ምዕራፍ ፲፬
የህዝቡ ክፋት በምድሪቱ ላይ እርግማን ያመጣል—ቆሪያንተመር ከጊልአድ፣ ከዚያም ከሊብ፣ እናም ቀጥሎ ከሺዝ ጋር ጦርነትን አደረገ—ደም እና እልቂት ምድሪቱን ሸፈነ።
፩ እናም እንግዲህ በህዝቡም ክፋት የተነሳ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ታላቅ እርግማን ሆነ፤ በዚህም አንድ ሰው መሳሪያውን ወይንም ጎራዴውን በራሱ መደርደሪያ ካስቀመጠ፣ ወይንም ማስቀመጥ በሚችልበት ስፍራ ካደረገ፣ እነሆ፣ በሚቀጥለው ቀን አያገኘውም፣ ስለዚህ እርግማኑ በምድሪቱ ላይ ታላቅ ሆኗልና።
፪ ስለዚህ እያንዳንዱ የራሱ የሆነውን በእጁ አጥብቆ ይይዛል፣ እናም ለሌላ አያበድርም እንዲሁም ከሌላም አይበደርም፤ እናም እያንዳንዱ ሰው ንብረቱን፣ እናም ህይወቱን፣ እናም የሚስቱን እናም የልጁን ህይወት ለመጠበቅ የጎራዴውን እጀታ በቀኝ እጁ ይይዛል።
፫ እናም እንግዲህ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ እናም ሻረድ ከሞተም በኋላ፣ እነሆ፣ የሻረድ ወንድም ተነሳ፣ እናም ከቆሪያንተመር ጋር ተዋጋ፣ በዚህም ቆሪያንተመርም አሸነፈው እናም ወደ አኪሽ ምድረበዳም አሳደደው።
፬ እናም እንዲህ ሆነ የሻረድ ወንድም በአኪሽ ምድረበዳ ውስጥ ከእርሱ ጋር ተዋጋ፤ እናም ጦርነቱም እጅግ የከፋ ነበር፣ እናም ብዙ ሺዎችም በጎራዴው ወደቁ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር ምድረበዳውን ከበበ፤ እናም የሻረድ ወንድም በምሽት ከምድረበዳው ሄደ እናም የሰከሩትን የቆሪያንተመርን ወታደሮች በከፊል ገደሉአቸው።
፮ እናም ወደ ሞሮን ምድር ሔደ፣ እናም እራሱን በቆሪያንተመር ዙፋን አስቀመጠ።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር ለሁለት ዓመታት ከወታደሮቹ ጋር በምድረበዳው ኖረ፤ በዚያም ሥፍራ ለወታደሮቹ ጥንካሬ ተቀበለ።
፰ እንግዲህ የሻረድ ወንድም ጊልአድ የሚባለው ደግሞ በሚስጢራዊ ሴራዎች የተነሳ ለሠራዊቱ ብርታትን አገኘ።
፱ እናም እንዲህ ሆነ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ሳለ ሊቀ ካህኑ ገደለው።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ከሚስጢራዊ ሴራዎች አንዱ በሚስጢራዊው መተላለፊያ ቦታ ውስጥ ገደለው፣ እናም መንግስቱን ለራሱ አደረገ፤ እናም ስሙም ሊብ ይባል ነበር፤ እናም ሊብም ከህዝቡ ሁሉ ሰዎች መካከል በላይ ጠንካራ አቋም የነበረው ሰው ነበር።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ በሊብ የመጀመሪያ ዓመት፣ ቆሪያንተመር ወደ ሞሮን ምድር መጣ፣ እናም ከሊብ ጋር ተዋጋ።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ከሊብም ጋር ተዋጋ፤ ሊብም በእጁ ላይ መትቶ አቆሰለው፤ ይሁን እንጂ፣ የቆሪያንተመር ሠራዊቶች ሊብን ገፉት፣ እርሱም በባህሩ ዳርቻ ወደ ወሰኑ ሸሸ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር ተከተለው፤ እናም ሊብም በባህሩ ዳርቻ ከእርሱ ጋር ተዋጋ።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ሊብ የቆሪያንተመርን ወታደሮች መታቸው፣ እነርሱም በድጋሚ ወደ አኪሽ ምድረበዳ ሸሹ።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እርሱ ወደ አጎሽ መስክ እስከሚመጣ ድረስ ሊብ ተከተለው። እናም ቆሪያንተመር ከሊብ በፊት ሲሸሽም በምድሯ በዚያ ክፍል የነበሩትን ህዝቦች በሙሉ ይዞ ሄዶ ነበር።
፲፮ እናም ወደ አጎሽ መስክ በመጣም ጊዜ ከሊብ ጋር ተዋጋ፣ እናም እስከሚሞት ድረስም መታው፤ ይሁን እንጂ፣ የሊብ ወንድም በቆሪያንተመር ላይ በምትኩ መጣበት፣ እናም ጦርነቱም እጅግ የከፋ ሆነ፤ በዚህም ቆሪያንተመር በድጋሚ ከሊብ ወንድም ሠራዊት ፊት ሸሸ።
፲፯ እናም የሊብ ወንድም ስሙ ሺዝ ይባል ነበር። እናም እንዲህ ሆነ ሺዝ ቆሪያንተመርን አሳደደው፣ እናም ብዙ ከተሞችንም ድል አደረገ፣ እናም ሴቶችን እና ልጆችን ገደለ፣ እና ከተሞችንም አቃጠለ።
፲፰ እናም በምድሪቱ ሁሉ ላይ ሺዝ ተፈራ፤ አዎን፣ በምድሪቱ ሁሉ ጩኸት ሆነ—የሺዝን ሠራዊት ማን ሊቋቋም ይቻለዋል? እነሆ፣ የምድሪቱ ገፅ በፊቱ ጠረጋት!
