2021 (እ.አ.አ)
ክርስቶስ ተነስቷል፤ በእርሱ ማመንም ተራራን ያነቃንቃል
ግንቦት 2021 (እ.አ.አ)


ወርሀዊ የ ሊያሆና መልዕክት፣ ግንቦት 2021 (እ.አ.አ)

ክርስቶስ ተነስቷል፤ በእርሱ ማመንም ተራራን ያነቃንቃል

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በዚህ ህይወት ለእኛ የሚገኝ ታላቁ ሀይል ነው። ለሚያምኑት ሁሉም ነገሮች የሚቻሉ ናቸው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህች የፋሲካ ሰንበት እናንተን ለማነጋገር ላገኘሁት እድል አመስጋኝ ነኝ።1 የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት እና ትንሳኤ የእያንዳንዳችንን ህይወት ለዘለአለም ቀይረዋል። እርሱን እንወዳለን እናም እርሱን እና የሰማይ አባታችንን በምስጋና እናመልካለን።

ባለፉት ስድስት ወራት ከአለም አቀፍ ወረርሸኝ ጋር መታገላችንን ቀጥለናል። በህመም፣ በኪሳራ እና በመነጠል ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁም ባላችሁ ጽናት እና መንፈሳዊ ጥንካሬ እደነቃለሁ። በሁሉም ሁኔታዎች ጌታ ለእናንተ የማይጠፋ ፍቅር እንዳለው እንዲሰማችሁ ያለማቋረጥ እጸልያለሁ። ለፈተናዎቻችሁ በጠንካራ ደቀ መዝሙርነት ምላሽ ሰጥታችሁ ከነበረ፣ ያለፈው ዓመት ከንቱ አልነበረም።

ዛሬ ጠዋት በምድር ላይ ሰው ከሰፈረባቸው ከያንዳንዱ አህጉር ከመጡ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሰምተናል። በእውነት የወንጌል በረከቶች ለሁሉም ዘር፣ ቋንቋ እና ህዝብ ናቸው። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ናት። ኢየሱስ ክርስቶስ መሪያችን ነው።

ደግነቱ ወረርሽኝ እንኳ የእሱን የእውነት የወደፊት ጉዞ ሊያንጓትተው አልቻለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በዚህ ግራ በተጋባ፣ በጭቅጭቅ በተሞላ እና አድካሚ በሆነ ዓለም ውስጥ በትክክል አስፈላጊ ነው።

እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጆች የኢየሱስ ክርስቶስን ፈዋሽ፣ የመቤዠት መልእክት ለመስማት እና ለመቀበል እድሉ ይገባቸዋል። አሁን እና ለዘላለም ለደስታችን ሌላ በጣም አስፈላጊ መልእክት የለም።2 የበለጠ በተስፋ የተሞላ ሌላ መልእክት የለም። በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን አለመግባባት ምንም ሌላ መልእክት ሊያስወግድ አይችልም።

በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ እምነት የሁሉም እምነት መሠረት እና የመለኮታዊ ኃይል መተላለፊያ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው፣ “ያለእምነትም [እግዚአብሄርን] ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደእግዚአብሄር የሚደርስ እግዚአብሄር እንዳለለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።”3

በህይወት ውስጥ ያለ ጥሩ ነገር ሁሉ–የዘለአለም ጠቀሜታ ያለው በረከት ሁሉ–በእምነት ይጀምራል። እግዚአብሔር በህይወታችን እንዲያሸንፍ መፍቀዳችን የሚጀምረው እኛን ለመምራት ፈቃደኛ እንደሆነ በማመን ነው። እውነተኛ ንስሐ የሚጀምረው ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን የማንፃት፣ የመፈወስ እና የማፅናት ኃይል እንዳለው በማመን ነው።4

“የእግዚአብሔርን ኃይል እንዳትክዱ” “ምክንያቱም እርሱ፣ በሰው ልጆች እምነት መሰረት ይሰራልና።”ብሎ አውጇል ነቢዩ ሞሮኒ5 የእግዚአብሔርን ሀይል በ ህይወታችን ውስጥ የሚከፍተው የእኛ እምነት ነው።

