“ትክክለኛውን ነገር አድርጉ፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፣ ሐምሌ 2021 (እ.አ.አ)፣ 18–19።
ወርሀዊ የ ለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ሐምሌ 2021 (እ.አ.አ)
ትክክለኛውን ነገር አድርጉ
ቅዱሳን መጽሐፍትን ስታጠኑ ሃሳባችሁን መፃፍ በእርግጥ እንድትማሩ ይረዳችኋል።
አንድ ሚስዮናዊ ለሚስዮን ፕሬዚዳንቱ እንዲህ ብሎ ነገረው “ቅዱሳን መጽሐፍትን ማንበብ ስጀምር እንቅልፍ ይይዘኛል!”። “ቅዱሳን መጽሐፍቱ ልክ እንደ የእንቅልፍ ኪኒን ናቸው!”
የእሱ ፕሬዚዳንት እንዲህ ብሎ መለሰ፣ “ስታነብ ማስታወሻ ትወስዳለህን?”
“አይ” አለ ሚስዮናዊው።
“ስታነብ መተኛት ወይም አዕምሮህ እንዲዋልል መፍቀድ ቀላል ነው” አለ ፕሬዚዳንቱ፣ “ነገር ግን ጽህፈትን ስታክልበት ያ ነገር አይሆንም!”
ይህ የሚስዮን ፕሬዚዳንት በችግር ላይ ላለው ሚስዮናዊ የሰጠው ምክር ትልቅ ለውጥን አመጣ። ሰለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁን ለማጠንከር አዲስ መንገድን እየፈለጋችሁ ከሆነ ሞክሩት። ስለምታነቡት ነገር ስትፅፉ፣ እራሳችሁን የበለጠ እየተሳተፋችሁ እና በተሻለ ሁኔታ እየተማራችሁ ታገኙታላቸሁ።
በርግጥ በጣም ጠቃሚ ሆነው ያገኘናቸው የተወሰኑ ዘዴዎች እነሆ።
ወንድም ስቲቭን ለንድ፦
በማነብበት ጊዜ ባጠገቤ ወረቀት አስቀምጣለሁ። በጥናቴ ጊዜ መንፈስ ሲያነሳሳኝ፣ እነዚያን መነሳሳቶች እፅፋለሁ።
ሃሳቡን ያገኘሁት “ከመንፈስ የምትማሯችውን ጠቃሚ ነገሮች በተጠበቀ ቦታ ውስጥ ፃፉ” ብሎ የአስራሁለቱ ሐዋርያት ምልዓተ ጉባኤ አባል ሽማግሌ ሪቻርድ ጂ ስካት (1928–2015 እ.አ.አ) ከተናገረው ነው። ውድ መነሳሳቶችን ስትፅፉ ያንን ታገኙታላችሁ፣ ብዙ ጊዜም እየበዛ ይመጣል። እንዲሁም የምታገኙት እውቀት በሕይወታችሁ ሙሉ ዝግጁ ይሆናል” (“To Acquire Knowledge and the Strength to Use It Wisely፣” ኢንዛይን፣ ሰኔ 2002 (እ.አ.አ)፣ 32)።
እነዚያ ቃላት እውነት እንደሆኑ አውቃለሁ። ንግግሮችን እና ትምህርቶችን ሳዘጋጅ ወደ ቅዱሳን መጽሐፍት ብቻ ሳይሆን እነሱን ሳነባቸው ወደ ፃፍኳቸው እሄዳለሁ።
ወንድም አህመድ ኮርቢት፦
በርዕስ ማጥናት እወዳለሁ። ቅዱሳን መጽሐፍትን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ አነባለሁ፣ ነገር ግን እየዘለልኩኝ ርዕሶችንም ማጥናት እወዳለሁ። ለምሳሌ፣ በእምነት ወይም በእስራኤል መሰብሰብ ላይ የሚያተኩሩ ቅዱሳን ፅሁፎችን ለማግኘት የርዕስ መምሪያን እጠቀማለሁ። ከዛ ማስታወሻ ብቻ አልወስድም ነገር ግን በትክክል እንደተረዳሁት ለማረጋገጥ ስለምማረው ነገር እፅፋለሁ። ይህን ሳደርግ ነገሮችን ምን ያህል በላቀ ሁኔታ እንደምረዳ ሁሌም እገረማለሁ። እንዲሁም የተወሰኑ ቅዱሳን ፅሁፎችን በቃሌ ለመያዝም እመርጣለሁ።
ወንድም በራድሊ ዊልካክስ፦
ቅዱሳን መጽሐፍትን በራሴ ቃላት የምፅፍበትን የጥናት ማስታወሻ እይዛለሁ። ለምሳሌ፣ “የተፈጥሮ ሰው የእግዚአብሔር ጠላት ነው” (ሞዛያ3፥19) የሚለው እንደሚከተለው ይቀየራል “ኩራተኛ እና ንስሃ የማይገባ ሰው የእግዚአብሔር ጠላት ለመሆን ይመርጣል ነገር ግን እግዚአብሔር የእሱ ጠላት አይደለም። እግዚአብሔር የእሱ መልካም ጓደኛ ነው”
እንዲሁም ጥያቄዎችን እፅፋለሁ። ከማንበቤ በፊት ሳስባቸው የነበሩ ጥያቄዎች ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ከማነበው የመነጩ ጥያቄዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ምንም ይሁን ምን እንዳተኩር ይረዳኛል።
ሃሳባችሁን የመፃፍ ኃይል
እያንዳንዳችን በአመራራችን ውስጥ ቅዱሳን መጽሐፍትን በተለየ መልኩ እናጠናለን፣ ነገር ግን ሁላችንም ስናጠና እንፅፋለን።
ማንበብ ሃሳቦችን እና ስሜቶችን የራሳችን እንድናደርጋቸው ይረዳናል። ያ ጠቃሚ ነው። ስንናገር ወይም ስንፅፍ ሃሳቦችን እና ስሜቶችን ከውስጥ ወደ ውጪ እናገኛለን እናም እንገልፃለን። የወንጌል እውነቶችን በተሻለ መልኩ የግል ለማድረግ እንደሚረዳን ይሰማናል።
አንድ ወጣት ወንድ በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ውስጥ ንግግር እንዲያደርግ ሲጠየቅ ይህን እውነት እራሱ አገኘ። ብዙ ሌሎች ሰዎች ንግግር ሲሰጡ ሰምቷል፣ ነገር ግን ዝርዝሮቹን ማስታወስ አልቻለም ነበር። ይህ ጊዜ ልዩ ነው። ለራሱ ንግግር ረቂቁን ሲፅፍ የተዋቀረ ንግግርን እንዲሰጥ ብቻ አልነበረም የረዳው ነገር ግን ለረጅም ጊዜም አስታወሰው።
በቅዱሳን መጽሐፍት ጥናታችሁ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት ይችላል። ቅዱሳን መፅሃፍቶቻችሁን በምትከፍቱ ጊዜ እንቅልፋችሁ ከመጣ የመንቃት ሰዓት ነው። እርሳስ፣ እስክሪብቶ፣ ስልክ ወይም ኮምፒውተር ማውጣትና መፃፍ ሞክሩ። ማምጣት በሚችለው ለውጥ ትገረማላችሁ!
© 2021 በ Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በሕግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ሐምሌ 2021 (እ.አ.አ)ትርጉም። Amharic። 17471 506