የቀዳሚ አመራር መልእክት ጥቅምት 2015 (እ.አ.አ)
ችቦአችሁ እየበራ ጨርሱ
በጥንቷ ግሪክ፣ ሯጮች ላምፓደድሮሚያ በሚባል መሽቀዳደሚያ ይጨርሱ ነበር።1 በእሽቅድምድሙ፣ ሯጮቹ ችቦ በእጃቸው ይይዙ እና የመጨረሻ የቡድኑ አባል የማጠናቀቂያውን መስመር እስኪያልፍ ድረስ ችቦውን ወደ ቀጣዩ ሯጭ ያስተላልፋሉ።
ሽልማቱ በፍጥነት ለሮጠው ቡድን አልነበረም የሚሰጠው— የሚሰጠው ችቦው እንደበራ የማጠናቀቂያ መስመሩ ጋር ለደረሰው የመጀመሪያ ቡድን ነበር።
በዚህ ጥልቅ የሆነ ትምህርት አለ፣ አንድ የጥንት እንዲሁም የዘመኑ ነብያት ትምህርት፤ ውድድሩን መጀመር አስፈላጊ ሲሆን፣ ችቦአችን እየበራ መጨረስ ደሞ የበለጠ አስፈላጊ ነው።
ሰለሞን በጥንካሬ ጀምሮ ነበር
ታላቁ ንጉስ ሰለሞን በጥንካሬ የመጀመር ምሳሌ የሆነ ሰው ነው። እርሱ ወጣት እያለ፣ “እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፣በአባቱም ዳዊት ስርዓት ይሄድ ነበር” (1 ኛ ነገስት 3፥3). እግዚአብሔርም በእርሱ ተደስተ እና እንዲህ አለው፣ “ምን እንድሰጥህ ለምን” (1ኛ ነገስት 3፥5)
ሀብትን እና እረጅም እድሜን ከመጠየቅ ይልቅ፣ ሰለሞን የጠየቀው “በህዝቡ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ አስተዋይ ልቦና” ነበር (1ኛ ነገስት 3፥9)።
ይሄም ጌታን በጣም አስደሰተው እና ሰለሞንን በጥበብ ብቻ ሳይሆን ግን ከቁጥር በላይ በሆነ ሀብት እና እረጅም ህይወትም ባረከው።
ሰለሞን በእርግጥም በጣም ጠቢብ እና ብዙ ታላቅ ነገሮችን ያደረገ ቢሆንም፣ በጥንካሬ አልጨረሰም ነበር። በአሳዛኝ ሁኔት፣ በቀጣይ ህይወቱ፣ “ሰለሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፣ እግዚአብሔርን በመከተል ፍፁም አልሆነም” (1ኛ ነገስት 11፥6)።
የእራሳችንን ውድድር መጨረስ
አንድ ነገር ጀምረን ያልጨረስነው ምን ያህል ጊዜ ነው? ክብደት መቀነስ? ስፖርት የመስራተት ፕሮግራም? በየቀኑ ቅዱስ መፅሀፍት የማንበብ ውሳኔዎች? የኢየሱስ ክርስቶስ የተሻለ ደቀመዝሙር የመሆን ውሳኔዎች?
በአዲስ አመት እቅዶችን አውጥተን እና በጋለ መነሳሳት ለጥቂት ቀናት፣ ለጥቂት ሳምንተት፣ ወይም ለጥቂት ወራት ቀጥለን ከዛ በአመቱ መጨረሻ፣ የልብ ውሳኔአችን ነበልባል ቀዝቀዝ ያለ አመድ ሆኖ የምናገኘው ምን ያህል ጊዜ ነው?
