2014 (እ.አ.አ)
ፍቅር— የወንጌል ፍሬ ነገር
ግንቦት 2014 (እ.አ.አ)


ፍቅር— የወንጌል ፍሬ ነገር

በዚህ የሟችነት ጉዞ ላይ ተጓዥ ጓደኞቻችንን የማንወድ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን በእውነት መውደድ አንችልም።

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ አዳኛችን በሰዎች መሀል ሲያገለግል ሳለ፣ በሚወደው የሕግ ሰው ጥያቄ ተጠይቆ ነበር፣ “መምህር ሆይ፣ ከሕግ ማናቸይቱ ትዕዛዝ ታላቅ ናት?”

ማቴዎስ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ እንደመለሰ ዘገበ፥

“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም አሳብህም ውደድ” (ማቴዎስ 22፥37)።

“ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

“ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።1

ማርቆስ መዝገቡን በአዳኙ ገለፃ አጠቃለለ፥ “ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትዕዛዝ የለችም።”2

በዚህ የሟችነት ጉዞ ላይ ተጓዥ ጓደኞቻችንን የማንወድ ከሆነ፣ እግዚአብሔርን በእውነት መውደድ አንችልም። እንደዚሁም፣ እግዚአብሔርን የማንወደው ከሆነ፣ ጓደኞቻችንን ሙሉ በሙሉ መውደድ አንችልም ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ይነግረናል፣ “እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትዕዛዝ ከእርሱ አለችን።”3 ሁላችንም የሰማይ አባታችን የመንፈስ ልጆች ነን፣ በመሆኑም፣ ወንድሞችና እህቶች ነን። ይህንን እውነታ በአእምሮአችን ውስጥ ስንይዝ፣ ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች መውደድ ቀላል ይሆናል።

በእርግጥ፣ ፍቅር የወንጌል የመጀመሪያ ፍሬ ነገር ነው እናም ኢየሱስ ክርስቶስ የኛ ምሳሌ ነው። ህይወቱ የፍቅር ውርስ ነው። በሽተኛዎችን የፈወሰ፣ የተጨቆኑትን ከፍ ያደረገ፣ ሀጢያተኛን ያዳነ። በመጨረሻ የተናደዱት ወንበዴዎች ሕይወቱን ወሰዱት። ይሁን እንጂ በጎለጎታ ኮረብታ ላይ4 — የርህራሄና የፍቅር ታላቅ ውጤታማ አገላለፅ የሆኑት እነዚህ ቃሎች ያስተጋባሉ፥ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁትምና፤ ይቅር በላቸው”።

ለምሳሌ፣ እንደ በጎነት፣ ትግስት፣ ራስ ወዳድ አለመሆን፣ መረዳት መቻል እና ይቅር ባይነት የሆኑ የፍቅር መገለጫ ብዙ ባህሪያቶች አሉ። በሁሉም ግንኙነቶቻችን ውስጥ እነዚህና ሌሎች እነዚህን መሰል ባህሪዎች፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ፍቅር ያረጋግጣሉ።

በብዛት፣ እርስ በእርስ በምናደርገው የቀን ተቀን ግንኙነቶች ውስጥ ፍቅራችን ይታያል። ሁሉም ጠቃሚ ነገር፣ የአንድን ሰው ፍላጎት የማወቁና ከዛም ምላሽ የመስጠቱ ችሎታችን ላይ ይሆናል። በዚህ አጭር ግጥም ውስጥ መገለፅ የቻለውን አጠቃልይ ስሜት ሁሌም እጓጓለታለው፥

በምሽት አምብቻለው

በምልከታ እጥረት ምክንያት

የአንድ ሰው ፍላጎት አይነ ስውር አደረገኝ።

እኔ ግን እስካሁን

ቅንጣትፀፀት አልተሰማኝም

ትንሽ በጣም ደግ በመሆኔ።5

በቅርቡ ያልተጠበቀ ውጤቶች የነበረውን የሚነካ የፍቅር ደግነት ምሳሌ ማየት እንድችል ተደረኩኝ። አመቱ 1933 (እ.አ.አ) ነበር፣ በታላቁ ክፉ ቀን ምክንያት የተቀጣሪነት እድሎች አናሳ በነበሩበት ወቅት ነበር። ቦታው በአሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል ነበር። አርሊን ቤይሲከር ልክ ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እንደተመረቀች ነበር። ከረጅም የስራ ፍለጋ በኋላ፣ በመጨረሻም በልብስ ፋብሪካ ውስጥ እንደ የሴት ልብስ ሰፊነት ስራ ማግኘት ቻለች። የፋብሪካው ሰራተኞች በየቀኑ ለእያንዳንዳቸው በትክክል ሰፍተው ለጨረሱት ቁራጮች ነበር የሚከፈላቸው። ብዙ ቁራጮችን ባመረቱ ቁጥር፣ ብዙ ይከፈላቸው ነበር።

