ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021 (እ.አ.አ)
ሐምሌ 5–11 (እ.አ.አ)። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥ “ዋጋቸውም ታላቅ እና ክብራቸውም ዘለአለማዊ ይሆናል።”


“ሐምሌ 5–11 (እ.አ.አ)። ትምህርትና ቃል ኪዳኖች 76፥ ‘ዋጋቸውም ታላቅ እና ክብራቸውም ዘለአለማዊ ይሆናል’” ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021 (እ.አ.አ) [2020 (እ.አ.አ)]

“ሐምሌ 5–11 (እ.አ.አ)። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰብና ለቤተሰብ፥ 2021 (እ.አ.አ)

ምስል
የጠፈር ከዋክብቶች

መሸሸጊያ፣ በሼሊን ኤብል

ሐምሌ 5–11 (እ.አ.አ)

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76

“ዋጋቸውም ታላቅ እና ክብራቸውም ዘለአለማዊ ይሆናል”

ክፍል 76 ውስጥ፣ ጌታ ምን ለእኛ ያህል እውነትን ሊገልጽልን እንደሚፈልግ ገልጿል (ቁጥር 7–10)። ልታውቁ የሚያስፈልጋችሁን “የእግዚአብሔርን ነገሮች” (ቁጥር 12) ሊገልጥላችሁ እንደሚችል እና እንዳለ በማመን ቅዱሳት መጻህፍትን አንብቡ። “ገና በመንፈስ እያላችሁ” (ቁጥር 28፣ 80፣ 113) ያገኛችሁትን ግንዛቤ መዝግቡ።

ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ

“ከሞትኩኝ በኋላ ምን እሆናለሁ?” ከሞላ ጎደል በአለም ያለ እያንዳንዱ ሃይማኖት ይህንን ጥያቄ በአንድ ወይም በሌላ መልክ ይዳስሱታል። ለብዙ መቶ አመታት፣ ብዙ የክርስቲያን ባህሎች በመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ በመመርኮዝ፣ ስለመንግስተ ሰማይ እና ገሃነም እንዲሁም ገነት ለጻድቃን እና ሰቆቃ ለክፉዎች እንደሆነ አስተምረዋል። ነገር ግን፣ በእውነት መላው የሰው ልጅ ቤተሰብ በጣም ጥብቅ በሆኑ ጥሩ እና መጥፎ በሚባሉ ክፍሎች ሊከፈል ይችላልን? መንግስተ ሰማይ የሚለው ቃል በእርግጥ ምን ማለት ነው? በየካቲት 1832 (እ.አ.አ)፣ ጆሴፍ ስሚዝ እና ስድኒ ሪግደን በጉዳዩ ላይ ብዙ ሊታወቅ የሚችል ነገር ይኖር እንደሆነ ተጠራጠሩ (ትምህርትና ቃል ኪዳኖች 76 የክፍል መግቢያ ይመልከቱ)።

በእርግጥም ነበር። በእነዚህ ነገሮች ላይ እያሰላሰሉ ሳሉ፣ ጌታ “የመረዳት አይኖቻ[ቸውን] ነካ እናም ተከፈቱ” (ቁጥር 19)። ጆሴፍ እና ስድኒ በጣም አስደናቂ፣ ሰፋ ያለ፣ እና በጣም የሚያበራ ራዕይ ተቀበሉ እና ቅዱሳንም “ራዕዩ” ብለው ጠርተውት ነበር። የሰማይን መስኮቶች ወለል አድርጎ ከፈተ እናም ለእግዚአብሔር ልጆች አእምሮን የሚያሰፋ የዘለአለማዊነት እይታ ሰጣቸው። ራእዩ መንግስተ ሰማይ ታላቅ እና ሰፋ ያለ፣ እንዲሁም ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት የበለጠ መሆኑን ገልጿል። እግዚአብሔር ከምንረዳው በላይ ይቅር ባይ እና ፍትሃዊም ነው። እናም የእግዚአብሔር ልጆች ከምናስበው በላይ የላቀ ክብራማ ዘለአለማዊ ፍጻሜ አላቸው።

