ሊያሆና
እግዚአብሔር ይረዳናል እናም ይጠብቀናል
ነሐሴ 2024 (እ.አ.አ)


“እግዚአብሔር ይረዳናል እናም ይጠብቀናል” ሊያሆና፣ ነሐሴ 2024 (እ.አ.አ)።

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ነሐሴ 2024 (እ.አ.አ)

እግዚአብሔር ይረዳናል እናም ይጠብቀናል

ልክ እንደ ሻምበል ሞሮኒ፣ በህይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙን ጦርነቶች መለኮታዊ እርዳታን እና ሃይልን መቀበል እንችላለን።

ምስል
ሻምበል ሞሮኒ የነጻነት አርማን ይዞ

ስዕል በኤሪክ ቻው

መጽሐፈ ሞርሞንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነብ፣ በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል የነበረውን የጦርነት ታሪክ ወደድኩኝ። 25 ዓመት ሲሞላው የሁሉም ኔፋውያን ጦር አለቃ ሆኖ በተመረጠው የጦር አዛዡ ሻምበል ሞሮኒ በተጠቀመው እምነት፣ ብልሃት እና ዘዴ ተደንቄ ነበር። ጥበበኛ፣ ጠንካራ እና ብልህ ነበር። ለህዝቦቹ ነጻነት እና ደህንነት እሱ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነበር። (አልማ 48፥11–12 ተመልከቱ።)

ወታደራዊ ስኬትን ለራሱ ከመስጠት ይልቅ፣ ሞሮኒ ስኬቱን ለእግዚአብሔር እና ሰራዊቱ ተዋጊ ካልሆኑ ሴቶች እና ልጆች ለተቀበሉት ቅዱስ እርዳታ አሳልፎ ሰጠ። የተሸነፈን የጠላት አለቃ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ጌታ … እናንተንም በእኛ እጅ ስር እንድትሆኑ አድርጓል። እናም አሁን ይህ በኃይማኖታችንና በክርስቶስ ባለን እምነት መሆኑን እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ።” ከዚያም ሞሮኒ ይህንን የነቢያዊ አስተያየት አካፈለ፦ “በእግዚአብሔር በእርሱ፣ እናም በእምነታችንና፣ በኃይማኖታችን ታማኝ ሆነን እስከቆየን [ይረዳናል]፣ [ይጠብቀናል] እንዲሁም [ያድነናል]” (አልማ 44፥3፣ 4)።

ከጊዜ በኋላ፣ የዘመናዊ ህይወታችንን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ እንዲረዳን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለንን መርሆዎች ሞሮኒ እንዳሳየን መገንዘብ ችያለው። የዓለም አዳኝ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ እምነትን ስንለማመድ፣ እርሱ በሃይሉ ይባርከናል። ነገር ግን እርሱ ይህንን ለማድረግ እና እኛ የእርሱን በረከቶች ለመገንዘብ አላማችንን መረዳት፣ ለስኬት መዘየድ እና ለሚያጋጥሙን ምሳሌአዊ ጦርነቶች መዘጋጀት ይኖርብናል። ይህንን ስናደርግ የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ ይረዱናል እናም ይጠብቁናል።

አላማችንን መረዳት

ሞሮኒ በተደጋጋሚ ህዝቦቹን ማን እንደነበሩ (የአብርሐም ቃል ኪዳን ወራሾች)፣ የማን እንደነበሩ (የእግዚአብሔር የተወደዱ ልጆች) እና የተፋለሙበትን ምክንያት (ለቤተሰብ፣ ለእምነት እና ለነጻነት) አስገነዘባቸው። የሚፋለሙት ለገዛ ደህንነታቸው እና ከጭቆና እና ከባርነት ነጻነት ለመውጣት እንደነበረ ሞሮኒ ህዝቦቹን አስተማራቸው። በተቃራኒው፣ የእነርሱ ጠላቶች እራሳቸውን ከፍ ለማድረግ እና ሌሎችን ለመግዛት ሃይል ለማግኘት ተዋጉ።

