“የቅዱስ ክህነት የቤተመቅደስ ልብስ፣” ሊያሆና መስከረም 2024 (እ.አ.አ)
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ መስከረም 2024 (እ.አ.አ)
የቅዱስ ክህነት የቤተመቅደስ ልብስ
የቤተመቅደስ የመንፈሥ ስጦታ አካል በመሆን፣ የክርስቶስ የራሱ ምልክት የሆነው የተቀደሠ አካላዊ አስታዋሽ ተሠጥቶናል።
ያለጥርጥር ዝግጁ እንዲሆኑ የተደረጉ ቢሆንም እንዲሁም የተሠጣቸውን ማረጋገጫ ለማስታወስ የሞከሩ ቢሆንም አዳም እና ሔዋን ገነት ከሆነችው የኤደን የአትክልት ሥፍራ ተባረው ወደ ወደቀው ዓለም መምጣታቸው የሚያስደንቅ ነገር ሆኖባቸው ነበር።
ሠላማዊ፣ ጭንቀት አልባ ህይወታቸውን በተቃውሞ እና በፊት ወዝ፣ በእሾህ እና በሀዘን—በመጨረሻም ሞት በሚባል ነገር መሸጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ተገነዘቡ። መጀመሪያ ላይ ይህ ሁሉ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል ሊያውቁ አልቻሉም ነበር፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ እያንዳንዷ ቀን አዲስ ችግር ይዛ እንደምትመጣ ተገነዘቡ። በእርግጥ፣ ከሁሉም በላይ የሚያሠቃይ የነበረው፣ ይህ ሁሉ የሚገጥሟቸው በሰማይ ካለው አባታቸው ተነጥለው መሆኑን መገንዘባቸው ነበር—ሙሴ በኋላ እንደመዘገበው፣ “ከእርሱ ፊት ተዘግተው ነበር”።
ቀዝቃዛ በሆነው የማያስደስት ዓለም ውስጥ በነበረው መነጠል እና ብቸኝነት ወቅት፣ አዳም እና ሔዋን አንድ ነገርን ማስታወሳቸው ለእነርሱ ምንኛ አጽናኝ ነበር፦ ይኸውም ተሥፋዎች መሰጠታቸው ሲሆን—ቃል ኪዳን የተሠኘ ቅዱስ እና ዘለዓለማዊ ነገር ነበር። በህይወት ዘመናቸው ሁሉ አብን እንደሚታዘዙ ቃል ገብተው ነበር፣ እርሱም ከህመማቸው እና ከሀዘናቸው እፎይታን የሚሠጣቸው፣ ሃጢያቶቻቸውን የሚያስተሠርይ እና በጥበቃ ወደ እርሱ መገኘት የሚመልሣቸው አዳኝ እንደሚልክ ቃል ገብቶ ነበር።
ሆኖም እነዚህ ሟቾች የገቡትን ቃል ኪዳን የሚያስታውሱት እንዴት ነው? ስላሉበት አደገኛ ሁኔታ በቀንም በማታም ሁል ጊዜ በማወቅ የሚመላለሡት እንዴት ነው?!
