“ግንቦት 26–ሰኔ 1፦‘ታማኝ፣ ሐቀኛ፣ እና ብልህ መጋቢ’፦ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51–57፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦችና ለቤተሰቦች፦ ትምህርትና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51-57፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
ግንቦት 26–ሰኔ 1፦ “ታማኝ፣ ሐቀኛ፣ እና ብልህ መጋቢ“
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51–57
በ1830ዎቹ (እ.አ.አ) ለነበሩት የቤተክርስቲያኗ አባላት፣ ቅዱሳኑን መሰብሰብ እና የፅዮንን ከተማ መገንባት፣ ከብዙ ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥባቸው ከሚገቡ ነገሮች ጋር መንፈሳዊም ስጋዊም ስራ ነበር፦ አንድ ሰው ቅዱሳን ሊሰፍሩ የሚችሉበትን መሬት መግዛት እና ማከፋፈል ነበረበት። አንዱ መጻህፍትን እና ሌሎች ህትመቶችን ማሳተም ነበረበት። አንዱ ደግሞ በፅዮን ለሚገኙ ሠዎች ቁሳቁስ ለማቅረብ የመጋዘን ስራን ማካሄድ ነበረበት። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51–57 ውስጥ በተመዘገቡት ራዕዮች፣ እነዚህን ስራዎች የሚሰሩ ሰዎችን ጌታ መድቧል እንዲሁም መመሪያ ሰጥቷል።
ነገር ግን በፅዮን የእነዚህ ነገሮች ክህሎቶች የሚያስፈልጉ ቢሆኑም፣ እነዚህ ራዕዮች፣ ጌታ ቅዱሳኑ የፅዮን ህዝብ—የእርሱ ህዝብ—ለመባል በመንፈሳዊ ብቁ እንዲሆኑ እንደሚፈልግም ያስተምራሉ። እያንዳንዳችን “ታማኝ፣ ሐቀኛ እና ብልህ መጋቢ፣” የተዋረደ መንፈስ ያለን፣ በተሾምንበት ስልጣን “[ጸንተን የምንቆም]” እንድንሆን ይጠራናል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51፥19፤ 52፥15፤ 54፥2 ተመልከቱ)። ያንን ማድረግ ከቻልን—ሥጋዊ ክህሎታችን ምንም ይሁን ምን—ጌታ ፅዮንን ለመገንባት ሊጠቀምብን ይችላል።
በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች
ጌታ ታማኝ፣ ሐቀኛ እና ብልህ መጋቢ እንድሆን ይሻል።
በ1831 (እ.አ.አ) የቤተክርስቲያኗ አባል የነበራችሁ ብትሆኑ ኖሮ፣ ንብረታችሁን በኤጲስ ቆጶሱ በኩል ለቤተክርስቲያኗ በማስረከብ የቅድስና ህግን እንድትኖሩ ትጋበዙ ነበር። ከዚያም፣ አብዛኛውን ጊዜ የሠጣችሁት ይመልስላችኋል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከሰጣችሁት በላይ ለእናንተ ይመልስላችኋል። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ንብረታችሁ አልነበረም—በመጋቢነት የምትጠብቁት እንጂ።
ዛሬ የአሰራር ቅደም ተከተሎቹ የተለዩ ናቸው፣ ነገር ግን መርሆዎቹ ዛሬም ለጌታ ስራ ወሳኝ ናቸው። ክፍል 51ን ስታነቡ፣ ጌታ ለእናንተ በአደራ ምን እንደሰጣችሁ አስቡ። በቁጥር 19 ውስጥ የሰፈረው “መጋቢ“ የሚለው ቃል እና በቁጥር 5 ውስጥ ያለው “በቅድስና … [መስጠት]” የሚሉት ቃላት እግዚአብሔር ከእናንተ ስለሚጠብቃቸው ነገሮች ምን ያመለክታሉ?
ፕሬዚዳንት ስፔንሰር ደብሊው. ኪምባል እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፦ “በቤተክርስቲያኗ ውስጥ፣ መጋቢነት ተጠያቂነት ያለበት የተቀደሰ መንፈሳዊ ወይም ሥጋዊ አደራ ነው። ሁሉም ነገሮች የጌታ ስለሆኑ፣ በአካላችን፣ በአእምሮአችን፣ በቤተሰባችን እና በንብረታችን ላይ መጋቢዎች ነን። (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 104፥11–15 ተመልከቱ።) ታማኝ መጋቢ በጽድቅ የሚያስተዳድር፣ ለራሱም የሚያስብ እንዲሁም ድሆችን እና የተቸገሩት የሚንከባከብ ነው” (“Welfare Services: The Gospel in Action፣” ኤንዛይን፣ ህዳር 1977 (እ.አ.አ)፣ 78)።
በተጨማሪም “The Law of Consecration” (ቪዲዮ)፣ የወንጌል ላይብረሪ ተመልከቱ።
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥9–11፣ 22–27
በምሄድበት ቦታ ሁሉ፣ ሌሎች ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመጡ መጋበዝ እችላለሁ።
ጌታ በርካታ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ወደ ሚዙሪ በላካቸው ጊዜ፣ በጉዞ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲጠቀሙ እና “እግረ መንገዳቸውን [እንዲሰብኩ]” ነገራቸው(ቁጥር 25–27)። ወንጌልን “እግረ መንገዳችሁን” ወይም በቀን ተቀን የህይወታችሁ ሁነቶች ውስጥ ማካፈል የምትችሉት እንዴት ነው?
