ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፫


ምዕራፍ ፫

ሞርሞን ለኔፋውያን ስለንሰሃ ጮኸ—እነርሱም ታላቅ ድልን አገኙ እናም በራሳቸው ብርታት ተመኩ—ሞርሞን እነርሱን አልመራም አለ፣ እናም ለእነርሱ የነበረው ፀሎትም በእምነት አልነበረም—መፅሐፈ ሞርሞን አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች በወንጌል እንዲያምኑ ይጋብዛል። ከ፫፻፷–፫፻፷፪ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን አሥር ተጨማሪ ዓመታት አስከሚያልፍ ድረስ በድጋሚ ለመዋጋት አልተመለሱም። እናም እነሆ፣ ምድሪቱንና የጦር መሳሪያዎችን ለጦርነት ጊዜ እንዲያዘጋጁ የሕዝቦቼ ኔፋውያን ጉልበታቸውን ተጠቀምኩ።

እናም እንዲህ ሆነ ጌታ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ ለዚህ ሕዝብ ጩኽ—ንሰሃ ግቡና፣ ወደእኔ ኑ፣ እናም ተጠመቁና፣ ቤተክርስቲያኔን በድጋሚ ሥሩ፣ እናም ትድናላችሁ።

እናም ለዚህ ሕዝብ ጮህኩ፣ ነገር ግን በከንቱ ነበር፤ እናም እነርሱም ጌታ እንዳዳናቸውና ለንሰሃም ዕድል የሰጣቸው እርሱ እንደነበር አልተረዱም። እናም እነሆ በጌታ በአምላካቸውም ላይ ልባቸውን አጠጥረውት ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ይህ አስረኛው ዓመት፣ በአጠቃላይ ክርስቶስ ከመጣ ሦስት መቶ ስልሳ ዓመት ካለፈ በኋላ የላማናውያን ንጉሥ ደብዳቤ ላከልኝ፣ ይኸውም እነርሱ ከእኛ ጋር ለጦርነት በድጋሚ ለመምጣት እንደሚዘጋጁ እንዳውቅ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ሕዝቤንም በዳርቻው ባለችው ከተማ በቀጭኑ ማለፊያ በምድሪቱ በስተደቡብ በኩል በሚወስደው ወደ ወደመችው ምድር በአንድነት እራሳቸውን እንዲሰበስቡ አደረግሁ።

እናም ላማናውያን ማንኛውንም ምድራችንን እንዳይወስዱብን ወታደሮቻቸውን እናስቆማቸው ዘንድ ሠራዊታችንን እዚያ አስቀመጥን፤ ስለዚህ ባለን ኃይል ሁሉ ተጠቅመን መሸግንባቸው።

እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ ስልሳ አንደኛው ዓመት ላማናውያን ከእኛ ጋር ለመዋጋት ወደ ወደመችው ከተማ ወረዱ፤ እናም እንዲህ ሆነ በዚያን ዓመት በድጋሚ ወደራሳቸው ምድር እስኪመለሱ አሸነፍናቸው።

እናም በሦስት መቶ ስልሳ ሁለተኛው ዓመት በድጋሚ ለመዋጋት መጡ። እናም በድጋሚ አሸነፍናቸውና፣ ብዙ ቁጥር ያላቸውንም ገደልናቸው፣ ሙታኖቻቸውም ወደ ባሕር ተጣሉ።

እናም እንግዲህ፣ ህዝቤ ኔፋውያን ባደረጉት በዚህ ታላቅ ነገር፣ በጉልበታቸው ተኩራሩና በሰማያት ፊትም በጠላቶቻቸው የተገደሉትን የወንድሞቻቸውን ደም እንደሚበቀሉ መማል ጀመሩ።

እናም ከጠላቶቻቸው ጋር ለመዋጋትና ከምድረገፅም እነርሱን ለማጥፋት በሰማያትና ደግሞ በእግዚአብሔር ዙፋን መሀላን አደረጉ።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ እኔ፣ ሞርሞን፣ በዚህ ህዝብ ክፋትና እርኩሰት የተነሳ ከእንግዲህ የዚህ ህዝብ አዛዥና መሪ በፍጹም አልሆንም አልኩኝ።

