“4. መሪነት እና ምክር ቤቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣” ከአጠቃላይ የመመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ [2023 (እ.አ.አ)]።
“4. መሪነት እና ምክር ቤቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣” ከአጠቃላይ የመመሪያ መፅሐፍ የተመረጡ
4.
መሪነት እና ምክር ቤቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን
4.0
መግቢያ
ከጌታ ስልጣን በተሰጣቸው አገልጋዮቹ መነሳሳት የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ሆናችሁ ተጠርታችኋል። የሰማይ አባትን “የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት የማምጣት” ሥራ የማገዝ እድል አላችሁ (ሙሴ 1፥39)።
4.2
የአመራር መርሆዎች በቤተክርስቲያኗ ውስጥ
በምድራዊ አገልግሎቱ ጊዜ፣ አዳኙ ለቤተክርስቲያኑ የመሪነት ምሳሌን ሰጥቷል። ዋና አላማው የሰማይ አባቱን ፈቃድ ማድረግ እና ሌሎች ወንጌሉን እንዲረዱ እንዲሁም እንዲኖሩት መርዳት ነበር (ዮሃንስ 5፥30፤ ሞዛያ 15፥7 ይመልከቱ)።
የጥሪያችሁን ግዴታዎች እንድትማሩ እና እንድታሟሉ ይረዳችሁ ዘንድ የጌታን መመሪያ ፈልጉ።
4.2.1
በመንፈስ ተዘጋጁ
ኢየሱስ ለምድራዊ አገልግሎቱ ራሱን በመንፈስ አዘጋጅቷል (ሉቃስ 4፥1–2)። እናንተም በተመሳሳይ መልኩ በጸሎት፣ በቅዱሳት መጻህፍት ጥናት እና ትዕዛዛቱን በመጠበቅ ወደ የሰማይ አባት ለመቅረብ በመንፈስ ተዘጋጁ።
የምትመሯቸውን ሰዎች ፍላጎት ለመረዳት እንዲሁም እግዚአብሔር እንድትሰሩ የጠራችሁን ስራ ለማከናወን ትችሉ ዘንድ ራዕይን ፈልጉ።
እንዲሁም ጌታ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለሚፈልጉ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 46፥8 ይመልከቱ)።
4.2.2
ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች አገልግሉ
ኢየሱስ እንዳደረገው የምታስተምሯቸውን ሰዎች ውደዱ። በእርሱ ፍቅር እንድትሞሉ “በሃይል በሙሉ ልባችሁ“ ጸልዩ (ሞሮኒ 7፥48)።
ግለሰቦች ጥልቅ መለወጥ እንዲያደርጉ እንዲሁም በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ እርዷቸው። የሚቀጥለውን ሥርዓት ሲቀበሉ ቃል ኪዳኖችን ለመግባት እንዲዘጋጁ እርዷቸው። የገቧቸውን ቃል ኪዳኖች እንዲጠብቁ እና የንስሃ በረከቶችን እንዲካፈሉ አበረታቷቸው።
4.2.3
የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል አስተምሩ
ሁሉም መሪዎች አስተማሪዎች ናቸው። አዳኙ የተወውን የአስተማሪነት ምሳሌ ለመከተል ጣሩ (ምዕራፍ 17፤ በአዳኙ መንገድ ማስተማር ይመልከቱ)። በንግግራችሁ እና በድርጊታችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እና የወንጌሉን መርሆዎች አስተምሩ (3 ኔፊ 11፥32–33፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥12–14)።
ከቅዱሳት መጻህፍት እና ከኋለኛው ቀን ነቢያት ቃሎች አስተምሩ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 52፥9ን ይመልከቱ)።
የቤተክርስቲያን ስብሰባን ወይም አክቲቪቲ እንድትመሩ ከተጠራችሁ ወይም ከተመደባችሁ፣ ትምህርቱ የሚያንፅ እንዲሁም አስተምህሮቱ ትክክል መሆኑን አረጋግጡ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 50፥21–23ን ይመልከቱ)።