የተወሰኑ ኔፋውያን ስልጣንን ለግላቸው ጥቅም ሲፈልጉ ፣ ሞሮኒ ኮቱን በመቅደድ በቁራጩ ላይ የእርሱን ዋና መልዕክት እንዲህ በማለት ጻፈበት፤ “አምላካችንን፣ ኃይማኖታችንን፣ እናም ነፃነታችንንና፣ ሰላማችንን፣ እናም ሚስቶቻችንንና፣ ልጆቻችንን ለማስታወስ።” “የነጻነት አርማ” ብሎ የጠራውን ይህን ባንዲራ በምሰሶ ጫፍ ላይ አስሮ ከፍ አደረገው እና ፍልሚያው ስለምን እንደነበረ ለማስታወስ እና ለአላማው ሊያነሳሳቸው ተጠቀመበት። (አልማ 46፥12–13፣ 19–20 ተመልከቱ።)

በህይወት መንፈሳዊ ጦርነቶች ውስጥ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ … ከጨለማ ዓለም ገዦች … [እና] ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” (ኤፌሶን 6፥12)። እኛም ፍልሚያው ስለምን እንደሆነ ልናስታወስ ይገባናል። ሽማግሌ ኒል ኤ. ማክስዌል [1926–2004 (እ.አ.አ)]፣ የቀድሞ የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን አባል፣ ይህንን ሃሳብ በአንደበተ ርዕቱ፣ አጭር በሆነ ንግግር ገለጹት።

በ2004 (እ.አ.አ)፣ ሽማግሌ ማክስዌልን ከመሞታቸው በፊት በሆስፒታል ክፍላቸው ውስጥ ጎበኘዋቸው። ለሚጎበኛቸው እና ለሚረዳቸው ሰዎች ሁሉ በጣም ደግ ነበሩ። የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ወደ ክፍላቸው ከገቡ በኋላ እያለቀሱ ይወጣሉ። ለእሳቸውም እንዲህ አልኳቸው፣ “ሽማግሌ ማክስዌል፣ ይህ በጣም ከባድ ነው።” እሳቸውም በመሳቅ እንዲህ አሉ፣ “ኦ፣ ዴል፣ እኛ በሟች ዓለም ውስጥ የምንኖር ዘለአለማዊ ፍጡሮች ነን። ልክ ከውሃ እንደወጣ አሳ እኛም ከአካላችን ውጬ ነን። የዘለአለም እይታ ሲኖረን ብቻ ነው ማንኛውም ነገር ትርጉም የሚኖረው።”

የእኛን መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ዘለአለማዊ እጣ ፈንታ እና የሚቃወሙንን ዲያብሎሳዊ ሃይሎች ትልቅ ስብጥር እይታ በፍጹም ማጣት የለብንም። በትክክል የሰማይ አባትን እቅድ መረዳት ለዘለአለማዊ ደህንነታችን እና ከመንፈሳዊ ባርነት ለነጻነታችን መዋጋታችንን ለመቀጠል ያበረታታናል።

ምስል
ሰዎች ምሽጎችን ሲያዘጋጁ

ለስኬት መዘየድ

ወታደሮቹ በተዋጉበት ጦርነቶች ሁሉ ሞሮኒ ስኬትን ለማረጋገጥ ዘየደ። የጠላቶቹን እንቅስቃሴዎች እና ሃሳቦች ለማወቅ ሰላዮችን ተጠቀመ። ከነቢዩ አልማ መመሪያን አሻ። ከዛም ሞሮኒ ያንን የተነሳሳ ሃሳብ ለጦርነቱ ተጠቀመበት። ብዙ ወታደሮችን ብዙ ምሽጎች በሌለባቸው ከተሞች ውስጥ በማሰማራት ግባቶችን እንደየፍላጎታቸው አሰራጨ። ወቅታዊ በሆነ መረጃ ላይ በመመስረት በስልት የተልእኮ እቅዶችን አስቀመጠ።

