ቅዱሳት መጻህፍት
ሔለማን ፩


መፅሐፈ ሔለማን

የኔፋውያን ታሪክ። የእነርሱም ጦርነትና ፀብ፣ እናም መለያየታቸው። እናም ደግሞ የሔለማን ልጅ በነበረው፣ የሔለማን መዝገብ መሰረት፣ እናም ደግሞ በልጆቹ መዛግብት መሰረት፣ ከክርስቶስ መምጣት በፊት እርሱ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የነበረው የብዙ ቅዱሳን ነቢያት ትንቢቶች። እናም ደግሞ ብዙ ላማናውያን ተለውጠዋል። የመለወጣቸው ታሪክ። እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ መፅሐፈ ሔለማን ተብሎ በተጠራው በሔለማንና በልጆቹ መዝገብ መሰረት የላማናውያን ፅድቅና፣ የኔፋውያን ኃጢያት፣ እና እርኩሰት፣ እናም ሌሎች የመሣሰሉ ታሪኮች።

ምዕራፍ ፩

ፓሆራን ሁለተኛው ዋና ገዢ ሆነ፣ እናም በቂሽቁመን ተገደለ—ፓኩሜኒ የፍርድ ወንበሩን ስፍራ ያዘ—ቆሪያንተመር የላማናውያን ወታደሮችን መራ፣ ዛራሔምላን ወሰደና፣ ፓኩሜኒን ገደለ—ሞሮኒያሃ ላማናውያንን አሸነፈና፣ ዛራሔምላን በድጋሚ ወሰደ፣ እናም ቆሪያንቱም ተገደለ። ከ፶፪–፶ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እነሆ እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ አርባኛ ዓመት የንግስ ዘመን፣ በኔፋውያን ህዝቦች መካከል ከባድ ችግር መሆን ጀመረ።

እነሆም ፓሆራን ሞተ፣ እናም ምድር ሁሉ ወደሚሄዱበት ሄደ፤ ስለዚህ የፓሆራን ልጆች ከነበሩት መካከል የፍርድ ወንበርን ማን መውሰድ ይገባዋል በሚል ከባድ ፀብ ተጀመረ።

እንግዲህ የፓሆራን ልጆች፣ ለፍርድ ወንበሩ ይጣሉ የነበሩት፣ ደግሞም ህዝቡ እንዲጣላ የሚያደርጉት ስማቸው እነዚህ ናቸው፥ ፓሆራን፣ ፓአንኪ፣ እናም ፓኩሜኒ ነበሩ።

እንግዲህ የፓሆራን ወንዶች ልጆች እነዚህ ብቻ አይደሉም (ምክንያቱም እርሱ ብዙ ነበሩት)፤ ነገር ግን እነዚህ ለፍርድ ወንበሩ ይጣሉ የነበሩት ናቸው፤ ስለዚህ፣ በህዝቡ መካከል ሶስት ቦታ መከፋፈል እንዲሆን አደረጉ።

ይሁን እንጂ፣ እንዲህ ሆነ ፓሆራን በህዝቡ ድምፅ ዋና ዳኛ፣ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ ገዢ እንዲሆን ተሾመ።

እናም እንዲህ ሆነ ፓኩሜኒ የፍርድ ወንበሩን ማግኘት እንደማይችል በተመለከተ ጊዜ፣ ከህዝቡ ድምፅ ጋር ተባበረ።

ነገር ግን እነሆ፣ ፓአንኪ እናም ከህዝቡ መካከል ገዢአቸው እንዲሆን ከፈለጉት ሰዎች ጥቂቶች እጅግ ተናደው ነበር፤ ስለዚህ ሰዎቹ በወንድሞቻቸው ላይ እንዲያምፁ መሸንገል ሊጀምር ተዘጋጅቶ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ይኸንን በሚያደርግበት ወቅት፣ እነሆ ተወስዶ ነበርና፣ እንደ ህዝቡም ድምፅ ክስ ቀርቦበት ነበር፣ እናም ሞት ተፈረደበት፤ ምክንያቱም እርሱ በአመፅ ተነሳስቶና፣ የህዝቡን ነፃነት ለማጥፋት ተመኝቶ ነበርና።

እንግዲህ ፓአንኪ ገዢአቸው እንዲሆን የፈለጉት ሰዎች ሞት እንደተፈረደበት በተመለከቱ ጊዜ፤ ስለዚህ ተናደው ነበር፣ እናም እነሆ፣ ወደ ፓሆራን የፍርድ ወንበርም አንድ ቂሽቁመንን ላኩ፣ እናም ፓሆራንን በፍርድ ወንበሩ ላይ እንዳለ ገደለው።

እናም የፓሆራን አገልጋዮችም ተከትለውት ነበር፤ ነገር ግን እነሆ የቂሽቁመን ሽሽቱ ፈጣን በመሆኑ ማንም ሰው ሊደርስበት አልቻለም።