በተጨማሪም ቅዱሳን፣ 1፥147–50፤ “ራዕዩ፣” ራዕይ በአገባብ፣ 148–54 ይመልከቱ።

ምስል
የግል ጥናት ምልክት

ለግል የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ሃሳቦች

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76

መዳን የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእግዚአብሔር ልጅ በኩል ነው።።

ክፍል 76 ውስጥ የተገለጸውን ራዕይ ውልፈርድ ውድረፍ ሲያነቡ፣ እንዲህ አሉ፣ “ከዚህ በፊት በህይወቴ ወድጄው ከማውቀው በላይ ጌታን የመውደድ ፍላጎት አደረብኝ” (“በዳግም የመመለስ ድምጾች” ከዚህ መዘርዝሮች መጨረሻ ላይ ይመልከቱ)። ይህንን ራዕይ ስታነቡ ምናልባት እናንተም ተመሳሳይ ስሜቶች ነበሯችሁ። በክፍል 76 ውስጥ የተገለጹት አስደናቂ በረከቶች ከአዳኝ ውጪ ሊኖሩ አይችሉምና። ምናልባት በክፍል 76 ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚጠቅሱትን እያንዳንዱን ጥቅስ መለየት ትችላላችሁ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ እርሱ እና በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ ስላለው ሚና ምን ያስተምሯችኋል? ስለእርሱ ባላችሁ ስሜት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? ስታነቡ እና ሰታሰላስሉ፣ “የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነት እንደምትቀበሉ” እና ይበልጥ ”ደፋር” እንደምትሆኑ ማረጋገጫዎችን ልትቀበሉ ትችላላችሁ።(ቁጥሮች 51፣ 79)

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥39–44፣ 50–112።

እግዚአብሔር “ሁሉም የእጆቹ ስራዎች“ እንዲድኑ ይፈልጋል።

አንዳንድ ሰዎች፣ የመጀመሪያዎቹን የቤተክርስቲያን አንዳንድ አባላት ጨምሮ፣ በክፍል 76 ውስጥ ያለውን ራዕይ ተቃውመዋል፣ ይህም ሁሉም እንደሚድኑ እና የተወሰነ የክብር ደረጃ እንደሚቀበሉ ያስተምር ነበርና። ተቃውሟቸው በከፊል እግዚአብሔርን እና ከእኛ ጋር ያለውን ዝምድና በትክክል ካለማወቅ የመጣ ሊሆን ይችላል። ይህንን ራዕይ ስታነቡ፣ ስለእግዚአብሔር ባህርይ እና ለልጆቹ ስላለው እቅድ ምን ትማራላችሁ?

በመዳን (ከአካላዊ እና ከመንፈሳዊ ሞት፤ ቁጥሮች 39፣ 43–44 ይመልከቱ) እና ከፍ ከፍ በመደረግ (ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እና እንደ እርሱ መሆን፤ ቁጥሮች 50–70 ይመልከቱ) መካከል ያለውን ልዩነት አስቡ።

ደግሞም ዮሀንስ 3፡16–17ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 132፥20–25 ይመልከቱ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥50–70፣ 92–95።

ሰማያዊ አባቴ ዘለአለማዊ ህይወትን በሰለስቲያል መንግስት ውስጥ እንድቀበል ይፈልጋል።

ለሰለስቲያል መንግስት ብቁ ስለመሆናችሁ ወይም ስላለመሆናችሁ—አስባችሁ —ተጨንቃችሁ—ታውቃላችሁን? ይህንን ክብር ስለሚቀበሉት ዝርዝር መገለጫቸውን ስታነቡ (ቁጥሮች 50–70፣ 92–95 ይመልከቱ)፣ ማድረግ ያለባችሁን ነገሮች ዝርዝር ብቻ ከመፈለግ ይልቅ፣ እንደእርሱ እንድትሆኑ ሊረዳችሁ እግዚአብሔር ምን ሰርቶ እንደነበር፣ እንዲሁም ምን እየሰራ እንደሆነ ፈልጉ። ራእዩን በዚህ መንገድ ማንበባችሁ ስለ ግል ጥረታችሁ በሚሰማችሁ ስሜት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራልን?