ከዛም በጠላት ወታደሮች ላይ የበላይነትን አገኘ። በቀድሞ ድሎች አልኮራም፣ በምትኩ የወደፊት ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ የእሱን እና የወታደሮቹን አቅም ማሻሻሉን ቀጠለ።

እኛም መንፈሳዊ ተቃዋሚዎችን ለመጋፈጥ ተመሳሳይ አቀራረብን መጠቀም እንችላለን። ሰይጣን በህይወታችን ውስጥ ምን እያደረገ እንዳለ በመገንዘብ መጀመር እንችላለን። ከአላማችን ሊያስተጓጉለን ይሞክራል። ፈተና ሲያጋጥመን እነዚህን ጥያቄዎች እራሳችንን መጠየቅ አለብን፤

  • ይህ የእኔ ተግባር ከተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል ጋር እንዴት ይነጻጸራል?

  • ይህንን ተግባር የመውሰድ ውጤቶች ምን ምን ናቸው?

  • ይህ ተግባር በምድር ላይ ያለኝን አላማ እንዳሳካ ይረዳኛልን?

ለትንሽ ፈተናዎች እጅ የመስጠትን የመጨረሻ ውጤት መገንዘብ ይኖርብናል። ለፈተና እጅ ስንሰጥ፣ “ቀስ በቀስ መርዝ” እንወስዳለን (አልማ 47፥18)፣ ይህም ወደ መንፈሳዊ ገዳይ ወጤቶች መምራት የሚችል የክፋት ሃይል የሚጠቀምበት በጣም ውጤታማ የሆነ ዘዴ ነው።

ከኋለኛው ቀን ነቢይ የምንቀበለውን ምሪት በመከተል እራሳችንን ከሰይጣን ፈተናዎች መሸሸግ እንችላለን። ይህን ማድረግ ተግባራችንን የምንገመግምበትን ዘለአለማዊ እይታ እንድንይዝ ይረዳናል። በህይወታችን በተለያየ አካባቢዎች ውስጥ የሚነሱ ፈተናዎች እንዴት እንደምንጋፈጥ መዘየድ በወቅቱ የበለጠ ትክክለኛ ምርጫዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። ቀድመው የሚታቀዱ ዘዴዎች ከዘለአለም አላማችን የሚያስተጓጉለንን ለመከላከል ይረዱናል።

አንደ ምሳሌ ቲክኖሎጂ ነው። ቴክኖሎጂ እንደ ባለ ሁሉት ስለት ጎራዴ ነው፣ እንደአጠቃቀማችን ጠቃሚ እና ጎጂ ነው። ሰለቁሳችን ብልህ የሆኑ ምርጫዎችን ለመምረጥ እንዲረዳን ወጣት እና አረጋውያን “Taking Charge of Technology [ቴክኖሎጂን ተቆጣጠሩ]” እና ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያን መመልከት ይችላሉ። እነዚህ አላማችንን ያስታውሱናል፣ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ይጠቁሙናል እና መንፈስ ቅዱስን ወደ ህይወታችን እንድንጋብዝ ይረዱናል። ቴክኖሎጂን እንዴት፣ መቼ እና የት እንደምንጠቀም ማቀድ ከመጥፎ ዓለማዊ ዘዴዎች ይከላከለናል።

ምስል
ላማናውያን የኔፋውያንን ምሽጎች ሲያጠቁ

ለምሳሌአዊ ጦርነቶች መዘጋጀት

የወደፊት ጦርነቶችን በመጠበቅ ሞሮኒ ህዝቦቹን አንድ በአንድ በደረት ኪሶች፣ በጋሻዎች፣ በራስ ቁሮች እና በወፍራም ልብሶች አዘጋጀ። ከተማዎችን በምሽጎች በመክበብ፣ በዚሪያቸው መሬቱን በማከማቸት ህዝቦቹን በአንድነት አዘጋጀ።