4.2.4
በፅድቅ ምሩ
እያንዳንዱ የበላይ መሪ የክህነት ቁልፎችን በያዘው ሰው አመራር ስር ሆኖ ይመራል (3.4.1 ይመልከቱ)። ይህ መዋቅር የጌታ ሥራ በሚሰራበት ጊዜ ግልፅ የኃላፊነት መስመር እና ተጠያቂነት ያስገኛል።
የበላይ መሪ በጊዜያዊነት በበላይነት የመምራት የስራ ምደባን በውክልና ለሌላ ሰው ሊሰጥ ይችላል።
በቤተክርስቲያን ድርጅት፣ ስብሰባ ወይም አክቲቪቲ በበላይነት የሚመራ መሪ፣ የጌታ ዓላማዎች መፈጸማቸውን ያረጋግጣል። መሪው ይህንን ሲያደርግ የወንጌል መርሆችን፣ የቤተክርስቲያን ፖሊሲዎችን እና የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ይከተላል።
በበላይነት የመምራት ጥሪ ወይም የሥራ ምደባን መቀበል ተቀባዩን ሰው ከሌሎች የበለጠ አስፈላጊ ወይም ዋጋ ያለው አያደርገውም (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥109–10 ይመልከቱ)።
በጌታ ቤተክርስቲያን ውስጥ በማንኛውም ድርጅት መሪ ለመሆን መፈለግ ተገቢ አይደለም (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 121፥34–37 ይመልከቱ)።
4.2.5
ኃላፊነትን በውክልና ስጡ እንዲሁም ተጠያቂነትን አረጋግጡ
አዳኙ ለደቀ መዛሙርቱ ትርጉም ያላቸው የስራ ምደባዎችን እና ኃላፊነቶችን ሰጣቸው (ሉቃስ 10፥1 ይመልከቱ)። ለተሰጣቸው ሥራ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ዕድልም ሰጥቷቸው ነበር (ሉቃስ 9፥10ን ይመልከቱ)።
እንደመሪ፣ የስራ ምደባዎችን ለእነርሱ በውክልና በመስጠት ሌሎች እንዲያድጉ መርዳት ትችላላችሁ። ሁሉም አባላት የእግዚአብሔርን ስራ እንዲሰሩ ለማሳተፍ ጥረት አድርጉ።
የሥራ ምደባዎችን በውክልና መስጠት አገልግሎታችሁን ውጤታማ ያደርገዋል። ቅድሚያ በምትሰጧቸው ነገሮች ላይ ማተኮር ትችሉ ዘንድ ምን በውክልና እንደምትሰጡ ለማወቅ የመንፈስ ቅዱስን መመሪያ ፈልጉ።
4.2.6
ሌሎች መሪዎች እና አስተማሪዎች እንዲሆኑ አዘጋጁ
በቤተክርስቲያን ጥሪዎች ወይም በስራ ምደባዎች ማን ሊያገለግል ይችላል ብላችሁ ስታስቡ ጸልዩ። እንዲሠሩ ያዘዛቸውን ሥራ መስራት እንዲችሉ ጌታ የሚጠራቸውን ብቁ እንደሚያደርጋቸው አስታውሱ። በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸው፣ የጌታን እርዳታ በትህትና መፈለጋቸው እና ብቁ ለመሆን ጥረት ማድረጋቸው ነው።
4.2.7
ስብሰባዎችን፣ ትምህርቶችን እና አክቲቪቲዎችን ስታቅዱ ግልፅ ዓላማ ይኑራቸው
ግልፅ ዓላማ ያላቸውን ስብሰባዎች፣ ትምህርቶች እና አክቲቪቲዎችን በምታቅዱበት ጊዜ የመንፈስን ምሪት ፈልጉ። እነዚህ ዓላማዎች ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን የሚያጠናክሩ፣ ወደ ክርስቶስ የሚያቀርቡ እና የእግዚአብሔርን የደህንነት እና በዘለአለማዊ ህይወት ከፍ ከፍ የማድረግ ሥራ እንዲከናወን መርዳት አለባቸው (ምዕራፍ 1 እና2ን ይመልከቱ)።
4.2.8
ጥረቶቻችሁን መመዘን
እንደ መሪ፣ ኃላፊነቶቻችሁን እና መንፈሳዊ እድገታችሁን በየወቅቱ ገምግሙ። የምትመሯቸውን ሰዎች እድገትንም ለመመዘን አስቡ።
እንደመሪ ስኬታችሁ በዋነኝነት የሚለካው የእግዚአብሔር ልጆች ታማኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ባላችሁ ቁርጠኝነት ነው። መንፈሱ በእናንተ አማካኝነት ሲሰራ ከተሰማችሁ ጌታ በጥረቶቻችሁ ደስ እንደተሰኘ ልታውቁ ትችላላችሁ።
4.3
የቤተክርስቲያኗ ምክር ቤቶች
