2013 (እ.አ.አ)
ለሚያመነታ ወንጌል ሰባኪ የተሰጠ ምክር
ፌብሩወሪ 2013


የቀዳሚ አመራር መልእክት፣ የካቲት 2013 (እ.ኤ.አ)

ለሚያመነታ ወንጌል ሰባኪ የተሰጠ ምክር

ምስል
በፕሬዘደንት ዲየትር ኤፍ ኡክዶርፍ

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙሮች ሁልጊዜም ወንጌሉን ለአለም ለመውሰድ ባለው ሀላፊነት ስር ያሉ ናቸው (ማርቆስ 16፥15–16 ተመልከቱ)። ይህም ቢሆን፣ አንዳንዴም አፋችንን ለመክፈት እና ስለሀይማኖታችን በአካባቢያችን ላሉት ለመንገር አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ አባላት ስለሀይማኖት ለሌሎች የመንገር ተፈጥሮ አዊ ተሰጦ ሲኖራቸው፣ ሌሎች ግን ይህን ለማድረግ ያመነታሉ ወይም ምቾት አይሰማቸውም ፣እፍረት ይሰማቸዋል ፣ ወይም እንዲሁ ይፈራሉ።

ለዚህም፣ ወንጌሉን “ለእያንዳንዱ ፍጡር” (ት. እና ቃ. 58፥64) ስበኩ የሚለውን የአዳኝን ጥሪ ለመከተል ማንኛውም ለማድረግ የሚችሉበትን አራት ነገሮች በሀሳብ ላቅርብ።

ብርሀን ሁኑ

“ወንጌልን ሁልጊዜም ስበኩ እናም አስፈላጊ ከሆነ ቃላትን ተጠቀሙ ባቸው” የሚለው የአሲሲ ቅዱስ ፍራንሲስ ብለውታል የሚባለው አባባል አለ።1 በዚህ አባባል የምንረዳው ቢኖር በጣም ሀይለኛ የሆኑ ስብከቶች በንግግር የተደረጉ እንዳልሆኑ ነው።

ፅኑ አቋም ሲኖረን እና በመሰረታዊ መርሆአችን ስንኖር፣ ሰዎች ያዩታል። ደስታን እና ስኬትን ስናሳይም፣ እነርሱም በልብ ይረዱታል።

ሁሉም ለመደሰት ይፈልጋል። እኛ ቤተክርስቲያኗ አባላት የወንጌልን ብርሀን ስናንጸባርቅ፣ ሰዎች ደስታችንን ያያሉ እናም የእግዚአብሔር ፍቅር ህይወታችንን ከሚቻለው በላይ ሲሞላም ይመለከታሉ። ለምን እንደሆነም ለማወቅ ይፈልጋሉ። ሚስጥራችንን ለማስተዋል ይፈልጋሉ።

ያም “ለምንድን ነው እንደዚህ ተደሳች የሆናችሁት?” ወይም “ለምንድን ነው እንዲህ አይነት ቀና አመለካከት ያላችሁ?” ወደሚል ጥያቄዎችም ይመራል። እነዚህን ጥያቄዎች መመለስም በዳግም ስለተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለመነጋገር መልካም እድል ይመራል።

ተግባቢ ሁኑ።

የሀይማኖት አርዕስትን በንግግር፣ በተለይም ከጓደኞቻችንና ከምንወዳቸው ጋር፣ ማንሳት የሚያስፈራና የሚያስቸግር ይመስላል። እንዲህም መሆን የለበትም። ብርቱ ከሆንን እና በአስተዋይነት ካደረግናቸው፣ መንፈሳዊ አጋጣሚዎችን ወይም ስለቤተክርስቲያን ስራዎች ወይም ድርጊቶችን መነጋገር ቀላል እና አስደሳች ለመሆን ይችላል።

