“ክህነት የእግዚያብሔር ሃይል ነው፣” ሊያሆና፣ ነሐሴ 2021 (እ.አ.አ)
ወርሀዊ የ ሊያሆና መልዕክት፣ ጥር 2021(እ.አ.አ)
ክህነት የእግዚያብሔር ሃይል ነው።
እግዚያብሔር በክህነት ሃይል ይባርከናል። የክህነት በረከቶች ለሁሉም ሰው ይገኛሉ።
ክህነት የእግዚያብሔር ሃይል ነው። ይህንን ሃይል ሁሉንም ልጆቹን ለመባረክ እና ተመልሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ለመርዳት ይጠቀማል። እግዚአብሔር በምድር ላሉ ልጆቹ የክህነት ሃይል ሰጥቷል። በዚህ ሃይል የክህነት መሪዎች ቤተክርስቲያኗን መምራት ይችላሉ እንዲሁም የክህነት ተሸካሚዎች ወደ እግዚያብሄር ለመቅረብ የሚረዱ እንደ ጥምቀት ያሉ ቅዱስ ስርአቶችን ሊያከናውኑ ይችላሉ። እያንዳንዳቸው በክህነት ስርዓቶች ውስጥ በብቃት የሚሳተፉ እና ቃል ኪዳኖችን የሚጠብቁ ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ የእግዚአብሔርን ኃይል በቀጥታ መጠቀም ይችላሉ።
የክህነት ሃይል ለጆሴፍ ስሚዝ ተሰጥቶት ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ቤተክርስቲያኑን በክህነት ሃይል መርቷል። እንዲሁም ይህንን ሃይል ለሐዋርያቶቹ ሰጥቷል። ከሞቱ በኋላ ባሉት ክፍለ ዘመናት ውስጥ ብዙ አባላት ከቤተክርስቲያኗ ቀስ በቀስ እየተለዩ መጡ። ወንጌልን እና ቤተክርስቲያን የምትሰራበትን መንገድ በተሳሳተ መንገድ ቀየሩ። የእግዚያብሔር ክህነት ከዛ በኋላ በምድር ላይ አልነበረም። በ1829 (እ.አ.አ)፣ ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስን እና ሐዋሪያቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ለጆሴፍ ስሚዝ የክህነት ስልጣን እንዲሰጡ ላካቸው። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከእግዚያብሔር የተሰጠ ስልጣን ያላት በምድር ብቸኛ ድርጅት ናት።
የክህነት ቁልፎች
የክህነት ቁልፎች ስርዓቶችን ለማከናወን ፍቃድ እንደመስጠት ያሉ የክህነትን አጠቃቀምን ለመምራት የሚያስችል ስልጣን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም የክህነት ቁልፎች ይይዛል። የቤተክርስቲያኗ ፕሬዘዳንት መላውን ቤተክርስቲያን ለመምራት የክህነት ቁልፎችን መጠቀም የሚችል በምድር ብቸኛው ሰው ነው። በእሱ መመሪያ መሠረት ሌሎች የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት የተወሰኑ ቁልፎችን መጠቀም ይችላሉ። እንደ ኤጲስ ቆጶሳት እና የካስማ ፕሬዚዳንቶች ያሉ መሪዎች አጥቢያቸውን እና ካስማቸውን ለመምራት የክህነት ቁልፎችን ይጠቀማሉ። ለማገልገል የሚሰጥ ጥሪ የሚመጣው የክህነት ቁልፎችን ከያዙ መሪዎች በመሆኑ በጥሪያቸውን የሚያገለገግሉ ወንዶች እና ሴቶች ሀላፊነታቸውን ሲወጡ የክህነት ስልጣንን ይለማመዳሉ።
የመልከ ጼዴቅ ክህነት እና የአሮናዊ ክህነት
ክህነት ሁለት ክፍሎች አሉት፦ የመልከ ጸዴቅ ክህነት እና የአሮናዊ ክህነት። በመልከ ጸዴቅ ክህነት አማካኝነት የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደ የሚስዮናዊ እና የቤተመቅደስ ስራዎች የመሳሰሉ ሁሉንም የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ስራዎች ይመራሉ። የአሮናዊ ክህነት በመልከ ጼዴቅ ክህነት ስልጣን ስር ይሰራል። የሚያገለግለውም እንደ ጥምቀት እና ቅዱስ ቁርባን ያሉ ስርዓቶችን ለማከናወን ነው።
የክህነት በረከቶች
በቃል ኪዳኖች እና በስርዓቶች አማካኝነት እግዚያብሔር የክህነት በረከቶችን ለሁሉም ልጆቹ የሚገኙ አድርጓል። እነዚህ በረከቶች ጥምቀትን፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን፣ ቅዱስ ቁርባንን እና የቤተመቅደስ ስርዓቶችን ያካትታሉ። የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበሉ ወንዶች እና ሴቶች የእግዚያብሔርን የክህነት ሃይል ስጦታ በቃል ኪዳኖቻቸው አማካኝነት ይቀበላሉ። የመፈወስ፣ የማጽናናት እና የመምራት የክህነት በረከቶችን ልንቀበልም እንችላለን።
ቅዱሳን መጽሐፍት ስለክህነት ምን ይላሉ?
በጥንት ጊዜ የነበረው ክህነት ያው ዛሬ ያለው ክህነት ነው( ሙሴ 6፥7ይመልከቱ)።
የክህነት ቁልፎች የጌታን ስራ በተገቢው መንገድ እያከናወንን እንደሆነ ለማረጋገጥ ይረዳሉ ( ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥11ይመልከቱ)።
የክህነት ስልጣንን የያዙ ወንዶች “በጽድቅ መሰረታዊ መርሆዎች ብቻ“ ሊጠቀሙት ይችላሉ(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥36)።
ክህነትን የያዙ ሰዎች ያሉባቸው አንዳንድ ሃላፊነቶች በ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥38–67ውስጥ ተገልጸዋል።
© 2021 by Intellectual Reserve, Inc. መብቱ በሕግ የተጠበቀ ነው። በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly Liahona Message, August 2021.ትርጉም። Amharic. 17472 506