“እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መንከባከብ፣” ሊያሆና፣ መስከረም 2023 (እ.አ.አ)።
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ መስከረም 2023 (እ.አ.አ)
እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መንከባከብ
እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል፣ የጌታን አስተምህሮት በመከተል እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን እንንከባከባለን። በማገልገል፣ እራሳቸውን እንዲችሉ በመርዳት እና ያለንን በማካፈል ሌሎችን እንከባከባለን።
የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ
ኢየሱስ ክርስቶስ በዙሪያው ያሉትን ይወዳቸው፣ ያጽናናቸው እና ይጸልይላቸው ነበር። “መልካም እያደረገ ዞረ”(የሐዋሪያት ስራ 10፥38)። በመውደድ፣ በማጽናናት፣ በማገልገል እና በዙሪያችን ላሉ ሰዎች በመጸለይ የእርሱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ሁልጊዜ ሌሎችን ለመርዳት መንገዶችን መፈለግ እንችላለን።
አገልግሎት
አገልግሎት የሚለው ቃል በቅዱሳት መጻሕፍት እና በጌታ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዴት እርስ በርሳችን እንደምንተሳሰብ ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል። የክህነት ተሸካሚዎች በአጥቢያ ወይም በቅርንጫፍ ላለ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ የአገልግሎት ወንድሞች በመሆን ተመድበዋል። የአገልግሎት እህቶች ለእያንዳንዷ አዋቂ ሴት ተመድበዋል። አገልጋይ ወንድሞች እና እህቶች ሁሉም የቤተክርስቲያኗ አባላት መታሰባቸውን እና እንክብካቤ ማግኘታቸውን ያረጋግጣሉ።
ሌሎች እራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ መርዳት
የቤተሰብ አባላት እና ጓደኞች ለችግሮቻቸው የረጅም ጊዜ መፍትሄ እንዲያገኙ በማበረታታት እራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ ልንረዳቸው እንችላለን። ከዚያም ግባቸው ላይ ሲሰሩ ልንደግፋቸው እንችላለን። በነሐሴ 2023 (እ.አ.አ) ሊያሆና የወንጌል መሠረታዊ ጽሑፍ ውስጥ ስለራስ መቻል የበለጠ መረጃን ፈልጉ።
ሌሎችን ማገልገል
በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች ማገልገል የምንችልባቸው እና ሥጋዊ፣ መንፈሳዊ እንዲሁም ስሜታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ልንረዳቸው የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ስለሌሎች ማወቅ እንዴት በተሻለ ሁኔታ ልናገለግላቸው እንደምንችል እንድናውቅ ይረዳናል። እንዲሁም ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምንችል ለማወቅ መመሪያ ለማግኘት መጸለይ እንችላለን።
ያለንን ማካፈል
እግዚአብሔር የባረከንን በማካፈል ሌሎችን ማገልገል እንችላለን። ለምሳሌ፣ ለጋስ የሆነ የጾም በኩራት ልንሰጥ ወይም ለቤተክርስቲያኗ የሰብአዊ እርዳታ ገንዘብ መለገስ እንችላለን። በማህበረሰባችን እና በቤተክርስቲያናችን ጥሪዎች ውስጥ ማገልገል እንችላለን።
የቤተክርስቲያን መሪዎች ተግባራት
ኤጲስ ቆፖሱ በአጥቢያው ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የመንከባከብ ስራን ይቆጣጠራል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን አባላት ለመርዳት ከጾም በኩራት የሚገኘውን ገንዘብ ሊጠቀም ይችላል። አማካሪዎቹን ጨምሮ ሌሎች መሪዎች፣ እንዲሁም የሴቶች መረዳጃ ማህበር እና የሽማግሌዎች ቡድን አመራሮች፣ አባላት ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚጠቀሙባቸውን ምንጮች ማግኘት እንዲችሉ ያግዟቸዋል።
የቤተክርስቲያን የበጎ አድራጎት ጥረቶች
ቤተክርስቲያኗ በአለም ዙሪያ ያሉ ሰዎችን በድንገተኛ አደጋ ምላሽ፣ በማህበረሰብ ፕሮጀክቶች፣ እንደ ንጹህ ውሃ እና ክትባቶች ባሉ በሌሎች ፕሮግራሞች ትረዳለች። የበለጠ ለመረዳት፣ ዳለን ኤች. ኦክስ፣ “ድሆችን እና የተጨነቁትን መርዳት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 6–8 ተመልከቱ።
© 2023 (እ.አ.አ) በ Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly Liahona Message, September 2023 ትርጉም። Language. 19047 506