ሊያሆና
የማያቋርጥ ጸሎት በማድረግ ነፍሳችሁን መግቡ
ሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ)


“የማያቋርጥ ጸሎት በማድረግ ነፍሳችሁን መግቡ፣” ሊያሆና፣ ሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ)

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ)

ተደጋጋሚ ጸሎት በማድረግ ነፍሳችሁን መግቡ

በሁሉም ቦታ እንዲሁም ሁል ጊዜ የሚገኘው ከሰማይ አባታችን ጋር የመነጋገር የመንፈሳዊ ምግብ በረከት ለሁላችንም ያስፈልገናል።

ምስል
ኢኖስ እየፀለየ

የኢኖስን ገጸ ባህርይ የሚጫወት ተዋናይ ፎቶ በማት ራየር

ከዚህ በፊት ሁላችንም ረሃብ ተሰምቶን ያውቃል። የረሃብ ስሜት ሰውነታችን ምግብ እንደሚያስፈልገው የሚነግረን መንገድ ነው። ስለሆነም ስንራብ፣ ምን ማድረግ እንዳለብን እናውቃለን — እንበላለን።

መንፈሶቻችንም መንፈሳዊ ምግብ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንድናውቅ የሚያደርጉበት መንገድ አላቸው። ነገር ግን ከሥጋዊ ረሃብ ይልቅ መንፈሳዊ ረሃብን በቀላሉ ችላ ማለት ለእኛ የሚቀለን ይመስላል።

ስንራብ ልንበላ የምንችላቸው ብዙ ዓይነት ምግቦች እንዳሉ ሁሉ፣ መንፈሳዊ ረሃባችንን ለማርካት ልናደርጋቸው የምንችላቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፣ ከቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እና በነቢያት ቃል አማካኝነት “የክርስቶስን ቃል [መመገብ]” (2 ኔፊ 32፥32) እንችላለን። በቋሚነት ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ እና ቅዱስ ቁርባንን መካፈል እንችላለን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 59፥9 ይመልከቱ)። እግዚአብሔርን እና ልጆቹን ማገልገል እንችላለን (ሞዛያ 2፥17 ይመልከቱ)።

ነገር ግን በማንኛውም ጊዜ፣ በህይወታችን በእያንዳንዷ ቅጽበት፣ ሁኔታችን ምንም ቢሆን ምን ሌላ የመንፈሳዊ ምግብ ምንጭ አለ። በጸሎት አማካኝነት ሁልጊዜ ከሰማይ አባት ጋር መነጋገር እንችላለን።

“ነፍሴ ተራበች”

ነቢዩ ኢኖስ በዱር ውስጥ አውሬዎችን እያደነ ሳለ “አባ[ቱ] ዘለዓለማዊ ህይወትንና የቅዱሳንን ደስታ በተመለከተ ሁልጊዜ ሲናገር [የሰማቸውን] ቃላት” አሰበ። እነዚህ ቃላት “ወደል[ቡ] ጠልቀው ገቡ” (ኢኖስ 1፥3)።

ኢኖስ በዚህ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ብርቱ ፍላጎት ተሰማው፦ “ነፍሴ ተራበች” (ኢኖስ 1፥4፤ አጽንዖት ተጨምሮበታል) በማለት ተናገረ ።

ኢኖስ የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎት የሆነው ይህ መንፈሳዊ ረሃብ በተሰማው ጊዜ ምን አደረገ? እንዲህም አለ፣ “በፈጣሪዬም ፊት ተንበረከክሁ፣ እናም ለነፍሴ በሀይለኛ ፀሎትና ልመና ወደእርሱ ጮህኩኝ” (ኢኖስ 1፥4)።

የኢኖስ መንፈሳዊ ረሃብ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ “ቀኑን ሙሉ … እናም ምሽቱ ሲመጣ ድም[ፁን] ሰማይ እስከሚደርስ ከፍ [አድርጎ]” ጸለየ (ኢኖስ 1፥4)። በመጨረሻም፣ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማ፣ ኃጢአቱንም ይቅር አለ። ኢኖስ በደሉ እንደተወገደ ተሰማው። ነገር ግን መንፈሳዊ ምግቡ በዚህ አላበቃም ነበር።

በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ማድረግ ስላለው ኃይል ተማረ፣ ነፍሱንም በሙሉ ለህዝቡ፣ እንዲሁም ለጠላቶቹም ጭምር አፈሰሰ። ከጌታ ጋር ቃል ኪዳኖችን ገባ እናም እርሱም ተስፋዎችን ሠጠው። ኢኖስ ከታላቅ ጸሎቱ በኋላ፣ ስለ ሰማውና ስላያቸው ነገሮች ትንቢት እየተናገረና እየመሰከረ በህዝቡ መካከል ሄደ። (ኢኖስ 1፥5–19 ይመልከቱ።)

እያንዳንዱ ጸሎት በእንደዚህ ዓይነት አስደናቂ መንገድ ምላሽ ላያገኝ ይችላል፣ ነገር ግን ከጸሎት ጋር ያለን ልምድ ትርጉም ያለው እና ህይወትን ሊቀይር የሚችል ሊሆን ይችላል። ከኢኖስ የጸሎት ልምድ አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶችን ልንማር እንችላለን። ለምሳሌ፦

  • ወንጌልን በተሟላ ሁኔታ ለመኖር መጣር መንፈሳዊ ረሃባችንን እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል።

  • መንፈሳዊ ረሃባችን ከሰማይ አባት እርዳታ ለመጠየቅ እንድንንበረክከ ሊያደርገን ይችላል፤ ማድረግም አለበት።

  • ወደ ሰማይ አባት መጸለይ መንፈሳዊ ረሃባችንን ለማርካት እና ከዚያም የበለጠ ለማድረግ ይረዳል።

  • በማንኛውም ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ መጸለይ እንችላለን።

  • ጸሎት ንስሐ እንድንገባ ሊረዳን ይችላል።

  • ጸሎት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነትሊያጠነክር ይችላል።

  • የሰማይ አባታችን እንደሚሰማን እና እንደሚያውቀን የግል ምስክርነት መቀበል እንችላለን።

  • በጸሎት አማካኝነት የምንቀበለው ምስክርነት እና ጥንካሬ ሌሎችን እንድናገለግል እና እንድናበረታ ይረዳናል።

ምስል
ሽማግሌ ሶሬስ በልጅነት

ስለ ጸሎት ሃይል ያለኝ ልምድ

ልክ እንደ ኢኖስ፣ እኔም በግሌ ባጋጠመኝ ነገር እነዚህን ተመሳሳይ ትምህርቶች ተምሬአለሁ። ወላጆቼ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የተቀላቀሉት ገና ትንሽ ልጅ ሳለሁ ነበር፣ እኔም የስምንት አመት ልጅ ሳለሁ ተጠመቅሁ። ስለሰማይ አባቴ እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዳግም ስለተመለሰው ወንጌሉ እና ስለ እርሱ ቤተክርስቲያን በልቤ ጥሩ እና ሞቅ ያለ ስሜት ሁልጊዜ ይሰማኝ ነበር። ነገር ግን ስለእነዚህ ነገሮች እውነተኝነት መጸለይ የጀመርኩት 16 ዓመት ገደማ በነበርኩ ጊዜ ነበር።

መነሳሳት የተሰማው ኤጲስ ቆጶሴ የወጣቶች የሰንበት ትምህርት ቤትን እንዳስተምር ጠየቀኝ። ማስተማር የነበረብኝም በጸሎት በኩል የወንጌልን ምስክርነት እንዴት ማግኘት እንደምንችል ነበር። ይህ ኤጲስ ቆጶሴ የሰጠኝ ሥራ ስለራሴ ምስክርነት በጥልቀት እንዳስብ አደረገኝ። መፅሐፈ ሞርሞንን ለማጥናት ጊዜ መድቤ ነበር እናም ሁልጊዜም ቤተክርስቲያኗ እውነት እንደሆነች ይሰማኝ ነበር። ሁልጊዜም በአዳኙ በኢየሱስ ክርስቶስ አምን ነበር፣ ነገር ግን በሞሮኒ 10፥4–5 ላይ የሚገኘውን የሞሮኒን ቃል ኪዳን በፍጹም ልብ አላልኩም ነበር። ስለ ወንጌል እውነትነት ጸልዬ አላውቅም ነበር።