የቃል ኪዳኖቻቸው አሰታዋሽ
እንዲህ ዓይነቱ አሰታዋሽ ይኖራቸው ዘንድ “የቁርበት ልብሥ” ሰጣቸው። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ እና ወቅታዊ ስጦታ ነበር። የተከለከለውን ፍሬ ከበሉ በኋላ አዳም እና ሔዋን እርቃናቸውን መሆናቸውን ወዲያውኑ አወቁ። በመጀመሪያ እርቃናቸውን በበለሥ ቅጠል ለመሸፈን ሞከሩ። እንዲሁም ያም በቂ እንዳልሆነ በመሥጋት ከጌታ ለመደበቅ ሞከሩ። (እንዲህ ያለው የሞኝነት ሙከራ ሥጋዊ ባህርይ በተግባር እየታየ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ነበር!) ከዚያ ቅጽበት ጀምሮ እስከ አሁን ድረሥ፣ አፍቃው አባት ልጆቹ ከተደበቁበት ወጥተው ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋብዟቸዋል። እንዲሁም የቁርበት ልብሥን ካለበሣቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እና ልዩ ልዩ ልብሶችን በሚያስለብሰን አሁን ድረስ፣ እርሱ በምህረቱ እርቃናችንን አልተወንም ነገር ግን ለእኛ ለምንታዘዘው የተሠጡንን የተሥፋ ቃሎች እና ቃል ኪዳኖቻችንን የሚያስታውስ “የጽድቅ መጎናጸፊያን” አልብሶናል። እነዚህ “የማዳን ልብሶች” ከሁሉ በላይ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ መሥዋዕት ያመለክታሉ።
የቤተመቅደስ ልብስ የአዳኙ ምልክት ነው።
እንግዲህ፣ ይህ ሁሉ ስለ አዳም እና ሔዋን፣ ስለ ቃል ኪዳኖች እና ስለ ልብስ ማሰብ ከአዕምሮ ሥራ የላቀ ነው። አዳም እና ሔዋን እንዴት ተሰምቷቸው የነበረ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፤ ምክንያቱም እኛም በዚህ በወደቀው ዓለም ውስጥ ችግሮች ያጋጥሙናል። እኛም ከእግዚአብሔር መገኘት ተነጥለናል፣ በተላለፍን ቁጥርም ራሳችንን የበለጠ እናርቃለን። እንደ አዳም እና ሔዋን ሁሉ፣ እኛም የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አልፋና ኦሜጋ የሆነው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ያው አዳኝ፣ ተሰጥቶናል። እንደ አዳምና ሔዋን ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል። የቤተመቅደስ የመንፈሥ ስጦታ አካል በመሆን፣ የክርስቶስ የራሱ ምልክት የሆነ የተቀደሠ አካላዊ አስታዋሽ ተሠጥቶናል። በእኛ ዘመን የቅዱስ ክህነት ልብስ ይባላል።
ይህንን ልብስ ከውጪያዊ ልብሳችን ሥር እንለብሳለን። ምንም አይነት ሀላፊነቶች ቢኖሩብኝ፣ በህይወቴ ውስጥ የምጫወተው ሚና ምንም ይሁን ምን፣ የዕለት ተዕለት የኑሮ ግዴታዎች ምንም አይነት ነገር የሚጠይቁ ቢሆን፣ ከእነዚህ ሁሉ ሥር ያሉት ሁልጊዜ እና ለዘለአለም ቃል ኪዳኖቼ ናቸው። ከሁሉም ሥር አጥብቄ የምይዛቸው እነዚያ ቅዱስ ቃል ኪዳኖች አሉ። የቤተመቅደስ ልብሱ ለዓለም ለታይታ ወይም እዩኝ እዩኝ ለማለት የሚገለጥ አይደለም፣ ቃል ኪዳኖቼም እንደዚያው ናቸው። ሆኖም ሁለቱንም ወደ እኔ በቅርበት እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ—በቅርቤ ላደርጋቸው የምችለውን ያህል በቅርቤ አደርጋቸዋለሁ። በጣም ሚሥጥራዊ እና እጅግ በጣም የተቀደሱ ናቸው።
