መፅሐፈ ሞሮኒ
ምዕራፍ ፩
ሞሮኒ ለላማናውያን ጥቅም ፃፈ—ክርስቶስን ያልካዱ ኔፋውያን ተገደሉ። ፬፻፩–፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እንግዲህ እኔ ሞሮኒ፣ የያሬዳውያንን ሰዎች ታሪክ አሳጥሮ መጻፉን ከጨረስኩ በኋላ፣ ከዚህ የበለጠ እፅፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ ነገር ግን እስካሁንም አልጠፋሁም፤ እናም ላማናውያን ያጠፉኛል ብዬ በመፍራቴ ራሴን አላሳወቅሁም።
፪ እነሆም፣ በመካከላቸው ያሉት ጦርነቶችም እጅግ ኃይለኛ ናቸው፤ እናም በጥላቻቸው ምክንያትም ክርስቶስን የማይክዱትን ኔፋውያን እያንዳንዳቸውን ይገድላሉ።
፫ እናም እኔ፣ ሞሮኒ፣ ክርስቶስን አልክደውም፤ ስለዚህ ለህይወቴ ደህንነትም ስል በምችለው ቦታ ሁሉ እዘዋወራለሁ።
፬ ስለዚህ ከገመትኩት ተቃራኒ የሆኑ ጥቂት ነገሮችን እፅፋለሁ፤ ከዚህ የበለጠ እንድፅፍ አልጠብቅም ነበርና፤ ነገር ግን በጌታ ፈቃድ ወደፊት አንድ ቀን ለወንድሞቼ ለላማናውያን ምናልባት ይጠቅማቸው ዘንድ ከዚህ የበለጠ ጥቂት ነገሮችን እጽፋለሁ።