አንድ ቀን፣ በፋብሪካ ውስጥ በቅርብ መስራት ከጀመረች በኋላ፣ አርሊን ግራ ያጋባትና ያሰላቻት ስርአት ገጥሟት ነበር። እየሰራችበት የነበረውን ቁራጭ ለመጨረስ ያልተሳካላትን ሙከራ ለማላቀቅ እየሞከረች በልብስ መስፊያዋ ማሽን ላይ ተቀመጠች። የሚረዳት ማንም ሰው ያለ አይመስልም፣ ምክንያቱም ሁሉም ሌሎች የሴት ልብስ ሰፊዎች መጨረስ እስከሚችሉት ድረስ ቁራጮች ለመጨረስ ሲጣደፉ ነበር። አርሊን እረዳት አልባና ተስፋ አልባ ስሜት ተሰማት። በፀጥታ፣ ማልቀስ ጀመረች።

ከአርሊን ማዶ በርኒስ ሮክ ተቀምጣለች። ተለቅ ያለችና እንደ ሴት የልብስ ሰፊ ብዙ ልምድ ያላት ነበረች። የአርሊንን መጨናነቅ በመመልከት፣ በርኒስ የራሷን ስራ ትታና ወደ አርሊን አጠገብ በመሄድ በደግነት ትምህርትና እርዳታ ሰጠቻት። አርሊን በራስ መተማመን እስክታገኝና ቁራጩን በውጤታማነት እስክትጨርስ ድረስ ቆየች። ከዛ በርኒስ ባትረዳት ኖሮ መጨረስ የምትችላቸውን በዙ ቁራጮችን የመጨረሱ እድል አምልጧት ወደ ራሷ ማሽን ተመለሰች።

በዚህኛው የፍቅር ደግነት ተግባር፣ በርኒስና አርሊን የረጅም ሕይወት ጓደኛሞች ሆኑ። ቀስ በቀስ እያናዳንዳቸው አገቡና ልጆች ኖራቸው። በ1950ዎቹ የሆነ ሰአት ውስጥ፣ የቤተክርሰቲያን አባል የነበረችው በርኒስ ፣ ለአርሊንና ለቤተሰቧ አንድ የመጽሐፈ ሞርሞን ቅጂ ሰጠቻት። በ1960፣ አርሊንና ባለቤቷ እንዲሁም ልጆቿ በመጠመቅ የቤተክርስቲያን አባሎች ሆኑ። ከዛ በኋላ በእግዚአብሔር ቅዱስ ቤተ-መቅደስ ውስጥ ታተሙ።

በበርኒስ ከራሷ መንገድ ወጥታ የማታውቃትን ሴት ነገር ግን በጭንቀት ውስጥ የነበረችውንና እርዳታ ያስፈልጋት የነበረውን ለመርዳት ባሳየችው ርህራሄ ምክንያት፣ የማይቆጠሩ ግለሰቦች በሕይወትም ያሉም የሞቱም የወንጌልን የማዳን ስነ-ሰርአት አሁን ያጣጥማሉ።

በእያንዳንዱ የሕይወታችን ቀኖች ውስጥ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ፍቅርንና ደግነትን ለማሳየት እድሎች ተሰጥተዉናል። ፕሬዘደንት ሰፔንሰር ደብሊው ኪምባል እንዲህ አሉ፥ “እነዛ በመኪና ማቆሚያዎች፣ ቢሮዎች፣ ሊፍቶችና ሌላ ቦታ የምናገኛቸው ሟቾች የሆኑ ሰዎች እንድንወዳቸውና እንድናገለግላቸው እግዚአብሔር የሰጠን የሰው ዘር አካል መሆናቸውን ማሰታወስ አለብን። በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች በሙሉ እንደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ካልቆጠርናቸው፣ ስለ የሰው ዘር አጠቃላይ ወንድማዊነት ማውራት ትንሽ መልካምን ነው የሚያደርግልን።6

