“በቤት እና በቤተክርስቲያን መማርን ለማሻሻል የሚረዱ ሃሳቦች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 ( እ.አ.አ)]
“በቤት እና በቤተክርስቲያን መማርን ለማሻሻል የሚረዱ ሃሳቦች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
በቤት እና በቤተክርስቲያን መማርን ለማሻሻል የሚረዱ ሃሳቦች
በቤት እና በቤተክርስቲያን የአዳኙን ወንጌል ስታጠኑ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ግምት ውስጥ አስገቡ፦
-
መንፈስ ቅዱስን ወደ ጥናታችሁ መጋበዝ የምትችሉት እንዴት ነው?
-
በጥናታችሁ ላይ ትኩረታችሁን በአዳኙ ላይ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
-
የዕለት ተዕለት የመማሪያ ጊዜያችሁን ጥቅም ላይ ማዋል የምትችሉት እንዴት ነው?
-
የቤተሰብ እና የክፍል አባላት ቅዱሳት መጻህፍትን በግል እንዲያጠኑ እና እየተማሩት ያሉትን ነገሮች እንዲያካፍሉ ማበረታታት የምትችሉት እንዴት ነው?
የእግዚአብሔርን ቃል ጥናታችሁን ለማሳደግ የምትችሉባቸው አንዳንድ ቀላል መንገዶች እነሆ።
መነሳሳትን ለማግኘት ፀልዩ
ቅዱሳት መጻህፍት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው፣ ስለዚህ ትረዷቸው ዘንድ እርዳታ እንዲሰጣችሁ እርሱን ጠይቁ።
ስለኢየሱስ ክርስቶስ እውነቶችን ፈልጉ
ሁሉም ነገሮች ስለ ክርስቶስ ይመሰክራሉ (2 ኔፊ 11፥ 4፤ ሙሴ 6፥63 ተመልከቱ)፣ ስለዚህ ስለአዳኙ በሚመሰክሩት፣ ለእርሱ ያላችሁን ፍቅር በሚያሳድጉት እና እርሱን እንዴት መከተል እንደሚቻል በሚያስተምሩት ጥቅሶች ላይ ማስታወሻ መፃፍን ወይም ምልክት ማድረግን አስቡ። አንዳንድ ጊዜ የአዳኙ እና የወንጌሉ እውነቶች በቀጥታ ይገለጻሉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምሳሌ ወይም በታሪክ አማካይነት ይገለጻሉ። እራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፣ “እነዚህ ጥቅሶች ምን ዘለዓለማዊ እውነቶችን ያስተምራሉ? እነዚህ ነገሮች ስለ አዳኙ ምን ያስተምሩኛል?”
መንፈስን ስሙ
ከምታነቡት ጋር የማይዛመዱ ቢሆኑም እንኳን፣ ለሀሳባችሁ እና ለስሜታችሁ ትኩረት ስጡ። እነዚህ ግንዛቤዎች የሰማይ አባታችሁ እንድትማሯቸው የሚፈልጋቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።
ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ።
በምታጠኑበት ጊዜ የሚመጡትን ግንዛቤዎች ለመመዝገብ የሚያስችሉ ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ፣ በቅዱሳት መፃህፍት ውስጥ የተወሰኑ የሚያስደንቋችሁ ቃላት ወይም ሐረጎች ልታገኙ ትችላላችሁ፤ በእነዚህ ላይ ምልክት ልታደርጉባቸው እንዲሁም ሀሳባችሁን በቅዱሳት መጻህፍቶቻችሁ ውስጥ እንደ ማስታወሻ ልትፅፉ ትችላላችሁ። እንዲሁም የምትቀበሏቸውን ግንዛቤዎች፣ ስሜቶች እና ሃሳቦች በማስታወሻ ደብተራችሁ ላይ መያዝ ትችላላችሁ።
እየተማራችሁ ያላችሁትን ለሌሎች አጋሩ።
ከግል ጥናታችሁ ያገኛችኋቸውን ግንዛቤዎች መወያየት ሌሎችን የማስተማር ጥሩ መንገድ ነው፣ እንዲሁም ስላነበባችኋቸው ነገሮች ያላችሁን ግንዛቤ ለማጠናከር ይረዳል። ከቤተሰብ አባላት ወይም ከጓደኞች (በግንባር ወይም በዲጂታል መልክ) ጋር ምን እየተማራችሁ እንደሆነ አጋሩ፣ ከዚያም እነርሱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ጋብዟቸው።
ቅዱሳት መጻህፍትን ከህይወታችሁ ጋር አመሳስሉ
እያነበባችኋቸው ያሉት ታሪኮች እና ትምህርቶች በህይወታችሁ ውስጥ እንዴት እንደሚሠሩ አስቡ። ለምሳሌ፣ እንዲህ ብላችሁ ራሳችሁን ለመጠየቅ ትችላላችሁ፣ “እያነበብኩት ካለው ነገር ጋር የሚመሳሰል ምን ተሞክሮዎች ነበሩኝ?”