፲፩ እናም ወደላኩት ሰዎች ዘንድ ሄደ፣ እናም ሁሉም ቃል ኪዳን ገቡ፣ አዎን፣ ቂሽቁመን ፓሆራንን መግደሉን ለማንም ላለመናገር በዘለአለማዊው ፈጣሪያቸው ስም ቃል ኪዳን ገቡ።

፲፪ ስለዚህ፣ ቂሽቁመን ፓሆራንን በገደለበት ጊዜ በመደበቁ፣ በኔፊ ህዝብ መካከል አይታወቅም ነበር። እናም ቂሽቁመንና ከእርሱ ጋር ቃል የገቡት ቡድኖቹ ሁሉ እንዳይገኙ በመሆን እራሳቸውን ከህዝቡ ጋር ቀላቀሉ፤ ነገር ግን የተገኙት በሙሉ ሞት ተፈረደባቸው።

፲፫ እናም አሁን እነሆ፣ ፓኩሜኒ በወንድሙ ፓሆራን ምትክ ለመንገስ በህዝቡ ድምፅ ዋና ዳኛና ገዢ እንዲሆን ተሹሞ ነበር፤ እናም ይህ በመብቱ መሰረት ነበር። ይህ ሁሉ የተደረገውም በመሣፍንቱ አርባኛው ዓመት የንግስና ዘመን ነበር፤ ይህም ፍፃሜው ነበር።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ አርባ አንደኛ ዓመት የንግስና ዘመን፣ ላማናውያን ለመቆጠር የማይችሉ ብዛት ያላቸውን ወታደሮች በአንድነት ሰበሰቡ፤ እናም በጎራዴም፣ በሻምላም፣ በጦርም፣ በቀስትም፣ እናም በብረት ኮፍያና፣ በደረት ኪስ እንዲሁም በሁሉም ዓይነት ጋሻዎች አስታጠቁአቸው።

፲፭ እናም ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት በድጋሚ መጡ። ቆሪያንተመር ተብሎ በሚጠራም ሰው ይመሩ ነበር፤ እርሱም የዛራሔምላ ትውልድ ነበር፤ እናም እርሱ ከኔፋውያን መካከል የተገነጠለ ነበር፤ እርሱም ትልቅና ኃያል ሰው ነበር።

፲፮ ስለዚህ፣ የላማናውያን ንጉስ ስሙም ቱባሎት ተብሎ የሚጠራ፣ የአሞሮን ልጅ የነበረ፣ ቆሪያንተመር ኃያል ሰው በመሆኑ፤ በጉልበቱ፣ እናም ደግሞ በታላቅ ጥበቡ ኔፋውያንን ለምቋቋም ይችላል፣ እርሱንም በመላክ በኔፋውያን ላይ ኃይልን አገኛለሁ ብሎ ገመተ—

፲፯ ስለዚህ ላማናውያንን በቁጣ እንዲነሳሱ አደረገና፣ ሠራዊቱን በአንድ ላይ ሰበሰበ፣ እናም ቆሪያንተመርን መሪያቸው እንዲሆን ሾመው፣ እናም ከኔፋውያን ጋር እንዲዋጉ ወደ ዛራሔምላ ምድር እንዲዘምቱ አደረገ።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ በመንግስቱም ውስጥ ባለው ፀብና ችግር የተነሳ፣ በዛራሔምላ ምድር በቂ የሆኑ ጠባቂዎችን አላስቀመጡም ነበር፤ ምክንያቱም ላማናውያኖች በምድራቸው መሐል ወደ ታላቋን የዛራሔምላ ከተማ መጥተው ለማጥቃት አይደፍሩም በማለትም ገምተው ነበርና።

፲፱ ነገር ግን እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር ከሰራዊቱ ፊት ዘመተና፣ ወደ ከተማዋ ነዋሪዎች መጣ፣ እናም ጉዞአቸውም በታላቅ ፍጥነት ስለነበር በዚህም የተነሳ ለኔፋውያን ወታደሮቻቸውን በአንድ ላይ ለመሰብሰብም ጊዜ አልነበራቸውም።

ስለዚህ ቆሪያንተመር በከተማው መግቢያ ላይ የነበሩትን ጠባቂዎች ገደለ፣ እናም ከመላው ሠራዊቱ ጋር ወደ ከተማው ገቡ፤ እናም ከተማዋን በሙሉ እስከሚወስዱ ድረስ ተቃዋሚዎቻቸውን በሙሉ ገደሉአቸው።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ዋና ዳኛ የነበረው ፓኩሜኒ፣ ከቆሪያንተመር ፊት ወደ ከተማዋ ግንብ ሸሸ። እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንትመርም ከግንቡ ጋር በማጋጨት መታው፣ በዚህም የተነሳ እርሱ ሞተ። የፓኩሜኒ ቀናትም በዚሁ ተፈፀሙ።

