ምዕራፍ ፪
የሔለማን ልጅ፣ ሔለማን፣ ዋና ዳኛ ሆነ—ጋድያንቶን የቂሽቁመንን ቡድን መራ—የሔለማን አገልጋይ ቂሽቁመንን ገደለው፣ እናም የጋድያንቶን ቡድን ወደ ምድረበዳው ሸሹ። ከ፶–፵፱ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ አርባ ሁለተኛ ዓመት የንግስ ዘመን ሞሮኒሀ በድጋሚ በኔፋውያን እና በላማናውያን መካከል ሰላምን ከመሰረተ በኋላ፣ እነሆ የፍርድ ወንበሩን ስፍራ የሚይዝ ማንም አልነበረም፤ ስለዚህ በህዝቡ መካከል የፍርድ ወንበሩን ማን ይያዘው በሚል ፀብ ተጀመረ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ የሔለማን ልጅ የነበረው፣ ሔለማን በህዝቡ ድምፅ የፍርድ ወንበሩን እንዲይዝ ተሾመ።
፫ ነገር ግን እነሆ፣ ፓሆራንን የገደለው ቂሽቁመን ደግሞም ሔለማንን ለማጥፋት አደፈጠ፤ እናም ኃጢአቱን ማንም እንዳያውቅበት ወደ ቃልኪዳኑ በገቡት ጓዶቹ ተደግፎ ነበር።
፬ በብዙ ቃላት እጅግ ባለሙያ የሆነ፣ እናም ደግሞ የግድያንና የዝርፊያን ድብቅ ስራ ለማከናወን ጥበብ የነበረው አንድ ጋድያንቶን የተባለ ነበር፤ ስለዚህ እርሱም የቂሽቁመን ቡድን መሪ ሆነ።
፭ ስለዚህ በፍርድ ወንበሩ ካስቀመጡት በቡድኑ ውስጥ ያሉትን አባላት በህዝቡ መካከል ኃይልና ስልጣን እንደሚሰጣቸውእነርሱን፣ እናም ደግሞ ቂሽቁመንንም ሸነገላቸው፣ ስለዚህ ቂሽቁመን ሔለማንን ለማጥፋት ፈለገ።
፮ እናም እንዲህ ሆነ ሔለማንን ለማጥፋት ወደ ፍርድ ወንበሩ በሚቀርብበት ጊዜ፣ እነሆ አንዱ የሔለማን አገልጋይ በምሽት ወጥቶ በድብቅ በዚህ ቡድን ሔለማንን ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ አውቆ እናም ስለአገኘው—
፯ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም ቂሽቁመንን አገኘውና ምልክት ሰጠው፤ ስለዚህ ሔለማንን ይገድለው ዘንድ የፍርድ ወንበሩን እንዲያሳየው በመፈለግ፣ ቂሽቁመን ዓላማውን ለእርሱ አሳወቃችው
፰ እናም የሔለማን አገልጋይ የቂሽቁመንን የልቡን ሀሳብና እንዴት ዓላማው ለግድያም እንደሆነ፣ እናም ደግሞ የእርሱ ቡድን አባሎች በሙሉ ለግድያና፣ ለዝርፊያና ስልጣንን ለማግኘት መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ (እናም ይህ ሚስጥራዊ ዕቅዳቸውና ህብረታቸው በመሆኑ) የሔለማን አገልጋይ ለቂሽቁመን እንዲህ አለው፥ ወደ ፍርድ ወንበሩ እንሂድ።
፱ እንግዲህ ይህ ቂሽቁመንን እጅግ አስደሰተው፤ ምክንያቱም ያቀደውን እፈፅማለሁ በማለት በመገመቱ ነበር፣ ነገር ግን እነሆ፣ የሔለማን አገልጋይ፣ ወደ ፍርድ ወንበሩ በሚሄዱበት ጊዜ፣ ቂሽቁመንን ልቡ ላይ ወጋው፣ እርሱም ሳያቃስት ወድቆ ሞተ። እናም አገልጋዩ ሮጠና፣ ለሔለማን የተመለከተውንና፣ የሰማውን፣ እናም ያደረገውን ነገሮች በሙሉ ነገረው።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ሔለማን እነዚህን የዘራፊ እናም የስውር ገዳዮች ቡድንን በህጉ መሰረት ተይዘው ይገደሉ ዘንድ ሰዎችን ላከ።
፲፩ ነገር ግን እነሆ፣ ጋድያንቶን ቂሽቁመን አለመመለሱን ባወቀ ጊዜ እጠፋለሁ በማለት ፈራ፤ ስለዚህ ቡድኖቹ እንዲከተሉት አደረገ። ከምድሪቱ በሚስጢር ወጥተው ወደ ምድረበዳ ሸሹ፤ እናም ከዚህ በኋላ ሔለማን እንዲያመጣቸው ሲላክ ከየትም መገኘት አልቻሉም።
፲፪ እናም ከዚህ በኋላ ስለጋድያንቶን ከዚህ በላይ ይነገራል። እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሳፍንቱ አገዛዝ አርባ ሁለተኛ ዓመት የንግስና ዘመን ተፈፀመ።
፲፫ እናም እነሆ፣ በዚህ መፅሐፍ መጨረሻ ይህ ጋድያንቶን የመሸነፍ አዎን፣ የኔፋውያን፣ ፍፁም መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ትመለከታላችሁ።
፲፬ እነሆ ይህን በመፅሐፈ ሔለማን መፈፀሚያ ውስጥ ነው ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን የፃፍኩትን ታሪክ በሙሉ ከወሰድኩበት ከኔፊ መፅሐፍ መጨረሻ ማለቴ ነው።