በምታጠኑበት ጊዜ ጥያቄዎችን ጠይቁ
ቅዱሳት መጻህፍትን ስታጠኑ፣ ጥያቄዎች ወደ አዕምሯችሁ ሊመጡ ይችላሉ። እነዚህ ጥያቄዎች ከምታነቡት ወይም በአጠቃላይ ከህይወታችሁ ጋር ሊዛመዱ ይችላሉ። እነዚህን ጥያቄዎች አሰላስሉ እንዲሁም ቅዱሳት መጻህፍትን ማጥናታችሁን ስትቀጥሉ መልሶቹን ፈልጉ።
የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት መርጃን ተጠቀሙ
በምታነቧቸው ጥቅሶች ላይ ተጨማሪ ግንዛቤዎችን ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹን፣ የአርዕስት መመሪያን፣ የመፅሐፍ ቅዱስ መዝገበ-ቃላትን፣ የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ እንዲሁም ሌሎች የጥናት እርዳታዎችን ተጠቀሙ።
የቅዱሳት መጻህፍትን አገባብ ከግምት ውስጥ አስገቡ
የአንድን የቅዱሳት መፃህፍት ምንባብ አገባብ እንዲሁም ሁኔታዎች ወይም የመጣበትን ጊዜና ቦታ ግምት ውስጥ ስታስገቡ ትርጉም ያላቸው ግንዛቤዎችን ማግኘት ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ እግዚአብሔር ያነጋግራቸውን ሰዎች የጀርባ ታሪክ እና እምነቶች ማወቅ እርሱ ምን ሊናገር እንደፈለገ በተሻለ ለመገንዘብ ይረዳችኋል። ስለእነርሱ በቅዱሳን፣ በራዕይ በአገባብ፣ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች የክፍል ርዕሶች ላይ እና በሌሎች ፅሁፎች ውስጥ ልትማሩ ትችላላችሁ።
የኋለኛው ቀን ነቢያትን እና ሐዋርያትን ቃል አጥኑ
የኋለኛው ቀን ነቢያት እና ሐዋርያት በቅዱሳት መጻህፍት ላይ ስለምታገኟቸው መርሆዎች ምን እንዳስተማሩ አንብቡ።
በተማራችሁት መሠረት ኑሩ
የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት እኛን በመንፈስ ማነሳሳት ብቻ ሳይሆን የምንኖርበትን መንገድ እንድንቀይር ሊያደርገን ይገባል። በምታነቡበት ጊዜ መንፈስ እንድታደርጉ የሚያነሳሳችሁን አድምጡ፣ ከዚያም በእነዚያ ማነሳሻዎች ላይ እርምጃ ውሰዱ።
ሙዚቃን ተጠቀሙ
በመላው ኑ፤ ተከተሉኝ ውስጥ የሚመከሩ መዝሙሮች እና የልጆች መዝሙሮች ይገኛሉ። መንፈስን ለመጋበዝ እንዲሁም እምነታችሁን እና የወንጌል እውነቶች ምስክርነታችሁን ጥልቅ ለማድረግ የተቀደሰ ሙዚቃን ተጠቀሙ።
የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችን በአዕምሯችሁ በመያዝ አስታውሱ
ለእናንተ፣ ለቤተሰባችሁ ወይም ለክፍላችሁ ትርጉም ያለው የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብን ምረጡ፣ ከዚያም በየዕለቱ በመደጋገም ወይም የማስታወስ ጨዋታ በመጫወት በአዕምሮአችሁ ያዙ።
ተግባራዊ ምሳሌ የሆኑ ትምህርቶችን በመጠቀም አጋሩ
ከምታነቧቸው ምዕራፎች እና ጥቅሶች ጋር የሚዛመዱ ነገሮችን ፈልጉ። እያንዳንዱ ነገር በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ካሉት ትምህርቶች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አስቡ።
ስዕል ሳሉ፣ ፈልጉ ወይንም ፎቶ አንሱ።
ጥቂት ጥቅሶችን አንብቡ፣ ከዚያም ካነበባችሁት ነገር ጋር የሚዛመድ አንድ ነገር ሳሉ። ወይንም በየወንጌል የአርት መፅሐፍ ወይንም በወንጌል ላይብረሪ በሌላ ቦታ ሥዕሎችን ልትፈልጉ ትችላላችሁ። የተማራችሁትን ነገር የሚገልፅ አንድ ፎቶ ማንሳትም ትችላላችሁ።
ታሪኩን በድራማ መልክ አቅርቡ
አንድ ታሪክ ካነበባችሁ በኋላ የቤተሰብ ወይንም የክፍል አባላት እንዲተውኑት ጋብዟቸው። ከዚያ በኋላ ታሪኩ እያለፋችሁባቸው ካሉት ተሞክሮዎቻችሁ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ተነጋገሩ።
በቤታችሁ ውስጥ ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ራሳችሁን ማስማማት የምትችሉ ሁኑ
በቤተሰብ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑ የቤተሰብ አባላት ካሏችሁ፣ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ሌሎች መንገዶችን ፈልጉ። ለምሳሌ፣ በተለመዱ ንግግሮቻችሁ ውስጥ ዘለዓለማዊ እውነትን ለማጋራት ወይም ስብከት ወይም ከመጠን በላይ በማይመስል መንገድ ትርጉም ያለው የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅስን ማጋራት ትችላላችሁን? የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ አንድ አይነት መምሰል የለበትም። አንዳንድ ልጆች ቅዱሳት መጻህፍትን አንድ ለአንድ ሲያጠኑ የተሻለ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። ጸልዩ እንዲሁም የመንፈስን ምሪት ተከተሉ።