“‘አስደሳች ህይወት’ [እየኖርኩ] ነውን?” ለወጣቶች ጥንካሬ, የካቲት 2024(እ.አ.አ).
ወርሀዊ የለወጣቶች ጥንካሬ መልዕክት፣ የካቲት 2024 (እ.አ.አ)
“አስደሳች ህይወት [እየኖርኩ]” ነውን?
ኔፊ ህዝቦቹ እንደኖሩ በተናገረበት መንገድ መኖር እንድትችሉ አንዳንድ ሀሳቦች እዚህ ይገኛሉ።
ከላማናውያን ተለይቶ ብዙም ሳይቆይ፣ ኔፊ ህዝቦቹ “አስደሳች ህይወት” እንደኖሩ ተናገረ (2 ኔፊ 5፥27)። እነርሱን ሊገድሉ የሚፈልግ ሌላ የሰዎች ቡድን እንዳሉ ከግምት ውስጥ ስናስገባ (2 ኔፊ 5፥1–6፣ 14 ተመልከቱ) ይህ ሊያስገርም ይችላል። በእንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ሰው እንዴት ደስተኛ ሊሆን ይችላል?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ “አስደሳች ህይወት [ኖሩ]” ማለት “እያንዳንዱ ኔፋያዊ ቀኑን እንዲሁም ሳምንቱን ሙሉ ደስተኛ ነበሩ” ማለት እንዳልሆነ አስተውሉ። በአጠቃላይ ወደ ደስታ የሚመራ አይነት ኑሮ እና ተግባር ፈጽመዋል ለማለት ነው። ፈተናዎች ቢኖሩባቸውም፣ በአጠቃላይ ጊዜያቸው አስደሳች ነበር።
ስለዚህ “አስደሳች ህይወት ምንድን ነው”? ፈታኝ በሆነው ህይወታችን ውስጥ እንዴት ልናበዛው እንችላለን? እስቲ እንመልከት!
-
ታዛዥ ሁኑ። “የጌታን ትእዛዝ … ለመጠበቅ ተቀበልን” (2 ኔፊ 5፥10)።
በወንጌል መኖር የመጀመርያው እርምጃ ነው። በኃጢያት ለጊዜው ደስተኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ፣ ነገር ግን ይህ ዘላቂ አይደለም። ሆን ብሎ እግዚአብሔርን አለመታዘዝ “አስደሳች ህይወት” አይደለም (አልማ 41፥10 ተመልከቱ)።
-
ቅዱሳት መጻህፍትን መርምሩ። “እኔ ኔፊ፣ በነሃስ ሰሌዳዎች ላይ የተቀረጹትን መዝገቦች … አመጣሁ” (2 ኔፊ 5፥12)። “እኛ … መርምረናቸዋል፣ እነሱም ጠቃሚ እንደሆኑ አዎን፣ ለእኛ ትልቅ ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ አግኝተናቸዋል” (1 ኔፊ 5፡21)።
የኔፊ ህዝቦች ቅዱሳት መጻህፍት ነበሯቸው። ነበሯቸው ብቻ ሳይሆን ይመረምሯቸውም ነበር።
-
መገለጥ የተቀበሉ መሪዎችን አድምጡ። “እኔ ኔፊ፣ ያዕቆብንና፣ ዮሴፍን በህዝቤ …ላይ ካህናትና መምህራን ይሆኑ ዘንድ ቀባኋቸው (2 ኔፊ 5፥26)።
እነዚህ አስተማሪዎች ቅዱሳት መጻህፍትን እንደ መመሪያ ተጠቅመዋል (2 ኔፊ 4፥15፤ 6፥4 ተመልከቱ)።
-
ወደ ቤተመቅደስ (እንዲሁም ወደ ሌሎች የተቀደሱ ቦታዎች) ሂዱ። “እኔ ኔፊ ቤተመቅደስን ሰራሁ” (2 ኔፊ 5:16)።
ደቀ መዛሙርት እንዲሰበሰቡ እና እንዲያመልኩ እንደ መሰብሰቢያ ቤቶች እና ቤተመቅደሶች ያሉ የተቀደሱ ቦታዎች መኖራቸው አስፈላጊ ነው። (ኔፋውያን ቤተመቅደስ ነበራቸው ብቻ ሳይሆን በእርግጥ ተጠቅመውት እንደነበር መገመት እንችላለን።) በቤተመቅደስ በአካል መገኘት ካልቻላችሁ የቤተሰብ ታሪክ ስራ ሁልጊዜ መስራት ትችላላችሁ።
-
ውጤታማ ሁኑ። “ህዝቤን ህንጻን እንዲሰሩ አስተማርኳቸው … እኔ … ህዝቤ ታታሪ እንዲሆኑና በእጃቸውም እንዲሰሩ አደረኩኝ” (2 ኔፊ 5፥15፣17)።
ማድረግ ያለብን ነገር መኖሩ በራሱ የ“አስደሳች ህይወት” አካል ነው! የተሰጠ ተግባር፣ ስራ፣ ሃላፊነት— (በእርግጥ ለመዝናናት ከተገቢው የእረፍት ጊዜ ጋር) ትኩረት እና አላማ የሚሰጥ ነገር። ሁል ጊዜ ድብርት የሚሰማችሁ ከሆነ ደስተኛ መሆን ከባድ ነው።
አሁን እየኖራችሁ ያለው ህይወት አስደሳች ነው ትላላችሁን? ካልሆነ፣ ምናልባት የኔፊ ምሳሌ እንዴት ማሻሻል እንድምትችሉ አንዳንድ ሃሳቦችን ሊሰጣጥችሁ ይችላል።
© 2024 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. በዩ.ኤስ.ኤ ውስጥ የታተመ። እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። Monthly For the Strength of Youth Message, February 2024 ትርጉም። Language. 19276 506