፳፪ እናም እንግዲህ ቆሪያንተመር የዛራሔምላን ከተማ መያዙን በተመለከተ ጊዜ፣ እናም ኔፋውያን በፊታቸው መሸሻቸውንና፣ መገደላቸውን፣ እናም መወሰዳቸውንና ወደ ወህኒ ቤት መጣላቸውን፣ እንዲሁም በምድሪቱ ሁሉ ጠንካራ ምሽግን እንደወሰደ በተመለከተ ጊዜ፣ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ይሄድ ዘንድ ልቡ ደፈረ።

፳፫ እናም እንግዲህ በዛራሔምላ ምድር አልቀረም፤ ነገር ግን ከብዙ ወታደሮቹ ጋር ወደ ለጋስ ከተማ ተጓዘ፤ ምክንያቱም የምድሪቱን ሰሜናዊ ክፍል ያገኝ ዘንድ ወደፊት መጓዝ እና መንገዱንም በጎራዴ ለማጥራት የእርሱ ውሣኔ ነበርና።

፳፬ እናም፣ ታላቁ ብርታታቸው በምድሪቱ መካከል መሆኑን ገመተ፤ ስለዚህ በትንሽ ቡድኖች ብቻ እንጂ እራሳቸውን በአንድነት ለመሰብሰብ ብዙ ጊዜ አልሰጣችውም፤ እናም በዚህም ሁኔታ አጠቁአቸውና፣ ወደምድርም ቆርጠው ጣሏቸው።

፳፭ ነገር ግን እነሆ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኔፋውያን ቢገደሉም፣ በምድሪቱ መካከል የነበረው የቆሪያንተመር ጉዞ ለሞሮኒያሃ ትልቅ ጥቅም ሰጠው።

፳፮ እነሆም ሞሮኒያሃ ላማናውያን በምድሪቱ ወደ መሐል ደፍረው እንደማይመጡ፣ ነገር ግን ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ከተሞቹን በዳር በኩል ያጠቃሉ በማለት ገምቶ ነበር፤ ስለዚህ ሞሮኒያሃ ጠንካራ የሆኑ ወታደሮቻቸው በስፍራዎች ዙሪያ የሚገኙትን እነዚያን ዳርቻዎች እንዲጠብቁ አደረገ።

፳፯ ነገር ግን እነሆ፣ ላማናውያን እንደርሱ ፍላጎት አልፈሩም ነበር፤ ነገር ግን ወደ ምድሪቱ መሃከል መጡ፣ እናም ዋና ከተማ የሆነችውን የዛራሔምላን ከተማን ወሰዱ፣ እናም በምድሪቱ ዋና ወደ ሆኑት ቦታዎችም እየሄዱ፣ ወንዶችና፣ ሴቶችንና ልጆችን በመግደል፣ ብዙ ከተሞችንና፣ ብዙ ጠንካራ ምሽጎችን እየወሰዱ ነበር።

፳፰ ነገር ግን ሞሮኒያሃ ይህንን ባወቀ ጊዜ፣ ሌሂ ከሠራዊቱ ጋር እነርሱን ወደ ለጋስ ምድር ከመምጣታቸው በፊት እንዲያስቆሙአቸው ወደ ግንባር ላከው።

፳፱ እናም እርሱም እንዲህ አደረገ፤ እናም ወደ ለጋስ ምድር ከመምጣታቸው በፊት አስቆማቸው፤ ወደ ዛራሔምላም ምድር ተመልሰው ማፈግፈግ እስኪጀምሩም ድረስ ተዋጋቸው።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒሀ ሲያፈገፍጉ ጦርነት ገጠማቸው፤ እናም እጅግ አሰቃቂ ደም መፋሰስ እስከሚሆንም ተዋጉ፤ አዎን፣ ብዙዎች ተገደሉ፤ ከተገደሉትም መካከል ቆሪያንተመር ይገኝ ነበር።

፴፩ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ላማናውያን በሁሉም አቅጣጫ በኔፋውያን በመከበባቸው በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅም ሆነ በምዕራብ በኩል ለማፈግፈግ አልተቻላቸውም።

፴፪ እናም ቆሪያንተመር ላማናውያን ኔፋውያን መካከል እንዲገቡ አድርጓል፤ በዚህም የተነሳ በኔፋውያን ኃይል ውስጥ ዋሉ፣ እርሱ ራሱም ተገደለ፣ እናም ላማናውያን ለኔፋውያን እጃቸውን ሰጡ።

፴፫ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒያሃ የዛራሔምላን ከተማ በድጋሚ ወሰደ፤ እናም እስረኛ ተደርገው የተወሰዱት ላማናውያን ከምድሪቱ በሰላም እንዲወጡ አደረገ።

፴፬ እናም የመሣፍንቱ አርባ አንደኛ ዓመት የንግስና ዘመን በዚሁ ተፈፀመ።