“ግንቦት 19–25፦ ‘ከእግዚአብሔር የሆነው ብርሀን ነው’፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49–50፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49–50፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
ግንቦት 19–25፦ “ከእግዚአብሔር የሆነው ብርሀን ነው”
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49–50
አዳኙ የእኛ “መልካም እረኛ” ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥44)። አንዳንድ ጊዜ በጎች ሊጠፉ እንደሚችሉና ምድረበዳውም ብዙ አደጋዎች እንዳሉበት ያውቃል። ስለዚህም በፍቅር ወደ ትምህርቱ ደህንነት ይመራናል። “አለምን የሚያታልሉ፣ በምድር ውስጥ የሚሄዱ፣ ብዙ የሀሰት መናፍስት የሆኑ መናፍስት” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥2) ከመሳሰሉት አደጋዎች ያርቀናል። አብዛኛውን ጊዜ እሱን መከተል ማለት የተሳሳቱ ሃሳቦችን እና ልማዶችን መተው ማለት ነው። ይህ ለሊመን ኮፕሌይ እና በኦሃዮ ለነበሩ ለሌሎች እውነት ነበር። ዳግም የተመለሰውን ወንጌል ተቀብለው ነበር፣ ነገር ግን አሁንም ትክክል ያልሆኑ አንዳንድ እምነቶችን እንደያዙ ነበር። ጌታ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49 ውስጥ እንደ ጋብቻ እና የአዳኙ ዳግም ምፅዓት በመሳሰሉ ርዕሶች ላይ የሊመንን የቀድሞ እምነቶች የሚያስተካክሉ እውነቶችን አሳውቋል። የኦሃዮ አዳዲስ አባላት “የማይገባቸውን መናፍስት ሲቀበሉ፣” የመንፈስን እውነተኛ መገለጫዎች እንዴት ማስተዋል እንደሚችሉ ጌታ አስተማራቸው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥15)። መልካሙ እረኛ “በጸጋ እና በእውነት እውቀትም ማደግ” ያለብንን እኛን “[ህፃናቱን]” ይታገሠናል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥40)።
በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች
ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን ወንጌል እውነት እንድቀበል ይፈልጋል።
ሊመን ኮፕሊ፣ ቤተክርስቲያኗን ከመቀላቀሉ በፊት በተለምዶ ሼከርስም ተብለው የሚጠሩ የዩናይትድ ሶሳይቲ ኦፍ ብሊቨርስ ኢን ክራይስትስ ሰክንድ አፒሪንግ የሀይማኖት ቡድን አባል ነበር ከሊመን ጋር ከተነጋገረ በኋላ፣ ጆሴፍ ስሚዝ ከጌታ ስለሼከርስ አንዳንድ አስተምህሮዎች ማብራሪያ ጠየቀ። ጌታም በክፍል 49 ውስጥ ባለው ራዕይ በኩል ምላሽ ሠጠ። የተወሰኑት የሼከሮች እምነቶች በክፍሉ መግቢያ ውስጥ ተጠቅሰዋል።
ጌታ በክፍል 49 ውስጥ የሼከሮቹን እምነት ለማስተካከል ምን አስተማረ? በዚህ ራዕይ ውስጥ የእርሱ እውነት ሙላት ለሌላቸው ሰዎች ስለሚያሳየው ፍቅር እና አሳቢነት ምን ማስረጃ ታያላችሁ? በፍቅር እና በአሳቢነት ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?