በብዛት ፍቅራችንን የምናሳይበት እድሎች ሳይታሰቡ ይመጣሉ። የዚህ አይነት እድል ምሳሌ በጥቅምት 1981 (እ.አ.አ) የጋዜጣ እትም ውስጥ ሰፍሯል። እዛ ውስጥ በተዛመደው ፍቅርና ርህራሄ በጣም በመደነቄ የጋዜጣውን ቁራጭ በመዝገቦቼ ውስጥ ከ30 አመታት በላይ አስቀምጬዋለው።

እትሙ የአላስካ አየር መንገድ 150 ተሳፋሪዎችን ይዞ ከአንከርኤጅ፣ አላስካ ወደ ሲያትል፣ ዋሽንግተን ቀጥታ በረራ ሲያደርግ በጣም የተጎዳ ልጅን ለማጓጓዝ ወደ አላስካ ሩቃማ ከተማ መታጠፉን ይጠቁማል። የሁለት አመቱ ወንድ ልጅ በቤቱ አቅራቢያ ሲጫወት በቁራጭ ጠርሙስ ላይ ወድቆ በክንዱ ላይ ያለውን የደም ቧንቧን ጎድቶት ነበር። ከተማው ከአንከርኤጅ 450 ማይሎች (725ኪሎ ሜትሮች) ደቡባማ ክፍል ነበር እናም በእርግጠኝነት በበረራው መንገድ አቅጣጫ አልነበረም። ይሁን እንጂ፣ በዛ ቦታ ያሉ ዶክተሮች ለእርዳታ ጥሪ ላኩ እናም ስለዚህ በረራው ልጁን ወደ ሲያትል ለመውሰድ እዛም በሆስፒታል ውስጥ ህክምና እንዲያገኝ ለማስቻል ተቀየሰ።

በረራው በሩቃማ ከተማው አቅራቢያ መሬት ሲነካ፣ ዶክተሮቹ ልጁ በጣም ባስከፊ ሁኔታ ደሙ እየፈሰሰ ስለሆነ ወደ ሲያትል በሚሄደው በረራ ውስጥ በሕይወት መቆየት እንደማይችል ለፓይለቱ ነገሩት። ሌላ 200 ማይሎች (320 ኪሎ ሜትር) ከጉዞ መስመር ውጪ ወደ ጁኖ፣ አላስካ በቅርበት ሆስፒታል ያላት ከተማ ለመብረር ተወሰነ።

ልጁን ወደ ጁኖ ካጓጓዙት በኋላ፣ አሁን ከሰአታታ የፕሮግራም ማርፈድ በኋላ፣ በረራው ወደ ሲያትል አቀና። ብዙዎቹ ተሳፋሪዎች ቀጠሮዎችንና አገናኝ በረራዎችን ቢያጡም እንኳን፣ አንዳቸውም አልተነጫነጩም። በእርግጥ፣ ደቂቃዎችና ሰአታቶች እየቆጠሩ ሲሄዱ፣ ግምታዊ የሚሆን ድምሮችን ለልጁና ለቤተሰቡ በማዋጠት መዋጮዎችን ማሰባሰብ ጀመሩ ።

በረራው በሲያትል ውስጥ ሊያርፍ ሲል፣ ፓይለቱ ልጁ ደህና እንደሚሆን በሬዲዮ ቃል መቀበሉን ባስተዋወቀ ጊዜ ተሳፋሪዎቹ በደስታ ፈነጠዙ።7

የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ወደ አእምሮዬ መጣ፥ “ልግስና ንፁህ የክርስቶስ ፍቅር ነው… በመጨረሻው ቀንም እርሱን የያዘ መልካም ይሆንለታል።”8

ወንድሞችና እህቶች፣ ፍቅራችንን ለማሳየት ከሚረዱን አንዳንድ ታላቅ እድሎቻችን መካከል በገዛ ቤቶቻችን ግድግዳዎች ውስጥ ይሆናል። ፍቅር የቤተሰብ ሕይወት ልብ መሆን አለበት፣ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሳይሆን ይገኛል። እጅግ ብዙ አለመታገስ፣ እጅግ ብዙ ጭቅጭቅ፣ እጅግ ብዙ ድብድብ፣ እጅግ ብዙ እምባዎች ሊኖር ይችላል። ፕሬዘደንት ጎርደን ቢ ሂንክሊ በሀዘኔታ ተናገሩ፥ “ለምንድን ነው [በጣም] የምንወዳቸው [ሰዎች] የመጥፎ ቃሎቻችን ኢላማቆች የሚሆኑት? ለምንድን ነው አንዳንድ ጊዜ ልክ በፍጥነት እንደሚቆርጥ እንደ ጩቤ የምንናገረው?”9 ምናልባት ለእያንዳንዳችን የነዚህ ጥያቄዎች መልስ ልዩ ሊሆን ይችላል፣ ይሁንና ዋናው ነገር ምክንያቶቹ ምንም አያደርጉም። እርስ በእርስ በመዋደድ ትዕዛዙን የምንጠብቅ ከሆነ፣ እርስ በራሳችን በደግነትና በክብር መንከባከብ አለብን።

