2013 (እ.አ.አ)
የጌታ ድምፅ
ጃንዩወሪ 2013


የቀዳሚ አመራር መልዕክት፣ ጥር 2013 (እ.አ.አ)

የጌታ ድምፅ

ፕሬዘደንት ሔንሪ ቢ አይሪንግ

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች በሁሉም ቦታ ያሉትን ሰዎች ሁሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ድምጽ እንዲሰሙ ይጋብዛል (ት. እና ቃ. 1፥2፣ 4፣ 11፣ 3425:16 ተመልከቱ)። ይህም ለተመረጡ ነቢያት በራዕይ በተሰጡ በመልዕክቶቹ፣ በማስጠንቀቂያዎቹ፣ እና በሚያበረታቱ ምክሮቹ የተሞሉ ናቸው። በእነዚህ ራዕዮች ውስጥ እንዴት እግዚአብሔር የእምነት ጸሎታችንን በትምህርት፣ በሰላም፣ እና በማስጠንቀቂያ መልእክቶች መልስ ሊሰጠን እንደሚችል እንመለከታለን።

በጸሎታችን እግዚአብሔር ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ፣ ሰላም እና ደስታን በዚህ ህይወት እና በሚመጣው ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚገባን፣ እና በፊት ለፊታችን ምን እንደሚጠብቀን ለማወቅ እንፈልጋለን። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች በተራ ሰዎች እና በነቢያት በትሁት ጸሎት የተጠየቁትን የእንደዚህ አይነት ጥያቄዎች መልሶች የተሞላ ነው። ለእያንዳንዳችንም ስለስጋዊ ደህንነታችን እና ዘለአለማዊ ደህንነታችን ላሉን ጥያቄዎች እንዴት መልስ ለማግኘት እንደምንችል የሚያስተምረን ውድ መመሪያ ለመሆን ይችላል።

ትህትና እና በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ዋና ናቸው። ኦሊቨር ካውደሪ መፅሐፈ ሞርሞንን ለመተርጎም ስላለው ፍላጎት ከጌታ መልስ ተቀብሎ ነበር፥ “ያለ እምነት ምንም ማድረግ እንደማትችል አስታውስ፤ ስለዚህ በእምነት ጠይቅ። በእነዚህም ነገሮች አትቀልድ፤ የማያስፈልጉህን ነገሮች አትጠይቅ” (ት. እና ቃ. 8፥10)።

በተደጋጋሚ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ፣ ጌታ እርዳታውን ከመስጠቱ በፊት እምነትን እና ትህትናን ይጠይቃል። ለዚህ አንዱ ምክንያት ቢኖር መልሶቹ እኛ በምንጠብቃቸው መንገድ ስለማይመጡ ይሆናል። ወይም ሁልጊዜ ለመቀበል ቀላል አይሆኑም።

የቤተክርስቲያኗ ታሪክ እና የዘር ሀረጎቻችን ተሞክሮዎች ይህን እውነት በግልጽ ያሳያሉ። በ1855 (እ.አ.አ) በዳግም የተመለሰው ወንጌል ሲሰበክ ሲሰማ ምን ማድረግ እንደሚገባው ለማወቅ ቅድመ አያቴ ሄንሪ አይሪንግ በጥብቅ ጸለየ። መልስም በህልም መጣለት።

የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን አባል ከሆኑት ሽማግሌ እራስቱስ ስኖው እና ውልያም ብራውን የሚባል ስም ካለው ሽማግሌ ጋር በጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጦ እንዳለ በህልም አየ። ሽማግሌ ስኖው የወንጌልም መሰረታዊ መርሆችን ኣንድ ሰአት ለሚሆን ጊዜ አስተማሩ። ከእዚያም ሽማግሌ ስኖው እንዲህ አሉት፥ እንድትጠመቅ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሀለሁ እናም ይህ ሰው [ሽማግሌ ብራውን] ያጠምቅሀል።”1 ሄንሪ አይሪንግ በጠዋቱ 7፥30 በዝናብ በተጠራቀመ ውሀ ውስጥ በሲይንት ሉውስ፣ ምዙሪ ዩ.ኤስ.ኤ፣ በሽማግሌ ብራውን ለመጠመቅ እምነት እና ትሁትነት ስለነበረው ቤተሰቤ ምስጋና ይሰማቸዋል።