አንድ ቀን ውሻ እራሱ በተለተለው ወረቀት ጎን ተኝቶ የሚያሳይ አስቂኝ ፎቶ አጋጠመኝ። እንዲህ ይላል፣ “የውሻ የመታዘዝ ስልጠና ሰርተፍኬት።”
አንዳንዴ እኛም እንደዛ ነን።
ጥሩ የመነሻ ሀሳብ አለን፤ በጥንካሬ እንጀምራለን፤ ምርጥ ለመሆን እንፈልጋለን። ነገር ግን በስተመጨረሻ እቅዳችን እንዲተለተሉ፣ ዋጋ እንዲያጡ እና እንዲረሱ እንተዋቸዋለን።
መንገዳገድ፣ መውደቅ፣ እና አንዳንዴ ከውድድሩ መውጣት መፈለግ የሰው ተፈጥሮ ነው። ነገር ግን እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙረት፣ ውድድሩን ለመጀመር ብቻ ሳይሆን ግን ለመጨረስም የልብ ውሳኔ አለን---እና ችቦአችን አሁንም በደምብ እያበራ ለመጨረስ። አዳኝ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ ቃል ገባ፣ “እስከ መጨረሻው የሚፀና ግን እርሱ ይድናል” (ማቴዎስ 24፥13)።
በእኛ ጊዜ አዳኝ የገባውን ቃል በእራሴ መንገድ ልግለፀው፤ ትእዛዛቱን ከጠበቅን እና ችቦአችን እንደበራ ከጨረስን፣ ዘለአለማዊ ህይወት ይኖረናል፣ ያም ከእግዚአብሔር ስጦታዎች ሁሉ ታላቁ ነው። (ት እና ቃ 14፥7፤ እና 2 ኔፊ 31፥20 ተመልከቱ)
ፈፅሞ የማይሞተው ብርሀን
አንዳንዴ ከመንገዳገድ፣ ከመውደቅ፣ ወይም ተስፋ ከመቁረጥ በኋላም፣ ብርታት እናጣለን እና ብርሀናችን እንደጠፋ እና ውድድሩን እንደተሸነፍን እናምናለን። ነገር ግን የክርስቶስ ብርሃን ሊጠፋ እንደማይችል እኔ እመሰክራለሁ። በጣም በጨለመው ምሽት ያበራል እና ልባችንን ወደ እርሱ ካደረግን ብቻ ወደ ልባችን ደግሞ ያበራል (ነገስት 8፥58 ተመልከቱ)።
ምንም ያህል ጊዜ ወይም በምን ያህል እርቀት ብንወድቅም፣ የክርስቶስ ብርሃን ሁሌም በብሩህ ይነዳል። በጥልቁ ጨለማም ውስጥ ቢሆን፣ ወደ እርሱ የምንመጣ ከሆነ፣ የእርሱ ብርሃን ጥላዎቹን ይውጣል እና ነብሳችንን ያነግሳል።
ይሄ የደቀመዝሙርነት ውድድር የአጭር እርቀት አይደለም፤ ማራቶን ነው። በምን ያህል ፍጥነት መጓዛችን የሚያመጣው ጥቂት ለውጥ ነው። በእርግጥ፣ ውድድሩን ልንሸነፍ የምንችለው በስተመጨረሻ መሸነፋችንን ስናምን እና ተስፋ ስንቆርጥ ነው።
ከፍ ማለታችንን እና ወደ ኣዳኛችን መጓዛችንን እስከቀጠልን ድረስ፣ ውድድሩን ችቦአችን በደምብ እየበራ እናሸንፋለን።
ችቦው ስለ እኛ ወይም ስለምናደርገው ነገር አይደለም።
ስለ ዓለም አዳኝ ነው።
እና ያ ብርሀን ደግሞ በፍፁም የማይጠፋ ነው። ያ ብርሃን ጨለማውን የሚውጥ ፣ ቁስላችንን የሚፈውስ፣ እና በጥልቅ ሀዘን መሀከል እና በማይለካ ጨለማ ውስጥ እንኳን የሚያበራ ነው።
ከመረዳት የሚልቅ ብርሀን ነው።
እያንዳንዳችን የጀመርነውን መንገድ እንጨርስ። እና በአዳኛችን እና ቤዛችን፣ በኢየሱሰ ክርስቶስ እርዳታ፣ በደስታ እና ችቦአችን አሁንም እየበራ እንጨርሳለን።
© 2015 በ Intellectual Reserve Inc. መብቶቹ በህግ የተጠበቁ። በዩ.ኤስ.ኤ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፥ 6/15 (እ.አ.አ)። ትርጉም የተፈቀደበት፥ 6/15 (እ.አ.አ)። First Presidency Message, October 2015 (እ.አ.አ) Amharic 12590 506 ትርጉም።