የሴቶች የቤት ለቤት ጉብኝት መልእክት ሰኔ 2015 (እ.አ.አ)
የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ባህሪ፥ መልካምነት
በጸሎት መንፈስ ይህንን መረጃ አንብቡት እና ምን እንደምታካፍሉ ለማወቅ እሹ። የአዳኝን ህይወት እና ተልእኮ መረዳት በእርሱ ያላችሁን እምነት የሚያሳድገው እና በሴቶች የቤት ለቤት ትምህርት ምክንያት የምትንከባከቧቸውን የሚባርከው እንዴት ነው? ለተጨማሪ መረጃ ወደreliefsociety.lds.org ሂዱ።
“አንጀትህም ለሁሉም ሰው እና ለእምነት ቤተ ሰዎች በልግስና ይሞላ፣ እና ምግባረ በጎነትም ሳያቋርጥ አስተሳሰብህን ያሳምር፤ ከዚያም ልበ ሙሉነትህ በእግዚአብሔር ፊት እየጠነከረ ይሄዳል፤ እና የክህነት ትምህርትም በነፍስህ ላይ እንደ ሰማይ ጠል ትንጠባጠብልሀለች።”(ት እና ቃ 121፥45)።
መልካምነት ምንድን ነው? ፕሬዘደንት ጀምስ ኢ ፋውስት [1920–2007 (እ.አ.አ)] እንደዚህ አሉ፥ “መልካምነት በሙሉ ትርጉሙ ስነ-ምግባራችንን ለመቅረፅ የሚረዳ የፅድቅን ባህሪያት ሁሉ ያጠቃልላል።”1ፕሬዘደንት ጎረርደን ቢ ሒንክሊ [1910–2008 (እ.አ.አ)] እንደዚህ በማለት ጨመሩ፥ “የእግዚአብሔር ፍቅር የሁሉም ጥሩነት፣ የሁሉም መልካምነት፣ የሁሉም የስነ-ምግባር ጥንካሬ ስር ነው።”2
በሴቶች እና በመልካምነት መሃል ስላለው ግንኙነትም፣ የአስራሁለት ሐዋርያት ምልአተ ጉባኤ አባል ሽማግሌ ዲ ታድ ክርስቶፈርሰን እንደዚህ አሉ፥ “ሴቶች ከራሳቸው ጋር የተወሰነ መልካምነት፣ እንዲሁም በግንኙነትና በባህል ውስጥ እምነት፣ ድፍረት፣ ሩህሩህነት እና ብልጽግና አይነት ውጤታዎችን የሚያመጡበት፣ መለኮታዊ ስጦታ ወደ አለም ይዘው ይመጣሉ። …
“እህቶች፣ ከግንኙነቶቻችሁ ሁሉ፣ የስነ-ምግባራችሁ ኃይል ምንጭ ከሆነው ከሰማይ አባታችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁን ግንኙነት ነው በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያ መስጠት የሚገባችሁ። የኢየሱስ ኃይል ለአባቱ ፈቃድ ባለው ብቸኛ ፍቅር አማካኝነት እንደመጣ አስታውሱ። … የአብ እና የወልድ እንደዛ አይነት ደቀመዝሙር ለመሆን ጣሩ፣ እና ተፅኖአችሁ መቼም አይደበዝዝም።”3
ተጨማሪ ጥቅሶች
መዝሙረ ዳዊት 24፥3–5፤ ፊልጵስዩስ 4፥8፤ 2 ጴጥሮስ 1፥3–5፤ አልማ 31፥5፤ ት እና ቃ 38፥23–24
ከቅዱሳት መጻህፍት
ዛሬ፣ መልካም ሴቶች በእምነት ተሞልተው ወደ አዳኙ ይቀርባሉ። በሉቃስ 8 ውስጥ ለ12 አመታት ሊድን ያልቻለ የደም ችግር ስላለባት ሴት እናነባለን። “ከ[ክርስቶስ] ጀርባ ስትመጣ” ፈውስ ፈለገች “እና የቀሚሱን ጫፍ ነካችው እና ወዲያው የደም ችግሯ [ቆመ]።“ኢየሱስም አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ።”4 ይህቺ መልካም ሴት ከፊቱ ወድቃ ለእርሱም “በሕዝቡ ፊት” “ነክታው” እና “እንደተፈወሰች” አወጀች። እርሱም ልጄ ሆይ እምነትሽ አድኖሻል በሰላም ሂጂ አላት”(ሉቃስ 8፥43–48፤ እንዲሁም 6፥17–19 ተመልከቱ)።
በመልካምነቱ አማካኝነት፣5 ወደ እርሱ በድፍረት እና በእምነት ለመምጣት ስንመርጥ፣ ክርስቶስም ለመፈወስ፣ ለማስቻል፣ ለማጠንከር፣ ለማፅናናት እና ለማስደሰት ይችላል።
በ © 2015 Intellectual Reserve, Inc. መብቶቹ በህግ የተጠበቁ። በዩ.ኤስ.ኤ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፥ 6/14 (እ.አ.አ) ትርጉም የተፈቀደበት፥ 6/14 (እ.አ.አ) Visiting Teaching Message, June 2015. Ahmaric. 12586 506 ትርጉም