የእርሱ ቤተክርስቲያን መሪዎች ስራውን በሚሰሩበት ጊዜ በጋራ እንዲመክሩ ጌታ አዟቸዋል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 41፥2–3 ን ይመልከቱ)። የምክር ቤት አባላት የእግዚአብሔርን ልጆች ፍላጎት ለመረዳት እና ለማሟላት እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ሲያቅዱ፣ ራዕይን መቀበል ይችሉ ዘንድ ምክር ቤቶች እድሎችን ይሰጣሉ።
4.4
የውጤታማ ምክር ቤቶች መርሆዎች
4.4.1
የምክር ቤቶች ዓላማዎች
አባላት ሥርዓቶችን ይቀበሉ ዘንድ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ተያያዥ የሆኑትን ቃል ኪዳኖች እንዲጠብቁ ለመርዳት ምክር ቤቶች ልዩ አፅንዖት ይሰጣሉ።
4.4.2
የምክር ቤት ስብሰባዎች ዝግጅት
አመራሮች እና ምክር ቤቶች በየወቅቱ መገናኘት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ መሪዎች የምክር ቤት ስብሰባዎችን በሚያቅዱበት ጊዜ የጌታን መመሪያ ይሻሉ። ስለምን እንደሚወያዩ በሚወስኑበት ጊዜም የምክር ቤቱን አባላት አስተያየት ይቀበላሉ።
መሪዎች የመወያያ አጀንዳውን ለምክር ቤቱ አባላት አስቀድመው ያሳውቃሉ። የምክር ቤቱ አባላት በአጀንዳዎቹ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማካፈል ይዘጋጃሉ።
4.4.3
ውይይት እና ውሳኔዎች
በምክር ቤት ስብሰባ ወቅት መሪው (ወይም መሪው የሚመድበው ሰው) እየታየ ስላለው ጉዳይ ይገልጻል። ከዚያም መሪው ጥያቄዎችን በመጠየቅ እና ሀሳቦችን በመፈለግ ሁሉም የምክር ቤት አባላት በውይይቱ እንዲሳተፉ ያበረታታል።
አባላት ሃሳቦቻቸውን ያጋራሉ እንዲሁም እርስ በርስ በመከባበር ይደማመጣሉ። የጌታን ፈቃድ ለማወቅ በሚፈልጉበት ጊዜ የመነሳሳት እና የአንድነት መንፈስ ይሰፍናል።
ሴቶችን እና ወንዶችን በሚያካትት ምክር ቤት መሪው ከሁለቱም ግንዛቤያቸውን እና ሃሳባቸውን ይጠይቃል። ብዙውን ጊዜ ሴቶች እና ወንዶች የተለያዩ እይታዎችን በማቅረብ የሚያስፈልገውን ሚዛን ያመጣሉ።
መሪው የምክር ቤት ስብሰባውን ውይይቶች ይመራል። ሆኖም ከመናገር ይልቅ ማዳመጥ አለበት።
ከውይይቱ በኋላ፣ መሪው ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ መወሰን ወይም ተጨማሪ መረጃ እና መመሪያ ለማግኘት ውሳኔውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ይችላል።
4.4.4
አንድነት
የምክር ቤት አባላት በፍላጎት እና በዓላማ ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ለመሆን መሻት አለባቸው። በውይይቶቻቸው እና በውሳኔዎቸቸው አንድ ለመሆን ይጥራሉ።
4.4.5
ድርጊት እና ተጠያቂነት
የምክር ቤት አባላት አብዛኛዎቹን ስራዎቻቸውን ከምክር ቤት ስብሰባዎች በፊት እና በኋላ ይሰራሉ። በስብሰባዎች ወቅት ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ ዕቅዶችን ለማዘጋጀት የመንፈስ መነሳሳትን ይሻሉ። የምክር ቤቱ መሪ ከእነዚህ እቅዶች ጋር የተያያዙ የሥራ ምደባዎችን እንዲያከናውኑ አባላትን ይጋብዛል።
የምክር ቤት አባላት ስለሥራ ምደባዎቻቸው ሪፖርት ያቀርባሉ። ብዙውን ጊዜ መሻሻል በስራ ምደባዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ትኩረት እና ክትትል ማድረግን ይጠይቃል።
4.4.6
ሚስጥራዊነት
መሪዎች አንድን የግል መረጃ ለምክር ቤት ሲያካፍሉ ማስተዋልን ይጠቀማሉ። በአጠቃላይ ይህንን መረጃ ለማጋራት የአባልን ፈቃድ ይጠይቃሉ።
የምክር ቤት አባላት ከምክር ቤቱ መሪ የተሰጣቸውን የስራ ምደባ ለማከናወን ካልሆነ በስተቀር የግል መረጃን ከምክር ቤቱ ውጭ ለሆኑ ማካፈል የለባቸውም።
አንዳንድ ጉዳዮችን በመላው ምክር ቤት ፊት ለማቅረብ በጣም ጥንቃቄን ይጠይቃል።