በቁጥር 2 ውስጥ ስላለው የጌታ እይታ ያስደነቃችሁ ምንድነው? የአንድን ፊልም የተወሰነ ክፍል ብቻ ብትመለከቱ፣ የአንድን የመገጣጠም ጨዋታ አንድ ክፍል ብታዩ ወይም የአንድን ወገን የክርክር ክፍል ብትሰሙ ሊሆን ከሚችለው ጋር ልታወዳድሩት ትችላላችሁ። የጌታ ማስጠንቀቂያ ከትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥24 ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ከጌታ ተጨማሪ ብርሃን ለማግኘት ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ አስቡ።
በተጨማሪም “Leman Copley and the Shakers፣” በRevelations in Context፣ 117–7 ውስጥ ተመልከቱ።
በወንዶች እና ሴቶች መካከል የሚፈፀም ጋብቻ ለእግዚአብሔር እቅድ አስፈላጊ ነው።
የሰማይ አባትን ዕቅድ ለማዳከም በሚያደርገው ጥረት፣ ሰይጣን ስለ ጋብቻ ግርታን ለመፍጠር ይፈልጋል። በሌላ በኩልም፣ ጌታ በነቢያቱ በኩል ስለ ጋብቻ እውነትን መግለፁን ቀጥሏል። አንዳንድ እውነቶችን በ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49፥15–17፤ በ ዘፍጥረት 2፥20–24፤ 1 ቆሮንቶስ 11፥11፤ እና በ “ቤተሰብ፦ ለዓለም የተላለፈ ዓዋጅ” ውስጥ ልታገኙ ትችላላችሁ። ያገኛችኋቸውን እውነቶች ዝርዝር አዘጋጁ። ጋብቻ ለእግዚአብሔር እቅድ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ሽማግሌ ዩልሲስ ሶሬስ “ዳግም የተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በምድራዊ እና በዘለዓለም ህይወት በሴት እና ወንድ መካከል ያለውን የሙሉ አጋርነት መርህ ያውጃል” ሲሉ አስተምረዋል (“In Partnership with the Lord፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022(እ.አ.አ)፣ 42)። “በወንድና በሴት መካከል ያለውን አጋርነት የሚያጠናክሩ” መርሆዎችን በመፈለግ መልእክቱን ማጥናት ትችላላችሁ። እነዚህን መርሆዎች በህይወታችሁ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? የሌላ እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ጋብቻ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ቢጠይቃችሁ ምላሽ የምትሠጡት እንዴት ነው? ለዚህ ግንዛቤ አመስጋኝ የሆናችሁት ለምንድን ነው?
በተጨማሪም Topics and Questions፣ “Marriage፣” “Family፣” ፤ወንጌል ላይብረሪ ዴቪድ ኤ. ቤድናር፣ “Marriage Is Essential to His Eternal Plan፣” ኤንዛይን፣ ሰኔ 2006 (እ.አ.አ)፣ 83–84፤ “Renaissance of Marriage” (ቪዲዮ)፣ ወንጌል ላይብረሪ።
የጌታ ትምህርቶች ከሰይጣን ማታለል ሊጠብቁኝ ይችላሉ።
በኦሃዮ የነበሩ አዳዲስ አባላት በቅዱሳት መጻህፍት ቃል የተገቡትን የመንፈሥ መገለጫዎች ለመቀበል ጓጉተው ነበር። ሆኖም ሰይጣንም ሊያታልላቸው ጓጉቶ ነበር። እነዚህ አባላት የመንፈስ ቅዱስን እውነተኛ መገለጫዎች እንዴት ለይተው ማወቅ እንደሚችሉ እንዲገነዘቡ እንድትረዷቸው ተጠይቃችሁ ቢሆን ኖሮ፣ ከትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50 ውስጥ ምንን ታጋራላችሁ (በተለይ ቁጥር 22–25፣ 29–34፣ 40–46ን ተመልከቱ)። አዳኙ በእውነት እና በሥህተት መካከል ያለውን ልዩነት እንድታውቁ የረዳችሁ እንዴት ነው?
በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 14፥1–28፤ 2 ጢሞቴዎስ 3፥13–17 ተመልከቱ።
አስተማሪዎች እና ተማሪዎች በጋራ በመንፈሱ ይታነጻሉ።
በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መኖር በቤት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ አስተማሪዎች እና ተማሪዎች ለመሆን ብዙ ዕድሎችን ይከፍታል። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥13–24ን ልታጠኑ የምትችሉበት አንደኛው መንገድ የአስተማሪ እና የተማሪ ምስልን በመሳል ነው። ከእያንዳንዱ ሥዕል አጠገብም ከእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ስለወንጌል መማር ማስተማር የሚያስተምሯችሁን ቃላት እና ሃረጋት በዝርዝር ፃፉ። በመማር ማስተማር ሂደት ላይ የመንፈሱን አስፈላጊነት ያስተማራችሁን ተሞክሮ ያገኛችሁት መቼ ነው? እንደ ወንጌል ተማሪ እና አስተማሪ ጥረታችሁን ለማሻሻል ምን ልታደርጉ እንደምትችሉ አስቡ።
“ከእግዚአብሔር የሆነው ብርሀን ነው።”
በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥23–25 ውስጥ ባሉት የጌታ ቃላት ላይ ስታሰላስሉ፣ የእግዚአብሔርን ብርሃን በህይወታችሁ እንዴት እንደምትቀበሉ እና ጨለማን እንዴት እንደምታስወግዱ አስቡ። ለምሳሌ፣ እነዚህ ጥቅሶች ጊዜያችሁን እንዴት እንደምታሳልፉ፣ ምን ዓይነት መዝናኛ ወይም ሜዲያ እንደምትፈልጉ፣ እንዲሁም በየትኞቹ ውይይቶች ላይ እንደምትሳተፉ፣ ምርጫዎቻችሁን የሚመሩት እንዴት ነው? እነዚህ ጥቅሶች በሌሎች በየትኞቹ ውሳኔዎቻችሁ ሊረዷችሁ ይችላሉ? እንደ “The Lord Is My Light፣” (መዝሙር፣፣ ቁጥር 89) ዓይነት መዝሙር ተጨማሪ ሃሳቦችን ሊያነሳሳ ይችላል።
በተጨማሪም “Walk in God’s light” የሚለውን በለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ፣ 16–21 ተመልከቱ።
ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች
ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል እችላለሁ።
-
በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ያሉትን መርሆዎች ለልጆቻችሁ ለማስተማር፣ አራት የወረቀት የእግር አሻራዎችን እና በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን፣ ንስሐን፣ ጥምቀትን፣ እና መንፈስ ቅዱስን መቀበልን የሚወክሉ አራት ሥዕሎችን ልታዘጋጁ ትችላላችሁ (በዚህ ሣምንት የአክቲቪቲ ገጽ ውስጥ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከቱ)። ልጆቻችሁ የእግር አሻራዎቹን ከሥዕሎቹ አጠገብ መሬት ላይ ማስቀመጥ ይችላሉ። ከዚያም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49፥12–14ን በምታነቡበት ጊዜ፣ ተራ በተራ በእግር አሻራዎቹ ላይ ሊራመዱ ይችላሉ። በእነዚህ ሥዕሎች ውስጥ ያሉትን ነገሮች ስናደርግ ኢየሱስ ክርስቶስን እየተከተልን እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው።
-
ልጆቻችሁ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49፥12–14ን ከየሐዋርያት ሥራ 2፥38 እና ከአራተኛው የእምነት አንቀፅ ጋር እንዲያነፃፅሩ ልትጋብዟቸውም ትችላላችሁ። ምን ተመሳሳይነትን ያገኛሉ? እነዚህ እውነቶች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
በወንድ እና ሴት መካከል የሚደረግ ጋብቻ ለእግዚአብሔር እቅድ አስፈላጊ ነው።
-
እነዚህን ጥቅሶች ለማስተዋወቅ ሼከሮች ሰዎች ማግባት እንደሌለባቸው የሚያምኑ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንደነበሩ ልታብራሩ ትችላላችሁ (የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49 የክፍል መግቢያን ተመልከቱ)። ልጆቻችሁ፣ ጌታ ስለጋብቻ ያስተማራቸውን ነገሮች በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 49፥15–17 ውስጥ እንዲፈልጉ ጋብዟቸው። “ጋብቻ ከእግዚአብሔር የተሠጠ ነው” ማለት ምን ማለት ነው? ምናልባት “ቤተሰብ፦ ለአለም የተላለፈ አዋጅን” የመጀመሪያ ሦስት አንቀጾች አብራችሁ ልታነቡ ትችላላችሁ። ከዚያም ጋብቻ እና ቤተሰብ ለሰማይ አባት ለምን እንደሚያስፈልጉ ተናገሩ።
“ከእግዚአብሔር የሆነው ብርሀን ነው።”
-
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥23–25ን ለማስተዋወቅ፣ በብርሃን እና በጨለማ መካከል ስላለው ልዩነት ከልጆቻችሁ ጋር ተነጋገሩ። ብርሃን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በ“Walk in God’s light” ውስጥ የመጀመሪያውን አንቀፅ ከለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ (ገፅ 17) ውስጥ፣ እንዲሁም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥23–25ን አብራችሁ ልታነቡ ትችላላችሁ። የእግዚአብሔርን ብርሃን ስለምንቀበልባቸው መንገዶች እና ጨለማን ስለምናስወግድባቸው መንገዶች ተነጋገሩ። ከዚያም እንደ “Shine On” (የልጆች የመዝሙር መጽሐፍ፣ 144) ያለ ስለመንፈሳዊ ብርሃናቸው የሚናገር መዝሙር አብራችሁ መዘመር ትችላላችሁ።
ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኛዬ ነው።
-
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥40–46ን አብራችሁ ካነበባችሁ በኋላ፣ በዚህ መዘርዝር መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የአዳኙን ምስል ማሳየት እና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ትችላላችሁ፦ እረኛ ስለ በጎቹ ምን ይሰማዋል? አዳኙ እንደ እረኛ የሆነልን እንዴት ነው?