ባለቤቴ ሄሪየት የዚህ መልካም ምሳሌ ነች። በጀርመን ስንኖር፣ ከጓደኞች ጋር እና ከምታውቃቸው ጋር ስትነጋገር፣ ስለቤተክርስቲያን ርዕስቶች የመነጋገር መንገድ ትፈልጋለች። ለምሳሌ፣አንድ ሰው ያሳለፈችው ቅዳሜና እሁድ እንደት እንደነበረ ሲጠይቃት፣ እንዲህም ትላለች፣ “በዚህ እሁድ ቤተክርስቲያን አስደናቂ ተሞክሮን አገኘን። የ16 አመት ልጅ አብረውን ተሰብስበው በነበሩ በ200 ሰዎች ፊት ንጹህ ህይወትን ስለመኖር አስደናቂ ንግግር አደረገ።” ወይም፣ “ከ500 በላይ የሆኑ ምንጣፎችን ሰርታ በአለም አቀፍ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እንዲሰጡ ለቤተክርስቲያናችን በጎ ድርገት ፕሮግራም ስለሰጡ የ90 አመትአሮጊት ተማርኩኝ።”

በአብዛኛው ጊዜ፣ ይህን የሚሰሙ ሰዎች በተጨማሪ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ጥያቄም ይጠይቃሉ። ይህም በብርቱነት እና በማያስገድድ ሁኔታ ስለወንጌል የመናገር እድል ወዳለበት ይመራናል።

በኢንተርኔት እና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከመጀመራቸው ጋር፣ አሁን ስለእነዚህ ነገሮች ለመነጋገር ከዚህ በፊት ከነበረው ይበልጥ ቀላል ነው። የሚያስፈገን ይህን የማድረግ ድፍረት ነው።

በጸጋ የተሞላችሁ ሁኑ

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ የማይስማማ ለመሆን በጣም ቀላል ነው። አብዛኛው ጊዜ እንጨቃጨቃለን፣ ሌሎችን እንደ ተራ እንመለከታለን፣ እናም በሌሎች እንፈርዳለን። ስንናደድ፣ ስንሳደብ፣ ወይም ሰዎችን ስንጎዳ፣ ስለእኛ ለማወቅ አይፈልጉም። አንድ ሰው ስለጎዳቸው ወይም የሚያስቀይም ነገር ስላሏቸው ስንት ሰዎች ከቤተክርስቲያኗ እንደወጡ ወይም አባል እንዳልሆኑ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

በዚህ አለም አሁን በጣም ብዙ ስርአት አልበኝነት አለ። በኢንተርኔት ማንነት ስለማይታወቅ፣ መጥፎ ወይም የሚጎዳ ነገሮችን ለማለት ከዚህ በፊት ከነበረው በላይ ቀላል ነው። እኛ የደጉ ክርስቶስ ተስፋ ያለን ደቀ መዛሙርቶች ከፍተኛ፣ ከዚህም በላይ የሆነ የልግስና መሰረት ሊኖረን አይገባንምን? ቅዱሳት መጻህፍት እንደሚያስተምሩት፣ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን” (ቄላስይስ 4፥6)።

ቃላችን እንደ ብሩህ ሰማይ ንጹህ እና በጸጋ የተሞላ የመሆኑን ሀሳብ እወዳለሁ። እንደዚህ አይነት መሰረታዊ መርሆችን ብንከተል ቤተሰቦቻችን፣አጥቢያዎቻችን ፣ ሀገሮቻችን፣ እና እንዲሁም አለም ምን አይነት እንደሚሆኑ ልታስቡበት ትችላላችሁን?