በመንፈሳዊነት፣ በግል የምንዘጋጀው የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይል በህይወታችን ውስጥ የሚስቡትን ቃል ኪዳኖች ከእግዚአብሔር ጋር እንገባለን እና እንጠብቃለን። ጸሎት፣ ጾም እና ቅዱሳት መጻሐፍትን መመርመር በመሳሰሉ የግል የአምልኮ ተግባራት እንሳተፋለን። በምንቀበለው መንፈሳዊ ምሪት ምላሽ በመስጠት በእምነትም እንተገብራለን። በህሊና እንዘጋጃለን እና በብቁነት ቅዱስ ቁርባንን እንካፈላለን። ይህን ስናደርግ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነቱ ብርቱ በነበረው ልክ ለሞሮኒ እውን እንደሆነ ሁሉ አዳኙ በህይወታችን ውስጥ የበለጠ እውን ይሆናል። ሞሮኒ ለምሪት እና ለነጻ መውጣት በአዳኙ ላይ መመካት እንደሚችል አወቀ (አልማ 48፥16)። እኛም ለምሪት እና ለነጻ መውጣት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መመካት እንችላለን።

ቤተሰባችንን በማጠንከር በበለጠ መዘጋጀት እንችላለን። ደስተኛ እንድንሆን እና ወደ እርሱ እንዴት መመለስ እንደምንችል ለማወቅ የሰማይ አባታችን በቤተሰብ ውስጥ አዋቀረን። ቤተሰባችን ለእኛ የእርዳታ ምንጭ መሆን ይችላሉ። የቤተሰባችን የግል ሁኔታዎች ምንም ይሁኑ ምን፣ እኛ የእግዚአብሔር ታላቅ ቤተሰብ አካል እንደሆንን በማስታወስ ደስታ እና ፍቅር ሊሰማን ይችላል።

የቅዱሳንን ማህበረሰቦች በመቀላቀል ለመንፈሳዊ ጦርነታች መዘጋጀት እና በጋራ ጥንካሬን ማግኘት እንችላለን። ካስማችን እና አውራጃችን እንደዚህ አይነት መሸሸጊያ እና መከላከያ ስፍራን ይሰጣሉ። ሁሌም እና በተለይም በፈተና ጊዜ፣ እርስ በእርስ በመንፈስ መመጋገብ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ መረዳዳት እና ክርስቶስ ላይ ለመመካት ማበረታታት እንችላለን። ስንሰባሰብ ጦርነታችንን ብቻችንን እንደማንፋለም እንገነዘባለን። ሊረዱን እና ሊጠብቁን የሚችሉ ጐደኞች፣ አስተማሪዎች እና መሪዎች አሉን። በአንድነት ስንዘጋጅ ሁላችንም ይበልጥ ጠንካራ እንሆናለን።

በሚያስደንቅ ሁኔታ፣ ሁሉም የህዝቦቹ ደስታ በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት እና ሃይማኖት ላይ ታማኝ በመሆናቸው ምክንያት እንደሆነ ሞሮኒ እውቅና ሰጠ። ልክ እንደ ሞሮኒ፣ ደስታ በሰማይ አባት እና በእርሱ እቅድ አማካኝነት እና በኢየሱስ ክርስቶስ እና በእርሱ የሃጢያት ክፍያው አማካኝነት እንደሚመጣ መገንዘብ ይኖርብናል። አላማችንን ስንረዳ፣ ለውጤት ስንዘይድ እና ለምሳሌአዊ ጦርነቶች ስንዘጋጅ፣ መለኮታዊ እርዳታን እና ሃይልን እንቀበላለን።

ልክ እንደ ሞሮኒ፣ የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻውን ከምርኮ ነጻነትን ማለትም ከሞት እና ከሃጢያት ነጻነትን እንደሚያመጡ አውቃለው። በሁሉም ነገሮች ወደ እነርሱ ስንመለከት በሃይላቸው ይባርኩናል።

ማስታወሻዎች

  1. Taking Charge of Technology [ቴክኖሎጂን ተቆጣጠሩ]፣” የወንጌል ቤተ መጽሐፍት።

  2. ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን ለማድረግ መመሪያ [2022 (እ.አ.አ )]፣ የወንጌል ቤተ መጽሐፍት።

  3. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 82 ተመልከቱ።

አትም