ቢሆንም፣ እምነትን መለማመድ ከባድ ሊመስልም ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በጣም የምንፈልጋቸውን በረከቶች ለመቀበል የሚያስችል በቂ እምነት መሰብሰብ እንችል ይሆን ብለን እናስብ ይሆናል። ሆኖም ጌታ እነዚያን ፍርሃቶች በመፅሐፈ ሞርሞን ነቢይ አልማ ቃላት አማካኝነት ድምዳሜ ሰጥቷቸዋል።

ምስል
የሰናፍጭ እህል ዘር

አልማ ቃሉን ዝም ብለን እንድንሞክር እናም “ ቅንጣት ያህል እምነትን [እንድንለማመድ]፣ አዎን ከማመን በላይ የበለጠ ለመፈለግ [ባንችልም]” ብሎ ይጠይቀናል።6 “ቅንጣት ያህል እምነትን” የሚለው ሀረግ፣ “ የሰናፍጭ ቅንጣት፣ የሚያህል እምነት” ቢኖረን “ይህን ተራራ፣ ከዚህ ወደዚያ እለፍ [ብንለው] ያልፋል፤ [የሚሳንንም] ነገር የለም” በማለት ጌታ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳስታውስ ያደርገኛል።7

ምስል
ወፎች በሰናፍጭ ዘር መሃል

ጌታ ስጋዊ ደካማችንን ይረዳል። አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም እንደናቀፋለን። ነገር ግን ታላቅ ችሎታችንንም ያውቃል። የሰናፍጭ ዘር በትንሹ ይጀምራል ነገር ግን ወፎች በቅርንጫፎቹ ውስጥ ጎጆ ሊሰሩ ወደሚችሉበት ትልቅ ዛፍ ያድጋል። የሰናፍጭ ዘር አንድ ትንሽ ግን የሚያድግ እምነትን ይወክላል።8

ጌታ ከእርሱ ፍጹም ሀይል ለመካፈል ከእኛ ፍጹም እምነትን አይጠብቅም። ነገር ግን እንድናምን ይጠይቀናል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህች የትንሳኤ ጠዋት የማቀርብላችሁ ጥሪ እምነታችሁን ማሳደግ ዛሬ እንድትጀምሩ ነው። በእምነታችሁ አማካኝነት ኢየሱስ ክርስቶስ በህይወታችሁ ውስጥ ያለውን ተራራ ለማነቃነቅ ያላችሁን ችሎታ ያሳድገዋል፣9 ምንም እንኳን የግል ፈተናዎቻችሁ እንደ ኧቨረስት ተራራ ያህል ታላቅ ቢሆኑም።

ተራራዎቻችሁ ብቸኝነት፣ ጥርጣሬ፣ ህመም ወይም ሌሎች የግል ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ተራራዎቻችሁ ይለያያሉ፣ ሆኖም ግን ለእያንዳንዱ ፈታኝ ሁኔታ መልሱ እምነታችሁን መጨመር ነው። ያም ሥራን ይጠይቃል ሰነፍ ተማሪዎች እና ሰነፍ ደቀ መዛሙርት የእምነትን ቅንጣት እንኳን ለመሰብሰብ ሁል ጊዜ ይታገላሉ።

ማንኛውንም ነገር በጥሩ ሁኔታ ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆንም ከዚህ የተለየ አይደለም። እምነታችሁን እና በእርሱ መታመናችሁን ማሳደግ ጥረት ይፈልጋል። ያንን እምነት እና መታመን ለማሳደግ የሚረዱ አምስት ሀሳቦች ላቅርብ።

መጀመሪያ፣ አጥኑ። ተሳታፊ ተማሪዎች ሁኑ። የክርስቶስን ተልእኮ እና አገልግሎት በተሻለ ለመረዳት በቅዱሳን መጻህፍት ውስጥ እራሳችሁን ንከሩ። ለህይወታችሁ ያለውን ኃይል ትገነዘቡ ዘንድ የክርስቶስን ትምህርት እወቁ። የኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በእናንተላይ የመስራቱን እውነት የራሳችሁ አድርጉ። እሱ የእናንተን መከራ፣ የእናንተን ስህተቶች፣ የእናንተን ድክመቶች እና የእናንተን ኃጢያቶች በራሱ ላይ ወስዷል። የማካካሻ ዋጋን ከፍሏል እናም መቼም የሚገጥሟችሁን ተራራዎች ሁሉ ለማንቀሳቀስ ኃይል ሰጥቷችኋል። ያንን ኃይል በእምነታችሁ፣ በመታመናችሁ እና እሱን ለመከተል ባላችሁ ፈቃደኝነት ታገኙታላችሁ።

