2024
ወንጌልን በመኖር የሚገኝ ዘላቂ ደስታ
የካቲት 2024 (እ.አ.አ)


“ወንጌልን በመኖር የሚገኝ ዘላቂ ደስታ፣” ሊያሆና፣ የካቲት 2024 (እ.አ.አ)።

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ የካቲት 2024 (እ.አ.አ)

ወንጌልን በመኖር የሚገኝ ዘላቂ ደስታ

ዘላቂ ደስታ የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በመጽናት እና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ በመርዳት ነው።

አዳምና ሔዋን፣ የኤደን ገነት በስተጀርባቸው እየታየ

የኤደን ገነት፣ በግራንት ሮምኒ ክላውሰን፤ ከኤደን ገነት መውጣት፣ በጆሴፍ ብሪኪ

የህይወታችን ዓላማ አጠር ያለ መግለጫ በሌሂ የሰው ልጅ ህይወት ጅማሬ ትንቢታዊ ትምህርቶች ውስጥ ይገኛል። በኤደን ገነት ውስጥ አዳምና ሔዋን በየዋህነት ይኖሩ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢቆዩ ኖሮ “ደስታ አይኖራቸውም፣ መከራን አያውቁምና፤ ኃጢአትን ባለማወቃቸው መልካምን አይሰሩም” (2 ኔፊ 2፥23) ነበር። ስለዚህ ሌሂ እንደገለጸው “ሰዎች እንዲኖሩ፣ አዳም ወደቀ፤ እና ሰዎች የሚኖሩትም ደስታም እንዲኖራቸው ዘንድ ነው” (2 ኔፊ 2፥25፤ በተጨማሪም ሙሴ 5፥10–11ን ተመልከቱ)።

በወደቀ ዓለም ውስጥ ስናድግ፣ በተማርነው እና በገጠመን ነገር አማካኝነት በመልካም እና በክፉ መካከል ያለውን ልዩነት እንማራለን። “የመልካሙን ነገር ሽልማት [እናውቅ] ዘንድ መራራውን [እንቀምሳለን]” (ሙሴ 6፥55)። ደስታ የሚመጣው መራራውን ስንተው እና መልካሙን ይበልጥ አጥብቀን ስንይዝ እና ስንንከባከብ ነው።

ደስታን ማግኘት

የሰማይ አባታችን ለእኛ ባለው ፍጹም ፍቅር ምክንያት ፍጹም የሆነውን ደስታውን አሁን እና ለዘለአለም ከእኛ ጋር ለመካፈል ይጓጓል። የእርሱን የደስታ እቅድ እና አንድያ ልጁ እኛን ለማዳን የከፈለውን መስዋዕትነት ጨምሮ፣ ከመጀመሪያ ጀምሮ በሁሉም ነገር እርሱን የሚያነሳሳ ይህ ነበር።

እግዚአብሔር ሓሴትን ወይም ደስታን በእኛ ላይ ሊጭንብን አይሞክርም፣ ነገር ግን እንዴት ማግኘት እንደምንችል ያስተምረናል። በተጨማሪ እሱ ደስታ የማይገኝበትን ቦታ ይነግረናል—“ክፋት በፍጹም ደስታ ሆኖ አያውቅም” (አልማ 41፥10)። የሰማይ አባታችን የደስታን መንገድ የሚገልጥልን በትእዛዛቱ አማካኝነት ነው።

ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን በዚህ መንገድ ገልጸውታል፦

“ታላቁ እውነት እዚህ አለ፦ ዓለም ኃይል፣ ሀብት፣ ተወዳጅነትና የሥጋ ደስታ ደስታን እንደሚያመጡ አጥብቆ ቢናገሩም፣ አያደርጉትም! ለማድረግ አይችሉም! የሚያፈሩት ነገር ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት [ለሚጠብቁ] የተባረከና [አስደሳች] ሁኔታ’ ምትክ ሊሆን ከማይችል በስተቀር ሌላ አይደለም [ሞዛያ 2፥41]።

“እውነታው ደስታ ፈጽሞ ሊገኝ በማይቻልበት ቦታ ደስታን መፈለግ በጣም አድካሚ ነው! ነገር ግን፣ ራሳችሁን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስታጣምሩ እና አለምን ለማሸነፍ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ስራ ስትሰሩ፣ እርሱ ብቻ ነው እናንተን ከአለም ጉተታ ከፍ ለማድረግ ሀይል ያለው።”1

ስለዚህ፣ ዘላቂ ደስታ የሚገኘው የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅ ነው፣ የእርሱ ትእዛዛት ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ይገኛሉ። ነገር ግን ምርጫው የእኛ ነው። ለጊዜው በድካማችን ምክንያት ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ካልቻልን አሁንም ዘወር ልንልና መራራውን ትተን መልካሙን መከተል እንችላለን። የእግዚአብሔር ፍቅር ኃጢአትን አያመካኝም—ይህ ምህረት ፍርድን ሰረቀ እንደማለት ነው—ነገር ግን በኃጢአት ክፍያው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት ስርየትን ያቀርባል።