በእምነት የተሞላችሁ ሁኑ

ሰዎች ወንጌልን በሚቀበሉበት ወቅት አንዳንዴ በራሳችን ላይ ለጥሩውም ይሁን ለመጥፎ ብዙ ሀላፊነት እንወስዳለን። ጌታ እኛ ሌሎችን እንድንቀይር እንደማይጠብቅብን ማስታወሱ አስፈላጊ ነው።

መቀየር የሚመጣው በቃላቶቻችን ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አገልግሎት ነው። አንዳንዴ የሚያስፈልገው ሌሎች በመንፈስ መነሳሳት እውነቶችን እንዲያጋጥማቸው የሚያደርግ አንድ የምስክራችን ወይም ልብን የሚያለሰልስ ወይም በርን የሚከፍት አጋጣሚን የሚገልጽ ሀረግ ነው።

ፕሬዘደንት ብሪገም ያንግ (1801–77) እንዳሉት ወንጌሉ እውነት እንደሆነ ያወቁት “‘በመንፈስ ቅዱስ ሀይል መፅሐፈ ሞርሞን እውነት እንደሆነ፣ ጆሴፍ ስሚዝ የጌታ ነቢይ እንደሆነ አውቃለሁ’ ለማለት ብቻ የሚችል ልሳነ-ቅንነት፣ ወይም በህዝብ የመናገር ችሎታ የሌለው ሰውን ሳይ ነው።” ፕሬዘደንት ያንግ እንዳሉት ያን ትሁት ምስክርነት ሲሰሙ ፣ “መንፈስ ቅዱስ ከዚያ ሰው መጥቶ መረዳትን፣ እና ብርሀንን፣ ክብርን፣ እና ዘላለማዊነትን በፊቴ አብራራው።”2

ወንድሞችና እህቶች፣ እምነት ይኑራችሁ። ጌታ የምትናገሩትን ቃላት ያጎላል እናም ሀይለኛ ያደርጋቸዋል። እግዚአብሔር እንድትቀይሩ ሳይሆን አፋችሁን እንድትከፍቱ ነው የሚጠይቃችሁ። የመቀየር ስራ የእናንተ አይደለም፣ ሀላፊነቱም የሚያዳምጠው ሰውና የመንፈስ ቅዱስ ነው።

እያንዳንዱ አባል ወንጌል ሰባኪ

ውድ ጓደኞቼ፣ አፋችንን የምንከፍትበት እና ከሌሎች ጋር የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን አስደሳች ዜና የምንካፈልበት ብዙ መንገዶች አሉ። ለሁሉም፣ እንዲሁም ለሚያመነታ ወንጌል ሰባኪም፣ በዚህ ታላቅ ስራ የሚሳተፉበት መንገድ አለ። ልዩ ችሎታችንን እና ዝንባልአችንን በመጠቀም አለምን በብርሀንና በእውነት የሞምላት ታላቅ ስራን የምንደግፍበት መንገድ ለማግኘት እንችላለን። ይህን ስናደርግ፣ ታማኝ ለሚሆኑት እና “በሁሉም ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ምስክር ለመቆም” (ሞዛያ 18፥9) ብርቱ ለሚሆኑት የሚመጣውን ደስታ እናገኛለን።

ማስታወሻዎች

  1. St. Francis of Assisi, in William Fay and Linda Evans Shepherd, Share Jesus without Fear (1999), 22።

  2. Teachings of Presidents of the Church: Brigham Young (1997), 67።

ከዚህ መልእክት ማስተማር።

የማስተማር አንዱ ውጤታማ መንገድ ቢኖር “የምታስተምሯቸው ያስተማራችሁትን መሰረታዊ መርሆች በህይወት ሊኖሩበት እንዲችሉ የሚረዳቸው እቅድ እንዲኖራቸው ማበረታታት” ነው (Teaching, No Greater Call [1999], 159)። የምታስተምሯቸው በዚህ ወር ለአንድ ወይም ለተጨማሪ ሰዎች ወንጌልን የመካፈል እቅድ በጸሎት እንዲይዙ ጋብዟቸው። ወላጆች ወጣት ልጆች እንዴት ለመርዳት እንደሚችሉ ለመወያየት ይችላሉ። የቤተሰብ አባላት በንግግር ውስጥ ስለወንጌል የሚነጋገሩበትን መንገዶች እንዲያስቡበት እና ጓደኛቸውን ወደሚመጣው የቤተክርስቲያን መሳተፊያ የሚጋብዙበትን እንዲያስቡበት ለመርዳት ትችላላችሁ።

አትም