ከተራራው ወጥተው ወደራሳቸው ምድር እንዲመለሱ ተገድደው ነበር።

፴፪ እናም እንዲህ ሆነ ይህ ዓመትም በዚሁ ተፈፀመ። እናም ዘራፊዎቹ አሁንም በጣም ጨመሩና፣ እየበረቱ ሄዱ፣ ስለዚህ የኔፊንና፣ ደግሞ የላማናውያንን ወታደሮች በሙሉ ተቋቋሟቸው፤ እናም በምድሪቱ ሰዎች ላይ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት እንዲመጣ አደረጉ።

፴፫ አዎን፣ የምድሪቱን ብዙ ክፍሎች ጎበኝተዋል፣ እናም በእነርሱ ላይም ታላቅ ጥፋትን አድርገዋልና፤ አዎን ብዙዎችንም ገድለው ነበር፣ እናም ሌሎችንም፣ አዎን፣ በተለይም ሴቶቻቸውን እንዲሁም ህፃናት ልጆቻቸውን በምርኮ ወደ ምድረበዳው ወስደዋቸዋል።

፴፬ እንግዲህ በክፋታቸው የተነሳ በህዝቡ ላይ የመጣው ይህ ታላቅ ጥፋት እርሱም ጌታ አምላካቸውን እንዲያስታውሱ አደረጋቸው።

፴፭ እናም የመሣፍንቱ ሰማንያ አንደኛ ዓመት የንግስና ዘመን በዚሁ ተፈፀመ።

፴፮ እናም በሰማንያ ሁለተኛው ዓመት በድጋሚ ጌታ አምላካቸውን መርሳት ጀመሩ። እናም በሰማንያ ሶስተኛው ዓመት በክፋታቸው መጠናከር ጀመሩ። እናም በሰማንያ አራተኛው ዓመት መንገዳቸውን አላሻሻሉም ነበር።

፴፯ እናም እንዲህ ሆነ በሰማንያ አምስተኛው ዓመት በኩራታቸውና፣ በክፋታቸው እየበረቱ ሄዱ፤ እናም እንደገና ለመጥፋትም እንደዚህ ደርሰው ነበር።

፴፰ እናም ሰማንያ አምስተኛው ዓመትም በዚሁ ተፈፀመ።