መመሪያ መጻህፍቶች እና ጥሪዎች
0.የመግቢያ አጠቃላይ አይታ


“0. የመግቢያ አጠቃላይ አይታ፣” ከአጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ [2023 (እ.አ.አ)]።

“0. የመግቢያ አጠቃላይ አይታ፣” ከአጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ

0.

የመግቢያ አጠቃላይ አይታ

0.0

መግቢያ

ጌታ “እያንዳንዱም ሰው ተግባሩን፣ በተመደበበት ሀላፊነትም በሙሉ ትጋት መስራትን ይማር” ሲል አስተምሯል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 107፥99)። በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ መሪ እንደመሆናችሁ መጠን የጥሪያችሁን ሀላፊነቶች ለማወቅ እና ለመፈጸም እንዲረዳችሁ የግል መገለጥ መሻት አለባችሁ።

ቅዱሳት መጻህፍትን እና የኋለኛው ቀን ነቢያትን ቃል ማጥናት ሀላፊነቶቻችሁን ለማወቅ እና ለመፈጸም ይረዷችኋል። የእግዚአብሔርን ቃል ስታጠኑ፣ የመንፈሱ ተጽእኖ የበለጠ የሚሰማችሁ ትሆናላችሁ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥85)።

በዚህ መመሪያ መጽሃፍ ውስጥ የተቀመጡትን መመሪያዎች በማጥናትም ሃላፊነቶቻችሁን ማወቅ ትችላላችሁ። እነዚህ መመሪያዎች የመንፈስን ምሪት በምንሻበት ጊዜ በተግባር ላይ የምናውላቸውን መርሆዎች፣ ፖሊሲዎች እና ሂደቶች ለመረዳት ጥቅም ላይ ከዋሉ መገለጥን መቀበልን ቀላል ሊያደርጉ ይችላሉ።

0.1

መመሪያ መፅሐፍ

General Handbook: Serving in The Church of Jesus Christ of Latter-day Saints [አጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ፦ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል] የሚል ርዕስ ያለው መመሪያ መፅሀፍ ለአጠቃላይ እና ለዋና አካባቢ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች መመሪያ ይሰጣል።

በዚህ የመመሪያ መፅሐፍ ውስጥ ያሉትን ርዕሰ ጉዳዮችን በቀላሉ ለማግኘት እና ለመጥቀስ ይቻል ዘንድ ርዕሶች እና ንዑስ ርዕሶች ቁጥር ተሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ፣ ማን በቤተመቅደስ መታተም እንደሚችል የሚመለከት መመሪያ በ27.3.1 ውስጥ ቀርቧል። 27 ቁጥር ምዕራፉን ሲያመለክት3 ቁጥር በዚያ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኝበትን ክፍል ያመለክታል፣ እንዲሁም 1 ቁጥር በዚያ ክፍል ውስጥ የሚገኝበትን ንዑስ ክፍል ያመለክታል።

0.2

ማስተካከያ እና አማራጭ መረጃዎች

ሁሉም ካስማዎች እና አጥቢያዎች አንድ ዓይነት ፍላጎቶች የሏቸውም።

መሪዎች የአባላትን ፍላጎት ለማሟላት የትኞቹን መመሪያዎች እና አማራጭ መረጃዎች መጠቀም እንዳለባቸው ለማወቅ የመንፈስን ማነሳሳት ይፈልጋሉ።

0.4

ስለመመሪያዎች የሚነሱ ጥያቄዎች

በቅዱሳት መጻህፍት፣ በህይወት ባሉ ነቢያት ቃል ወይም በዚህ የመመሪያ መጽሀፍ ውስጥ ያልተዳሰሱ ጥያቄዎች ሲነሱ፣ የቤተክርስቲያኗ አባላት ከእግዚአብሔር ጋር በገቧቸው ቃል ኪዳኖች፣ በአጥቢያ መሪዎቻቸው ምክር እና በመንፈስ መነሳሳት ላይ መደገፍ አለባቸው።

መሪዎች በዚህ የመመሪያ መጽሃፍ ውስጥ ስለሚገኝ መረጃ ወይም እርሱ ስለማያነሳቸው ጉዳዮች ጥያቄዎች ካሏቸው በበላይነት ከሚመራው የቅርብ ባለስልጣን ጋር ይመክራሉ።

0.5

ቃላት

በሌላ መልኩ ካልተገለጸ በስተቀር፦

  • በዚህ የመመሪያ መፅሐፍ ውስጥ ኤጲስ ቆጶስ እና የኤጲስ ቆጶስ አመራር የሚሉት ቃላት በተጨማሪም የቅርንጫፍ ፕሬዚዳንቶችን እና የቅርንጫፍ አመራሮችን ያመለክታሉ፡፡ የካስማ ፕሬዚዳንት እና የካስማ አመራር የሚሉት ቃላት በተጨማሪም የአውራጃ ፕሬዚዳንቶችን እና የአውራጃ አመራሮችን ያመለክታሉ፡፡ የአውራጃ ፕሬዚዳንቶች ስልጣን እና ከካስማ ፕሬዚዳንቶች ስልጣን እንዴት እንደሚለይ ማጠቃለያ ለማግኘት፣ 6.3 ይመልከቱ።

  • በአጠቃላይ አጥቢያዎችን እና ካስማዎችን የሚያመለክቱት ቅርንጫፎችን፣ አውራጃዎችን እና ሚስዮኖችንም ያመለከታሉ።

  • እሁድ በየአካባቢው የሰንበት ቀን የሚከበርበትን የትኛውንም ቀን ያመለክታል።

  • ክፍል የሚለው ቃል አጥቢያ እና ቅርንጫፍንም ያመለክታል።

  • በአጠቃላይ ወላጆችን የሚያመለክቱት ህጋዊ አሳዳጊዎችንም ያመለከታሉ።

የኤጲስ ቆጶስ እና የቅርንጫፍ ፕሬዚዳንት ጥሪዎች በሥልጣን እና በኃላፊነቶች እኩል አይደሉም፤ የካስማ ፕሬዚደንት እና የአውራጃ ፕሬዚዳንት ጥሪዎችም እንዲሁ እኩል አይደሉም። ኤጲስ ቆጶስ በክህነት ውስጥ ያለ አንድ ክፍል ሲሆን ሹመቱ የሚፈቀደውም በቀዳሚ አመራር ብቻ ነው። የካስማ ፕሬዚዳንቶች የሚጠሩት በአጠቃላይ ባለሥልጣናት እና በአካባቢ ሰባዎች ነው።

0.6

የቤተክርስቲያኗ ዋና መስሪያ ቤትን ወይም የዋና አካባቢ ቢሮን ማነጋገር

በዚህ መመሪያ መጽሃፍ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ምዕራፎች ከቤተክርስቲያኗ ዋና መሥሪያ ቤት ወይም ከዋና አካባቢ ቢሮው ጋር ግንኙነት ስለማድረግ የሚመለከቱ መመሪያዎችን ያካትታሉ። ከቤተክርስቲያኗ ዋና መሥሪያ ቤት ጋር ግንኙነት ስለማድረግ የሚመለከቱ መመሪያዎች ተግባራዊ የሚሆኑት በዩናይትድ ስቴትስ እና በካናዳ ብቻ ነው። ከዋና አካባቢ ቢሮው ጋር ግንኙነት ስለማድረግ የሚመለከቱ መመሪያዎች ተግባራዊ የሚሆኑት ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከካናዳ ውጪ ላሉት ነው።