ደግሞም ስለሰለስቲያል መንግስት እነዚህን ዝርዝሮች ማወቅ እንዴት ታላቅ በረከት እንደሆነ ልታስቡ ትችላላችሁ። ይህ የሰለስቲያል ክብር ራዕይ ኑሯችሁን በምትመለከቱበት መንገድ እና የዕለት ተዕለት ሕይወታችሁን እንዴት ለመኖር እንደምትፈልጉ ባላችሁ አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

በተጨማሪም ሙሴ 1፥39፤ ጆይ ዲ. ጆንስ “ዋጋ ከመጠን በላይ፣” ኢንዛይን ወይም ሊያሆና፣ ህዳር 2017 (እ.አ.አ)፣ 13–15፤ ጄ. ደቭን ኮርኒሽ፣ “እኔ በቂ ነኝ ወይ? እደርሳለው ወይ?ኢንዛይን ወይም ሊያሆና፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 32–34 ይመልከቱ።

ምስል
የአስራ ዘጠነኛው መቶ አመተ ምህረት ቤት ክፍል

ጆሴፍ ስሚዝ የክብር ደረጃዎችን ራዕይ ያየው በዚህ ቤት ውስጥ ነው።

ምስል
የቤተሰብ ጥናት ምልክት

ለቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናትና ለቤተሰብ የቤት ምሽት ሃሳቦች

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥22–24፣ 50–52፣ 78–79፣ 81–82ከእነዚህ ጥቅሶች ስለምስክርነታችን ጠቃሚነት ምን እንማራለን? ምስክርነቶቻችን በዘለአለማዊ እጣ ፈንታችን ምን ሚና ይጫወታሉ? ደፋር የሚለውን ቃል ትርጉም መፈለግ “በኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ደፋር እንድትሆኑ” (ቁጥር 79) ለመወያየት ሊጠቅም ይችላል። “ጀግና እሆናለሁ ፣” የሚለውን መዝሙር ልትዘምሩ ትችላላችሁ (የልጆች መዝሙር መጽሃፍ፣ 162)።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥24ቤተሰባችሁ በክፍል 76ውስጥ ያለውን እውነት እና እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ በሚለው መዝሙር ውስጥ ባሉት ትምህርቶች መካከል ያለውን ተዛምዶ ልታስተውሉ ትችላላችሁ (የልጆች መዝሙር መጽሃፍ፣ 2–3)፤ ከእነዚህ እውነቶች አንደኛው በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥24 ውስጥ ይገኛል። እያንዳንዳችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ብንገነዘብ ዓለም እንዴት አሁን ካለችበት የተለየች ትሆን ነበር? ይህ እውነት ከሌሎች ጋር ባሉን ግንኙነቶች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ምናልባትም በዚህ ምድር ላይ ያሉትን የተለያዩ የእግዚአብሔር ወንድና ሴት ልጆች ስዕሎች መመልከቱ ቤተሰባችሁ በዚህ ጥያቄ ላይ እንዲያሰላስሉ ሊረዳቸው ይችላል? (“ቪድዮ አቅራቦት፥ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፣” ChurchofJesusChrist.org ይመልከቱ።)

እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” የሚለውን መዝሙር በጋራ መዘመር እና በክፍል 76 ውስጥ ከሚገኙት መርሆች ጋር የሚገናኙ ሌሎችን ለመፈለግ አስቡበት (ለምሳሌ ቁጥር 12፣ 62፣ 96 ይመልከቱ)።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥40–41በእነዚያ ቁጥሮች ውስጥ ያሉትን “የምስራቾች” (ቁጥር 40) ወይም መልካም ዜናዎች ጠቅለል አድርገን በአጭሩ በጋዜጣ አርዕስት ወይም በትዊተር መግለጽ ቢኖርብን፣ ምን እንላለን? በክፍል 76 ውስጥ ምን ሌላ የምስራቾችን እናገኛለን?