በእርግጥ ቅጣት የሚያስፈልግበት ጊዜ ይኖራል። ይሁን እንጂ፣ በትምህርትና ቃል-ኪዳን— ውስጥ የሚገኘውን ምክር እናስታውስ፣--ማለትም፣ ሌላ ሰውን ማስተካከል ሲኖርብን፣ ከዛ በኋላ የጨመረ ፍቅርን እናሳያለን።10

በዙሪያችን ላሉት ሰዎች አስተሳሰቦች፣ ስሜቶችና ሁኔታዎች አሳቢና ተጨናቂ ለመሆን ሁልጊዜ እንደምንጥር ተስፋ አደርጋለው። አናዋርድ ወይም አናሳንስ። ይልቅ፣ ሩህሩህዎችና አበረታቾች እንሁን። በግድ የለሽ ቃሎች ወይም ተግባሮች የሌላ ሰውን በራስ መተማመን እንዳናፈርስ መጠንቀቅ አለብን።

ይቅር ባይነት ከፍቅር ጋር እጅ ለእጅ መሄድ አለበት። በቤተሰቦቻችን ውስጥ፣ እንዲሁም በጓደኞቻችን ውስጥ፣ የተጎዱ ስሜቶችና አለመስማማት መሆን ሊኖሩ ይችላሉ። እንደገና፣ ምንም እንኳን ጉዳዩ ትንሽ ቢሆንም ግድ የለም ። እንዲበላሽ፣ ስር እንዲሰድና በመጨረሻም እንዲያፈርሳችሁ መተው መቻል የለባችሁም እንዲሁም አይኖርባችሁም። በሰው ላይ መፍረድ ቁስሉ ክፍቱን እንዲቆይ ያደርጋል። ይቅር ባይነት ብቻ ይፈውሳል።

ከዚህ በኋላ የሞተችው አንድ ውድ ሴት እኔን አንድ ቀን ጎበኘችኝ እናም ሳይታሰብ የተወሰነ ቁጭቶችን ነገረችኝ። ከብዙ አመታት በፊት ስለተከሰተና አንድ የጎረቤት አረሶ አደርን ስለሚመለከት፣ የሆነ ሰአት ላይ መልካም ጓደኛሞች ስለነበሩና ነገር ግን እርሷና ባለቤቷ ለብዙ ወቅቶች ስምምነት ስላልነበራቸው ስለሆነ ገጠመኝ አወራች። አንድ ቀን አርሶ አደሩ ወደ ራሱ ማሳ ለመድረስ በአርሷ ይዞታ ውስጥ ያለውን አቋራጭ መንገድ መጠቀም ይችል እንደሆነ ጠየቃት። በዚህ ሰአት ታሪኩን ለኔ መንገሯን አቆመችና በሚንቀጠቀጥ ድምፅ እንዲህ አለች፣ “ወንድም ሞንሰን፣ በዛ ሰአትና ከዛም በኋላ የኛን ይዞታ እንዲያቋርጥ አልፈቀድኩለትም፣ ነገር ግን ወደራሱ ይዞታ እንዲደርስ ረጅሙን መንገድ በእግሩ ዞሮ እንዲወስድ አደረኩት። ትክክል አልነበርኩም እናም ተፀፅቻለው። አሁን ሞቷል፣ ነገር ግን፣ እንዴት ‘በጣም ይቅርታ’ ለማለት እንድችል እመኝ ነበር። ደግ ለመሆን ሁለተኛ እድል ባገኝ ምን ያህል እመኝ ነበር።”

እርሷን በማዳምጥበት ወቅት፣ የጆን ግሪንሊፍ ዋይተር አሳዛኝ ምልከታ ወደ አእምሮዬ መጣ፥ “ከአሳዛኝ የምላስ ወይም የእስከረቢቶ ቃላቶች በላይ፣ የበለጠ አሳዛኞቹ እነዚህ ናቸው፥‘ ይሆን ነበር!’”11 ወንድሞችና እህቶች፣ ሌሎችን በፍቅርና በደግነት አመለካከት ስንንከባከብ፣ እንደዚ አይነት ፀፀትን እናስወግዳለን።

