አዲስ ኪዳን 2023 (እ.አ.አ)
መጋቢት 6–12 (እ.አ.አ)። ማቴዎስ 9–10፣ ማርቆስ 5፤ ሉቃስ 9፦ “እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው”


“መጋቢት 6–12 (እ.አ.አ)። ማቴዎስ 9–10፣ ማርቆስ 5፤ ሉቃስ 9፤ ‘እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው’” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፦ አዲስ ኪዳን 2023 (እ.አ.አ) [2022 (እ.አ.አ)]

“መጋቢት 6–12 (እ.አ.አ)። ማቴዎስ 9–10፣ ማርቆስ 5፤ ሉቃስ 9፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፦ 2023 (እ.አ.አ)

ምስል
ኢየሱስ ጴጥሮስን ሲሾም

መጋቢት 6–12 (እ.አ.አ)

ማቴዎስ 9–10ማርቆስ 5ሉቃስ 9

“እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው”

በዚህ የመማርያ ረቂቅ ውስጥ ያሉ የመማርያ ሃሳቦች በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ግላዊ ትርጉም እንድታገኙ እንዲረዷችሁ ነው። ሆኖም ግን የትኛውን ምዕራፍ እና እንዴት ማጥናት እንዳለባችሁ የምትቀበሉትን ግላዊ መገለጥን መተካት የለባቸውም።

ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ

የክርስቶስ የፈውስ ተአምራት ወሬ በፍጥነት እየተዛመተ ነበር። ከህመሞቻቸው ፈውስን ለማግኘት በተስፋ ብዙዎች ተከተሉት። ነገር ግን አዳኙ ህዝቡን ሲመለከት ከአካላዊ ህመማቸው በላይ ነበር ያየው። በሃዘን ተሞልቶ “እረኛ [የሌላቸውን] በጎች” (ማቴዎስ 9፥36) አየ። “መከሩ ብዙ … ሠራተኞች ግን ጥቂቶች [እንደሆኑ]”(ማቴዎስ 9፥37) ተመለከተ። ስለዚህ አስራ ሁለት ሐዋርያትን ጠራ፥ “ሥልጣን ሰጣቸው፣” እንዲያስተምሩ እና እንዲያገለግሉ “የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች” (ማቴዎስ 10፥1፣ 6) ላካቸው። ዛሬም የሰማይ አባት ልጆችን ለማገልገል የሚያስፈልጉ ሰራተኞች ብዙ ናቸው። አሁንም አስራ ሁለት ሐዋርያት አሉ፣ ነገር ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” (ማቴዎስ 10፥7) ብለው ለሁሉም ሰዎች የሚያውጁ ብዙ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት አሉ።

ምስል
የግል ጥናት ምልክት

ለግል የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ሃሳቦች

ማቴዎስ 9፥18–26ማርቆስ 5፥22–43

“እመን ብቻ እንጂ አትፍራ”

መጀመርያ ኢያኢሮስ “ልትሞት [የቀረበችውን]” ልጁን ኢየሱስ እንዲፈውስለት ሲጠይቅ በችኮላ ነገር ግን ተስፋ በመሞላት “በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት ተናገረ (ማርቆስ 5፥23)። ነገር ግን እየሄዱ ሳለ መልዕክተኛ “ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ?” (ቁጥር 35) በማለት እንደረፈደ ነገረው። በተመሳሳይ ሁኔታ በማርቆስ 5፥25–34 ላይ 12 አመት ለታመመችው ሴት በጣም የረፈደ ሊመስል ይችላል።

እነዚህን ቁጥሮች ስታነቡ በእናንተ ወይም በቤተሰባችሁ ፈውስ ስለሚያስፈልጋቸው ነገሮች ልታስቡ ትችላላችሁ—“[ሊሞት የቀረበ]” ወይም ለፈውስ እጅግ የዘገየ ነገርን ጨምሮ። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ስላሉ የእምነት አገላለጾች የሚያስደንቃችሁ ምንድነው? ኢየሱስ ለሴቲቷ እና ለኢያኢሮስ የሚለውን ልብ በሉ። ለእናንተ ምን እያለ እንደሆነ ይሰማችኋል?