ተራራችሁን ማንቀሳቀስ ተዓምር ያስፈልገው ይሆናል። ስለተዓምራት ተማሩ። ተዓምራት የሚመጡት በጌታ ባላችሁ እምነት መሰረት ነው። የዚያ እምነት እምብርት የሆነውም የእርሱን ፈቃድ እና የጊዜ ሰሌዳ ማለትም በምትፈልጉት ተአምራዊ እርዳታ እንዴት እና መቼ እንደሚባርካችሁ መታመን ነው። የእናንተ አለማመን ብቻ ነው እግዚአብሔር በእናንተ ህይወት ውስጥ ያሉትን ተራራዎች ለማነቃነቅ በሚያስችሉ ተዓምራት መባረኩን የሚገድበው።10

ስለአዳኙ የበለጠ ስትማሩ በምህረቱ፣ ማለቂያ በሌለው ፍቅሩ እና በሚያጠናክረው፣ በሚፈውሰው፣ በመቤዥው ኃይሉ ላይ እምነት መጣል ቀላል ይሆናል። ተራራን በእምነትከምንጋፈጥበት ወይም ከምንወጣበት ጊዜ ይልቅ አዳኙ መቼም ለእናንተ የሚቀርብበት ጊዜ የለም።

ሁለተኛ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ምረጡ። ስለ እግዚአብሔር አብ እና ስለውዱ ልጁ፣ ወይም ስለዳግም መመለስ እውነትነት ወይም ስለጆሴፍ ስሚዝ የነቢይነት መለኮታዊ ጥሪ ጥርጣሬ ካላችሁ ማመንን ምረጡ11 እናም ታማኝ ሁኑ። ጥያቄአችሁን ወደ ጌታ እና ወደ ሌሎች የእምነት ምንጮች ውሰዱ። በነቢዩ ህይወት ውስጥ እንከን ለማግኘት ወይም በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ልዩነት ለማግኘት ሳይሆን ለማመን በመፈለግ አጥኑ። የሌሎችን ጥርጣሬዎች በመደጋገም የራሳችሁን ጥርጣሬ አታሳድጉ። ጌታ በመንፈሳዊ ግኝት ጉዟችሁ እንዲመራችሁ ፍቀዱ።

ሶስተኛ፣ በእምነት አድርጉ ። አሁን ካላችሁ ተጨማሪ እምነት ቢኖራችሁ ምን ታደርገጉ ነበር? አስቡበት። ስለዚያም ጻፉ። ከዚያም፣ ተጨማሪ እምነት የሚያፈልግን ነገር በማድረግ የበለጠ እምነትን ተቀበሉ

አራተኛ፣ ቅዱስ ስርዓቶችን በብቁነት ተቀበሉ ። ስርዓቶች የእግዚአብሔርን ሀይል በህይወታችሁ ውስጥ ያስከፍታሉ።12

እናም አምስተኛ፣ የሰማይ አባታችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እርዳታ ጠይቁ

እምነት ሥራን ይጠይቃል። ራእይን መቀበል ስራን ይጠይቃል። ነገር ግን “የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ እናም የሚፈልግም ያገኛል፤ እናም ለሚያንኳኩ ይከፈትላቸዋል።”13 እግዚአብሔር እምነታችሁን ለማሳደግ ምን እንደሚረዳ ያውቃል። ጠይቁ፣ ከዚያም እንደገና ጠይቁ።

የማያምን እምነት ለደካማ ነው ይል ይሆናል። ነገር ግን ይህ ሃሳብ የእምነትን ሀይል ይንቃል። የአዳኝ ደቀ መዛሙርት እርሱን የሚጠራጠሩ ቢሆኑ ኖሮ ከእርሱ ሞት በኋላ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የእርሱን ትምህርት በማስተማር ይቀጥሉ ነበርን?14 ጆሴፍ እና ሀይረም ስሚዝ እውነት ስለመሆኑ የተረጋገጠ ምስክርነት ካላገኙ በስተቀር የጌታን ቤተክርስቲያን በዳግም መመለስ በመከላከል የሰማዕታትን ሞት ይቀበሉ ነበርን? የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በዳግም እንደተመለሰ እምነት ባይኖራቸው ኖሮ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ቅዱሳን በአቅኚነት መንገድ ላይ ይሞቱ15 ነበርን? በእውነትም እምነት ለማከናወን የሚችል የማይመስልን የማይቻለውን እንዲፈጽም የሚያስችል ኃይል ነው።