ፍቅር በብዙ የሚታወቁ መንገዶች ሊገለፅ ይችላል፥ ፈገግታ፣ የእጅ ማውለብለብ፣ ደግ አስተያየት፣ ሙገሳ። ሌሎች መገለጫዎች ምናልባት የበለጠ ቀጥተኛ ያልሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ፣ እንደ በሌሎች እንቅስቃሴች ላይ ፍላጎትን ማሳየት፣ አንድን መርህ በደግነትና በትግስት ማስተማር፣ የታመመን ሰው ወይም እቤት የቀረን ሰው መጎብኘት። እነዚህ ቃላቶችና ተግባሮች እንዲሁም ብዙ ሌሎች፣ ፍቅርን መናገር ይችላሉ።

በጣም ታዋቂ የአሜሪካ ደራሲና አስተማሪ የነበረው ዴል ካርኒጊ፣ “ብቸኛ ለሆነ ወይም ላልተበረታታ ሰው ከልብ የመነጨ የተወሰነ የአድናቆት ቃሎችን በመስጠት” እያንዳንዱ ግለሰብ በውስጡ ወይም በውስጧ የአለምን ደስተኛነት የአጠቃላይ ድምር የመጨመር ኃይል እንዳላቸው ያምን ነበር። እንዲህም አለ፣ “ምናልባት ዛሬ የምትሉትን ደግ ቃሎች ነገ ልትረሱ ትችላላችሁ፣ ነገር ግን ተቀባዮቹ ዕድሜ ልክ ይጠብቋቸዋል።” 12

አሁን ፣ በዚሁ ቀን፣ የቤተሰባችን አባልም ሆኑ፣ ለጓደኞቻችን፣ ለተራ ትውውቆቻችን ወይም ለመላ አዲስ ሰዎች ለእግዚአብሔር ልጆች ፍቅርን መግለፅ እንጀምር። በእያንዳንዱ ጠዋት በምንነሳበት ሰአት፣ በመንገዶቻችን ለሚመጡ ለማንም አይነት ነገሮች በፍቅርና በደግነት ለመመለስ እንወስን።

ወንድሞችና እህቶች፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር መረዳት ከሚቻለው በላይ ነው። በዚህ ፍቅር ምክንያት፣ የዘላለም ሕይወት ይኖረን ዘንድ ሕይወቱን ለእኛ ሲል እስኪሰጥ ድረስ የወደደንን፣ ልጁን ላከው። ይህን ከምንም ጋር የማይወዳደረውን ስጦታ ወደ መረዳቱ ስንመጣ፣ ልቦቻችን ለዘላለም አባታችን፣ ለአዳኛችንና ለሁሉም የሰው ዘር በፍቅር ይሞላል። ያ እውን መሆን ይችል ዘንድ የእኔ የውስጥ ፀሎቴ የሚሆነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. ማቴዎስ 22፥36–39

  2. ማርቆስ 12፥31

  3. 1 ዮሐንስ 4፥21

  4. ሉቃስ 23፥34

  5. ደራሲ አይታወቅም፣ በ ሪቻርድ ኤል ኢቫንስ “The Quality of Kindness፣” Improvement Era፣ ውስጥ ግምቦት 1960 (እ.አ.አ)፣ 340 ።

  6. The Teachings of Spencer W. Kimball፣ ed. Edward L. Kimball (1982)(እ.አ.አ)፣ 483

  7. “Injured Boy Flown to Safety፣” ደይሊ ሲትካ ሴንቲኔል (አላስካ)፣ ጥቅምት 22፣ 1981 (እ.አ.አ)ተመልከቱ።

  8. ሞሮኒ 7፥41

  9. ጎርደን ቢ ሂንክሊ፣ “Let Love Be the Lodestar of Your Life፣” Ensign፣ ግምቦት 1989 (እ.አ.አ)፣ 67።

  10. ትምህርት እና ቃል ኪዳን 121፥43 ተመልከቱ።

  11. “Maud Muller,” በጆን ግሪንሊፍ ዋይተር ያለቁ የግጥም ስራዎች ውስጥ (1878) እ.አ.አ፣ 206፤ አተኩሮት ተጨምሮበታል።

  12. ዴል ካርኒጊ ለምሳሌ በላሪ ቻንግ Wisdom for the Soul (2006) እ.አ.አ፣ 54. ውስጥ

አትም