በተጨማሪም ሉቃስ 8፥41–56፤ ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይል ወደ ህይወታችን ማምጣት፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2017 (እ.አ.አ) 39–42፤ የቤተክርስቲያኗ ፕሬዝዳንቶች ትምህርቶች፤ ጎርደን ቢ. ሂንክሊይ (2016 (እ.አ.አ))፥ 333–42ን ተመልከቱ።

ምስል
አንዲት ሴት የኢየሱስን ልብስ ለመዳሰስ እየዘረጋች

በጌታ እመኑ፣ በሊዝ ሌመን ስዊንድል

ማቴዎስ 10ሉቃስ 9፥1–6

ጌታ የእርሱን ስራ እንዲሰሩ ለአገልጋዮቹ ሃይልን ይሰጣል።

ማቴዎስ 10 ላይ ኢየሱስ ለሐዋርያት የሰጠው ትዕዛዝ ለእኛም ይሰራል፣ ምክንያቱም ሁላችንም በጌታ ስራ ድርሻ ስላለን ነው። ሐዋርያት ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ እንዲረዳቸው ክርስቶስ ምን ሃይል ሰጣቸው? እንድትሰሩ በተጠራችሁበት ስራ ላይ ሃይሉን እንዴት ማግኘት ትችላላችሁ? (2 ቆሮንቶስ 6፥1–10ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥34–46ን ተመልከቱ)።

ክርስቶስ ለሐዋርያት ስለሰጠው ስራ ስታነቡ ጌታ እንድትሰሩ ስለሚፈልገው ነገር ሊሰማችሁ ይችላል። እንደሚከተለው አይነት ካርታ ሃሳባችሁን እንድታቀናጁ ሊረዳችሁ ይችላል፦

ማቴዎስ 10

የሚሰማኝ ነገር

አዳኙ ለደቀመዛሙርቱ ኃይልን ሰጣቸው።

እግዚአብሔር ስራዬን እንድሰራ ሃይልን ይሰጠኛል።

በተጨማሪም ማርቆስ 6፥7–13የእምነት አንቀጽ 1፥6፤ የመጽሃፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ “ሃዋርያ”፤ “ኢየሱስ አስራ ሁለት ሐዋርያት እንዲሰብኩ እና ሌሎችን እንዲባርኩ ጠራቸው” (ቪድዮ)፣ ChurchofJesusChrist.orgን ተመልከቱ።

ማቴዎስ 10፥17–20

በጌታ ስራ ውስጥ ስሆን ምን መናገር እንዳለብኝ ያሳውቀኛል።

ጌታ የእርሱ ደቀመዛሙርት እንደሚያሳድዷቸው እና ስለ እምነታቸው እንደሚጠየቁ አስቀድሞ አይቶ ነበር—ደቀመዛሙርት አሁን ላይ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አይነት ማለት ነው። ነገር ግን ለደቀመዛሙርቱ በመንፈስ አማካኝነት ምን ማለት እንዳለባቸው እንደሚያውቁ ቃል ገባላቸው። ምናልባት ምስክርነታችሁን ስታካፍሉ፣ በረከት ስትሰጡ፣ ወይም ከሆነ ሰው ጋር ስትነጋገሩ በህይወታችሁ ይህ መለኮታዊ ቃል ኪዳን የተፈጸመበት አጋጣሚ ኖሮ ያውቃልን? እነዚህንም አጋጣሚዎች ለምትወዱት ሰው አካፍሉ ወይም በጥናት ደብተራችሁ ውስጥ መፃፍን ያስቡ። እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ይበልጥ እንዲኖራችሁ ምን ለማድረግ ተነሳሽነት ይሰማችኋል?

በተጨማሪም ሉቃስ 12፥11–12ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥85ን ይመልከቱ።

ማቴዎስ 10፥34–39

ኢየሱስ “ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም” ሲል ምን ለማለቱ ነው?