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ሁሉ ላይም ህዝቡ ከሠራዊቱ ጋር በአንድነት ተሰባሰበ።
፳ እናም እነርሱም የተከፋፈሉ ነበሩ፤ እናም ግማሹ ወደ ሺዝ ወታደሮች ሸሹ፤ ግማሹ ወደ ቆሪያንተመር ወታደሮች ሸሹ።
፳፩ እናም ጦርነቱ እጅግ ታላቅ እና ረጅም ስለነበር፣ እናም ደም መፋሰሱ እና እልቂቱ እይታም እጅግ ለረጅም ጊዜ ስለነበር፣ ምድሪቱም ገጽታዋ በሙሉ በሙታን ተሸፍኖ ነበር።
፳፪ እናም ፈጣን ጦርነት ስለነበር ሙታንን ለመቅበር የቀረ ማንም አልነበረም፣ ነገር ግን የወንዶችን፣ የሴቶችን፣ እና የልጆችን ሙታኖቻቸውን በምድር ገፅ ላይ እንደተዘረጉ፣ ለስጋ ትል ምግብ እንዲሆኑ በመተው ከደም ማፋሰስ ወደ ደም ማፋሰስ ዘመቱ።
፳፫ እናም የዚህ ሽታም በምድሪቱ ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድሩ ገጽ ላይ ሁሉ ሆነ፤ ስለዚህ ህዝቡ በሽታው ምክንያት በምሽት ሆነ እንዲሁም በቀን ተቸግረው ነበር።
፳፬ ይሁን እንጂ፣ ሺዝ ቆሪያንተመርን ማሳደዱን አልተወም፤ የተገደለውን የወንድሙን ደም በቆሪያንተመር ላይ ለመበቀል፣ እናም ጌታ ቆሪያንተመር በጎራዴ እንደማይሞት ለኤተር ነግሮት በነበረው ቃል ላይ ለመበቀል፣ በመሃላ እራሱን አነሳስቶ ነበርና።
፳፭ እናም በቁጣው ሙላት ጌታ እንደጎበኛቸው፣ እናም ክፋቶቻቸው እና እርኩሰቶቻቸው ለዘላለማዊው ጥፋታቸው መንገድ እንዳዘጋጁ እንመለከታለን።
፳፮ እናም እንዲህ ሆነ ሺዝ ቆሪያንተመርን በስተምስራቅ በኩል እስከባህሩ ዳርቻ ወሰን አሳደደው፣ እናም ለሦስት ቀናትም ከሺዝ ጋር ተዋጋ።
፳፯ እናም በሺዝ ወታደሮች መካከል ጥፋቱ አሰቃቂ ስለነበር ህዝቡ መፍራት ጀመሩ፣ እናም ከቆሪያንተመር ወታደሮች ፊት መሸሽ ጀመሩ፤ እናም ወደ ቆሪሆር ምድር ሸሹ፣ እናም በፊታቸው የነበሩትን ነዋሪዎች ከእነርሱ ጋር ያልተቀላቀሉትን በሙሉ ጠረጉአቸው።
፳፰ እናም በቆሪሆር ሸለቆ ውስጥ ድንኳናቸውን ተከሉ፤ እናም ቆሪያንተመርም ድንኳኑን በሹር ሸለቆ ተከለ። እንግዲህ የሹር ሸለቆ ከቆምኖር ኮረብታ አጠገብ ነበር፤ ስለዚህ፣ ቆሪያንተመር ወታደሮቹን በቆምኖር ኮረብታ ላይ በአንድነት ሰበሰባቸው፣ እናም የሺዝን ወታደሮች ለጦርነት ለመጋበዝ መለከትን ነፋ።
፳፱ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም መጡ፣ ነገር ግን በድጋሚ ወደ ኋላ አባረሩአቸው፤ እናም ለሁለተኛ ጊዜ መጡ፤ እናም ለሁለተኛ ጊዜም ተባረሩ። እናም እንዲህ ሆነ ለሦስተኛ ጊዜ በድጋሚ መጡ፤ እናም ጦርነቱም እጅግ የከፋ ሆነ።
፴ እናም እንዲህ ሆነ ሺዝም ቆሪያንተመርን መትቶ በበርካታ ቦታዎች ላይ አቆሰለው፤ እናም ቆሪያንተመር ደም ስለፈሰሰው እራሱን ሳተ፣ እናም የሞተም ይመስል ስለነበር በሽከማ ተወሰደ።
፴፩ እንግዲህ በሁለቱም በኩል የሞቱት ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ብዙ ስለነበሩ፣ ሺዝ ወታደሮቹ የቆሪያንተመርን ወታደሮች እንዳያባርሩአቸው አዘዘ፤ ስለዚህ እነርሱም ወደ ጦር ሰፈራቸው ተመለሱ።