“አሙሌቅ … [እንዳለው] … እርሱ ጌታ በእርግጥ ህዝቡን ለማዳን እንደሚመጣ ተናግሯልና፤ ነገር ግን ኃጢአታቸው ሊያድናቸው እንጂ፣ከነኃጢአታቸው ሊፈውሳቸው አይመጣም።

እናም ጌታ በንስሃ የተነሳ ከኃጢአታቸው እንዲያድናቸው ከአብ ስልጣን ተሰጥቶታል፤ ስለዚህ ህዝቡን ወደማዳን ስልጣን እንዲሁም ወደ ነፍሳቸው ደህንነት የሚያመጣቸውን የንስሃን የምስራች ሁኔታ ለመናገር መላዕክቱን ልኳል” (ሔለማን 5፥10–11፤ አጽንዖት ተጨምሯል)።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፤

“እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፤ ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።

“ደስታዬ በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐንስ 15፥10–11)።

ሌሂ በህልሙ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚወክለውን የህይወት ዛፍ ፍሬ ሲቀምስ የተሰማው ይህ ነው። እንዲህ አለ “ከዚህች ፍሬ ስካፈልም ይህም ነፍሴን በደስታ ሞላው” (1 ኔፊ 8፥12፤ በተጨማሪም 11፥21–23 ተመልከቱ)።

ደግሞም ሌሂ “ቤተሰቦቼም ደግሞ [ፍሬውን] ይካፈሉት ዘንድ መመኘት ጀመርኩ” (1 ኔፊ 8፥12) በማለት በህይወታችን ደስታን የምናመጣበትን ሁለተኛ መንገድ ገልጧል።

ከበስተጀርባው ዛፍ ያለ አንድ እጅ ፍሬን ለሌላ እጅ ሲያሳልፍ

የህይውት ዛፍ፣ በካዙቶ ዩኦታ

ሌሎች ደስታን እንዲያገኙ መርዳት

ልክ እንደ ንጉስ ቢንያም ሰዎች፣ የኃጢአታችንን ስርየት ስንቀበል እና “የህሊና ሰላም” ስናገኝ “በደስታ [እንሞላለን]” (ሞዛያ 4፥3)። ወደ ውጭ ስንመለከት፣ የቤተሰብ አባላት እና ሌሎች ይህን ተመሳሳይ ደስታ እና ሰላም እንዲያገኙ ለመርዳት ስንፈልግ እንደገና ይሰማናል።

በወጣትነቱ፣ አልማ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በሚቃረን ሁሉ ነገር ደስታን ፈለገ። በመልአኩ ከተገሠጸ በኋላ፣ “[ሊሞት ሲል]” ሞዛያ 27፥28) በንስሃ እና በአዳኙ የተትረፈረፈ ጸጋ “ከመራራ” ወደ “መልካም” ረጅም መንገድ ተጓዘ። ከዓመታት በኋላ፣ አልማ ለልጁ ሔለማን በደስታ እንዲህ ሲል አወጀ፦

“እናም አቤቱ፣ እንዴት ያለ ደስታ ተሰማኝ፤ እናም ምን ዓይነት አስደናቂ ብርሃንን አይቻለሁ፤ አዎን፣ ነፍሴ በህመም እንደተሰቃየች ሁሉ ታላቅ በሆነም ደስታ ተሞላች! …

“አዎን፣ እናም ከዚያን ጊዜ እስከአሁን ድረስ እንኳን፣ ነፍሳትን ወደ ንስሃ አመጣ ዘንድ፣ እኔ ወደ ቀመስኩት ታላቅ ደስታ እነርሱንም እንዲቀምሱ አመጣቸው ዘንድ፣ …

“አዎን፣ እናም አሁን እነሆ ልጄ ሆይ፣ ጌታ በስራዬ ፍሬም እጅግ ታላቅ የሆነ ደስታን ይሰጠኛል።

“እኔ እንዳውቀው ባደረገው ቃል [የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል] የተነሳ፣ እነሆ ብዙዎች ከእግዚአብሔር ተወልደዋልና፣ እኔ የቀመስኩትን ቀምሰዋል፤ እናም እኔ የተመለከትኩትን ተመልክተዋል” (አልማ 36፥20፣ 24–26)።

በሌላ ጊዜ አልማ እንዲህ በማለት መስክሯል፦

“ይህም ምናልባት ጥቂት ነፍሳትን ወደ ንስሃው በማምጣት በእግዚአብሔር እጅ መሳሪያ እሆን ዘንድ በዚህ እመካለሁ።

“እናም እነሆ፣ ብዙዎቹ ወንድሞቼ በእውነት ንስሃ መግባታቸውን፣ እና ወደጌታ አምላካቸው መምጣታቸውን በተመለከትኩ ጊዜ፣ ከዚያም ነው ነፍሴ በደስታ የተሞላችው” (አልማ 29፥9–10)።