የጸሎቱ መልስ በሚሰማ ድምጽ ከጌታ አልመጣም። ይህም የመጣው፣ ለሌሂ እንደነበረው በምሽት በራዕይ እና በህልም ነበር (1 ኔፊ 8፥2 ተመልከቱ)።

መልሶችም በስሜት ሊመጡ እንደሚችሉ ጌታ አስተምሮናል። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ፣ ለኦሊቨር ካውደሪ እንዲህ አስተምሮታል፣ “እነሆ፣ በአንተ ላይ በሚሆነው እና በልብህም በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በአዕምሮህ እና በልብህ እነግርሀለሁ።” (ት. እና ቃ. 8፥2)።

ኦሊቨርንም በዚህ መንገድ አበረታትቶታል፥ “ይህንን ነገር በተመለከተ ለአምሮህ ሰላምን አልተናገርኩምን? ከዚህስ የበለጠ ከእግዚአብሔር ምንስ አይነት ምስክርነትን ታገኛለህ?” (ት. እና ቃ. 6፥23)።

መልሶች እንደ ማስጠንቀቂያ እና እንደ የሰላም ስሜት ለመምጣት እንደሚችሉ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ እና ከተጠመቀ በኋላ በወንጌል ሰባኪነቱ ጊዜ ሄንሪ አይሪንግ የጠበቃቸው ታሪኮች አስተምረውኛል።

በሚያዝያ 1857 (እ.አ.አ)፣ የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ቡድን አባል ሽማግሌ ፓርሊ ፒ. ፕራት አሁን ኦክላሆማ፣ ዩ.ኤስ.ኤ. በሚባለው ቦታ ውስጥ በጉባኤ ተሳተፉ። ሽማግሌ ፕራት “አዕምሮአቸው ወደፊት የሚሆነውን ባለመረዳት ወይም የሚያመልጡበት ምንም መንገድ ባለማየት በአሳዛኝ አስፈሪ ስሜት እንደተሞሉ”2 ሄንሪ አይሪንግ ጻፉ። ሄንሪ የሚያሳዝነውን ዜና የጻፉት ሐዋርያው እንደ ስማዓት ከሞቱ ከትንሽ ጌዜ በኋላ ነበር። ሽማግሌ ፕራት፣ ልክ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ወደ ካርቴጅ እንደሄደው፣ አደጋው ቢሰማቸውም በጉዞአች ቀጥለው ነበር።

ይህም ጌታ ለትሁት የእምነት ጸሎትን ሁልጊዜ መልስ እንደሚሰጥ ምስክሬ ነው። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች እና የግል አጋጣሚዎቻችን እነዚህን መልሶች እንዴት እንደምናውቅ፣ እና መመሪያዎች፣ የእውነት ማረጋገጫዎች፣ ወይም ማስጠንቀቂያዎች ቢሆኑም፣እነርሱን በእምነት እንዴት ለመቀበል እንደምንችል ያስተምሩናል። ሁልጊዜም የጌታን አፍቃሪ ድምጽ እንድናዳምጥ እና እንድናውቅ ጸሎቴ ነው።

ማስታወሻዎች

  1. “The Journal of Henry Eyring: 1835–1902” (ጸሀፊው ያላቸው ያልታተሙ ጽሁፎች)።

  2. “The Journal of Henry Eyring: 1835–1902።”

ከዚህ መልእክት ማስተማር።

1. በእዚህ መልዕክት ውስጥ ስለጸሎት ያለውን ጽሁፍ አብራችሁ ለማንበብ አስቡበት። ስታነቡም፣ እግዚአብሔር እንዴት ለጸሎቶች መልስ እንደሚሰጥ በጥንቃቄ እንዲያዳምጡ የቤተሰብ አባላትን ጠይቁ። ስለጸሎት አስፈላጊነት ለመመስከርም አስቡበት።

2. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ሰዎች በጸሎት ለሚጠይቁት ጥያቄዎች መልሶች የተሞላ ነው። ለጥያቄአቸው መልሶች (ራዕዮች) ፈጽሞውኑ ካልተመዘገቡስ? የመንፈስ ግፊቶችን እንዲያውቁ እና እንዲከተሉ የቤተሰብ አባላትን አበረታቱ። ስለጸሎት ያላቸውን ሀሳቦች ለመመዝገብ ይፈልጉም ይሆናል።