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፥50–70በሰለስቲያል መንግሥት ውስጥ የዘላለምን ህይወት በጉጉት ለመጠበቅ እና ለማዘጋጀት ቤተሰባችሁን እንዴት ትረዳላችሁ? በትምህርትና ቃል ኪዳኖች 76፥50–70 ውስጥ ከሚገኙት ሃረጎች ጋር የሚገናኙ ምስሎችን፣ የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችን፣ እና ነቢያዊ ትምህርቶችን ለማግኘት አብራችሁ ልትሰሩ ትችላላችሁ። እነዚህን ነገሮች በChurchofJesusChrist.org የቤተክርስቲያን መጽሄቶች ውስጥ ልታገኙ ትችላላችሁ። ከዚያም እነዚህን ስዕሎች፣ የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችን፣ እና ትምህርቶች ቤተሰባችሁን ዘለአለማዊ ግቦቻችሁን ሊያስታውሳቸው በሚችል ፖስተር ላይ ልትሰበስቡ ትችላላችሁ።

ልጆችን ለማስተማር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት፣ የዚህን ሳምንት ዝርዝርኑ፣ ተከተሉኝ—ለመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ይመልከቱ።

የሚመከር መዝሙር፥ “አዳኝ እንዳለ አውቃለሁ፣” መዝሙሮች፣ ቁጥር 136።

ምስል
በዳግም የመመለስ ድምጾች ምልክት

በዳግም የመመለስ ድምጾች፥ “የራዕዩ“ ምስክርነቶች

ውልፈርድ ውድረፍ

ውልፈርድ ውድረፍ ጆሴፍ ስሚዝ እና ስድኒ ሪግደን በትምህርት እና ቃልኪዳኖች 76 ውስጥ የሚገኘውን ራእይ ከተቀበሉ ከሁለት አመት በኋላ በታህሳስ 1833 (እ.አ.አ) በቤተክርስቲያኗ ተቀላቀሉ። በወቅቱ በኒው ዮርክ ይኖሩ ነበረ እናም በአካባቢው ከነበሩ ሚስዮናውያን ስለ “ራእዩ” አወቁ። ከዓመታት በኋላ በዚህ ራዕይ ላይ ስለነበራቸው ግንዛቤ ተናግረዋል።

“ከልጅነቴ ጀምሬ አንድ መንግስተ ሰማይ እና አንድ ሲኦል እንዳለ ነበር የተማርኩት እናም ክፉዎች አንድ አይነት ቅጣት እንዲሁም ጻድቃን አንድ ክብር … እንዳላቸው ተነግሮኝ ነበር።

“… ራዕዩን ሳነብ …፣ አዕምሮዬን አበራልኝ እንዲሁም ታላቅ ደስታ ሰጠኝ፣ ይህን መርህ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ጥበበኛ፣ ፍትሃዊ እና እውነተኛ፣ ሁለቱንም ምርጥ ባህሪዎች እና የእውቀት ባለቤት እንደሆነ ተገለጠልኝ፤ እርሱ ከፍቅር፣ ምሕረት፣ ፍትህ እና ከፍርድ ጋር የማይለዋወጥ እንደሆነ ተሰማኝ እናም በህይወቴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጌታን እንደወደድኩት ተሰማኝ።”1

“ይህ ‘መግለጫ’ በማንኛውም መጽሐፍ ውስጥ ካለው ከማንኛውም ራዕይ የበለጠ ብርሃን፣ የበለጠ እውነት እና የበለጠ መርህ የሚሰጥ ራዕይ ነው። አሁን ስላለንበትን ሁኔታ፣ ከየት እንደመጣን፣ ለምን እዚህ እንደመጣንና የት እንደምንሄድ ያለንን ግንዛቤ ግልፅ ያደርገዋል። ማንኛውም ሰው በዚያ ራዕይ አማካኝነት የእርሱ ክፍል እና ሁኔታ ምን እንደሆነ ሊያውቅ ይችላል።”2