ያላችሁን እምነት ዝቅ አታድርጉ። የቤተክርስቲያኗ አባል ለመሆን እና በታማኝነት ለመቆየት እምነት ያስፈልጋል። ከጥበበኞች እና ከብዙዎች አስተያየት ይልቅ ነቢያትን መከተል እምነት ይጠይቃል። በወረርሽኝ ጊዜ ሚስዮናዊ አገልግሎት መስጠት እምነት ይጠይቃል። የእግዚአብሔር ንፅህና ህግ አሁን ጊዜ ያለፈበት ነው እያለ ዓለም ሲጮህ ንጹህ ህይወት መኖር እምነት ይጠይቃል። በዓለማዊ ዓለም ውስጥ ላሉ ልጆች ወንጌልን ማስተማር እምነትን ይጠይቃል። ለሚወዱት ሰው ህይወት መማፀን እምነት ይፈልጋል እንዲያውም ተስፋ አስቆራጭ መልስ መቀበል የበለጠ እምነት ይጠይቃል።

ከሁለት አመት በፊት፣ እህት ኔልሰን እና እኔ ሳሞአ፣ ቶንጋ፣ ፊጂ፣ እና ታሂቲን ጎበኘን። በእያንዳንዱ በእነዚያ የደሴት ሀገሮች ለብዙ ቀናት ከባድ ዝናብ ጥሎ ነበር። አባላት የውጪ መሰብሰቢያ ቦታዎቻቸው ከዝናቡ እንዲጠበቁ ጾመውና ጸልየው ነበር።

በሳሞአ፣ ፊጂ፣ እና ታሂቲ ውስጥ ልክ ስብሰባው ሲጀምር ዝናቡ ቆመ። በቶንጋ ውስጥ ግን ዝናቡ አልቆመም ። ሆኖም 13 ሺህ ታማኝ ቅዱሳን መቀመጫ ለማግኘት ከብዙ ሰዓታት ቀደም ብለው መጡ፣ በማያቋርጥ ዝናብ ውስጥ በትዕግሥት ጠበቁ ከዚያም በጣም በስብሰው የሁለት ሰዓት ስብሰባ ተቀመጡ።

ምስል
የቶንጋ ቅዱሳን በዝናብ ውስጥ

በእነዚያ በእያንዳንዱ የደሴቲቱ ነዋሪዎች መካከል ንቁ እምነት ሲሰራ ተመለከትን—ዝናቡን ለማቆም የሚያስችል በቂ እምነት እንዲሁም ዝናቡ ባላቆመም ጊዜ የሚፀና እምነት።

በህይወታችን ውስጥ ያሉ ተራራዎች ሁልጊዜም እኛ በምንፈልገው መንገድ ወይም ጊዜ አይነቃነቁም። ነገር ግን እምነታችን ሁልጊዜ ወደፊት ይገፋናል። እምነት ሁልጊዜም የአምላካዊ ኃይል ተደራሽነትን ይጨምራል።

እባካችሁ ይህን እወቁ፦ እናንተ የምታምኗቸው በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ነገሮች እና ሁሉም ሰዎች ቢተውአችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቤተክርስቲያኗ በጭራሽ አይጥሏችሁም። ጌታ በጭራሽ አያንቀላፋም ወይም አይተኛም።16 እርሱ “ትናንትም ዛሬም ነገም ያው ነው ”17 እርሱ ቃል ኪዳኖቹን፣18 የተስፋ ቃሉን፣ ወይም ለህዝቡ ያለውን ፍቅር አይተውም። ዛሬም ተዓምራትን ይሰራል እናም ነገም ተዓምራትን ይሰራል።19

በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በዚህ ህይወት ለእኛ የሚገኝ ታላቁ ሀይል ነው። ለሚያምኑት ሁሉም ነገሮች ይቻላሉ።20

በእርሱ ላይ እያደገ የሚመጣው እምነታችሁ ምድርን የሚያስውቧትን የዓለት ተራሮች ሳይሆን በህይወታችሁ ውስጥ ያሉ የመከራ ተራሮችን ያነቃንቋቸዋል። የሚያብበው እምነታችሁ ተግዳሮቶችን ተወዳዳሪ ወደሌለው ዕድገትና ዕድል ለመቀየር ይረዳችኋል።