እነዚህን ወጣቶች በጸሎት እንዴት ምስክርነት ማግኘት እንደሚችሉ የማስተምር ከሆነ፣ እኔ ራሴ ምስክርነትን ለማግኘት መጸለይ እንዳለብኝ በልቤ ውስጥ የተሰማኝን አስታውሳለሁ። ነፍሴ ተራበች—ምናልባት ከኢኖስ በተለየ መንገድ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳለኝ ሆኖ ተሰማኝ።

ትምህርቱን ሳዘጋጅ፣ በውስጤ የተሰማኝን እውነት ለማረጋገጥ ተንበርክኬ የልቤን መሻት ለሰማዩ አባቴ አቀረብኩ። ምንም አይነት ታላቅ መገለጫን አልጠበኩም ነበር። ነገር ግን ወንጌሉ እውነት እንደሆን ጌታን ስጠይቀው፣ በጣም ደስ የሚያሰኝ ስሜት ወደ ልቤ መጣ — ትንሽ የዝምታ ድምጽ፣ ይህ እውነት መሆኑን እና የማደርገውን መቀጠል እንዳለብኝ አረጋገጠልኝ።

ስሜቱ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ያንን መልስ ፈጽሞ ችላ ማለት እና አላወኩም ለማለት አልቻልኩም ነበር። ያን ቀን ሙሉ በጣም ደስተኛ በመሆን አሳለፍኩ። በልቤ ያለውን አስደሳች ስሜት እያሰላሰለ አእምሮዬ በሰማያት ነበር።

በቀጣዩ እሑድ፣ ከእኔ በእድሜ ከሚያንሱ ሦስት ወይም አራት የክፍል ጓደኞቼ ፊት ቆምኩ። እምነት ካላቸው የሰማይ አባት ጸሎታቸውን እንደሚመልስላቸው መሰከርኩላቸው።

ምስል
ሽማግሌ ሶሬስ

ሽማግሌ ሶሬስ በወጣትነታቸው ያገኙት የጸሎት መልስ፣ እንደ ሚስዮናዊ (ከላይ)፣ እንደ አባት እና ባል እንዲሁም እንደ ሐዋርያ የሰማይ አባት በእምነት የሚደረጉ ጸሎቶችን እንደሚመልስ እንዲመሰክሩ አስችሏቸዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ምስክርነት ከእኔ ጋር ቆይቷል። በተለይ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ ውሳኔዎችን እንዳደርግ ረድቶኛል። በዚያን ቀን ያደረኩት ጸሎት፣ ባለፉት ዓመታት ከተቀበልኳቸው ተጨማሪ ምስክርነቶች ጋር፣ ሰዎች በእምነት ከጸለዩ ከሰማይ አባት መልስ ማግኘት እንደሚችሉ በእርግጠኝነት መመስከር እንድችል አድርገውኛል። ይህ እንደ ሚስዮናዊ፣ እንደቤተክርስቲያን መሪ፣ እንደ አባት እና ባል፣ እንዲሁም ዛሬ እንደ ሐዋርያ እንደመሰከርኩት እውነት ነው።

መቼ እና እንዴት ጸሎት መፀለይ እንዳለብን

በእርግጥ የምንጸልየው ጠንካራ መንፈሳዊ ፍላጎት ሲሰማን ብቻ አይደለም። ስለዚህ መጸለይ ያለብን መቼ ነው? ስለ ምንስ መጸለይ አለብን? አጭሩ መልስ በማንኛውም ጊዜ እንዲሁም ስለማንኛውም ነገር ነው።

እግዚአብሔር የሰማይ አባታችን ነው። ይህንን ማወቅ የምንጸልይበትን መንገድ ይቀይረዋል። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንዲህ አስተምሯል፦ “እግዚአብሔርን ስናውቅ፣ ወደ እርሱ እንዴት መቅረብ እንዳለብን እና መልስ ለማግኘት እንዴት እንደምንጠይቅ ማወቅ እንጀምራለን። … ወደ እርሱ ለመቅረብ ዝግጁ ስንሆን እርሱ ወደ እኛ ለመምጣት ዝግጁ ነው።”1

