የሔለማን ልጅ የኔፊ ትንቢት—ለኃጢአታቸው ንስሃ ካልገቡ የኔፊን ህዝብ እግዚአብሔር ፍፁም ለማጥፋት በቁጣው እንደሚጎበኛቸው አስፈራራቸው። እግዚአብሔር የኔፊን ህዝብ በቸነፈር መታ፤ ንስሃ ገቡ እናም ወደ እርሱ ተመለሱ። ላማናዊው ሳሙኤል ለኔፋውያን ተነበየ።
ከምዕራፍ ፯ እስከ ፲፮ አጠቃሎ የያዘ።
ምዕራፍ ፯
ኔፊ በሰሜን ተቀባይነትን አላገኘም እናም ወደዛራሔምላ ተመለሰ—በአትክልቱ ስፍራ ግንብ ላይ ፀሎት አደረገ፣ እናም ለህዝቡ ንስሃ እንዲገቡ አለበለዚያም እንደሚጠፉ ተናገረ። ከ፳፫–፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እነሆ እንግዲህ እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ስልሳ ዘጠነኛ የንግስና ዘመን የሔለማን ልጅ ኔፊ፣ ከምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ወደ ዛራሔምላ ምድር ተመለሰ።
፪ በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ከነበሩት ሰዎች መካከል ነበር፣ እናም የእግዚአብሔርን ቃል ለእነርሱ እየሰበከ፣ እናም ብዙ ነገሮችን ለእነርሱ እየተነበየ ነበርና፤
፫ እናም ቃሉን ሁሉ አልተቀበሉትም ነበር፤ ስለዚህ ከእነርሱ ጋር መቆየት አልቻለም ነበር፤ ነገር ግን በድጋሚ ወደ ትውልድ ስፍራው ተመለሰ።
፬ እናም ህዝቡ በአሰቃቂው ኃጢያት መሆናቸውን እንዲሁም የጋድያንቶን ሌቦች የፍርድ ወንበሩን መያዛቸውን—በምድሪቱም ላይ ያለአግባብ ኃይልና ስልጣኑን በማግኘታቸው፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ወደጎን በመተዋቸው፣ እናም በፊቱም በትንሽም እንኳን መልካምን ባለማድረጋቸው፤ ለሰው ልጆችም በጻድቅ ባለመፍረዳቸው በመምልከት፤
፭ ፃድቃኖችንም ፃድቃን በመሆናቸው በመኮነን፤ ጥፋተኞችን፣ እንዲሁም ክፉዎችን በገንዘባቸው ያለቅጣት እንዲሄዱ በመፍቀዳቸው፤ እናም ከዚህ በተጨማሪ በስልጣን የበላይ በመሆን በመቀጠል እንዲገዙ እንደፍቃዳቸው ለመስራት ጥቅምንና የዓለም ክብርን ያገኙ ዘንድ፣ እናም ከዚህ በተጨማሪ፣ በቀላሉ ዝሙትን እንዲፈፅሙና፣ ይሰርቁና፣ ይገድሉ፣ እናም እንደፈቃዳቸው ይፈፅሙ ዘንድ በመፍቀዳቸው—
፮ እንግዲህ ብዛት በሌላቸው ጊዜአት ውስጥ ይህ ታላቅ ኃጢያት በኔፋውያን ላይ መጣ፤ እናም ኔፊ ይህንን በተመለከተ ጊዜ ልቡ በደረቱ ውስጥ በሀዘን ተሞልቶ ነበር፤ እናም በነፍሱም ስቃይ ተናገረ፥
፯ አቤቱ አባቴ ኔፊ ከኢየሩሳሌም ምድር ለመጀመሪያ በመጣ ጊዜ መኖር ብችል እመኝ ነበር፤ በቃል ኪዳኑም ምድር ከእርሱ ጋር ለመደሰት ይቻለኝ ነበር፤ የእርሱ ሰዎችን በቀላል ልመናን ያዳምጡ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅ ፅኑ፣ እናም ክፋትን ለመስራት የማይቸኩሉ ነበሩ፤ እናም የጌታን ቃላት ለማዳመጥ ፈጣኖች ነበሩ—
