“እኔ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነኝ “ ለወጣቶች ጥንካሬ፣ ጥር 2024 (እ አ አ)
ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ ጥር 2024 (እ.አ.አ)
እኔ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነኝ
አዳኙን መከተል እና ቃሉን ለሌሎች ማሰራጨት ትችላላችሁ።
ሰዎችን ከፈወሰ በኋላ፣ ኢየሱስ የተወሰኑት ለማንም እንዳይናገሩ ነግሯቸው ነበር( ማርቆስ 7፥36ይመልከቱ)፤ ለምን እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁ? አንዱ ምክንያት ምናልባት እርሱ ይፈልጋቸው ከነበረው የተከታዮች አይነት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ሰዎች ስለመፈወሳቸው ቢያወሩ ለኢየሱስ ሰዎችን የመሳቢያ ጥሩ መንገድ ሊሆን ይችል ነበር ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የፈለገው የሚከተሉትን ብቻ አልነበረም። እርሱ የፈለገው ደቀመዛሙርትን ነበር።
ኢየሱስም ጴጥሮስን እና እንድርያስን “ተከተሉኝ“ (ማቴዎስ 4፡19) አላቸው። የዚህ ጥቅስ የጆሴፍ ስሚዝ ትርጉም እንዲህ ይነበባል፣ “እኔ በነቢያት የተጻፈለት እርሱ ነኝ፤ ተከተሉኝ“ (የጆሲፍ ስሚዝ ትርጉም፣ ማቴዎስ 4:18 [በ ማቴዎስ 4:19፣ የግርጌ ማስታወሻ a]) ግብዣውም ለወቅቱ ጊዜያቸውን ከእርሱ ጋር እንዲያሳልፉ አልነበረም። ለዘለአለም የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር።
ሰዎችን ሲያስተምር፣ ሰዎችን ሲወድ እና ተዓምራትን ሲያደርግ እንዲያዩት ብቻ አልፈለገም ነበር። እነርሱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ፈልጎ ነበር። የእርሱ ስራ የእነርሱም ስራ እንዲሆን ፈልጎ ነበር። ለእነርሱ፣ ክርስቶስን መምረጥ ማለት እርሱ እንዳገለገለው ማገልገልን እንዲሁም እርሱ በሚያስብበት መንገድ ማሰብን መማር ማለት ነበር። እርሱ እንደኖረው መኖርን ይለማመዳሉ፣ እርሱም ያስተምራቸዋል እንዲሁም ይበልጥ እርሱን መምሰል ይችሉ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን እገዛ ያደርግላቸዋል።
ደቀመዝሙር ለሚለው ቃል የግሪክኛ አቻው ማቴተስ ነው። ተከታይ ወይም ተማሪ ከሚለው የበለጠ ትርጉም አለው። አብዛኛውን ጊዜ የሥራ ላይ ተለማማጅ ተብሎ ይተረጎማል። በክርስቶስ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርት አስተማሪያቸውን የመተካት ዝንባሌ በመያዝ እንዲያስተምራቸው የሚፈልጉትን አስተማሪ ይመርጡ ነበር። ክርስቶስ ይህንን ልምምድ አልተከተለም ነበር። እርሱ ግን በተገላቢጦሽ የእርሱን ደቀ መዛሙርት ፈለገ። ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም ወደ እርሱ እንድንቀርብ ጥሪ ያደርግልናል። የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን እንዲሁም የዘለአለም ህይወት ይኖራችዉ ዘንድ ቃሉን ለሰዎች እንድናውጅ ጥሪ ያደርግልናል ( 3 ኔፊ 5፡13ይመልከቱ)።
በካሪቢያን በምትገኘው በሄይቲ ነዋሪ የሆነች አንዲት ወጣት ሴት የቤተክርስቲያን አባል ያልሆነች ጓደኛዋን ወደ ኤፍ ኤስ ዋይ አብራት እንድትመጣ በመጋበዝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆን ፍላጎትዋን አሳይታለች። መጀመሪያ ላይ የጓደኛዋ አባት ልጃቸው እንድትሄድ ፈቃድ መስጠት አልፈለጉም ነበር። የቤተክርስቲያን መሪዎች ስለሚጠብቋት አዎንታዊ ተሞክሮዎች አስረዷቸው፤ እንዲሁም ድንቅ የሆኑት ወጣት ጎልማሳ አማካሪዎች እንደሚንከባከቧት ገለፁላቸው። አባትየውም ልጃቸው እንድትታደም ፈቀዱላት፤ ከዚያም በህይወትዋ ላይ ያመጣውን ለውጥ ከተመለከቱ በኋላ በቤተከርስቲያን ስብሰባዎች ላይም እንድትሳተፍ ፈቃድ ሰጧት፤ ከስድስት ወራት በኋላም ተጠመቀች።
በደቡብ አሜሪካ አርጀንቲና ዉስጥ ነዋሪ የሆነ አንድ ወጣት ሰው በአውቶብስ ወደ ትምህርት ቤት በመጓዝ ላይ ሳሉ የተወሰነውን ከረሜላ ለጓደኛው በማካፈል የክርስቶስ ደቀመዝሙር የመሆን ፍላጎቱን አሳይቷል። የቡና ጣእም ያለው አንድ ፍሬ ባገኘ ጊዜ፣ የዚያን ጣእም ምንነት በጭራሽ እንዳላዳበረና ይህም የሆነው በቤተሰቡ ውስጥ ማንም ቡና ስለማይጠጣ እንደሆነ አስረዳ። ያም ስለቤተክርስቲያኗ ወደሚደረግ ውይይት ያመራ ሲሆን፣ ውይይቱም ወደ ቤተክርስቲያን ስብሰባ እንዲመጣ ወደ መጋበዝ አመራ፤ በመጨረሻም ጓደኛው ቤተክርስቲያኗን እንዲቀላቀል እና በቺሊ ሚሲዮን እንዲያገለግል በር ከፈተ።
ስለቤተክርስቲያኗ የነገራችኋቸው ወይም ወደ ቤተክርስቲያኗ አክቲቪቲዎች የጋበዛችኋቸው በሙሉ መቀላቀል ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። ያ ምንም አይደለም። በተመሳሳይም፣ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ያናገራቸው ሁሉ አልተቀላቀሉም። አሁንም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ስንመርጥ እና የእርሱን ቃል ስንናገር፤ ድፍረትን እና መለኮታዊ እርዳታን ይሰጠናል። ይበልጥ እርሱን እንዴት መምሰል እንደምንችል እንማራለን፤ ደቀ መዛሙርት የሚያደርጉትም ያንን ነው።
© 2024 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። የ ወርሃዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልእክት፣ ጥር 2024 (እ.አ.አ) ትርጉም Language. 19273 506