ጌታ ከመታለል እንድርቅ ይረዳኛል።
ብዙ ሰዎች የመንፈስ መገለጫዎች አለን ይሉ ስለነበረ፣ የመጀመሪያዎቹ ቅዱሳን እንዳይታለሉ ይሰጉ ነበር። ጌታ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥14 ውስጥ ምን ማስጠንቀቂያ ሠጣቸው? የሠጠው መፍትሄስ ምን ነበር? ( ቁጥር 14-19 ተመልከቱ)።
ንድፍ በመደበኛነት እና ሊተነበይ በሚችል መልኩ የሚደጋገም ነገር ነው። በሙሉ ቁጥሮች መቁጠር ወይም በየቀኑ የፀሐይ መውጣት እና መጥለቅ በምሳሌነት ይካተታሉ። ምን ሌሎች ምሳሌዎችን ማሰብ ትችላላችሁ? እናንተ ትምህርትና ቃል ኪዳኖች 52፥14-19ን ስትመረምሩ፣ ጌታ መታለልን የሚያርቅበትን ንድፍ ለዩ። “መዋረድ” የትህትናን እና የንስሐን ስሜት እንደሚያመለክት፣ “የዋህ” ገርነትን እና ራስን መግዛትን እንደሚጠቁም፤ እንዲሁም “ማነጽ” ማለት ማስተማር፣ ማሻሻል ወይም መገንባት ማለት እንደሆነ ማስተዋሉ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የጌታ ንድፍ እነዚህን ባህርያት እንዲሁም መታዘዝን የሚያካትት የሚመስላችሁ ለምንድነው? ይህን ንድፍ ከመታለል ለመራቅ መጠቀም የምትችሉት እንዴት ነው?
በዘመናችን የመታለል ጥቂት ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? እየተታለልን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ለምሳሌ፣ የፊልሞች፣ የሙዚቃ እና የማህበራዊ ሚዲያዎች ምርጫዎቻችሁን “Walk in God’s light ” በሚለው በለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ፣16–21 ውስጥ ባሉት መሥፈርቶች መሠረት መገምገምን ታስቡ ይሆናል።
በተጨማሪም፣ ጌሪ ኢ. ስቲቨንሰን፣ “Deceive Me Not፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2019 (እ.አ.አ)፣ 93–96፤ “Guide Me to Thee፣” መዝሙር፣ ቁጥር 101፤ Topics and Questions፣ “Seeking Truth and Avoiding Deception፣” የወንጌል ላይብረሪ ተመልከቱ።
በሌሎች ሰዎች ምርጫ በምጎዳበት ጊዜ ወደ ጌታ ለመመለስ እችላለሁ።
የምትተማመኑበት ሰው ቃሉን ባለመጠበቁ ምክንያት ተስፋ ቆርጣችሁ ታውቃላችሁ? ይህ የተከሠተባቸው በኦሃዮ ውስጥ በሚገኘው በሊመን ኮፕሊ መሬት ላይ እንደሚሰፍሩ ሲጠብቁ በነበሩት የኮልስቪል፣ ኒው ዮርክ ቅዱሳን ላይ ነው። ከዚህ ተሞክሮ ለመማር የክፍል 54ን መግቢያ መከለስን አስቡ (በተጨማሪም saints፣ 1፥125–28፤ “A Bishop unto the Church፣” በRevelations in Context፣ 78–79 ውስጥ ተመልከቱ)። በኮልስቪል ከሚገኙ ቅዱሳን መካከል ጓደኛ ቢኖራችሁ ኖሮ፣ በክፍል 54 ውስጥ ለእነሱ የምታካፍሉት ምን ምክር ማግኘት ትችላላችሁ?
በልባቸው ንጹህ የሆኑ የተባረኩ ናቸው።
በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጌታ ለሃብታሙም ለድሃውም ተናግሯል፤ ለእነዚህ ሁለቱም ቡድኖች የሰጠውን ምክር ማነፃጸር አስደሳች ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለእናንተ በግል የሚጠቅሙ የሚመስሉት የትኛዎቹ ናቸው?
ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች
ሐቀኛ መሆን እችላለሁ።
-
ልጆቻችሁ ሐቀኛ መሆን ምን ማለት እንደሆነ እንዲያውቁ ለመርዳት፣ “ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 56፥9ን አብራችሁ ማንበብ እንዲሁም ሃቀኝነታቸውን የሚመለከት ውሳኔ ማድረግ ስለሚጠበቅባቸው ልጆች ታሪኮችን ማካፈል ትችላላችሁ። ታሪኮቹን የበለጠ የሚስቡ ለማድረግ ሥዕሎችን፣ በካልሲ የሚሰሩ አሻንጉሊቶችን ወይም የወረቀት አሻንጉሊቶችን መጠቀም ትችላለህ። ታማኝ ለመሆን በምንጥርበት ጊዜ ጌታ ባርከን እንዴት ነው?
-
ከልጆቻችሁ ጋር ጨዋታ መጫወትን አስቡ። ከዚያም አንድ ሰው አጭበርብሮ ቢሆን ኖሮ ጨዋታው እንዴት ሌላ መልክ ሊይዝ ይችል እንደነበረ ተወያዩ። አንዱ ከሌላው ጋር “በቅንነት መስራት” አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥10፤ 53፥3፤ 55፥1
እጆችን በመጫን፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን እቀበላለሁ።
-
እጆችን በመጫን መንፈስ ቅዱስን መቀበል በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 51-57 ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ምናልባት ይህ ልጆቻችሁን ስለዚህ ሥርዓት ለማስተማር መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ አንድ ልጅ ማረጋገጫ ሲቀበል የሚያሣይ ምሥልን ሊመለከቱ እና በሥዕሉ ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ሊገልጹ ይችላሉ። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥10፤ 53፥3፤ 55፥1ን በሚያነቡበት ጊዜ፣ “እጆችን በመጫን” ወይም “እጅንም በመጫን” የሚሉትን ቃላት ሲሰሙ በእጆቻቸው እንዲያጨበጭቡ ጠይቋቸው።
-
“The Holy Ghost፣ ”(የልጆች መዝሙር መጽሃፍ፣ 105) የሚለውን መዝሙር ወይም ሌላ ተመሳሳይ መዝሙር ልትዘምሩም ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ በመዝሙሩ ውስጥ ስለ መንፈሥ ቅዱስ ስጦታ የሚያስተምሩ ቃላትን እና ሀረጎችን እንዲፈልጉ እርዷቸው።
እግዚአብሔር እንዳልታለል እኔን የሚረዳበት ንድፍ አለው።
-
ጌታ ማታለልን ለማስወገድ ስላለው ንድፍ ለማስተማር፣ ልጆች በተፈጥሮ፣ በቀለማት ባሸበረቁ ብርድ ልብሶች ላይ ወይም በልብሶች ላይ፣ ወይም በዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ያሉ ምሳሌዎችን እንዲፈልጉ በመርዳት መጀመር ትችላላችሁ። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥14–15ውስጥ ጌታ የሰጠውን ንድፍ እንዲያገኙ እርዷቸው። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ያሉትን ማናቸውንም የማይታወቁ ቃላት መረዳታቸውን አረጋግጡ። እውነትን ለማወቅ ይህን ንድፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
ሁል ጊዜ ቃል ኪዳኔን መጠበቅ አለብኝ።
-
በሊመን ኮፕሊ መሬት ላይ ለመኖር የመጡት ቅዱሳን ምን እንደሆኑ በራሳችሁ ቃላት ለልጆቻችሁ አካፍሉ (የክፍል 54 መግቢያን ተመልከቱ)። ልጆቻችሁ ወደ ኦሃዮ የደረሱ የቤተክርስቲያኗ አባላት እንደሆኑ ማስመሰል ይችላሉ። ሊመን ቃል ኪዳኑን ካፈረሰ በኋላ እንዴት ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል? ይህ ቃል ኪዳኖቻችንን ወይም ቃላችንን ስለመጠበቅ ምን ያስተምረናል? ቃል ኪዳናቸውን የሚጠብቁ ሰዎች የሚቀበሏቸውን በረከቶች ለማግኘት ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 54፥6 በጋራ አንብቡ።
እግዚአብሔር የሰጠኝን በረከቶች ሌሎችን ለመባረክ መጠቀም እችላለሁ።
-
ክፍል 55ን ለማስተዋወቅ፣ ዊልያም ደብሊው. ፌልፕስ ወንጌልን አጥንቶ ቤተክርስቲያኗን የተቀላቀለ ጋዜጣ አሳታሚ እንደነበር ማስረዳት ልትፈልጉ ትችሉ ይሆናል። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 55፥1–4ን ከልጆቻችሁ ጋር አንብቡና እግዚአብሔር ዊልያም እንዲያደርግ ይፈልግ የነበረውን እንዲያውቁ እርዷቸው። የዊሊያምን ችሎታዎች ለመጠቀም ያቀደው እንዴት ነበር? ይህ እግዚአብሔር ልጆቹን ለመባረክ ችሎታችንን እንድንጠቀም እንዴት ሊጋብዘን እንደሚችል ወደሚደረግ ውይይት ሊያመራ ይችላል።