የሰማይ አባታችን ሁል ጊዜ እኛን ለማዳመጥ ዝግጁ ነው እንዲሁም ወደ እርሱ ዘወትር ያለማቋረጥ እንድንጸልይ ይፈልጋል። “በሥራ[ችን] ሁሉ ከጌታ ጋር [መማከር]” (አልማ 37፥37) እና በጠዋት፣ ቀትር እና ማታ መጸለይ አለብን። በቤታችን፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በየትኛውም ቦታ ብንሆን፣ ስለማንኛውም ጥረታችን መጸለይ አለብን (አልማ 34፥17–26 ይመልከቱ)።

በቤተሰባችን ውስጥ መጸለይ አለብን (3 ኔፊ 18፥21 ይመልከቱ)። “ድም[ጻችንን] አውጥተ[ን] እናም በአለም ፊት እና በስውር” መጸለይ አለብን (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 81፥3 ይመልከቱ)። እናም “ወደ ጌታ በማንጮ[ህበት] ጊዜ፣ ልባች[ን] ለደህንነታች[ን]፣ ደግሞ በዙሪያች[ን] ላሉት ደህንነት ባለማቋረጥ በፀሎት ወደ እርሱ በመትጋት ሙሉ ይሁን” (አልማ 34፥27)። እናም ሁል ጊዜም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወደ አብ መጸለይ አለብን (3 ኔፊ 18፥19–20 ይመልከቱ)።

ምስል
ጆሴፍ ስሚዝ በወጣትነቱ

የጆሴፍ ስሚዝ ስዕል በዋልተር ራኔ፣ መቅዳት የተከለከለ ነው

የሰማይ አባታችንን መቅረብ

የሰማይ አባታችን ሊባርከን ይፈልጋል። ከጠየቅነው ደግሞ እርሱ ያደርገዋል። ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ “ካልጠየቅን ምንም መቀበል እንደማንችል አስታውሱ። ስለዚህ፣ በእምነት ጠይቁ፣ እናም እግዚአብሔር ለእናንተ ሊሰጥ የሚፈልገውን በረከቶች ትቀበላላችሁ” በማለት አስተምሯል። 2

የእኛ የዘወትር እንዲሁም የማያቋርጡ ጸሎቶች ለተራበ ነፍሳችን መንፈሳዊ የተመጣጠነ ምግብ ወሳኝ አካል ናቸው። በጸሎት ከሰማይ አባት ጋር መገናኘት በሁሉም ቦታ እና ሁልጊዜም የሚገኝ እንዲሁም ተቀባይነት ያለው ነው።

ከምወዳቸው የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶች መካከል አንዱ ለጸሎት ስንንበረከክ ወደ ሰማይ አባታችን እንዴት መቅረብ እንዳለብን ያስተምራል፦ “ትሁት ሁን፤ እና ጌታ አምላክህ እጅህን ይዞ ይመራሀል፣ እና ለጸሎቶችህም መልስ ይሰጥሀል” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 112፥10)። ትሁት እና ታዛዥ ስንሆን የሰማይ አባት ከእኛ ጋር ይሆናል። በእጁ ይመራናል። የት መሄድ እንዳለብን እና ምን ማድረግ እንዳለብን መነሳሳት ይሰጠናል። ጸሎታችንን እንደ ፈቃዱ፣ እንደ መንገዱ፣ በጊዜው እና ለእኛ ስለሚጠቅመን ባለው ፍፁም እውቀት መሰረት ይሰጠናል።

ይህንን ማስታወስ እና ወደ እግዚአብሔር ዙፋን መቅረብ እና ከእጁ በረከቶችን መቀበል የመቻላችንን እድል ዋጋ ልንሰጠው ይገባናል።

ማስታወሻዎች

  1. Teachings of Presidents of the Church: Joseph Smith [የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንቶች ትምህርቶች፦ ጆሴፍ ስሚዝ] (2011)፣ 40፣ 41።

  2. Teachings: Joseph Smith [ትምህርቶች፦ ጆሴፍ ስሚዝ]፣ 131።

አትም