“በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት፣” ሊያሆና፣ ሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ)።
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሚያዝያ 2023 (እ.አ.አ)
በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነትን ማኖር የወንጌል የመጀመሪያው መርህ ነው (የእምነት አንቀጽ 1፥4 ተመልከቱ)። እምነታችን ወደ ሰማይ አባታችን በድጋሚ እንድንመለስ የሚመሩንን ምርጫዎች እንድናደርግ ይረዳናል። በመላ ህይወታችን ውስጥ እምነታችንን ለማጠንከር መስራት እንችላለን።
እምነት ምንድን ነው?
እምነት ማለት በጥብቅ ማመን ወይም በአንድ ነገር ላይ መተማመን ማለት ነው። እምነትን ማድረግ ማለት እነሱን ማየት ባንችልም ወይም በሙሉ መረዳት ባንችልም እንኳን እውነት በሆኑ ነገሮች ተስፋ ማድረግን እና ማመንን ያካትታል ( ዕብራውያን 11፥1፤ አልማ 32፥21ይመልከቱ)።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ እምነት
ወደ ደህንነት እንዲመራ፣ እምነታችን እርሱ አዳኛችን እና ቤዛችን በመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከላዊ የሚያደርግ መሆን አለበት። በክርስቶስ እምነትን ማድረግ ማለት በእርሱ መተማመን ማለት ነው። ይህ ማለት ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ መመካት ማለትም በዘለአለማዊ ኃይሉ፣ እውቀቱ እና ፍቅሩ ማመን ማለት ነው። የእርሱን ትምህርቶች ማመንን እና መከተልንም ይጨምራል።
እምነታችንን ማሳደግ
እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ነገር ግን እምነትን መሻት አለብን እንዲሁም አጠንክረን ለማቆየት መስራት አለብን። በመጸለይ እና ቅዱሳት መጻህፍትን እና የኋላኛው ቀን ነቢያትን ትምህርቶች በማጥናት እምነታችንን ማሳደግ እንችላለን። በጽድቅ ስንኖር እና ቃል ኪዳኖቻችንንስንጠብቅ እምነታችንን ማጠንከርም እንችላለን።
በእምነት መኖር
እምነት ከማመን የላቀ ነው። በዚያ እምነት ላይ መተግበርን ያካትታል። በምንኖርበት መንገድ እምነታችንን እናሳያለን። በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የእርሱን ፍጹም ምሳሌ እንድንከተል ያበረታታናል። እምነታችን ትዕዛዛቶችን ወደመጠበቅ፣ ለኃጢያቶቻችን ንስሃ ወደመግባት እና ቃል ኪዳኖችን ወደማድረግ እና ወደመጠበቅ ይመራል።
እምነት ወደ ተዓምራት ሊመራ ይችላል።
እውነተኛ እምነት ተአምራትን፣ ራዕይን፣ ህልምን፣ ፈውስን እና ከእግዚአብሔር የሚመጡ ሌላ ስጦታዎችን ጨምሮ ያመጣል። ቅዱሳት መጻህፍት በእርሱ ባላቸው እምነት ምክንያት ተአምራቶችን ከጌታ የተቀበሉ ብዙ ሰዎችን ታሪኮች ይዘዋል። ለተወሰኑ ምሳሌዎች “ተአምራት” የሚለውን በቅዱሳት መጻህፍት መምሪያ ውስጥ ተመልከቱ።
እምነት ሰላምን ሊያመጣ ይችላል።
በእግዚአብሔር እና በደህንነት እቅዱ ላይ እምነትን ማኖር በፈተናዎቻችን ጊዜ ሊያጠነክረን ይችላል። ወደፊት ለመጓዝ እና ችግሮቻችንን በድፍረት ለመጋፈጥ እምነት ጥንካሬን ሊሰጠን ይችላል። የወደፊታችን ግልጽ ሳይመስል ሲቀር እንኳ በአዳኛችን ያለን እምነት ሰላምን ሊሰጠን ይችላል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እምነት ወደ ደህንነት ያመራል
በክርስቶስ እምነትን መለማመድ ወደ ደህንነታችን ይመራል። ክርስቶስ የዘለአለም ህይወትን እንድንቀበል መንገዱን አዘጋጅቶልናል። በእርሱ ባለን እምነት ስንኖር ለኃጢያቶቻችን ይቅርታን እናገኛለን እና ከእግዚአብሔር ጋር በድጋሚ ለመኖር እንመለሳለን።
© 2023 (እ.አ.አ) Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly Liahona Message, April 2023 ትርጉም።Language. 19006 506