የሁለትዮሽ ቃል ኪዳኖች የሆኑትን እነዚያን ቃል ኪዳኖች በማስታወስ፣ በህይወታችን ሙሉ የቤተመቅደሥ ልብሱን እንለብሳለን። ይህ ልምምድ አዳኙ በህይወታችን ውስጥ ዘላቂ ተጽዕኖ እንዲኖረው ያለንን ፍላጎት ያሳያል። ሌሎቹ ውድ የሆኑ ምልክቶች ወቅት አላቸው። የምንጠመቀው በህይወታችን አንዴ ነው። ቅዱስ ቁርባንን በሣምንት አንዴ እንካፈላለን። ሁኔታችን በፈቀደው መጠንበቤተመቅደስ እንሣተፋለን። የቅዱስ ክህነት ልብስ ግን የተለየ ነው፡ ይህን ምልክት ሁል ጊዜ በቀን እና በማታ እናከብራለን።
ለቃል ኪዳኖችም እንዲሁ ነው—በምቾት ጊዜ ወይም በግዴለሽነት ወደ ጎን የማይደረጉ እንዲሁም ከህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እና ፋሽን ጋር ለማጣጣም ማስተካከያ የማይደረግባቸው ናቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዝሙር ሕይወት፣ የዓለም መንገድ ከቃል ኪዳኖቻችን ጋር ለመጣጣም ይችሉ ዘንድ መስተካከል አለባቸው እንጂ በተገላቢጦሽ ቃል ኪዳኖቻችን አይስተካከሉም።
የቤተመቅደስ ልብሣችንን ስንለብስ፣ ቀዳሚ አመራር እንዳስተማሩን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ምልክት እየለበስን ነን። ነገሩ እንዲህ ሆኖ ሣለ ለምንድነው ያንን ምልክት ለማውለቅ ምክንያት የምንፈልገው? የቤተመቅደስ ልብሱ የሚወክለውን የኃይል፣ የጥበቃ እና የምህረት ተስፋ ከመቀበል ራሳችንን የምንገድበው ለምንድን ነው ? በተቃራኒውም፣ የቤተመቅደስ ልብሱን ለተወሠነ ጊዜ ማውለቅ ግዴታ ሲሆንብን፣ በተቻለ ፍጥነት መልሰን ለመልበስ መጓጓት ይኖርብናል፣ ምክንያቱም ለቃል ኪዳኖቻችን ምክንያት የሆኑትን የተስፋ ቃሎችን እና አደጋዎችን እናስታውሳለን። ከሁሉም በላይ የክርስቶስን መስቀል እና ባዶ መቃብር እናስታውሳለን።
አንዳንዶች “ኢየሱስን የማስታውስበት ሌሎች መንገዶች አሉኝ” ሊሉ ይችላሉ። እኔም ያ ድንቅ ነው በማለት ምላሽ እሠጣለሁ። ተጨማሪ መንገድ መኖሩ የተሻለ ነው። ሁላችንም “ሁልጊዜ እርሱን ለማስታወስ” ያለንን ቁርጠኝነት ለመጠበቅ የምንችልባቸውን ያህል ብዙ መንገዶች እናስብ። ሆኖም ይህን በምናደርግበት ጊዜ፣ ጌታ ራሱ የቤተመቅደሥ የመንፈሥ ሥጦታ ለተቀበሉ ሆን ብሎ የሠጠውን ማሣሰቢያ፣ እንዲሁም የቅዱስ ክህነትን ልብስ፣ ችላ ማለት ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ እና ወንጌሉ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ናቸው። ሁሉም የዘለዓለም ተስፋዎቼ እና ምኞቶቼ፣ የምወደው ነገር ሁሉ፣ በእነርሱ ላይ የተመኩ ናቸው። እርሱ ሌሎች ብዙ ነገሮችን ጭምሮ፣ “የደህንነቴ ዓለት፣” የሠማይ አባትን የማገኝበት መንገድ፣ ብቁ በመሆኔ ምክንያት ቀድሞ ወደነበረኝ እና አሁን እንደገና ማግኘት ወደምፈልገው የምመለስበት ብቸኛ መንገድ ነው። ለእኛ የሰጠን ሥጦታ እስካሁን ከተቀበልኩት ሁሉ የላቀ የቸርነት ሥጦታ፣ ከሁሉ የላቀ የቸርነት ሥጦታ ነው—ይኸውም ወሰን በሌለው ሥቃይ የተገዛ፣ ወሠን የለሽ ለሆነ ቁጥር የቀረበ፣ ወሰን በሌለው ፍቅር የተሠጠ ሥጦታ ነው። እሾህና አሜከላ፣ ሥቃይ እና ጭንቀት፣ የዚህ የወደቀ ዓለም ሐዘን እና ኃጢአት ሁሉ “በክርስቶስ ተውጠዋል”።
ስለዚህ ከ64 ዓመት በፊት የ19 ዓመት ልጅ እያለሁኝ ከተሰጠኝ ጊዜ ጀምሮ፣ የቅዱስ ክህነት ልብስን ሁል ጊዜ በቀን እና በማታ እለብስ ነበር—ምክንያቱም እርሱን ስለምወደው እና የሚወክለው የተስፋ ቃል ስለሚያስፈልገኝ ነው።
የቤተመቅደስ ልብስ ስለመልበስ የሚቀርቡ ጥያቄዎች?