ሽማግሌ ዲ. ቶድ ክርስቶፈርሰን “ብዙዎቻችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ስትቀበሉ እና ወደ እርሱ የቃል ኪዳን መንገድ ስትገቡ በአባት እና እናት፣ በወንድሞች እና እህቶች እንደተጠላችሁ እና እንደተገለላችሁ እርግጠኛ ነኝ። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለክርስቶስ ያላችሁ ከፍ ያለ ፍቅር ለእናንተ ውድ የሆኑ ግንኙነቶችን መስዋዕት እንድታደርጉ አድርጓችኋል፣ ብዙም እንባ አፍስሳችኋል። ይህም ሆኖ ፍቅራችሁ ሳይቀንስ በእግዚአብሔር ልጅ እንደማታፍሩ እያሳያችሁ በመስቀሉ ስር ቆይታችኋል” (“ህይወታችሁን ማግኘት፣” ኢንዛይን፣ መጋቢት 2016 (እ.አ.አ)፣ 28)።

አዳኙን ለመከተል ስትሉ የምትወዱትን ግንኙነቶችን ለመተው ፈቃደኛ መሆናችሁ “ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል” (ማቴዎስ 10፥39) ከሚል ቃል ኪዳን ጋር ይመጣል።

ምስል
የቤተሰብ ጥናት ምልክት

ለቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናትና ለቤተሰብ የቤት ምሽት ሃሳቦች

ማርቆስ 5፥22–43ቤተሰባችሁ ይህን ታሪክ በአንድነት ሲታነብቡ፣ ምንባብን በማቆም በማለት የቤተሰባችሁ አባላት በኢያኢሮስ፣ በሴቲቷ ወይም በታሪኩ ላይ ያሉ ሌሎች ሰዎች ቦታ ላይ ቢሆኑ ምን እንደሚሰማቸው ጠይቋቸው። ስለዚህ ታሪክ በዚህ ረቂቅ ላይ እንዳሉት አይነት ፎቶዎች ማሳየትም ትችላላችሁ። እነዚህ ፎቶዎች በታሪኩ ላይ ያሉ ሰዎችን እምነት እንዴት ነው የሚያሳዩት? (በተጨማሪ ም “ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ አስነሳ” እና “ኢየሱስ እምነት ያላትን ሴት ፈወሰ” የሚል ር እስ ያላቸውን ቪድዮዎች በChurchofJesusChrist.org ላይ ማየት ትችላላችሁ።) በተጨማሪም ቤተሰባችሁ የሚገጥመውን አንዳንድ ፈተናዎች ማሰብ ትችላላችሁ። “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” የሚለውን ቃል እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን? (ማርቆስ 5፥36)።

ማቴዎስ 10፥39ሉቃስ 9፥23–26 ህይወታችንን “[ማጣት]” እና “[ማግኘት]” ምን ማለት ሊሆን ይችላል? (ማቴዎስ 10፥39)። ምናልባት የቤተሰብ አባላት በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ያለውን የኢየሱስ አስተምሮት የሚያሳዩ ልምዶችን ሊያካፍሉ ይችላሉ።

ማቴዎስ 10፥40የአሁን ጊዜ ነቢያትን ምክር መከተል ላይ እናንተ እና ቤተሰባችሁ እንዴት ናችሁ? ለእነሱ ምክር ታዛዥነታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያቀርበን እንዴት ነው?

ሉቃስ 9፥61–62ዕርፍን በእጅ ይዞ ወደ ኋላ መመልከት ምን ማለት ነው? ይህ ባህርይ ለእግዚአብሔር መንግስት ተገቢ ያልሆንን የሚያደርገን ለምንድነው?

ልጆችን ለማስተማር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ሳምንት ዝርዝርኑ፣ ተከተሉኝ—ለመጀመሪያ ክፍልን ይመልከቱ።

በሃሳብ የሚቀርብ መዝሙር፦ “እምነት ሲጸና፣” መዝሙሮች፣ ቁጥር 128

የግል ጥናትን ማሻሻል

መንፈሱን አድምጡ በምታነቡበት ጊዜ ከምታነቡት ጋር የማይዛመዱ ቢመስሉም ለሀሳባችሁ እና ለስሜታችሁ ትኩረት ስጡ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 8፥2–3ን ተመልከቱ)። ምናልባት እነዚያ ግንዛቤዎች ራሳቸው እግዚአብሔር እንድትማሩ የፈለጋቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

ምስል
ኢየሱስ ሴት ልጅን ከአልጋ ላይ እያስነሳት

ጣሊታ ቁሚ፣ በኤቫ ኮሌቫ ቲሞቲይ

አትም