በዚህ ትንሳኤ ሰንበት በጥልቅ የፍቅር እና የምስጋና ስሜቶቼ “ክርስቶስ በእርግጥም ተነስቷል” በማለት አውጃለሁ። ቤተክርስቲያኑን ለመምራት ተነስቷል። በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ህይወት ለመባረክ ተነስቷል። በእርሱም በማመን በህይወታችን ውስጥ ያሉትን ተራሮች ለማነቃነቅ እንችላለን። እንዲህ የምመሰክረው በቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።

የቦታ ያዥ ምስል ውል

ማስታወሻዎች

  1. በአንዳንድ የአለም ክፍሎች ሰዎች በተለየ ሁኔታ በትንሳኤ ጠዋት ሰላምታ ይሰጣጣሉ። በአካባቢያቸው ቋንቋ ሰላምታ የሚሰጠው “ክርስቶስ ተነስቷል!” ይላል። ሰላምታ የተሰጠውም ሰው “በእውነትም! ተነስቷል!” ሲል ይመልሳል ለምሳሌ፣ የራሽያ ቋንቋ ተናጋሪዎች የትንሳኤ ሰላምታን የሚጀምሩት “Христос воскрес” (ክርስቶስ ተነስቷል [በትንሳኤ ከሞት ተነስቷል]!) በማለት ነው፣, የሚመለሰውም “Воистину! воскрес!” (በእውነትም! ተነስቷል!) ይላል።

  2. ሞዛያ 2፥41ተመልከቱ።

  3. ዕብራውያን 11፥6Lectures on Faith [የእምነት ትምህርቶች] እንደሚለው እምነት “በሁሉም ላይ ኃይል፣ ግዛት እና ስልጣን ያለው የመጀመሪያው ታላቅ ዋና መርህ ነው” ([1985 (እ.አ.አ)]፣ 5)።

  4. ማቴዎስ 11;28–30አልማ 7፥12–13ኤተር 12፥27ተመልከቱ።

  5. ሞሮኒ 10፥7፤ ትኩረት ተጨምሯል።

  6. አልማ 32፥27፤ ትኩረት ተጨምሯል።

  7. ማቴዎስ 17፥20፣ ትኩረት ተጨምሯል፤ ደግሞም ሔላማን 12፥9፣ 13ተመልከቱ።

  8. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 78፥17–18ተመልከቱ። ተፈጥሮአዊውን ሰው የማስወገዱ ዋጋ “በጌታ በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ቅዱስ” መሆን ነው (ሞዛያ 3፥19)።

  9. 1 ኔፊ 7፥12ተመልከቱ።

  10. ሞርሞን 9፥19-21ኤተር 12:30ተመልከቱ።

  11. 2 ኔፊ 33፥10–11ተመልከቱ።

  12. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥20ተመልከቱ።

  13. ማቴዎስ 7፥8

  14. ያለእምነት ኃይል፣ አቢናዲ እውነት መሆኑን ያወቀውን ለመካድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በእሳት ይሞታልን? ( ሞዛያ 17፥7–20ተመልከቱ)። እምነታቸው ቢያወግዙ ኖሮ ህይወታቸው የበለጠ ምቾት የሚኖረው እንደሆነ እያወቁ፣ ያለዚያ ኃይል ኤተር በድንጋይ ዋሻ ውስጥ ይደበቅ ነበርን ( ኤተር 13፥13–14ተመልከቱ)ሞሮኒስ ለብዙ ዓመታት ብቸኝነትን በጽናት ተቋቁሞ ይኖር ነበር ( ሞሮኒ 1፥1–3ተመልከቱ)?

  15. ሜልቭንኤል. ባሾር፣ ኤች.ዴኒስ ቶሌ፣ እና የቢዋይዩ መስራቾች ሟች ቡድን፣ “Mortality on the Mormon Trail፣ 1847–1868 (እ.አ.አ)፣” BYU Studies፣ ይዘት 53፣ ቁጥር 4 (2014 እ.አ.አ)፣ 115ን ተመልከቱ።

  16. መዝሙር 121፥4ተመልከቱ።

  17. ሞሮኒ 9፥9

  18. ኢሳይያስ 54፥103 ኔፊ 22፥10ተመልከቱ።

  19. ራዕይ 9፥10–11፣ 15ተመልከቱ።

  20. ማርቆስ 9፥23ተመልከቱ።

አትም