፰ አዎን፣ ቀናቶቼ በነዚያ ዘመናት ለመሆን ቢችሉ ኖሮ ነፍሴ በወንድሞቼ ፅድቅ ትደሰት ነበር።
፱ ነገር ግን እነሆ፣ እነዚህ የእኔ ቀናት እንዲሆኑ ተደርገዋል፣ እናም ነፍሴ በዚህ በወንድሞቼ ክፋት የተነሳ በሀዘን ትሞላለች።
፲ እናም እነሆ እንግዲህ እንዲህ ሆነ ይህም ወደ ዋናው ገበያ በሚያመራው አውራ ጎዳና፣ በዛራሔምላ ከተማ በነበረው በአትክልት ስፍራው ግንብ ላይ ነበር፤ ስለዚህ ኔፊ በአትክልት ስፍራው በሚገኘው ግንብ አጎንብሶ ነበር፣ ግንቡም ደግሞ ወደ አውራ ጎዳናው በሚያመራው በመግቢያ በር አጠገብ ነበር።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ አንዳንድ ሰዎች በሚያልፉበት ወቅት ኔፊ በግንቡ ላይ ሆኖ ነፍሱን ለእግዚአብሔር ሲያፈስ ተመለከቱ፤ እናም ሮጡና፣ ለህዝቡ ምን እንደተመለከቱ ተናገሩ፣ ህዝቡም በዚህ ህዝብ ክፋት ታላቅ የሆነው ሀዘኑን ምክንያት ያውቁ ዘንድ በአንድ ላይ በመሆን መጡ።
፲፪ እናም አሁን ኔፊ በተነሳበት ጊዜ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ተመለከተ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ አፉንም በመክፈት እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ እነሆ፣ ለምንድን ነው ራሳችሁን የሰበሰባችሁት? ስለክፋታችሁ እነግራችሁ ዘንድ ነው?
፲፬ አዎን በታላቅ ክፋታችሁም ምክንያት ልቤ እጅግ በማዘኑ፣ ለአምላኬ ነፍሴን አፈስ ዘንድ በግንቤ ላይ ቆሜአለሁ!
፲፭ እናም በሀዘኔ እንዲሁም በልቅሶዬም ምክንያት በአንድነት ተሰብስባችኋልና፣ ተደንቃችኋል፤ አዎን፣ እናም ለመደነቅ እጅግ ያስፈልጋችኋል፤ አዎን፣ መገረምን ይገባችኋል ምክንያቱም ዲያብሎስ በልባችሁ ታላቅ ስፍራን በመያዙ ራሳችሁን ሰጥታችሁታል።
፲፮ አዎን፣ ነፍሳችሁን ወደ ዘለዓለማዊው ስቃይ እንዲሁም መጨረሻ ወደ ሌለው ዋይታ እንዲወረውር ለሚፈልገው መንገድስ እንዴት አድርጋችሁ ትሰጡታላችሁ?
፲፯ አቤቱ ንስሃ ግቡ፣ ንስሃ ግቡ! ለምን ትሞታላችሁ? ወደ ጌታ አምላካችሁ ተመለሱ፣ ተመለሱ። ለምንስ እርሱ ይተዋችኋል?
፲፰ ይህም ምክንያቱ ልባችሁን ስላጠጠራችሁ ነው፣ አዎን የመልካሙን እረኛ ድምፅ አታዳምጡምም፤ አዎን በእናንተም ላይ እንዲቆጣ አነሳስታችሁታል።
፲፱ እናም እነሆ እናንተን ከመሰብሰብ፣ ንስሃን የማትገቡ ከሆነ እነሆ ለውሾች እንዲሁም ለዱር አውሬዎች ስጋ እስከምትሆኑ ድረስ እናንተን ይበትናችኋል።
፳ አቤቱ፣ እርሱ ባዳናችሁ በዚያው ቀን አምላካችሁን እንዴት ልትረሱት ቻላችሁ?