“ጆሴፍን ከማየቴ በፊት ስለዕድሜው ወይም ምን ያህል ትልቅ ወይ ትንሽ እንደሆነ ግድ አልነበረኝም። ምን ይመስል እንደነበረ፣ ጸጉሩ ረዥም ይሁን አጭር፣ ግድ አልነበረኝም፤ ያንን ራዕይ የተቀበለ ሰው የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር። እኔ ለራሴ አውቄዋለሁ።”3

ፊቢ ክሮዝቢ ፔክ

ፊቢ ፔክ ጆሴፍ እና ስድኒ “ራዕዩን“ ሲያስተምሩ ስትሰማ፣ በምዙሪ ትኖር የምትኖር እና በነጠላ ወላጅነትም አምስት ልጆችን ታሳድግ ነበር። ራዕዩ ስለመሰጣት እና ስላነቃቃት ከዘመዶችዋ ጋር የተማረችውን ለማካፈል የሚከተለውን ጻፈች፥

“ጌታ የሰማያዊ መንግስቱን ሚስጥሮች ለልጆቹ እየገለጸ ነው።… ጆሴፍ ስሚዝ እና ስድኒ ሪግደን ባለፈው ጸደይ ወቅት ጎበኙን፣ እንዲሁም እዚህ ሳሉ ብዙ አስደሳች ስብሰባዎች ነበሩን፣ እናም ብዙ ሚስጥሮች ለእኛ እይታ ተገልጠውልን ነበር፤ ይህም ለእኔ ትልቅ ማበረታቻ ሰጥቶኝ ነበር። ለልጆቹ የሰላም ማረፊያ ስፍራን በማዘጋጀቱ የእግዚአብሔርን ትህትና ማየት እንችላለን። የወንጌሉን ሙላት የማይቀበል እና ለክርስቶስ መልካም ስራ እንደ ጀግና ወታደሮች የማይቆም ሁሉ በአብ እና በወልድ ፊት መኖር አይችልም። ሆኖም ለማይቀበሉት ሁሉ የተዘጋጀ ቦታ አለ፣ ነገር ግን በሰለስቲያል መንግሥት ውስጥ ከመኖር በጣም ያነሰ ክብር ያለው ቦታ ነው። አሁን በህትመት ላይ ስለሆኑ እና ወደ ዓለምም እየሄዱ ስለሆነ ስለ እነዚህ ነገሮች በተመለከተ ሌላ ምንም ለመናገር አልሞክርም። እናም ምናልባት ራሳችሁ ለማንበብ ዕድል ይኖራችኋል፣ እናም ካነበባችሁ በጥንቃቄ እና በጸሎት ልብ እንደምታነቡት ተስፋ አደርጋለሁ፤ እነዚህ ነገሮች ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸውና። እነሱን እንድትመረምሩ እፈልጋለሁ፣ ምክንያቱም በዚህም ሆነ በሚመጣው አለም ለደስታችን አስተዋጽዖ የሚያደርገው እርሱ ነውና።”4

ማስታወሻዎች

  1. ንግግሮች፣” ዴዘረት ኒውስ፣ ግንቦት 27፣ 1857 (እ.አ.አ)፣ 91።

  2. ዴዘረት ኒውስ፣ ነሃሴ 3፣ 1881 (እ.አ.አ)፣ 481፤ እንዲሁም Teachings of Presidents of the Church: Wilford Woodruff [የቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንቶች አስተምህሮ፥ ውልፈርድ ውድረፍ [2004 (እ.አ.አ)]፣ 120–21

  3. “ንግግሮች፣” ሳምንታዊ ዴዘረት ኒውስ፣ መስከረም 5፣1891 (እ.አ.አ)፣ 322።

  4. የፊቢ ክሮዝቢ ፔክ ለአና ጆንስ የተላከ ደብዳቤ፣ ነሃሴ 10፣ 1882 (እ.አ.አ)፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ ቤተመጽሃፍት፣ ሶልት ሌክ ሲቲ፤ አጻጻፉ እና ስርዐተ ነጥቡ ዘመናዊ ተደርጓል።

ምስል
ሦስት የክብር መንግሥታትን በንድፍ

ክብር በደረጃዎች፣ በአኒ ሄንሪ ናደር

አትም