አልማ ነፍስን ወደ ክርስቶስ በማምጣት ሌሎች ሲሳካላቸው የተሰማውን ታላቅ ደስታ ማወጁን ቀጠለ፦

“ነገር ግን በራሴ ስኬታማነት ብቻ አልደሰትም፣ ነገር ግን በኔፊ ምድር በነበሩት ወንድሞቼ [የሞዛያ ወንድ ልጆች] ስኬታማነት ደስታዬ ይበልጥ ሙሉ ነው።

“እነሆ፣ እነርሱ እጅግ ሰሩም፣ በርካታ ፍሬን አምጥተዋልም፤ እናም ደመወዛቸው እንዴት ታላቅ ይሆናል!

“አሁን፣ የእነዚህን የወንድሞቼን ስኬት ባሰብኩ ጊዜ ነፍሴ ከስጋዬ እንደተለየች ያህል ትወሰዳለች፣ በመሆኑም ደስታዬም ታላቅ ነው” (አልማ 29፥14–16)።

ሌሎችን “በክርስቶስ ንፁህ ፍቅር” (ሞሮኒ 7፥47፤ በተጨማሪም ቁጥር 48ን ተመልከቱ) ስንወድ፣ ዳግም የተመለሰውን እውነት ለእነርሱ ስናካፍል እና ከቃል ኪዳኑ ሰዎች ጋር እንዲሰበሰቡ ስንጋብዛቸው ተመሳሳይ ደስታን ማግኘት እንችላለን።

አዳኙ በጌቴሴማኒ

አባቴ ሆይ፣ በሳይመን ዱዊ

በመከራ መካከል ደስታ

በምድር የሚያጋጥሙን መከራዎች እና ፈተናዎች ደስታችንን ይከለክላሉ ወይም ያጠፋሉ ብለን መፍራት የለብንም። አልማ ለሌሎች የነበረው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎቱ ዋጋ ያስከፈለው ሰው ነበር። በእስር፣ ረዘም ላለ ጊዜ በረሃብና በጥማት፣ በድብደባ፣ በህይወቱ ላይ አደጋ እንዲሁም በተደጋጋሚ መሳለቂያነት እና በተቃውሞ ተሰቃይቶ ነበር። ሆኖም፣ ሁሉም “በክርስቶስ ደስታ [ተውጦ]” ነበር (አልማ 31፥38)። ምናልባትም የአልማ ስቃይ፣ ተከትሎት የመጣውን ደስታ ታላቅ አድርጎታል።

ፕሬዘደንት ኔልሰን ደስታ በአዳኙ ስቃይ ወቅት ሚና እንደተጫወተ ያስታውሱናል—“በፊቱም ስላለው ደስታ [እርሱ] በመስቀል ታገ[ሰ]” (ዕብራውያን 12፥2)።

“ስለዚያ አስቡ! በምድር ላይ ካሉ የሚያሳቅቁ ተሞክሮዎችን ለመጽናት፣ አዳኛችን ያተኮረው በደስታ ላይ ነው።!

“በፊቱ ያለው ደስታ ምን ነበር? እርግጥም እኛን የማጽዳት፣የመፈወስ፣ እናም የማጠንከር ደስታ፤ ንስሃን ለሚገቡ የሚከፈለው የሃጢያት ክፍያ ደስታ፤ ለእኔና ለእናንተ ወደቤታችን—በንጽህና እና በብቁነት—ከሰማያዊ ወላጆቻችን እና ቤተሰቦቻችን ጋር ለመኖር እንድንመለስ የሚያስችል ደስታ ነው።

“ወደ እኛ ወይም ወደምንወዳቸው ሰዎች በሚመጣ ደስታ ላይ ካተኮርን አሁን በጣም የሚያስጨንቅ፣ የሚያም፣ የሚያስፈራ፣ ኢፍትሃዊ ወይም በቀላሉ የማይቻል የሚመስለውን መጽናት እንችላለን?” 2

ዘላቂ ደስታ የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በመጽናት እና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ በመርዳት ነው። ዘላቂ ደስታ የሚመጣው በእግዚአብሔር ፍቅር ስንኖር፣ ትእዛዛቱን ስንጠብቅ እና የአዳኙን ጸጋ ስንቀበል ነው። በወንጌል መንገድ፣ በጉዞው ውስጥ እንዲሁም በስተመጨረሻ ደስታ አለ። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የዕለት ተዕለት የደስታ መንገድ ነው።

ማስታወሻዎች

  1. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አለምን ማሸነፍ እና እረፍትን ማግኘት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 97።

  2. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” Liahona፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 83።