፲፪ እነሆ፣ እነርሱን መርቼ ነበር፣ ኃጢአተኞች ቢሆኑም በብዙ ጊዜ በጦርነት መራኋቸውና፣ በውስጤ ባለው በእግዚአብሔር ፍቅር ከልቤ በሙሉ ወደድኳቸው፤ እናም ቀኑን ሙሉ ነፍሴ ለአምላኬ ስለእነርሱ ፀሎትን ታፈስ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ ልባቸውን በማጠጠራቸው ይህ በእምነት አልነበረም።

፲፫ እናም ለሦስት ጊዜም ከጠላቶቻቸው እጅ አስለቅቄአቸዋለሁ፣ እናም እነርሱ ለኃጢአቶቻቸው ንሰሃ አልገቡም ነበር።

፲፬ በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተከለከሉትን በሙሉ በማሉ ጊዜ፣ እናም ከጠላቶቻቸው ጋር ለመዋጋትና የወንድሞቻቸውን ደም እራሳቸው ሊበቀሉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ እነሆ የጌታ ድምፅ ወደ እኔም እንዲህ ሲል መጣ፥

፲፭ በቀል የእኔ ነው፣ እናም ራሴ እከፍለዋለሁ፤ እናም ምክንያቱም ይህ ሕዝብ እኔ ካዳንኳቸው በኋላ ንሰሃ ስላልገቡ፣ እነሆ፣ እነርሱ ከምድረ ገፅ ይጠፋሉ።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚም ጠላቶቼ ላይ ለመሄድ በጥብቅ ተቃወምኩ፤ ልክ ጌታ እንዳዘዘኝ አደረግሁም፤ እናም ስለሚመጡት ነገሮች ስለመሰከረው የመንፈስ መገለጥ መሰረት፣ ስላየኋቸውና ስለሰማኋቸው ነገሮች ለዓለም ለመግለፅ ብቸኛ ምስክር በመሆን ቆምኩኝ።

፲፯ ስለዚህ ለእናንተ ለአህዛብና ደግሞ ሥራው በሚጀመርበት ጊዜ ወደ ትውልድ ምድራችሁ ለመመለስ ለምትዘጋጁት የእስራኤል ቤት ለሆናችሁት እጽፋለሁ፤

፲፰ አዎን፤ እነሆ፣ ለሁሉም ለዓለም ዳርቻ፣ አዎን፣ በኢየሩሳሌም ምድር ኢየሱስ በመረጣቸው በአስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት እንደስራችሁ ወደሚፈረድባችሁ ወደ እናንተ አስራ ሁለት የእስራኤል ነገዶች እጽፋለሁ።

፲፱ እናም በዚህች ምድር ኢየሱስ በመረጣቸው በአስራ ሁለቱ ወደሚፈረድባቸው የሕዝቦች ቅሪት ደግሞ እጽፋለሁ፤ እናም እነርሱም ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በመረጣቸው ይፈረድባቸዋል።

እናም እነዚህን ነገሮች መንፈስ ለእኔ ይገልፅልኛል፤ ስለዚህ ለሁላችሁም እጽፋለሁ። በዚህም ምክንያት ሁላችሁም፣ አዎን፣ የአዳም ቤተሰብ የሆኑት እያንዳንዱ ነፍስ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት መቆም እንዳለባችሁ እንድታውቁ እጽፋለሁ፤ እናም መልካምም ይሁን መጥፎ እንደስራችሁ እንዲፈረድባችሁ መቆም አለባችሁ።

፳፩ እናም ደግሞ በመካከላችሁ በሚሆነው የክርስቶስን ወንጌል ታምኑ ዘንድ፤ እናም ደግሞ የጌታ ቃል ኪዳን ሕዝብ የሆኑት አይሁዶች ከተመለከቱት፣ እናም ከሰሙት፣ ከገደሉት ከኢየሱስ በተጨማሪ፣ የጥንቱ ክርስቶስና የጥንቱ አምላካቸው እንደነበረ ሌላ ምስክር ይኖራቸዋል።

፳፪ እናም በዓለም ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ንሰሃ እንድትገቡና በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ለመቆም እንድትዘጋጁ ለማሳመን እፈልጋለሁ።