አንዳንዶቻችሁ ይህን ጽሑፍ የምታነቡት ስለቤተመቅደሥ ልብሱ የተለየ ጥያቄ እንደምመልሥላችሁ ተስፋ በማድረግ ይሆናል። በአንድ በሚያሳሥባችሁ ጉዳይ ላይ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል”—ወይም “አገልጋዮቹ እንዲህ ይላሉ”— የሚል ምላሽ ማግኘትን ተሥፋ አድርጋችሁ ይሆናል። ጥያቄያችሁ ከሥራ፣ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ከንፅህና አጠባበቅ፣ ከአየር ንብረት፣ ከልከኝነት፣ ከንፅህና መጠበቂያ ክፍሎች ወይም ከጤና ሁኔታ ጋር ከተያያዘ የግል ሁኔታ የመነጨ ሊሆን ይችላል።
እንደነዚህ ለመሣሠሉ ጥያቄዎች የሚሆኑ አንዳንድ መልሶች በtemples.ChurchofJesusChrist.org እና በአጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ ክፍል 38.5 ላይ ሊገኙ ይችላሉ። እምነት የሚጣልባቸው የቤተሰብ አባላት እና መሪዎች ስለ አንድ የግል ጉዳይ ምክር ሊጠየቁ ይችላሉ። ሆኖም በቤተመቅደሥ የመንፈሥ ሥጦታ የመጀመሪያ ሥርዓቶች ላይ የሚሠጥ በጣም ግልጽ የሆነ መመሪያ አለ፣ እንዲሁም የሚያውቃችሁ እና የሚወዳችሁ፣ ስለሁኔታችሁም ሁሉንም ነገር የሚረዳ፣ የሰማይ አባታችሁን ከዘለዓለም እስከዘለዓለም አለ። እነዚህን ጥያቄዎች በግል ብትጠይቁት ይደሰታል።
እባካችሁ ግራ እንዳትጋቡ። መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ስትፈልጉ፣ መንፈስ ቅዱስ በቤተመቅደስ ውስጥ ከተቀበላችኋቸው መመሪያዎች እና የቀዳዊ አመራር በቅርብ ጊዜ በሠጡት መግለጫ ውስጥ ያካፈሉትን ትንቢታዊ ምክር ከመከተል ያነሰ እንድታደርጉ አያነሳሳችሁም ። አፍቃሪ አባት አሁንም ለዘለዓለምም የሚባርካችሁን ከእርሱ የታማኝነት እና የትህትና መስፈርት ጋር ልትሥማሙ ከምትችሉት ያነሠ ለማድረግ ምክንያታዊ እንድትሆኑ አይረዳችሁም። ለመሆኑ፣ ጥያቄዎቻችሁን ተረድቷልን፣ እንዲሁም የቤተመቅደሥ ልብሱን የማክበር እና ቃል ኪዳኖቻችሁን የመጠበቅ በረከቶችን እንድትቀበሉ ይረዳችኋልን? አዎ! አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ ብቃት ካላቸው የህክምና እና የጤና ባለሙያዎች ጋር መመካከር ይኖርባችኋልን? ትክክል ነው! የማመዛዘን ችሎታችሁን ችላ ማለት ይኖርባችኋል ወይስ ከሚፈለገው በላይ ታተኩራላችሁን? ያንን እንዳታደርጉ እፀልያለሁ።
ላሏችሁ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት አልችልም። እኔ ራሴ ላሉኝ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት አልችልም። ሆኖም የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ እንደመሆኔ፣ ከእርሱ ጋር የገባችኋቸውን ቃል ኪዳኖች በምትጠብቁበት ጊዜ አሁን ልትረዱትም ሆነ ልትተነብዩት በማትችሉት መንገድ፣ እያንዳንዱን ስኬታችሁን እና በረከታችሁን እንድታገኙ የሚሻውን የአፍቃሪ አምላክን እርዳታ እንደምታገኙ ቃል ልገባላችሁ እችላለሁ።
© 2024 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። የMonthly Liahona Message, September 2024 ትርጉም። Amharic. 19295 506