2016 (እ.አ.አ)
ከእኔ ተማሩ
ማርች 2016


የቀዳሚ አመራር መልእክት፣ መጋቢት 2016 (እ.አ.አ)

“ከእኔ ተማሩ”

በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ሁላችንም አስተማሪዎች ነን እናም ሁላችንም ተማሪዎች ነን። ከጌታችን ይህ የረጋ ግብዣ ለሁላችንም መጥቷል፥ “ከእኔም ተማሩ፥ … ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”1

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን በሙሉ ለማስተማር እና ለመማር የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያሰላስሉት እና ይህን በማድረግም አዳኝን እንደ መሪያችን እንዲመለከቱ እጋብዛለሁ። ይህ “ከእግዚአብሔር የመጣ አስተማሪ”2 ከአስተማሪ በላይ እንደሆነ እናውቃለን። በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ ጥንካሬአችን፣ እና በሙሉ አዕምሮአችን ጌታችን እግዚአብሔርን እንድንወድ፣ እና ጓደኞቻችንን እንደራሳችን እንድንወድ ያስተማረን መምህር እና የፍጹም ህይወት ምሳሌ ነው።

እንዲህም ያወጀው እርሱ ነው፥ “ኑ ተከተሉኝ።”3 “ምሳሌም ትቼላችኋለሁ።”4

ካልተቀየራችሁ በስተቀር

ኢየሱስ በማቴዎስ ውስጥ በተመዘገበው ቀላል ሆኖም ታላቅ ትርጉም ያለው እውነት አስተማረ። እርሱና ደቀመዛሙርቱ ከመቀየሪያ ተራራ ከወረዱ በኋላ፣ በጋለሊ ቆዩ እናም ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። በዚያም ደቀመዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ መጡ፣ ይህንም ጠየቁት፥

“በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?

“ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ፣

“እንዲህም አለ፣ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።”5

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ፣ የወንጌል ትምህርት አላማ በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ ወይም በሚስዮን ውስጥ በእግዚአብሔር ልጆች አዕምሮ ውስጥ መረጃዎችን ለማፍሰስ አይደለም። ወላጅ፣ አስተማሪ፣ ወይም ሚስዮን ምን ያህል እንደሚያውቁ ለማሳየት አይደለም። ወይም ይህም ስለአዳኝ እና ስለቤተክርስቲያኑ ያለውን እውቀት ለመጨመር ብቻ አይደለም።

የማስተማር ዋና አላማ የሰማይ አባት ወንድ እና ሴት ልጆችን ወደ እርሱ ለመመለስ እና ከእርሱ ጋር የዘለአለም ህይወት እንዲደሰቱበት ለመርዳት ነው። ይህን ለማድረግ፣ የወንጌል ትምህርት እነርሱ በየቀኑ በደቀመዛሙርትነት እና በቅዱስ ቃል ኪዳናት መንገድ እንዲጓዙ ማበረታታት አለበት። አላማው ግለሰቦች የወንጌል መሰረታዊ መርሆችን እንዲያስቡበት፣ እንዲሰማቸው፣ እና ከዚያም በዚህ እንዲኖሩ ለማነሳሳት ነው። አላማው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነትን ለማሳደግ እና ወደ ወንጌሉ ለመቀየር ነው።

የሚባርክ እና የሚቀይር እናም የሚያድን ትምህርት የአዳኝን ምሳሌ የሚያንፀባርቅ ነው። የአዳኝን ምሳሌ የሚከተሉ አስተማሪዎች የሚያስተምሯቸውን ያፈቅራሉ እናም ያገለግላሉ። የሚያዳምጧቸውን በመለኮታዊ እውነት ዘለአለማዊ ትምህርት ያነሳሳሉ። እነርሱም በምሳሌ ለመከተል ብቁ የሆነ ህይወት ይኖራሉ።

ፍቅር እና አገልግሎት

የአዳኝ አገልግሎት በሙሉ ጎረቤትን በማፍቀር ምሳሌ የተሞላ ነበር። በእርግጥም፣ ፍቅሩ እና አገልግሎቱ አብዛኛውን ጊዜ የእርሱ ትምህርቶች ነበር። በዚህም አይነት፣ በደንብ የማስታውሳቸው አስተማሪዎች ስለተማሪዎቻቸው የሚያውቁ፣ የሚያፈቅሩ፣ እና የሚያስቡ አስተማሪዎች ናቸው። የጠፉትን በጎች ይፈልጋሉ። ሁልጊዜም የማስታውሰውን የህይወት ትምህርት አስተምረዋል።

ሉሲ ገርትች እንደዚህ አይነት አስተማሪ ነበሩ። እያንዳንድ ተማሪዎቻቸውን ያውቃሉ። እሁድ በዚያ ያልነበሩትን ወይም ያልመጡትን ሁልጊዜ ይጎበኙ ነበር። ስለእኛ ያስቡ እንደነበር እናውቅ ነበር። ማንኛችንም እርሳቸውን እና ያስተማሩንን አልረሳንም ነበር።

ከብዙ አመቶች በኋላ፣ ሉሲ ወደ ህይወታቸው መጨረሻ ሲደርሱ፣ ጎበኘኋቸው። ከረጅም ጊዜ በፊት አስተማሪያችን ስለነበሩበት ቀናት አስታወስን። ስለክፍላችን እያንዳንዱ አባላት ተነጋገርን እናም እያንዳንዳቸው ምን እንደሚያደርጉ ተወያየን። ፍቅራቸው እና ሀሳባቸው በህይወት በሙሉ የተስፋፋ ነበር።

በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ የሚገኘውን የጌታ ትዕዛዝ እወዳለሁ፥

“የመንግስቱን ትምህርት እርስበርስ ትማማሩም ዘንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።

“በትጋት አስተምሩ እናም ጸጋዬ ከእናንተ ጋር ይገኛል።”6

ሉሲ ገርትች በትጋት አስተማሩ ምክንያቱም በማይደክም ሁኔታ ያፈቅሩ ነበርና።

ተስፋ እና እውነትን አቅርቡ

ሐዋርያው ጳውሎስ እንደመከረው፣ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።”7

አስተማሪ መስጠት ከሚችለው ተስፋ ታላቁ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ ነው።

“እናም ተስፋ የምታደርጉበት ምንድን ነው?” ብሎ ሞርሞን ጠየቀ። “እነሆ በክርስቶስ የኃጢአት ክፍያ እናም በትንሳኤው ኃይል ለዘለዓለም ህይወት እንዲኖራችሁ ተስፋ ይኑራችሁ እላችኋለሁ እናም ይህም በእርሱ ባላችሁ እምነት ለእናንተ በገባላችሁ ቃል ኪዳን መሰረት ነው።”8

አስተማሪዎች፣ ድምጻችሁን ከፍ አድርጉ እናም ስለአምላክ እውነተኛ ፍጥረት መስክሩ። ስለመፅሐፈ ሞርሞን ምስክራችሁን አውጁ። በደህንነት እቅድ ውስጥ የተያዙትን እውነቶች ግርማዊነት እና ወብት ተናገሩባቸው። በቤተክርስቲያን ፈቃድ የተሰጠባቸው ነገሮች፣ በተለይ ቅዱስ መጻህፍትን፣ በዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን እውነቶች በንጹህነታቸው እና በቀላልነታቸው አስተምሩ። “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” ብሎ አዳኝ ያዘዘውን አስታውሱ።9

የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ ህይወት ምን እውነተኛ እና አስፈላጊ እንደሆነ እንዲረዱ እርዳታ ስጧቸው። በዘለአለም ህይወት መንገድ በደህንነት እንዲቆዩ የሚያደርጓቸውን መንገዶች እንዲመርጡ የሚያስችላቸው ጥንካሬ እንዲያገኙ እርዳታ ስጧቸው።

እውነትን አስተምሩ፣ እናም መንፈስ ቅዱስ በጥረታችሁ ይረዳችኋል።

“ከእኔ ተማሩ”

ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቱ በፍጹም ታዛዥ እና ትሁት ስለነበረ፣ እርሱም “በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።”10 ይህን ለማድረግ የልብ ውሳኔ አለን? ኢየሱስ “ጸጋ ለጸጋ እንደተቀበለ፣”11 ወንጌልን ለመማር በምንጥርበት በትእግስት እና በፅናት ከእግዚአብሔር ብርሀንን እና እውቀትን መፈለግ አለብን።

ማዳመጥ የመማር አስፈላጊ ክፍል ነው። ለመማር በሚዘጋጀት ጊዜ፣ በጸሎት መነሳሳትን እና ማረጋገጫን ከመንፈስ ቅዱስ እንፈልግ። እላሰላስላለን፣ እንጸልያለን፣ የወንጌል ትምህርቶችን እንጠቀምበታለን፣ እናም አብ ለእኛ ያለውን ፍላጎት እንፈልጋለን።12

ኢየሱስ “ብዙ ነገር በምሳሌ አስተማረ”13 ይህም የሚያዳምጡ ጆሮዎች፣ የሚያዩ አይኖች፣ እና የሚረዳ ልብ ያስፈልገዋል። በብቁነት ስንኖር፣ “ሁሉን [ሊያስተምረን] [እርሱ የነገረንን] ሁሉ [ሊያሳስበን]”14የሚችለውን የመንፈስ ቅዱስ መሾክሾክን በተሻለ ሁኔታ ለማዳመጥ እንችላለን።

“ከእኔ ተማሩ” የሚለውን የረጋ የጌታ ግብዣን መልስ ስንሰጥ፣ የመለኮታዊ ሀይሉ ተካፋይ እንሆናለን። ስለዚህ፣ ምሳሌአችንን እርሱ እንድናስተምር በሚፈልገው መልኩ በማስተማር እና እንድንማር በሚፈልገው በመማር በታዛዥነት መንፈስ ወደፊት እንሂድ።

ከዚህ መልእክት ማስተማር

ፕሬዘደንት ሞንሰን “ለማስተማር እና ለመማር [የምናደርገውን] ጥረት [እንድናሰላስል] እና ይህን በማድረግም ወደ አዳኝ እንደ መመሪያ [እንድንመለከት]” ጋብዘውናል። ከምታስተምሯቸው ጋር ኢየሱስ ያስተማረበትን እና የተማረበትን መንገዶች አስተያየት ለማግኘት ቅዱሳን መጻህፍትን ለመፈተሽ አስቡበት። ፕሬዘደንት ሞንሰን በጠቀሷቸው እንደ ማቴዎስ 11፥29፣ ዮሀንስ 5፥30፣ እና ማርቆስ 4፥2 አይነት ቅዱሳት መጻህፍትን ለመጀመር ትችላላችሁ። ስለክርስቶስ የተማራችሁት “የመለኮታዊ ሀይሉ ተካፋይ” ለመሆን እንዴት እንደሚረዳችሁ ለመወያየት ትችላላችሁ።

አትም