“ግባችን መለወጥ ነው፣” ኑ! ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“ግባችን መለወጥ ነው፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
ግባችን መለወጥ ነው
ሁሉም ወንጌልን የመማር እና የማስተማር አላማ በጥልቅ እንድንለወጥ እና ይበልጥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመስል እኛን መርዳት ነው። በዚህ ምክንያት፣ ወንጌልን በምናጠናበት ጊዜ፣ አዲስ መረጃን ብቻ የምንፈልግ አይደለንም፤ “አዲስ ፍጥረት” ለመሆን እንፈልጋለን (2 ቆሮንቶስ 5፥17)። ይህም ልባችንን፣ አመለካከታችንን፣ ድርጊቶቻችንን፣ እና ተፈጥሯችንን ለመለወጥ ይረዳ ዘንድ በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መታመን ማለት ነው።
ነገር ግን እምነታችንን የሚያጠናክር እና ወደ ተዓምራዊ ለውጥ የሚመራው የወንጌል ትምህርት በሙሉ በአንድ ጊዜ አይከሰትም። ከመማሪያ ክፍል በላይ ወደ ግለሰብ ልብ እና ቤት ይሰፋል። ወንጌልን መረዳት እና መኖር የማያቋርጥ የዕለት ተዕለት ጥረትን ይጠይቃል። እውነተኛ ለውጥ የመንፈስ ቅዱስን ተፅዕኖ ይፈልጋል።
መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ይመራናል እንዲሁም ስለዚያ እውነት ይመሰክራል (ዮሐንስ 16፥13 ተመልከቱ)። እርሱ አዕምሯችንን ያበራል፣ ግንዛቤያችንን ያፋጥናል እናም የእውነት ሁሉ ምንጭ በሆነው በእግዚአብሔር ራዕይ ልባችንን ይነካል። መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ያነጻል። በእውነት የመኖርን ፍላጎት በውስጣችን ያነሳሳል፣ እንዲሁም ይህን የምናደርግባቸውን መንገዶች በሹክሹክታ ይነግረናል። በእውነትም፣ “መንፈስ ቅዱስ … ሁሉንም ያስተምረናል” (ዮሐንስ 14፥26)።
በእነዚህ ምክንያቶች፣ ወንጌልን ለመኖር፣ ለመማር፣ እና ለማስተማር በምናደርገው ጥረት፣ በመጀመሪያ እና ከሁሉም በላይ መንፈሱ አብሮን እንዲሆን መፈለግ አለብን። ይህ ግብ ምርጫዎቻችንን መቆጣጠር፣ እንዲሁም ሀሳቦቻችንን እና ድርጊቶቻችንን መምራት ይገባዋል። የመንፈስን ተጽዕኖ የሚጋብዘውን ማንኛውንም ነገር ሁሉ መፈለግ እና የእርሱን ተጽዕኖ ከሚያርቁ ነገሮች መራቅ አለብን—እኛ ለመንፈስ ቅዱስ መገኘት ብቁዎች ለመሆን ከቻልን፣ እንዲሁ ከሰማያዊ አባት እና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን ለመኖር ብቁ ለመሆንም እንደምንችል እናውቃለንና።