፳፩ ነገር ግን እነሆ፣ ይህ ጥቅምን ለማግኘት ነው፣ በሰዎችም ለመሞገስ፣ አዎን፣ እናም ወርቅና ብርንም ታገኙ ዘንድ ነው። እናም ልባችሁን በሀብት እንዲሁም በዚህ በዓለም ከንቱ ነገሮች ላይ አድርጋችኋል፤ ለዚህም ገድላችኋልም፣ ዘርፋችኋልም፣ ሰርቃችኋልም፣ እንዲሁም በጎረቤቶቻችሁ ላይ በሀሰት ምስክር ሆናችኋል፤ እናም ሁሉንም ዓይነት ክፋት ፈፅማችኋል።
፳፪ እናም በዚህም ምክንያት ንስሃ ካልገባችሁ ዋይታ በእናንተ ላይ ይመጣል። ንስሃ የማትገቡ ከሆነ፣ እነሆ፣ ይህች ታላቅ ከተማ፣ እናም በዙሪያው ያሉት፣ በእኛ የተያዙት እነዚያ ታላላቅ ከተሞች ሁሉ ይወሰዱባችኋል፣ በእነርሱም ሥፍራ አይኖራችሁም፤ እነሆም ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም ቀደም ሲል እንዳደረገው ጌታ ብርታትን አይሰጣችሁም።
፳፫ እነሆም ጌታ እንዲህ ይላል፥ ለኃጢአታቸው ንስሃ ከገቡት እናም ቃሌን ካዳመጡት በቀር ለሌሎች ከአንዱ ኃጢአት ይበልጥ ለሌላው ኃይሌን አላሳይም። ስለዚህ አሁን፣ ወንድሞቼ ንስሃ ካልገባችሁ፣ ከእናንተ ይልቅ ላማናውያን እንደሚሻልላቸው እንድታዩ እፈልጋለሁ።
፳፬ እነሆም፣ እናንተ በተቀበላችሁት ታላቅ እውቀት ላይ ኃጢያትን ባለመፈፀማቸው እነርሱ ከእናንተ የበለጠ ፃድቃን ናቸው፤ ስለዚህ ንስሃ ካልገባችሁ ፈፅሞም በምትጠፉበትም ጊዜ እንኳን ጌታ ለእነርሱ መሃሪ ይሆናል፤ አዎን ዘመናቸውን ያራዝማል፣ ዘራቸውንም ያበዛል።
፳፭ አዎን፣ በመካከላችሁ ባለው ታላቅ እርኩሰት የተነሳ ለእናንተ ወዮውላችሁ፤ እናም አዎን በጋድያንቶን በተቋቋመው ሚስጥራዊ ቡድን ራሳችሁን አንድ አድርጋችኋል!
፳፮ አዎን፣ እጅግ ሀብታም በመሆናችሁ፣ ከመልካሙም ባሻገር ከፍ እንዲያደርጋችሁ ወደ ልባችሁ እንዲገባ ባደረጋችሁት ኩራት የተነሳ ዋይታ በእናንተ ላይ ይመጣል!
፳፯ አዎን፣ በክፋታችሁ እንዲሁም በእርኩሰታችሁ የተነሳ ዋይታ ይሁንባችሁ!
፳፰ እናም ንስሃ ካልገባችሁ ትጠፋላችሁ፤ አዎን፣ ምድራችሁም ከእናንተ ትወሰዳለች፣ እናም ከምድረ ገፅ ትጠፋላችሁ።
፳፱ እነሆ አሁን፣ እነዚህን ነገሮች በራሴ ይሆናሉ አልልም፣ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች በራሴ አይደለም የማውቃቸው፤ ነገር ግን እነሆ ጌታ እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች እንዳውቅ ስላደረገኝ እውነት መሆናቸውን አውቃለሁ፣ ስለዚህ እነርሱ እንደሚሆኑም እመሰክራለሁ።